ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ፡ ክፍል 2 – “ፍርሃትን በፍርሃት”

“ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ” በሚለው ተከታታይ ፅሁፍ በክፍል-1 “የፀረ-ሽብር ሽብር” በሚል ርዕስ በዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት እና በደርግ የቀይ-ሽብር ዘመቻ መካከል ያለውን ተመሣሣይነት እና የተሳሳቱ እሳቤዎች ተመልክተናል። በአሸባሪዎች ለተፈፀመ “ወንጀል” ጦርነት ማወጅና ሽብርን በሌላ ሽብር ለመመከት መሞከር ፍፁም ስህተት ነው። ምክንያቱም፣ መንግስት “በፀረ-ሽብር” ስም የሚፈጥረው ሽብር የትኛውም የአሸባሪ ቡድን ሊያደርስ ከሚችለው በላይ የከፋ ነው።

በእርግጥ አሜሪካኖች አንድ ግዜ ብቻ ነው የተሳሳቱት። የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር የፈጸፀመውን ስህተት ፕ/ት ባራክ ኦባማ አስተካክሎታል። የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ከ2002 ዓ.ም (እ.አ.አ) ጀምሮ ሲያካሄድ የነበረውን የስቃይ ምርመራ ኦባማ  በ2009 ዓ.ም (እ.አ.አ) እንዲቋረጥ አድርጓል፣ የጓንታናሞ እስር ቤቱም እንዲዘጋ ውሳኔ አስተላልፏል። ከ40 ዓመት በፊት በመንግስቱ ኃይለማሪያም የታወጀው የቀይ-ሽብር ዘመቻ የተፈጠረው ጠባሳ ዛሬም ድረስ በኢትዮጲያኖች ፊት ላይ በግልፅ ይታያል። “ዓይን-በዓይን” በሚል የተሳሳተ እሳቤ በማዕከላዊ ሲፈፀም የነበረው የስቃይ ምርመራ ዛሬም ድረስ አለ። የዚያ የክፉ ዘመን የመታሰቢያ ሙዚዬም መሆን ነበረበት ማዕከላዊ ዛሬም ድረስ የስቃይ ጩኸት ይሰማል። የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ግን በሁለት የቀድሞ የመንግስት አስተዳደሮች፤ በኢትዮጲያ የመንግስቱ ኃይለማሪያም እና በአሜሪካ የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር የፈፀሟቸውን ስህተቶችን ለመዘርዘር አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ አሁን በኢትዮጲያን ያለው የኢህአዴግ መንግስት ከእነዚህ ስህተቶች ምን መማር እንዳለበትና ሊተካከሉ የሚገቡ ክፍተቶችን ለመጠቆም ያለመ ነው።

የኢህአዴግ መንግስት ሁለት መሰረታዊ ስህተቶችን እየፈፀመ ይገኛል። የመጀመሪያው ነገር፣ በቀይ-ሽብር ዘመን ደርግ ሲያደርግ የነበረውን የስቃይ ምርመራ ዛሬም ኢህአዴግ በማዕከላዊ እንዲከናዎን በመፍቀድ የደርግን ስህተት እየደገመ ይገኛል። ሁለተኛ፣ አሜሪካኖች በፀረ-ሽብር ጦርነቱ ወቅት የፈፀሙትን ስህተት ተቀብለው፤ እንደ ጓንታናሞ ያሉ እስር ቤቶችን እየዘጉ፣ የስቃይ ምርመራን እያስቀሩ፣ እንዲሁም በፀረ-ሽብር ጦርነቱ ወቅት ያወጧቸውን የዜጎችን ሰብዓዊ መብትና ነፃነት የሚገድቡ መመሪያዎች እና ሕጎች እየሻሩ ይገኛሉ። የኢህአዴግ መንግስት ግን የፀረ-ሽብር ጦርነቱን ተከትሎ የፀደቀውንና የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች የሚጋፋውንና የሕገ-መንግስቱን መሰረታዊ መርሆች የሚፃረር ይዘት ያለው የፀረ-ሽብር ህግ ለማሻሻል እንኳን ዝግጁ አይደለም። በተሳሳተ እሳቤ መሰረት የወጣውን የፀረ-ሽብር ህግ መሰረት በማድረግ፣ የቀይ-ሽብር ዘመን ቅሬት በሆነው ማዕከላዊ የስቃይ ምርመራ እያደረገ ይገኛል። በአጠቃላይ፣ ዛሬ በማዕከላዊ እስር ቤት የስቃይ ምርመራ እየተፈፀመባቸው ያሉት እስረኞች በዋናነት በፀረ-ሽብር ህጉ የተከሰሱ መሆናቸው፣ ኢህአዴግ ካለፈ ስህተት የማይማር፣ ከሌሎች ስህተትን ብቻ የሚማር እንደሆነ ያሳያል።

እንደ አልቃይዳ ያሉ አሸባሪ ድርጅቶች ሆነ አንደ ደርግ ያሉ አምባገነን መንግስታት ዓላማቸው የፍርሃትና ስጋት ድባብ በመፍጠር የራሳቸው የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ አጀንዳ፣ እንዲሁም የራሳቸውን አመለካከት ማስረፅ ነው። ናጄሪያዊው ሎሬት “Wole Soyinka” እ.አ.አ በ2004 ዓ.ም “Climate of Fear” በሚል ርዕስ በሰጠው ትንታኔ በአምባገነኑ ደርግና እና በአልቃይዳ ዓይነት የአሸባሪ ድርጅቶች መካከል ያለውን ልዩነትና ተመሣሣይነት እንዲህ ይገልፀዋል፤

“The totalitarian state is easy to define, easy to identify and thus, offers a recognizable target at which the archers of human freedom can direct their darts. Not so obliging is what I refer to as the quasi-state, that elusive entity that may cover the full gamut of ideologies and religions, contends for power but is not defined by physical boundaries that mark the sovereign state.

Especially frustrating is the fact that the quasi-state commences with a position whose basic aim – a challenge to an unjust status quo – makes it difficult to separate from progressive movements of dissent, and with which it sometimes forms alliances of common purpose. …

The formal state, in its dictatorial mutation, usually represents power at its crudest – …. To fully apprehend the neutrality of the suzerainty of fear in recent times, indifferent to either religious or ideological base, one need only compare the testimonies of Ethiopian victims under the atheistic order of [H/]Mariam Mengistu, or indeed the Taliban of Afghanistan. …[Mengistu’s regime] is gone; Afghanistan of the Taliban is no more. It is this quasi-state that today instills the greatest fear…” (ምንጭ፡- BBC, Reith Lecture)

በመሰረቱ፣ አምባገነኑ ደርግና አልቃይዳ ተመሣሣይ አጀንዳ ነው ያላቸው። ይህም በሕብረተሰቡ ውስጥ የፍርሃትና ስጋት ድባብ በመፍጠር የራሳቸውን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ አመለካከት በሌሎች ላይ መጫን ነው። ነገር ግን፣ በሽብር ዘመቻ ኢላማ ከሚደረገው የሕብረተሰብ ክፍል አንፃር ሲታይ በደርግና አልቃይዳ መካከል መካከል መሰረታዊ ልዩነት አለ። ምክንያቱም፣ እንደ ደርግ ባሉ አምባገነን መንግስታት የኃይል እርምጃና ኢሰብዓዊ ድርጊቶች የሚፈፅሙት የእነሱን የፖለቲካ አቋም በሚቃወም የሕብረተሰብ ክፍል፣ በአብዛኛው በተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ነው። ለምሳሌ፣ የቀይ-ሽብር ዘመቻ በዋናነት ኢላማ ያደረገው በመጀመሪያ የኢህአፓ አባላትን ሲሆን በመቀጠል ወደ ሌሎች የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች እንደተስፋፋ ይታወቃል።

የአሸባሪ ድርጅቶች ዓላማና ተግባር ግን በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ላይ የፍርሃትና የስጋት ስሜት መፍጠር ሲሆን፣ የሚፈፅሙት የሽብር ጥቃትም በተቻለ መጠን ከፍተኛ የፍርሃት ድባብ ለመፍጠር ያለመ እንጂ የተለየ ኢላማ የለውም። በእርግጥ እንደ መስከረም 1 (9/11) ዓይነት የሽብር ጥቃት ሲደርስ በሀገሪቱ ሕዝብና መንግስት ላይ ከፍተኛ ድንጋጤና ፍርሃት ሊፈጠር ይችላል። ሆኖም ግን፣ የሀገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር እና ሊሂቃን በሙሉ በተመሣሣይ ስሜታዊነት ውስጥ መግባት የለባቸውም። በእንዲህ ዓይነት የፍርሃትና ስጋት ድባብ ውስጥ ሆነው የፖለቲካ ምርሆችን፣ መመሪያዎችንና ሕጎችን መቀየር ወይም የአሰራር ደምቦችን መቀየር የለባቸውም።

የአሜሪካ መንግስት በፀረ-ሽብር ጦርነቱ ወቅት ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በቁጥጥር ስር ባዋላቸው ሰዎች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊት ከመፈፀሙ በተጨማሪ፣ የብዙ ሚሊዮን አሜሪካዊያንን የስልክ መስመር በድብቅ በመጥለፍና ውይይታቸውን በሚስጥር በማዳመጥ የዜጎቹን የግለሰብ ነፃነት የሚጋፋ ተግባር ፈፅሟል። ይህ አብዛኞቹ የጆርጅ ቡሽ አስተዳደር ባለስልጣናት በአልቃይዳ ፍርሃትና ስጋት ውስጥ ወድቀው ስለነበረ የሆነ ነው።

ከአሜሪካ ባለስልጣናት ውስጥ ለፍርሃት ያልተገዛ፤ የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ዕሴቶች፡- የነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ መርሆችን ወደጎን በመተው፣ ሽብርን-በሌላ-ሽብር አፀፋ ለመስጠት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በይፋ ለመቃወም የደፈረ ባለስልጣን አንድ ብቻ ነበረ። እሱም፡- በወቅቱ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የኮንዶሊዛ ራይስ አማካሪ የነበረው “Philip D. Zelikow” ነው። ይህ ከፍተኛ አማካሪ በአልቃይዳ ተጠርጣሪ እስረኞች ላይ የስቃይ ምርመራ አንዲፈፀም የሚፈቅደውን ፕ/ት ጆርጅ ቡሹ የሰጡትን መመሪያ፤ “ከሞራል፣ ሕግና ከፖሊሲ አንፃር ስህተት ነው” በማለት በይፋ ለመቃወም የደፈረ ብቸኛ ባለስልጣን ነበር። የአሜሪካን መንግስት በወቅቱ የወሰደው እርምጃ በጉዳዩ ዙሪያ አማካሪው የተፃፃፋቸውን የውስጥ ደብዳቤዎች (Memos) ሰብስቦ እንዲጠፉ ማድረግ ነበር። በመጨረሻም፣ “Philip D. Zelikow”፤ “Fear and anxiety were exploited by zealots and fools” በማለት በወቅቱ በአልቃይዳ የሽብር ጥቃት ምክንያት የተፈጠረውን የፍርሃትና ስጋት ድባብ ሞኞችና ስግብግቦች ብቻ እንደተጠቀሙበት ተናግሯል።

እንግዲህ ከላይ በተገለፀው የፍርሃትና ስጋት ድባብ ውስጥ ሆነው ነው አሜሪካኖች “ዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት” የሚለውን የሞኞችና ስግብግቦች ጨዋታ የጀመሩት። በዚህ መልኩ አሜሪካ፣ እንደ ሎሬት “Wole Soyinka” አገላለፅ፣ “Quasi-state” ከሆኑ፤ የራሳቸው ሉዓላዊ ሀገርና ድንበር ከሌላቸው፣ መዋቅርና የሚከላከሉት ግዛት ከሌላቸው አሸባሪ ድርጅቶች ጋር ጦርነት የገጠመችው። ይህ ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ “ሉዓላዊ” የሆነችውን ኢራቅን ወራለች። ዛሬ በ”Islamic State in Iraq and Syria- ISIS” እየታመሰች ያለችው ኢራቅ የቀድሞውን አምባገነን መሪ፥ ሳዳም ሁሴን’ን ትናፍቃለች። በዚሀ መልኩ፣ አብዛኞቹ የፕ/ት ጆርጅ ቡሽ አስተዳደር በስሜታዊ ግብዝነትና ፍርሃት ውስጥ ሆኖ ያወጀው የፀረ-ሽብር ጦርነት በመጨረሻ የአልቃይዳ ዓላማና ግብ ማስፈፀሚያ ሆኗል፡፡ለዚህም፣ አሁን ከናጄሪያ-አፍጋኒስታን፣ ከሲሪያ-ሶማሊያ የተፈለፈሉትን አሸባሪ ድርጅቶች ማሳያ ናቸው። 

የቀድሞዋ እንግሊዝ የሀገር ውስጥ ደህንነት (MI5) ዳይሬክተር “Eliza Manningham Buller”፣ በጓንታናሞ እስር ቤት ሲደረግ የነበረውና በማዕከላዊ አሁንም እየተደረገ ያለው የስቃይ ምርመራ የሀገሪቱ መንግስታት ለአሸባሪዎች ተገዢ የመሆናቸው ውጤት እንደሆነ ትጠቅሳለች። ከዚሁ ጋር አያይዛም፣ ሀገሯ እንግሊዝ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት የተፈፀመባት ቢሆንም እንደ ጓንታናሞና ማዕከላዊ የስቃይ ምርመራ ፈፅሞ እንደማይኖራት ትናገራለች። “ለምን?” ለሚለው ጥያቄ የሰጠችው መልስ ከላይ የተነሳውን ሃሳብ ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።

በመጀመሪያ ዳይሬክተሯ ወደኋላ ተመልሳ፣ በ2ኛ የዓለም ጦርነት የናዚ ጀርመን እንግሊዝን በመውረር የግዛቱ አካል ሊያደርጋት በነበረበት ወቅት አንድ የጀርመን ስለላ ሰራተኛ በእንግሊዞች ቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበር ታስታውሳለች። ግዙፉ የናዚ ፍሽታዊ ኃይል በሀገሯ ሉዓላዊነት ላይ ቀጥተኛ አደጋ በፈጠረበትና እንግሊዚያዊያን በፍርሃትና ስጋት ውስጥ ተውጠው በነበረበት ወቅት እንኳን የእንግሊዝ የድህንነት ቢሮ ኃላፊዎች በቁጥጥራቸው ስር ባለው የጀርመን የስለላ ሰራተኛ ላይ የስቃይ ምርመራ ለማድረግ አለመፍቀዳቸውን በማስታወስ፤ “ያኔ ያልተደረገ ዛሬ ላይ ለምን ይደረጋል?” በማለት ትጠይቃለች።

በማንኛውም መስፈርት፣ የአልቃይዳ ድርጅት በ2ኛው ዓለም ጦርነት ወቅት ከነበረው የሂትለር ጦር ጋር አይወዳደርም። እንግሊዝ አሁን ላይ እንደ አሜሪካ በፖለቲካና ኢኮኖሚ ልዕለ-ሃያል ሀገር አይደለችም፣ ወይም በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት መላ አውሮፓን በመብረቃዊ ፍጥነት ከወረራት የናዚ ጀርመን ጦር ጋር የሚነፃፀር ኃይል አልነበራትም። ሆኖም ግን፣ ያኔም ለጀርመን ጦር አልተንበረከከችም፣ ዛሬም ለአልቃይዳ እጅ አልሰጠችም። ስለዚህ፣ እንግሊዝ ለምን በአየር-ላንድ አማፂያን፣ በሎከርቢ የአውሮፕላን እና በለንደን የ7/11 የሽብር ጥቃት ተጠርጣሪዎች ላይ የስቃይ-ምርመራ አልፈፀመችም? ለዚህ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ።

አንደኛ፡- በመሰረቱ የጓንታናሞና ማዕከላዊ ዓይነት የስቃይ ምርመራ ቁንፅል ስሜታዊነትና አርቆ ያለማስተዋል ችግር ውጤት፣ ሽብርን በሌላ ሽበር ለመከላከል የሚደረግ የሞኞችና የስግብግቦች ጨዋታ ከመሆኑም በላይ፣ የአሸባሪዎች ዓላማና ግብ ማስፈፀሚያ መሆን ነው። ይህን የዜሮ-ድምር ጨዋታ ናጄሪያዊው ሎሬት “Wole Soyinka” እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፤ “Terror against terror may be emotionally satisfaying and immediate. But who really wants to live under permanent shadow of a new variant mutually assured destruction?”

ሁለተኛ፡- የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚል በመንግስት የሚወሰዱ ማናቸውም ዓይነት እርምጃዎች የዜጎችን ነፃነት መገደብ የለባቸውም። እንደ “Eliza Manningham Buller” አገላለፅ፣ የሀገር ሰላምና ደህንነት ከዜጎች ነፃነት ተለይቶ አይታይም። ስለዚህ፣ የአንድ ሀገር የፀጥታና ደህንነት ስራ መሰረታዊ ዓላማና ግቡ የዜጎችን ነፃነት ማረጋገጥ ነው። ሆኖም ግን፣ እንደ አሜሪካና ኢትዮጲያ በፀረ-ሽብር ትግል ስም የሰዎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ ከመሰረታዊ ዓላማው ጋር የሚጣረስ ነው። ይህን በቀጣዩ ክፍል-3 በስፋት የምናይ ይሆናል።

ክፍል ሁለትን ለማጠቃለል ግን፤ የሽብር ጥቃትና አሻባሪዎች በፈጠሩት ፍርሃት ስር ሆኖ፣ “ፍርሃትን በፍርሃት” ለመታገል መሞከር የአሸባሪዎች አጀንዳ ማስፈፀሚያ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም። አሸባሪዎች ለፈጠሩት ፍርሃትና ስጋት ተገዢ መሆን፣ የሀገርና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ሳይሆን የአሸባሪዎች ዓላማና ግብ ማስፈፀም ነው። በእርግጥ እንደ ጓንታናሞ እና ማዕከላዊ ያሉ እስር ቤቶች የፍርሃት ውጤቶች እና የአሸባሪነት የድል ምልክቶች ናቸው። በእርግጥ ጓንታናሞ ተዘግቷል፣ ማዕከላዊም መዘጋት አለበት!

*********

ከጓንታናሞ እስከ ማዕከላዊ ተከታታይ ፅሁፍ

-> ክፍል 3 – “የአሸባሪዎች ሕግ”

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories