ከጥቂት አመታት በፊት ትግራይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተሳትፎ ጥሩ ሊባል የሚችል ክልል ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ የተጫወቱ ብዛት ያላቸው ተጨዋቾች ከማፍራቱም ባሻገር ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ሁለት በፕሪምየር ሊግ ደረጃ የሚሳተፉ  ጠንካራ ክለቦች ነበሩት፡፡ በእግር  ኳስ አሰልጣኞችም እስካሁን በክለብ ደረጃና ብሔራዊ ቡድን ማሰልጠን የደረሱ ባለሞያዎችም በከፍተኛ ሁኔታ ያፈራ ክልል ነው፡፡

ትራንስ ኢትዮጵያና ጉና ከተመሰረቱበት 1992 ና 1993 ዓ.ም ጀምሮ የፕሪምየር ሊጉ ኣድማቂዎች ነበሩ፡፡ የ1980 ዓ.ም የምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ገ/መድህን ሃይሌ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የቅ/ጊዮርጊሰ ግብ ጠባቂ ደሳለኝ ገ/ጊዮርጊስ፣ ፀጋየ ኪ/ማርያም(ንግድ ባንክ አሰልጣኝ)፣ፀጋዝኣብ(የረጅም ጊዜ የመብራት ሃይል በረኛ)፣ሃይላት /ወዲቀሺ/፣ መድሃንየ፣ ኤፍሬም ዘርኡ ከዚሁ ክልል የፈለቁ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ከዚሁ ተሳትፎ በኋላ ላለፉት 5 እና 6 ኣመታት የክልሉ እግርኳስ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቀዛቀዘ ይገኛል፡፡ ሁለቱ ዋና ክለቦች ከፕሪምየር ሊጉ መሰናበታቸው ተከትሎ በፋይናንስ ችግሮችና ትኩረት በማጣት ሙሉ ለሙሉ በመፍረሳቸው አብዛኛው ተጫዋችና ባለሞያ ሊፈልስ ችሏል፡፡ ክለቦቹን በዋናነት ሲደጉም የነበረው ትእምት(EFFORT) ድጋፉን  አቋርጧል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ትእምት አነስተኛ ወጪ ካላቸው የአትሌቲክስ እና የብስክልት ክለቦች  በስተቀር በስሩ ምንም አይነት የእግር ኳስ ክለብ የለውም፡፡ ትግራይም በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ (ብሄራዊ ሊግ) ከሚሳተፉት የከተማ መስተዳድር ክለቦች – ወልዋሎ፣ ኣክሱምና መቐለ የሚባሉ ክለቦች – በስተቀር በፕሪምር ሊጉ ተወካይ ክለብ የላትም፡፡

Photo - Mekelle football stadium
Photo – Mekelle football stadium

መቐለ ከተማ እግር ካስ ቡድን

በ1960ዎቹ ላይ ክለቡ ሲጠነሰስ ስሙ ‹‹የእንደርታ ምርጥ›› ነበር፡፡ በደርግ ዘመን ከፍተኛ 1 እና ከፍተኛ 2 በሚል ለሁለት ተከፍሎ፤ ተጨማሪ የስፖርት ኣይነቶችም ኣካቶ በአገር አቀፍ ደራጃ ተሳታፊ ነበር፡፡

አሁን ባብዛኛው በኣሰልጣኝነት ሞያ የምናያቸው፣ ገ/መድህን ሀይለ(መከላክያ)፣ ፀጋየ ክ/ማርያም(ባንኮች)፣ ንጉሴ ደስታ(ወልድያ) የነዚህ ሁለት ክለቦች ፈርጦች ነበሩ፡፡ይህ ወቅት በቡድኑ ረጅም ታሪክ በንጽጽር የተሻለ የሚባል ዘመን ነዉ፡፡ በአካባቢዉ የነበረዉ ጦርነት ምክንያት ቡድኑ ቢፈርስም፤ 1984 ዓ.ም የመቐለ ከተማ ምክርቤት እንደገና ሲዋቀር የክልሉ ዋና ቡድን ሆኖ ቀጥሎ 1992፣1993 ዓ.ም ላይ ትራንስ ና ጉና ሲመሰረቱ ክለቡ ደብዛው እስኪጠፋ ድረስ የእነዚህ ሁለት ክለቦች መጋቢ ቡድን እንዲሆን ተደርገዋል፡፡

2002 ዓ.ም ላይ ክለቡ እንደገና ሲመሰረት፤ በአመቱ በ2003 ዓ.ም  የብሔራዊ ሊግ ተሳትፎውን ኣረገግጧል፡፡ በእስከአሁኑ ተሳትፎውም ከ2006 ዓ.ም በስተቀር በየዓመቱ ወደ መጨረሻ የጥሎ ማለፍ ውድድር ተሸጋግሯል፡፡ በዘንድሮ 2008 ዓ.ም ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት የሚደረገውን የመጀመርያውን ዙር ውድድር በምድብ 1 ከመሪው ወልድያ ከነማ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ በ3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዘንድሮ ባወጣዉ አዲስ መመርያ መሰረት ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት ከእያንዳንዱ ምድብ ሁለት ቡድኖች ያልፋሉ፡፡ይህም ቡድኑ እያስመዘገበ ካለዉ ዉጤት ባለፈ  ሌላ ተጨማሪ እድሎች ይዞ መጥቷል፡፡

Photo - Mekelle city football stadium
Photo – Mekelle city football stadium

የክለቡ ስራ ኣስከያጅ ኣቶ መኮነን ጎደፋ ይህ ክለብ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት እስካሁን  ያደረጋቸውን ጥረቶች ሲገልፁ፡-

“የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን እስከ 2007 መጨረሻ ድረስ ሲከተለው የነበረው የውድድር ፎርማትና ድባብ እጅግ ጎድቶናል፡፡ አመቱን ሙሉ የለፋንበት፣ ሁለት ሳምንት በሚደረግ ውድድር ተጫዎቾቻችን ከቁጥጥር ውጪ ሁነው ጨዋታው ላይ ከማተኮር ይልቅ አዲስ የሚያስፈርማቸው ክለብ ፍለጋ ሲውተረተሩ የነበሩ ሲሆን ክለቡ ልፋቱ መና ሁኖ አምና በድሬዳዋ አንድም ጨዋታ ሳናሸንፍ ተመልሰናል”፡፡

ክለቡ አሁን ባለው ቁመና ዘመናዊ የሚባል የእግርኳስ አደረጃጀት፤ የፋይናንስ ምንጭ በጣም ውሱን ሲሆን የራሱ የሆነ የትራንፖርት ኣውቶብስ እንኳን የለውም፡፡ እነዚህ ክፍተቶች ለመሙላት ከመስተዳደሩ የሚሰጠውን ገንዘብ በተጨማሪ ባለሃብቶችን እያነጋገሩ እንደሆነና ተክለብርሃን እምባየ ኣውቶብስ ስለመግዛት ቃል እንደገባላቸው ኣቶ መኮነን ገልፀውልናል፡

ይህ የገንዘብ ምንጭን ከፍ ለማድረግ በሚደረግ ጥረት የራሱ የሆነ ጋሬጣዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡የመቐለ ስቴድየም  ግንባታ መጓተት በህዝቡ ዘንድ ያስከተለው ጠባሳና ኣለመተማመን ተመልካቹ እግር ኳስ ክለብን ለመርዳት ሞራል ለያሳጣው ይችላል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሳምንት ሱር ኮንስተራክስን ትግራይን ወክለው የሚወዳደሩ ወልዋሎ፣ ኣክሱምና መቐለ ከተማ እግር ካስ ቡድኖች ለእያንዳንዳቸው 1.5 ሚልዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

መቐለ ከተማ እግር ካስ ቡድን ዘንድሮ እያስመዘገበ ያለው ውጤት አብዛኛውን የከተማዋ እግር ኳስ ተመልካች ያነቃቃ ሆኗዋል፡፡ በኣጠቃላይ በክልሉ ሁለቱ ዘመናዊ ስታድየሞች ከተጠናቀቀ እና ሶስቱ የከፍተኛ ሊግ (ብሄራዊ ሊግ) ቡድኖች ማበረታታት ከተቻለ እግር ኳስ ተመልካች የሚጠብቀው የፕሪምየር ሊግ እና የብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተሳትፎ መመለስ እንደሚቻል የተመልካቹ እምነት ነዉ፡፡
*******

Nebyu Kahssay

more recommended stories