ደርግነት እያቆጠቆጠ – ዴሞክራሲው እየጨላለመ ነው – ህዝቦች ጠንቀቅ በሉ! (ሜ/ጄ አበበ ተክለሃይማኖት)

አበበ ተክለሃይማኖት(“ጆቤ”)
(ሜጀር ጄኔራል፣ PhD Candidate)

መግቢያ

የሃገራችን መንግስትና የገዢው ፓርቲ አጠቃላይ ችግር ዉስጥ በመግባታቸው ምክንያት እዚህና እዝያ እሚታዩ ችግሮች እየተስተዋሉ ነው። ሰሞኑን እንዃ ብናይ ከኦሮሞ ህዝባዉ ዓመፅ፣ ሜቴክና ስዃር ፋብሪካ፣ ከጋምቤላ ጠለፋና ግድያ፣ በኤርትራ በኩል የሚመጣ ተከታታይነት ያለው ዜጎቻችንን የማበሳበስ ሁኔታ እያስተዋልን ነው። የድርቁና በየክልሉ የሚታዩ የህዝቦች መነሳሳት ተጠቓሽ ናቸው። እነዚህ የሚፈጠሩ ነገሮች ካጠቃላይ ሕገ መንግስታዊ ማእቀፉና ከህዝቦች ፍላጎት አንፃር ማየት አለብን።

አንድ ጏደኛየ “ህወሓት የለችም ማለት የትግራይ ህዝብ የለም ማለት ነው፤ ስለዚ ህወሓት ማለት ህዝብ ነው፤ ኢህአዴግ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት ነው” ማለት ምን ማለት ነው ብሎ ጠየቀኝ። እኔም እንዲህ ብሎ ነገር የለም ከየት አመጣሀው አልኩት፤ እሱም የሃገራችን ኢታማዦር ሹሙ ናቸው የተናገሩት አለኝ በትግርኛ የግንቦት ሃያ ስብሰባ ላይ መቐለ ከተማ የተናገሩት ብሎ ሊንኩን ሰጠኝ:: ቪድዮው የ ሶስት ሰዓትና ሃያ ሁለት ደቂቃ ርዝመት ያለው ስለሆነ፤ ይህንን ሁሉ ለማየት ግዜም ፋላጎትም ላይኖራቹህ ስለሚችል ከ2ሰዓት እና 23 ደቒቃ ( 2:23)ጀምራቹህ እንድትመለከቱት እጋብዛለሁ።

ባለፈው ፁሁፌ እንደገለፅኩት የወታደራዊ ክፍሉ ጡንቻ እየፈረጠመ የመሄዱ አዝማምያ ያሰጋኝ እንደነበር ገልጬ ነበር። ይህንን ቪድዮ ሳየው ግን ወታደራዊ ታልቃ ገብነቱ ከምገምተው እና ከጠበቅኩት ፍጥነት በላይ ሆኖ ሳገኘው ደርግነት ተመልሶ እየመጣ ይሆን እንዴ? ብየ ለመጠየቅ ተገደድኩ።የዴሞክራሲ እጥረት ወይም ምህዳር መጥበብ ማለት ደርግነት መንገስ ማለት ነው፤ ሱፍም ወታደራዊ ልብስም ሊለብስ ይችላል።

Photo - Major General Abebe Teklehaimanot
Photo – Major General Abebe Teklehaimanot

ደርግነት ምንድን ነው?

ደርግነት ወታደራዊ ክፍሉ ፖለቲካዊ አመራር ከኔ በላይ የሚችለው የለም ብሎ ስልጣን መቆናጠጥ ነው። ደርግነት ሁሉም ዴሞክራስያዊ መብቶች በሃይል ለማፈን የሚደረግ አስተሳሰብ እና ድርጊት ነው። ደርግነት የኢትዮጵያ ህዝቦች አንገዛም ማለት ሲጀምሩና ፖለቲካዊ አመራሩ መምራት ሲያቅተው ወታደራዊ ክፍሉ ድሮስ ከኔ በላይ ማን አለ በሚል ትዕቢት ጠብመንጃ ቤተ መንግስትን ሲቆጣጠር ነው። ደርግነት ሲጀምር “የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ ምርጥ ልጆቹ እንደተሰበሰቡ”  ለማሳየት እንቅስቃሴ ማድረግ ነው። ደርግነት የ “አንድ ህዝብ፣  አንድ ፓርቲ፣ አንድ መሪ”  የሚሰብክ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ተግባር ነው።

ደርግነት አንድ ህዝብ፣ አንድ መንግስት (One State)፣ አንድ መሪ (führer) የሚለዉን የናዚ አስተሳሰብ ተቀጥያ ነው። በኢትዮጵያም አንድ ህዝብ፣ አንድ ፓርቲ (ኢሰፓ) አንድ መሪ (መንግስቱ ሃይለ ማርያም) እንደ ማለት ነው።  በዘመናችን ደግሞ የኤርትራው ዲክቴተር እንደሚሉት “አንድ ህዝብ፣ አንድ ልብ፣ የራሳቸው አንድ የፖለቲካ ድርጅት፣ ራሳቸው ብቸኛና አንድ መሪ”፤ ከዚህ ዉጪ ያለ መሪም ሆነ ድርጅት የኤርትራ ጠላት አድርጎ የመመልከት አስተሳሰብ ነው ደርግነት። ደርግነት አለመተማመን ነው፤ አንዱ ሌላዉን የሚያሸማቅቅበት ሰርዓት ነው። ፕሬዝዳንት መንግስቱ ሃይለማርያም ቢሆኑም በመፈንቅለ መንግስት ስልጣናቸው እንዳይወሰድባቸው ተሸማቅቀው የሚሮሩበት ነው። ደርግነት ኔትዎርኪንግ ነው፤ መጠላለፍ ነው።

የፈለገ ዓይነት ችግር ቢመጣ “ያው አፍሪካዉያን ስለሆንን በወታደር እንፈታዋለን” የሚል አስተሳሰብ የደርግነት ሀሁ ነው።ፖለቲካዊ መፍትሄ የማይታየው፣ ጭንቀት የፈጠረው ገር አስተሳሰብ ወይም ሁን ተብሎ ጠባብ ጥቅምን ለማስጠበቅ የሚሰነዘር ሃሳብ ነው።ህዝብን በጉልበት እንደሚነዳ እንስሳ የሚቆጥር ኃላ ቀር አስተሳሰብ ነው። ለመጨቆን የሚደረግ መንገድ ጠረጋ ነው። ለአፈና የሚደረግ መንደርደር ነው፤ ባጭሩ የደርግነት መነሻ ነው። የኣፍሪካዊ ሰው ሰብኣዊ እኩልነት አለማመን ነው፤ የቀኝ ገዢ አስተሳሰብ ነው። አይደለምና በደሙ ደርግነትን ያሸነፉት ለኢትዮጵያ ህዝቦች ለማነኛዉም የሰዉ ፍጡር በወታደር የሚሽከረከር ሃገር ኣልመኝም፤ ምክንያቱም ሕገ መንግስታዊና ዴሞክራስያዊ ስርዓት ለመገንባት እከል ስለሚሆን። ለራሳቹህ ጠባብ ጥቅም ለመጠበቅ ስትሉ  “ኢትዮጵያዉያንን በጉልበት ነው መግዛት” እያላቹህ ወታደራዊነት እምታቀነቅኑ ፀረ ሕዝብና ፀረ ዴሞክራሲ መሆናቹህን መገንዘብ አለባቹህ፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበረሰቡ ይህንን ክፉና አደገኛ አስተሳሰብ በንጭጩ ለመቅጨት መታገል አለበት።  

ደርግነት ተሻንፊነት ነው። ደርግ በጥቁር አፍሪካ አለ የሚባል ስመ ገናና ጦር ይዞ፣ በክፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ መኮንኖች አስልፎ፣ የራሽያ ሙሉ ድጋፍ እየተቸረው በኢትዮጵያ ህዝቦች ፊት ግን ተሸናፊ ሃይል ከመሆን አልዳነም። ለምን ቢባል የፈለገ ወታደራዊ አቅም ቢያዝ ፖለቲካዊ ምክንያት እና ሰልፍ ነው የሚያሸንፈው፤ የደርግ ጠብመንጃም በፍትሕ ፈላጊ ኢትዮጵያዉያን ፖለቲካ ተደመሰሰ። ደርግነት ፀረ ህዝብነት ነው፤ የንቀት እና የማንቛሸሽ ስርዓት ነው።

ውቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካና ደርግነት

የኢትዮጵያ ህዝቦች ከህግ ዉጪ አንገዛም ማለት ጀምረዋል። የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራስያዊ እንቅስቃሴ፣ የቅማንት ህዝቦች ዴሞክራስያዊ ትግል፣ በትግራይ ደግሞ እንደ እምባሰነይቲ ዓይነት ዴሞክራስያዊ እንቅስቃሴ፣ የኮንሶ ህዝቦች ዴሞክራስያዊ ጥያቄን እንደ ምሳሌ ሊወሰዱ ይችላሉ። ገዢው ፓርቲ ቆሟል ወይም ወደ ኃላ እየነጎደ ነው፤ ባጭሩ ጥልቕ ፖለቲካዊ ችግር (political crisis) አለ። ሆኖም ይህንን ችግር መፈታት ያለበት ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ እንጂ ከዛ ዉጪ በሆነ መንገዶች መሆን የለበትም።

ኢህአዴግ ዉስጣዊ ቐዉስ አጋጥሞታል፤ ወታደራዊ ክፍሉ የአመራር ክፍተትን ለሞሙላት ምን እያደረገ ነው? የሚለው ማየት ተገቢ ነው። በተለያዩ መጣጥፎቼ የዴሞክራሲ እጥረት (democratic deficiency) በሚኖርበት ሁኔታ ሕገ መንግስታዊ ተቛሞች ልፍስፍስ በሚሆኑበት ግዜ ባለጠመንጃው ሁለት ሶስት ግዜ ማስብ ይጀምራል ብየ ነበር፤ የተወሰኑ ምልክቶችም ጠቁሜ ነበር። እንደኛ ባሉ በሽግግር ላይ በሚገኙ ማህበረሰቦች፤ የዴሞክራሲና ሕገ መንግስታዊ ተቛሞች ተገቢ ስራቸዉን መስራት አለመቻላቸው ለጉልበተኛ አካል እድል መስጠታቸው ያገራችን ህልዉናና የህዝቦችን ዋስትና ሲፈታተን ይታያል። ከዚህ አንፃር አሁን ማየት የምፈልገው ወታደራዊ ክፍሉ እያሳየ ስላለው የፖለቲካዊ ፍላጎት ጭላንጭል ነው።

ፖለቲካዊ ሚና የማይኖረው ሕገ መንግስታዊ ተልእኮዉን ብቻ የሚወጣ የመከላከያ ሃይል ለመገንባት የኢትዮጵያ ህዝቦች ከፍተኛ መስዋእትነት ክፍለዋል። የሲቪሉን አስተዳደር ህዝባዊ ስልጣን አክብሮና ለሕገ መንግስቱ ተገዢ ሆኖ ግዴታዉን የሚፈፅም፣ አገሩን በብቃት የሚከላከል፣ ጥቃትን የሚያስቀር ወይም በቂ ምላሽ መስጠት የሚችል ሃይል ሆኖ መገኘት ነው መሰረታዊ ተልእኮው። አሁን ግን በከፍተኛ አመራሮቹ እየታየ ያለው ነገር አንዳንድ ስጋቶችን እየጫረ ይገኛል።

የመቐለው ፓናል

በቅርቡ ኢታማዦር ሹሙ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ግንቦት ሃያን አስመልክተው በመቐለ ከተማ ያካሄዱት ዉይይት ላይ ያነስዋቸው ሃሳቦችና እና የተናገርዋቸው ነገሮች በጣም እሚያሳዝኑና ሕገ መንግስቱን ገድል ግባ ያሉበት መድረክ ነበር። ከ ሀ እስከ ፐ  ስለ ሲቪል አስተዳደሩ ድክመት፣ ልፍስፍስነት፣ ስለ ወታደራዊ ክፍሉ የመተካካት ልዩ ችሎታና ስለ ሰራዊቱ የአሁንና የወደፊት ጥንካሬ ሲያወሩ ላየ ጄኔራሉ ምን እያለ እንደሆነ ይገባዋል ወይ? የሚል ጥያቄ ያጭራል። “ፖለቲካዊ አመራሩ እንጂ ወታደራዊ ክፍሉ ጤነኛ ነው” እሚል መልእክት አደገኛ አካሄድ ነው፤ እኔ ልምራ አይነት አንደምታ ያለው ንግ ግር ነው። የሲቪል መንግስት በወታደራዊ ክፍሉ የሚገመገምበት አሰራርም ሆነ ሕገ መንግስታዊ መርህ ወይም ድንጋጌ የለም። ሲቪል አስተዳደሩ ወታደሩን ሊቆጣጠር ሲገባው በተገላቢጦሽ ወታደራዊ ክፍሉ ሲቪሉን አትረባም፣ ሞተሃል፣ አመራር አታዉቅም እያለው ነው።

ሲጀመር ስብሰባው ምን አላማ ታሳቢ አድርጎ በማን ለምን እንደተዘጋጀ መጠየቅ አለበት። እዉነት የግንቦት ሃያ መንፈስ ለማስረፅ ነው የተዘጋጀው? የግንቦት ሃያ መንፈስ ሕገ መንግስታዊ መርሆችና ድንጋጌዎች እየተጣሰ ነው እንዴ እሚከበረው? ሕገ መንግስቱን በግላጭ እየደረመሱ ግንቦት ሃያን ማክበር ብሎ ነገር አለ እንዴ? በዶከተር ዛይድ አወያይነት የተጀመረው የሁለቱ ንግግር ከ 1967ዓ.ም እስከ 1983 ዓ.ም የነበረዉን ፖለቲካዊና ወታሃደራዊ ሁኔታ በዝርዝር አስቀምጠዋል። አሁን ስላለው ፖለቲካዊን ችግሮች ሁለቱም ለየቅልና ተቃራኒ ሓሳቦች አስቀመጡ፤ ኢታማዦር ሹሙ በዚህ ጉዳይ መግባት ባይኖራቸዉም።

አቶ ኣባይ ፀሃየ አሁን ያሉት ፖለቲካዊ ችግሮች የዴሞክራሲ እጦት፣ የሙስና መስፋፋት እና የበላይ አመራሩ እርስበርሱ አለመታገል (አድርባይነት) ነው አሉ። መፍትሔዉም ዴሞክራሲን ማስፋፋት እና በዚህ እና በመልካም አስተዳደር ያሉትን ችግሮች የበላይ አመራሩ ያለ ማቅማማት መታገል ነው አሉ። ጄኔራል ሳሞራ ደግሞ የችግሮቹ ምንጭ ኪራይ ሰብሳቢነትና ዕድገት ነው አሉ። መፍትሔ ሲጠቁሙ ደግሞ አቶ ኣባይ ያሉትን በመፃረር ወይም የኣቶ አባይ መነሻ ሃሳብና መፍትሔ ገሸሽ በማድረግ ላይኛዉ አመራር ፕሮጀክት መምራት እና በቴሌቭዥን መታየት ስራው በማድረግ በቦታው አለመገኘቱ ነው አሉ። የፖሊሲ፣ የመመርያ፣ የአሰራር ችግሮች ዋነኞቹ ችግሮች ናቸው በሚል ያለዉን ፀረዴሞክራሲ አስተሳሰብ ለማድበስበስ ሲፈላሰፉ ታይቷል።

አመራር ማለት ፕሮጀክቶች መምራት እና በቴሌቭዢን መታየት አይደለም ብለዋል ጄኔራሉ፤ ማንን ለመምታት ይሆን? የሚለው መጠየቅ ተገቢ ነው። ሲጠቃለል የኢህአዴግ መንግስት ችግር አቶ ኣባይ ፀሃየ እንዳስቀመጡት ነው ወይስ ጄኔራሉ እንዳሉት? የአቶ አባይ ፀሃየ ፖለቲካዊ ግምገማ በጄኔራሉ ሲቪል አስተዳደሩን የማንቛሸሽ ንግግር ታጅቦ የቀረበበት ፖለቲካዊ ምክንያት ምንድን ነው? ማን ምን ቢፈልግ ነው እንዲህ አይነት ዘመቻ የተጀመረው? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነገር ነው እየታየ ያለው።

ከሁሉም በላይ የሰቀጠጠኝ ነገር ግን ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ባጠቃላይ ስለ ትግራይ ህዝብ ደግሞ በዋናነት ያሉት ነገር ነው። ለሳቸው የትግራይ ህዝብ ማለት ህወሓት ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት ደግሞ ኢህአዴግ ነው። ህወሓት/ኢህወዴግ የለም ይባላል እርስዋስ ምን ይላሉ ተብለው ሳይተየቁ በራሳቸው አነሳሽነት የሃገር ኢታማዦር ሹም ምን እንዳለ ላካፍላቹህና አሉና “አንዳንድ ሰዎች ህወሓት የለም ይላሉ ፤ እንዲህ እሚሉት ሰዎች ራሳቸው ላይኖሩ ይችላሉ። ለኔ ህወሓት ማለት መስመር ነው፣ ህወሓት ማለት ህዝብ ነው፣ ሌላ አይደለም። እኔ የሚገባኝ ህወሓት የለችም ማለት የትግራይ ህዝብ የለም ማለት ነው፤ ስለዚ ህወሓት ማለት ህዝብ ነው፤ ኢህአዴግ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት ነው” ብለው ተናገሩ

በዘመናት የትዉልድ ቕብብሎሽና ዉርስ ታሪኩና ማንነቱ በክብር ያቆየዉን የኢትዮጵያ ህዝብ በዚ መልኩ ወደ ድርጅት ጀረጃ አውርዶ ማሳነሱ ሳይበቃ የዚህ ኩሩ ህዝብ ህልዉና በፖለቲካዊ ድርጅቶች ሲረጋገጥ የቆየ ይመስል ኢህአዴግ የለም ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ የለም ማለት ነው ብሎ ንግግር ክትዕቢት (Arrogance) እንጂ ከሌላ ሊመነጭ አይችልም። ህወሓት ሆነ ኢህወዴግ እንደ መድረክ ወይም ኢዴፓ ወይም ሌሎች ፓርቲዎች አንድ የፖለቲካ ድርጅት እንጂ የትግራይን ወይም የኢትዮጵያን ህዝብ መተካት የሚችሉ የህዝብ አቻ የሆኑ መዋቅሮች አይደሉም። ሲጀመር የሚያደጉት ነገር ከሕገ መንግስት አንፃር ምን ማለት እንደሆነ ሳይገባቸው ቀርቶ ነው?

ህወሃት ማለት የትግራይ ህዝብ ነው የሚለው አነጋገር ፀረ ህዝብነቱ የሚጎላው ፀረ ሕገ መንግስታዊ ይዘቱ ስንረዳ ነው። ህብረ ፓርቲነት በሕገ መንግስትዋ ያወጀች አገር ፣ ለዛዉም በስንት መስዋእትነት በመጣ ሕገ መንግስት፣ አንድ ኢታማዦር ብድግ ብሎ ህወሓት ማለት የትግራይ ህዝብ ነው፣ ኢህአዴግ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ሲል ያሳፍራል። የትግራይ ህዝብ ህወሓትን ፈጠረ እንጂ ህወሓት የትግራይ ህዝብን አልፈጠረችዉም።

የትግራይ ህዝብ የጋራ የሆነ ፍላጎቶችና ክብሮች ቢኖሩትም ሁሉም ነገሩ ግን አንድ አይደለም። የትግራይ ህዝብ ስንል ገበሬው፣ ላብአደሩ፣ ተማሪና ሙሁሩ፣ ባለሃብቱ እና ወዘተ ነው። የትግራይ ህዝብ ስንል ክርስትያኑ፣ እስላሙ፣ ኩናማው ፣ኢሮቡ ፣ ወጣቱ፣ ሽማግሌው፣ ሴት፣ ወንድ ነው። የተለያየ ፍላጎትና እሴቶች አሉት። ብዙሃነትን የሚያስተናግድ ህዝብ ነው። እነዚህ የተለያዩ ጥቅሞችና እሴቶች የተለያየ መስመርና አደረጃጀቶች ሊተይቅ ይችላል። የተለያዩ ድርጅቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፤ ከሁሉም በላይ ግን አንድ መስመር የሚሉት ፀረ ዴሞክራሲ አባዜ ነው። ጥቂት የተመረጡ የበላይ አመራሮች ለህዝብ የሚጠቅመው ይህ ነው ማለታቸው ብቻ በቂ አይደለም ። የትግራይ ህዝብ ስለ ህወሃት ምን እንደሚል የህወሓት የንደፍ ሃሳብ ልሳን የሆነዉን <ወይን< ምን እንደሚል እስኪ ያንብቡት።

የአገር መከላከያ ኢታማዦር ሹም በጠራራ ፀሃይ የሕገ መንግስቱ አንቀፅ 87 ( 87/4የመከላከያ ሰራዊት በማናቸዉም ግዜ ለሕገ መንግስቱ ተገዢ ይሆናል 87/5 “የመከላከያ ሰራዊት ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ ኣዃሃን ያከናዉናል”) እና ሌሎች ሕጎችን በመፃረር ለህወሓት ጥብቅና መቆም ምን ይባላል? ህወሓት ልክ እንደ ሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶች ያለዉን ቀዉስ አንዱን ወገን ደግፈው በመንግስት ገንዘብ ጊዜ ኮኮብ እየሰሩ ነው እኮ። እነዛ የተደረደሩት ኮኮቦች ሕገ መንግስቱን መጣስ ሲጀምሩ አፈር እንደሚሆኑ ዘነጉት እንዴ? በህወሓት ዉስጥ እርስዎ የሚደግፉት ወገን ህወሓት የለችም ማለት የትግራይ ህዝብ የለም ማለት ነው የሚል ከሆነ እንጦርጦሱ ይግባ።

የሁለት ትዉልዶች ወግ

ጄኔራል ሳሞራ ህወሓት የለችም የሚሉ ምናልባት ራሳቸው የሌሉ እንዳይሆኑ ካሉ በኃላ፤ በጉባኤው ተሳታፊ የነበረችው ወዛም ታደለ የተባለች አምስተኛ ዓመት የህግ ተማሪ “እኔን ጨምሮ ኣብዛኛው ወጣት ህወሓት የለም እምንለው መሬት ላይ ካለ የመልካም አስተዳደር ችግር ተነስተን ነው፤ ብዙ ነገር ጠብቀን እምንፈልገው ነገር ስለማናገኝ ነው፣ ስለዚህ የህወሓት ህልዉና ከዚ ጋር ኣያይዘው እንዲገነዘቡት ነው እምፈልገው” ብላ ትምህርት ስጥታ ጥያቄዋን ሰነዘረች። ጀግና ወጣት ናት!

ጄኔራሉ ህወሓት አለች ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ አለ ሲሉ ጅግናዋ ልጂትም አይ ለኔ ህወሓት እምገነዘባት መሬት ላይ ካለ የመልካም አስተዳደር ሁኔታ ጋር ነው፤ ከመንግስታዊ ድርጊት ጋር ነው ብላ “በዚ መልኩ ሊገነዘቡት ይገባል” ብላ ታሪክ የማይረሳው ትምህርት ስጥታለች። በተማረው ወጣቱ ትዉልድ ያለኝኝ ተስፋ በተማሪ ወዛም ታደለ በኩል ማየቴ ብኮራም፤ በስልጣን ላይ ባለዉ ትዉልድና በሚመራው ትዉልድ መሃል ያለው የመረዳትና የእዉቀት ልዩነት ግን የሰማይና የምድር ያህል መራራቁ ግልፅ ያደረገ መድረክ ነበር።

ግለሰቦች ተቛምና የሃገር ደህንነት

የሜቴክ እና የመከላከያ ዕቃ ግዢ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች የመልካም አስተዳደር ችግር ያለው በሲቪል መንግስት ብቻ ነው፤ መከላከያው ግን በጣም ጠንካራ ነው እያሉ ፕሮፖጋንዳ ይነፋሉ። ጄኔራሉም የዚህ ፕሮፖጋንዳ ሰለባ ሆነው መከላከያን እያንቆለጳጰሱ ለአሁኑም ለወደፊቱም እንደተዘጋጁ ሲነግሩን የመንግስት ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩን ደግሞ ትምህርት ቤት ክፍተው ስለ አመራር ለማስተማር የተዘጋጁ ይመስላሉ::

በዚህ ጉዳይ ከኣንዳንድ ሰዎች ጋር ስነጋገር ጄኔራል ሳሞራን ኣትንካ፤ የአገራችን አለኝታ ናቸው። ያለሳቸው መከላከያዉም ብሎም አገራችን ችግር ዉስጥ ትገባለች አሉኝ፤ ምን ማለት ነው? ሕገ መንግስቱና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በግላጭ ሲጥሱስ ብየ ጠየቅዃቸው። <ቢሆንም ይሁን< ነበር መልሳቸው።

በትጥቅ ትግል ግዜ ከጀግኖች መሪዎች አንዱ ነበሩ፤ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ም ቢሆን እንደ ፊልድ ኮማንደር ልዩ አስተዋፅኦ ነበራቸው፤ ጦርነቱ ተንገራግጮ ከዚህ በላይ መቀጠል ኣንችልም እስኪባል ድረስ። ጀግና የነበረ ሁል ግዜ ጀግና፤ ለህዝብ ተቆርቛሪ የነበረ በቀጣይነት እንደዛ ይሆናል ባይባልም ከፈተኛ ክብር ግን ይገባቸዋል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝቦች የተዋደቁለትንና በብዙ መስዋእትነት እዉን ያደረጉትን ሕገ መንግስትና ስርዓቱን በግላጭ ሲንዱ ተው መባል አለባቸው።

የኔ ተስፋ መከላከያ ተቛማዊ አስራር ገንብቶ ማንም መሪ ቢሄድ ቢመጣ ስርዓቱን ተከትሎ የሚሄድ ጠንካራ መዋቅር ሆኖ ማየት ነው። ካልሆነ ግን በግለሰቦች እሚንጠለጠል ተቛም ተሁኖ ይህን አገር መከላከል አይቻልም።

ከአስራ አምስት አመት በላይ የአገር መከላከያ ኢታማዦር ሹም ሆነው ሲያገለግሉ፣ ብዙ ጀግኖችና ብቃታቸው ያረጋገጡ ከፈተኛ መኮንኖች የነበሩት መከላከያ እሳቸው ከተነሱ አደጋ ዉስጥ የሚገባ ከሆነ እማ አስራ ኣምስት ዓመት ጥፋት ሲፈፅሙ ነበር ማለት ነው፤ እሳቸው በሌሉበት እንደ ተቛም የበለጠ ተጠናክሮ የማይሰራ ከሆነ ይች አገር በእዉነትም አደጋ ላይ ነው ያለችው።

ከዚህ ጋር የተሳሰረ ወጣቶች ያወጉኝን ላካፍላቹህ።የስዃር ኮርፖሬሽን አመራሮች ፓርላማ ቀርበው “ያሸማቁቁናል፣ ሜቴክን መቅጣት እንደማንችል ሁላቹሁም ይገባቹሃል” ባለቡት ሳምንት ሁለት ወጣቶች አግኝቼ ከሌሎች ሁሉት ጏደኞቻቸው ሆነው ሁለት ለሁለት ተከፍለው በዚህ ዙርያ የጦፈ ክርክር ማድረጋቸው ነገሩኝና ስለምን? ብየ ጠየቋቸው። ሁሉም የተማሩ ወጣት የትግራይ ልጆች ናቸው። ዉይይታቸው ፓርላማ ሜቴክን እንደዛ መጠየቁና ብልሹ አስራር መታገል እንዳለበት ቢስማሙም በተወሰነ ነጥብ እንደተለያዩ ነገሩኝ። ሁለቱ ወጣቶች እዉነታው አሳዛኝ ቢሆንም ኣላማው ትምክህተኞች ትግራይን ለመጉዳት ሆነ ብለው ያቀነባበሩት ሴራ ስለሆነ ከሚጮሆም ጋር ኣብረን መጮህ የለብንም ሲሉ የተቀሩት ሁለቱ ወጣቶች ደግሞ የለም በሴራ ሃሳብ ገብተን ሌብነትን ከብሄር ጋር እያገናኘን እማይገባቸው ከለላ መስጠት የለብንም፤ እንደዉም ለፍትህ መቅረብ አለባቸው፤ ሜቴክም አጠቃላይ አሰራሩ መፈተሽ አለበት ብለው እንደሞገትዋቸው ከሁለቱም ጎራ የነበሩ ሁለቱ ወጣቶች ነገሩኝ።

ሜቴክ አመራር ላይ በርከት ያሉ የትግራይ ተወላጆች ሊኖሩ ይችላሉ። በትግራይ ይሁን በሌላው ኢትዮጵያ እንደ ትግራይ ተቛም አድርጎ ማየቱ ( percieve  ማድረጉ) መሰረታዊ ስህተት ነው። ሜቴክ የቴክኖሎጂ ማእከል የኢትዮጵያ ሽግግር (Transformation) ሻምፒዮና የሚሆንበት ሂደት እንደ ትግራይ/ኢትዮጵያ ሁላችንንም ሕገ መንግስቱ ማእከል አድርጎ ተጠያቂነት፣ ግልፅነት፣ የሕግ የበላይነት ያለንን የሰው ሃይል እና በመቶ ቢልየኖች ቆጥቦ ሲሰራ እንኮራበታለን። እጅጉን እናመሰግነዋለን።

ሜቴክ ተጠያቂነት፣ ግልፅነት፣ የሕግ የበላይነት የማይመለከተው አካል ሆኖ የአገራችንን ከፍተኛ ሃብት ሲያጠፋፋ ግን እንደ ኢትዮጵያዉያን ራሳችንን ደፍተን እናዝናለን። እዛ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ጥቂት ቀጣፊዎችና ከነሱ ጋር የሚቀራረቡትን ይጠቀማሉ እንጂ የትግራይ ህዝብን እየበደሉት ነው፤ ለዛዉም ባለ ሁለት ስለት በደል። ባንዱ በኩል እንደ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የሃገራቸው ሃብት እየተዘረፈ ነው፤ በሌላ በኩል በስሙ እየነገዱ ነው፣ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ደግሞ ወደ አላስፈላጊ ጥርጣሬ እንዲገቡ ሊያደርግ ይችላል።

ከየትኛዉም ብሄር ብሄረሰብ ወይም ህዝቦች ሕገ መንግስትን፣ ፖሊሲዎችንና ሕጎችን አክብረው በተጠያቂነትና ግልፅነት ቀንና ሌሊት ሰርተው አገራችንን በመለወጥ የድርሻቸዉን ሲወጡ እደጉ ተመንደጉ እንደምንለው ሁሉ፤ ከዚህ በተፃራሪ የሚሰሩትን ቀጣፊዎችን ደግሞ ቀጣፊዎች እንበላቸው አልዃቸው።

ስዃር ኮርፖሬሽን እና ሜቴክ በሚመለከት ጉድ የተባለለት ሪፖርት “ሾልኮ” ለፓርላማና ለህዝቡ ተገልፆ መወያያ በሆነበት ግዜ እና ፓርላማው የመጨረሻ ዉሳኔ ባልሰጠበት ሁኔታ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቛሚ ኮሚቴ እያንዳንዱ በሜቴክ ተቛሞች እየተዘዋወረ ምስጋና እየደረደረ ነው። የሚገባቸው ከሆነ ይበል የሚያስብል ነው። ግን ደርግነት መንገስ በጀመረበት ከባቢ (Environment) ቛሚ ኮሚቴው ተሸማቆ ይሆን እንዴ እንዲህ የሚያደርገው> የሚል ጥያቄ ሰዎች ያነሳሉ።

መደምደምያ

ደርግነት በሁለት ኢ-ሕገ መንግስታዊና ስርዓት-የለሽ በሆነ መንገድ ሊከሰት ይችላል።አንደኛው በግላጭ መፈንቅለ መንግስት ማድረግ ነው። ሁለተኛው የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ብሎም የኢህአዴግ ምክር ቤት ወይም ፈፃሚዉን መመርያ በመስጠትና በማስፈራራት “እከሌ ሊቀ-መንበር እንዲሆን እከሌን አዉርዱት” ወዘተ በማለት ሊሆን ይችላል። በድርጅቱ ባለው ሁኔታ ይህ አይቻልም ማለት የዋህነት ነው። የግንቦት ሃያ በዓል አስመልክቶ የተደረገው ፓነል ይህን ለማስረገጥ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን። ኢህአዴግ ዉስጥ ያለው ችግር ባልተመሰቃቀለና ሕገ መንግስታዊ በሆነ መልኩ ከህዝቦች እና ሌሎች ፓርቲዎች ተሁኖ መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው፤ ያለ ምንም የወታደር ጣልቃ ገብነት።

የኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማት እና ዴሞክራሲ በ ህዝቦች ተሳትፎ እና ትግል ስ ለሚረጋገጥ ሁሉም ሰው መታገል አለበት። ትልቁን የኣሜሪካን መንግስት የደገሰለትን ኢ ፍትሓዊ የጦርነት ጥሪ አልቀበልም በማለት የሚከተለዉን የቦክሰኛዉ መሓመድ ዓሊ ጥቅስ አንድ ጏደኛየ በኢሜል ልኮልኝ እኔም እጅግ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘሁት ላካፍላቹህ ወደድኩ።

“My conscience won’t let me go shoot my brother, or some darker people, or some poor hungry people in the mud for big powerful America. And shoot them for what? They never called me nigger, they never lynched me, they didn’t put no dogs on me, they didn’t rob me of my nationality, rape and kill my mother and father. … Shoot them for what? How can I shoot them poor people? Just take me to jail.”

********

በሆርን አፌይርስ የታተሙ የሜ/ጄ አበበ ተክለሃይማኖት ጽሑፎች፡-

የተገኝዉን ሰላምና እድገት የሚንድ የአመራር ዘይቤ ባስቸዃይ ይታረም!

ብልሹ አስተዳደርን የዴሞክራሲ ምህዳር በማስፋትና በተቋማት ግንባታ

Guest Author

more recommended stories