ነፃነት “የፈጣሪ”፣ ፍርሃት “የሰይጣን” ነው!

ነፃነት ለሰው ልጅ የተሰጠ ተፈጥሯዊ ፀጋ እንደመሆኑ፤ በነፃነት ማሰብ፣ መናገርና መፃፍ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ነፃነት ሰብዓዊ መብት ሳይሆን የሰብዓዊነት ተግባራዊ መገለጫ ነው። በመሆኑም፣ ነፃነት ከሌለው ሰው ሰብዓዊ ክብሩን ያጣል። ይህን ተፈጥሯዊ ባህሪ የመስጠትና የመግፈፍ ስልጣን ያለው ፈጣሪ ብቻ ነው። ምክንያቱም፣ በሕይወት የተሰጠኝ ነፃነት በሞት ይወሰዳል። ሞትን የደገሰልኝ ፈጣሪ ሕይወትን ጠንስሶልኛልና እሱ ብቻ የሰጠውን ነፃነት መውሰድ ይችላል። ከፈጣሪ በስተቀር ሌላ ማንም የእኔን ነፃነት የመግፈፍ ስልጣን የለውም። መንግስት፥ ህዝብ፥ ቡድን፥…ወዘተ፣ ሁሉም በራሳቸው የሌላቸውን ነገር ለእኔ መስጠትም ሆነ ከእኔ መውሰድ አይችሉም።

ነፃነት ከፈጣሪ የተሰጠ ነውና ይህን ተፈጥሯዊ ፀጋ ለመግፈፍ የሚሞክር ማንኛውም አካል፣ ለፈጣሪም ሆነ ለፍጥረታት ክብር የሌለው ነው። በነፃነት ከመኖር፥ ከማሰብ፥ ከመናገር፥ ከመፃፍ፥… የሚያግዱኝ በሙሉ፤ ከፈጣሪ የተሰጠኝን ፀጋ ለመግፈፍ የሚጥሩ፣ ያልተሰጣቸውን በእብሪት ለመውሰድ የሚሞክሩ ናቸው። ሹመኞች ሆኑ አመፀኞች፣ ዳኞች ሆኑ ወንጀለኞች፣… ሁሉም የሌሎች ሰዎችን ነፃነት የሚጋፋ ተግባር የሚፈፅሙ በሙሉ አላዋቂዎች ናቸው።

ፍርሃት ባለበት ኣላዋቂነት ይነግሳል፣ መተማመን ያጠፋል። ያለማወቅ የክፋት ምንጭ ነው! ባለማወቅ ያለመተዋወቅ፣ ባለመተዋወቅ ያለመግባባት፣ ባለመግባባት ጥላቻ ይወለዳል። አላዋቂዎች፤ ይጣላሉ እንጂ አይወያዩም፣ ይጯጯኋሉ እንጂ አይደማመጡም። ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ አመፀኞች እና ተቃውሞውን ለመበተን በተላኩ ወታደሮች መካከል ሁሌም ጥላቻ አለ። ሁለቱም አያውቁም፥ አይተዋወቁም። ነገር ግን፣ ተቃውሞውን ለመበተን የመጡትን ወታደሮች ተብትቦ ያሰራቸው የዕዝ ሰንሰለት፣ ወጣቶቹ በአመፅ ሊበጥሱት ከሚታገሉት የችግር ሰንሰለት ጋር ተመሣሣይ ነው። ወጣቶቹን ወደ ፊት የሚስባቸው “ድፍረት” ወታደሮቹን ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ከሚገፋቸው “ፍርሃት” ጋር እኩል ነው።

በመነጋገር መግባባት ይሰፍናል፣ በውይይት ምክንያታዊነት ይዳብራል፣ በፍርሃት ተገዢነት ሥር ይሰዳል። በምክንያታዊነት ዕውቀት ይዳብራል፣ በዕውቀት ነፃነት ይገኛል። በነፃነት ማሰብ ግንዛቤ ያዳብራል፤ በነፃነት መናገር አመለካከት ያሰፋል፣ በነፃነት መፃፍ ዕውቀት ይጨምራል። በፍርሃት ማሰብ ግንዛቤ ይቀንሳል፣ በፍርሃት መናገር አመለካከት ያጠባል፣ በፍርሃት መፃፍ ዕውቀት ያቀጭጫል።

ትክክለኛ ዕውቀት እውነታን በትክክል መገንዘብ፣ መናገርና መፃፍ ይጠይቃል። በፍርሃት ውስጥ እውነታን መገንዘብ፣ እውነትን መናገርና መፃፍ አይቻልም። እውነትን በትክክል ለመገንዘብ፣ ለመናገርና ለመፃፍ ምሉዕ ነፃነት ያስፈልጋል። ስለዚህ፣ የዜጎች ነፃነት በተከበረበት ሀገር ኃይል ከዕውቀት ይመነጫል፣ ስልጣን በነፃነት (በነፃ ምርጫና አማራጭ) ይረጋገጣል። በነፃ ውይይት ሃሳብ ይዳብራል፣ በነፃ ክርክር አማራጭ ይቀርባል፣ በነፃ ፍላጎት ምርጫ ይካሄዳል። የሰዎች ተግባራዊ እንቅስቃሴ በበቂ ዕውቀትና በነፃ ፍቃድ ይመራል። በዚህም፣ የግለሰብ ነፃነት ይከበራል፣ የለውጥና መሻሻል መንፈስ በሕብረተሰቡ ውስጥ ይሰርፃል፣ የሀገር ዕድገትና ብልፅግና ይረጋገጣል። 

የፍርሃት ቆፈን በሰፈነበት ሀገር ዕውቀት ከኃይል ይመነጫል፣ ስልጣን በጉልበት (ምርጫና አማራጭ በማሳጣት) ይረጋገጣል። ፍርሃት በነገሰበት ሁሉ ነፃነት እንደ ጥፋት ይቆጠራል። በነፃነት ማሰብ ወንጀል ይሆናል፣ በነፃነት መናገር ከአመፅ ይቆጠራል፣ በነፃነት መፃፍ ለእስርና ስደት ይዳርጋል። በእንዲህ ያለ ክፉ ዘመን ውሸት እድሜን ያረዝማል፣ እውነት እድሜን ያሳጥራል፤ ከማወቅ ይልቅ ያለማወቅ ይመረጣል። በውይይት ያልዳበረ ሃሳብ ጠባብነትን ያረግዛል፣ አማራጭ የሌለው ምርጫ አምባገነንነትን ይወልዳል። የሰዎች ተግባራዊ እንቅስቃሴ በቁንፅል ግንዛቤና በጉልበት ይመራል። በዚህ ምክንያት፣ የግለሰቦች ነፃነት ይጣሳል፣ የለውጥና መሻሻል ይከስማል፣ ሀገር በኋላ-ቀርነትና ድንቁርና አረቋ ውስጥ ትዘፈቃለች።

ነፃነት በዕውቀት ይመራል፣ ፍርሃት በኣላዋቂነት ይነዳል። ፍርሃት ሀገርን ወደ ኋላ-ቀርነትና ድንቁርና ይወስዳል፤ ነፃነት ከእድገትና ብልፅግና ያደርሳል። ነፃነት ወደ ምሉዕነት ይወስዳል፣ ፍርሃት ከባዶነት ያደርሳል። ስለዚህ፣ በግዜ ሂደት ኣላዋቂነት በዕውቀት ይሸነፋል፣ ፍርሃት በነፃነት ይፈርሳል። ምክንያቱም፣ ነፃነት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ፣ ከፈጣሪ የተሰጠ ፀጋ ነው። ፍርሃት ግን የሰይጣን ሥራ፣ የክፋት ውጤት ነው። 

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories