ወደ ምስራቅ እርቆ የተጓዘ ሰው መድረሻው ምዕራብ ይሆናል። በተመሣሣይ፣ የልማትና እድገት መነሻቸው እና መድረሻቸው ነፃነትና ዴሞክራሲ ናቸው። ከአዳም ስሚዝ ካፒታሊዝም፣ ወይም ከፓርክ ቹንግ ሂ (Park Chung Hee) – ልማታዊ መንግስት እስከ መለስ ዜናዊ – ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት፣ የልማትና እድገትን ፅንሰ-ሃሳብ በጥልቀት የመረመረ፤ ልማት ማለት ነፃነት፣ እድገትና ዴሞክራሲ መሆኑን ይረዳል። አንዱ የሌላኛው ማረጋገጫ እንጂ አማራጭ እንዳልሆነ ያውቃል። ልክ እንደ ምስራቅና ምዕራብ አርቆ የመመልከት ችግር ካልሆነ በስተቀር፤ ልማትና ነፃነት፥ ዴሞክራሲና እድገት የአቅጣጫ ወይም የመነሻና መድረሻ ቦታ ልዩነት የላቸውም። ይህ በምናባዊ እሳቤ ላይ የተመሰረተ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ በነባራዊ እውነታ የሚረጋገጥና በዝርዝር ጥናታዊ መረጃ የተደገፈ ነው።

እ.አ.አ ከ2006 – 2010 ዓ.ም ድረስ የእድገትና ልማት ኮሚሽን (Commission on Growth and Development) ሊቀመንበርና ከሌሎች ሁለት የዘርፉ ምሁራን ጋራ በ2001 ዓ.ም በስነ-ምጣኔ (ኢኮኖሚክስ) የአለም ኖቤል ሎሬት አሸናፊ የሆነው ሚካኤል ስፔንስ (Michael Spence) በሰጠው አስተያየት፣ በመጀመሪያ የእድገት ደረጃ ላይ ባሉ ሀገራት (early – stage developing countries) በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት በቅድሚያ የኢኮኖሚ እድገት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቅሳል። ከዚሁ ጋር አያይዞ፣ የአንድ ሀገር ልማትና እድገትን ለማስቀጠል የመንግስት አስተዳደር (Governance) እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይገልፃል።

እንደ ሚካኤል ስፔንስ ያሉ የዘርፉ ምሁራን በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰፀጧቸው አስተያየቶችና ትንታኔዎች በኢኮኖሚ እድገት እና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መካከል ያለውን ተያያዥነት በግልፅ ለይተው አያሳዩም። በተለይ እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራት፤ የህዝቡ ጥያቄ እንዴት ከቁሳዊ ሃብትና ንብረት ወደ ነፃነትና መብት እንደሚሸጋገር፣ ይህንንም ተከትሎ የመንግስት ትኩረት መቼና እንዴት ከኢኮኖሚ እድገት ወደ መልካም አስተዳደር መዞር እንዳለበት በግልፅ መለየት የሚያስችል መስመር ያስፈልጋል። ይህ ፅሁፍ፣ የኢትዮጲያ መንግስት ትኩረት መቼና እንዴት መቀየር እንዳለበት በግልፅ ለመጠቆም አላማ ያደረገ ነው።

የአንድ ሀገር ለውጥና መሻሻል አራት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ እነሱም፡- ህልውና (Survival)፣ እድገት (Growth)፣ ልማት (development) እና ብልፅግና (Evolution) ናቸው። ከሁለት ዓመት በፊት በኢህአዴግ የተዘጋጀ አንድ የስልጠና ሰነድ ውስጥ የኢትዮጲያን የወደፊት የልማትና እድገት አቅጣጫ ለመግለፅ፤ “ደቡብ ኮሪያዎች የረገጡትን ድንጋይ በመርገጥ….” የሚል ሐረግ በተደጋጋሚ መጠቀሱን አስታውሳለሁ። በመሆኑም፣ ደቡብ ኮሪያ ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ በ40 ዓመት ያስመዘገበችውን ለውጥና መሻሻል እና ሀገራችን ኢትዮጲያ ከ1991 (1983 ዓ.ም) ጀምሮ ለ25 ዓመታት ያስመዘገበችውን ለውጥና መሻሻል እንደ መነሻ በመውሰድ፣ እያንዳንዱን የለውጥ ደረጃ በዝርዝር ለማየት ተሞክሯል።

1ኛ፡- ህልውናን ማረጋገጥ

በየትኛውም ሀገር ለውጥና መሻሻል ለማምጣት ቀዳሚው ተግባር የሀገሪቱን አስተዳደራዊ መዋቅር መዘርጋት እንደ አዲስ መዘርጋት ወይም የነበረውን ማሻሻል ነው። ይህ፣ በኢትዮጲያ ከ1991 – 2002 (1983 – 1994 ዓ.ም) ባለው ወቅት የተከናወነ ሲሆን በደቡብ ኮሪያ ደግሞ ከ1961 – 1971 ዓ.ም ድረስ ባለው ግዜ ውስጥ የተከናወነ ነው። የደርግ ሥርዓትን በኃይል አስወግዶ ወደ ስልጣን የመጣው የኢህአዴግ መንግስት የመጀመሪያዎቹን አስር አመታት አዲስ ፖለቲካዊ አስተዳደር ስርዓት በመዘርጋትና ሥርዓቱን ህልውና በመጠበቅ ላይ ተወጥሮ የነበረበት ግዜ ነው። ለምሳሌ፣ በሽግግሩ ወቅት እንደ ኦነግና ኦብነግ ካሉ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር የነበረው ፍጥጫና ግጭት፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ በኢህአዴግ ውስጥ የተከሰተው መከፋፈል እና የመሳሰሉት በመንግስታዊ ሥርዓቱ ህልውና ላይ፣ እንዲሁም በሀገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ የተጋረጡ አደጋዎች ነበሩ።

ለዚህ ፅሁፍ ዋና የኢኮኖሚ መረጃ ምንጭ የሆነው “Trading Economics” ድረገፅ የደቡብ ኮሪያን መረጃ ያጠናቀረው ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ ስለሆነ ሀገሪቱ በመጀመሪያዎቹ አስር አመታት የነበራትን እድገት የሚያሳይ ምስልን ማቀናበር አልተቻለም። በእርግጥ ደቡብ ኮሪያ ከኢትዮጲያ በተሻለ የተማረ የሰው ሃይል ስለነበራት፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ፈጣን እድገት ብታስመዘግብም፣ የግብርናው ዘርፍ ግን በመጀመሪያዎቹ አስር አመታት ውስጥ እድገት እንዳላሳየ የጥናት ውጤቶች ይጠቁማሉ። በአጠቃላይ፣ ደቡብ ኮሪያ ከ1961 -1971 ዓ.ም የነበራት የኢኮኖሚ እድገት ኢትዮጲያ ከ1991 – 2002 (ከ1983 – 1994 ዓ.ም) ከነበራት ጋር ተመሳሳይ ነበረ። ከታች በምስሉ ላይ እንደሚታየው የመጀመሪያዎቹ አስር አመታት የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሁኔታ የሚዋዥቅ እንደነበረ መገንዘብ ይቻላል።

Chart - Ethiopia GDP 1991-2014
Chart – Ethiopia GDP 1991-2014

ምስል 1፡ የኢትዮጲያ አመታዊ የምርት መጠን እድገት፣ ከ1991 – 2014 (1983 – 2007) ዓ.ም. ምንጭ፡ Trading Economics

በኢትዮጲያ የተዘረጋው መንግስታዊ ሥርዓት መስራችና መሪ የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው። በተመሣሣይ፣ በደቡብ ኮሪያ የተዘረጋው የልማታዊ መንግስት መስራችና መሪ በ1961 ዓ.ም በመንፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጡት ፓርክ ቹንግ ሂ ናቸው። እንደ መለስ ዘናዊ፣ ፕረዜዳንት ፓርክ በመጀመሪያ አስር አመታት (1961 – 1971 ዓ.ም) ዋና ትኩረታቸው የሥርዓቱን ህልውና ማረጋገጥ ነበር። የኢኮኖሚ ትብብርና ድጋፍ ለማግኘት፤ ፓርክ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ሀገራት ፊቱን ያዞረበትና መለስ ዜናዊ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ሀገራት የዞረበት ሁኔታ ተመሣሣይ ነው። ሁለቱ መሪዎች የተከተሉት የፋይናንስ ዲፕሎማሲ ስልት ተመሣሣይነት ለማሳየት፤ ፓርክ ከቀድሞዋ ቅኝ-ገዢ ጃፓን እና መለስ ደግሞ ከጣሊያን ጋር የተፈራረሟቸውን የብድርና እርዳታ ስምምነቶች መጥቀስ በቂ ነው።
በአጠቃላይ፣ በመጀመሪያዎቹ አስር አመታት ሁለቱም መሪዎች “ድህነት ዋና ጠላታችን ነው” የሚል አቋም ነበራቸው። ከዚህ በተጨማሪ፣ ድህነትና ኋላ-ቀርነት ስር ላለ ማህብረሰብ ዴሞክራሲ ቅንጦት ነው የሚል እሳቤ ነበራቸው። ፕ/ት ፓርክ በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፤

The gem without luster called democracy was meaningless to people suffering from starvation and despair

ስለዚህ፣ ድህነትን ማስወገድ እስካልተቻለ ድረስ የመንግስታዊ ሥርዓቱን ህልውና ማረጋገጥ አይቻልም። በህልውና ላይ የተጋረጠን አደጋ ለማስወገድ የሚደረግ የሞት-ሽረት ትግል ግን የለውጥ ሂደቱን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ያሸጋግረዋል።

2ኛ፡ የኢኮኖሚ እድገት

በመጀመሪያዎቹ አስር ዓመታት ህልውናን ለማረጋገጥ ያደረጉት ጥረት ሁለቱንም ሀገራት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንዲያስመዘግቡ አስችሏቸዋል። ይህ ወቅት በኢትዮጲያ ከ2003 – 2013 (1995 – 2005) ዓ.ም፣ በደቡብ ኮሪያ ደግሞ ከ1972 – 1982) ያለው ግዜ ነው። በሁለተኛው አስር አመታት፣ የኢኮኖሚ እድገት ዘመን፣ የመንግስትና የህዝቡ ትኩረት በዋናነት በሀገሪቱ የኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ይሆናል። በዚህ ወቅት አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ትኩረቱን የኢኮኖሚ እድገቱ ባስገኘለት ቁሳዊ ሃብትና ንብረት ላይ ይሆናል።

በመሰረቱ፣ እድገት ህልውናን ለማረጋገጥ የሚደረግ ትግል ውጤት ሲሆን በዋናነት የጎንዮሽ መስፋፋት ነው። ይህ ወቅት በኢትዮጲያ ለዘመናት በከተማው ማህብረሰብ ዘንድ ብቻ ተወስነው የነበሩ ማህበራዊ አገልግሎቶች፣ የመሰረተ-ልማቶች አውታሮች እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ወደ አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል፣ ወደ ገጠር የተስፋፉበት ወቅት ነበር። የሀገሪቱ የገጠር የመንገድ፣ ትምህርትና የጤና ሽፋን በከፍተኛ ፍጥነት ያደገበት፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት አውታሮች ግንባታ እና አገልግሎት ለገጠሩ ማህብረሰብ ተደራሽ መሆን የጀመሩበት፣ የግብርና ምርቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረበትና በዚህም የአርሶ-አደሮች እና አርብቶ-አደሮች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያደገበት ወቅት ነበር።

ከታች በምስል-2 ላይ እንደሚታየው፣ ከ2003 (1995) ዓ.ም ጀምሮ ያለው የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት ፈጣንና ብዙም መዋዠቅ የማይታይበት ነው። በተመሣሣይ፣ የደቡብ ኮሪያ ኢኮኖሚ በዋናነት በኤክስፖርት ላይ ያተኮረ መሆኑን ተከትሎ ከ1979 – 81 ዓ.ም በከፍተኛ ግሽበት ምክንያት የኢኮኖሚ እድገቱ ተቀዛቅዞ ነበር። የፓርክ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ከ18 ዓመት በኋላ ያጋጠመው የኢኮኖሚ ግሽበት፣ ኢህአዴግ ከ17 ዓመት በኋላ በ2008 (በ2000 ዓ.ም) ካጋጠመው ከፍተኛ ግሽበት ጋር ተመሳሳይ ነው። ይህ፣ መጠኑ የተለያየ ቢሆንም፣ በሁለተኛው አስር አመት መገባደጃ አከባቢ ሁለቱም ሀገራት ተመሳሳይ የኢኮኖሚ ችግር እንዳጋጠማቸው ያሳያል።

Chart - Comparison of Ethiopia and S. Korea growth rate
Chart – Comparison of Ethiopia and S. Korea growth rate

ምስል 2፡ የደ.ኮሪያ እና የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት ፍጥነት ንፅፅር:: ምንጭ፡ Trading Economics

የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት እስከ 2002 (1994) ዓ.ም ድረስ ከፍተኛ መዋዠቅ የሚታይበት ሲሆን ከዚያ በኋላ ባሉት አመታት ግን መረጋጋት አሳይቷል። በተመሣሣይ፣ በ1980ቹ መጀመሪያ ላይ ካጋጠመው ከፍተኛ መዋዠቅ በስተቀር የደቡብ ኮሪያ ኢኮኖሚ በተመሣሣይ ፍጥነት አድጓል። ሆኖም ግን፣ በሁለተኛው አስር አመት መገባደጃ ላይ የሁለቱም መንግስታት በተመሣሣይ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ይገባሉ። የመጀመሪያው ነገር፣ ሁለቱም ሀገራት የመንግስታዊ ሥርዓት መስራቾች የሆኑትና በሀገሪቱ ፖለቲካ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት፤ ፕ/ር ፓርክ በ1979 ዓ.ም፣ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በ2012 (2004) ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ። ከዚህ በኋላ ባሉት ጥቂት አመታት የሀገራቱ የፖለቲካ ሁኔታ ይቀየራል።

3ኛ፡ ልማትና ነፃነት
የኢኮኖሚ እድገቱ፤ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ያለውን የመረጃ አቅርቦትና አጠቃቀም ያሻሽለዋል፣ ማህበራዊ ግንኙነቱን ፈጣንና ስር-ነቀል ያደርገዋል። በዚህም የሕብረተሰቡ የፖለቲካ ንቃተ-ህሊናን ይጎለበታል። ዜጎች መብትና ግዴታቸውን ማወቅና መጠየቅ ይጀምራሉ። በዚህ ምክንያት፣ በሦስተኛው አስር አመት ላይ የሚነሳውን የለውጥ ወጀብ ዴሞክራሲና የኢኮኖሚ እድገትን እንደ አማራጭ መጠቀም አይቻልም። ለዚህ ደግሞ ሦስት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ።

ሀ) የኢኮኖሚ እድገቱ ፍጥነት በነበረበት ማስቀጠል አይቻልም።
በእርግጥ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እየገዘፈ በሄደ ቁጥር የሚያድግበት ፍጥነት ይቀንሳል። ከላይ በምስል-2 ላይ እንደሚታየው፣ የደቡብ ኮሪያ ኢኮኖሚ እድገት ፍጥነቱን እየቀነሰ እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል። በተመሣሣይ፣ የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት በፍጥነት እያደገ ቢመስልም፣ ቀጥሎ ባለው ምስል-3 ላይ እንደሚትመለከቱት ፍጥነቱን ከወዲሁ መቀነስ ጀምሯል። በመጀመሪያዎቹ አስር አመታት የሚታየው የኢኮኖሚ እድገት በዋናነት ከመንግስት የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያዎች ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው። በመቀጠል፣ በ2ኛው አስር አመት ለሚታየው የኢኮኖሚ እድገት የመንግስት ድጋፍና ማበረታቻ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል። በሦስተኛው አስር አመትና ከዚያ በኋላ ባሉት አመታት ግን መንግስት ድጋፍና ማበረታቻ የመስጠት አቅሙ እየቀነሰ ይመጣል። ከዚህ በኋላ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መሰረቱ አዳዲስ ፈጠራዎችና ቴክኖሎጂዎች፣ የምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ አሰራሮች እና አደረጃጀቶች ይሆናሉ።

Chart - Ethiopia GDP growth 2003 -2014
Chart – Ethiopia GDP growth 2003 -2014

ምስል 3፡ የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ እድገት፣ ከ2003 – 2014 (1995 – 2006) ዓ.ም:: ምንጭ፡ Trading Economics

ለ) ተከታታይ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት የሚጨምረው እሴት ዝቅተኛ ይሆናል
ሁለቱም መንግስታት የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል ጠንክረው እየሰሩ ቢሆንም፣ የህዝቡ ጥያቄ ግን ከቀድሞው የተለየና ሰፊ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ላይ የታየው ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ቁሳዊ ሃብትና ንብረት በሕብረተሰቡ ዘንድ የነበራቸውን ዋጋ ያሳጣቸዋል። አንድ ደቡብ ኮሪያዊ በወቅቱ በዚህ ወቅት ስለነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ባደረገው ጥናት የሚከተለውን የማጠቃለያ ሃሳብ አስቀምጧል፣

“…it can be generalized that a bureaucratic authoritarian regime will not be efficient unless it can co-opt societal interests, especially when prolonged economic success nullifies the effectiveness of material gains at the cost of political freedom”

ሐ) ዴሞክራሲ በራሱ የኢኮኖሚውን እድገትን ለማስቀጠል ዋና ግብዓት ስለሆነ
የኢኮኖሚ እድገቱን ከማስቀጠል ጋር ተያይዞ በተራ.ቁ (ሀ) ላይ እንደተገለፀው፣ ከሦስተኛው አስር አመት በኋላ የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት በዋናነት በአዳዲስ ፈጠራዎችና ቴክኖሎጂዎች፣ የምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ የተሻሻሉ የአሰራር ዘዴዎች እና አደረጃጀቶች ላይ የተመሰረተ ነው። መንግስት ምንም ያህል በጀትና ድጋፍ ቢያደርግ ዜጎች አዳዲስ ፈጠራዎች፣ ቴክኖሎጂዎች እና አሰራሮችን እንዲፈጥሩ ማድረግ አይችልም። ነፃ የመረጃ ፍሰት በሌለበት፣ ሃሳብን በነፃ መግለፅ በማይቻልበት እና በራስ ፍላጎትና ምርጫ መንቀሳቀስ በማይቻልበት ሁኔታ ለአዳዲስ ፈጠራዎች ምቹ የሆነ አከባቢ መፍጠር አይቻልም። በመሆኑም፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ እንደ አማራጭ የሚቀርብ ሳይሆን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገቱ የማስቀጠል ወይም ያለማስቀጠል ጥያቄ ነው።

4ኛ፡- ብልፅግና 
ብልፅግና፤ 1ኛ ደረጃ ላይ የመንግስታዊ ሥርዓቱን ህልውና በማረጋገጥ፣ 2ኛ ደረጃ ላይ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ፣ እንዲሁም 3ኛ ደረጃ ላይ የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመዘርጋት የሚመጣ ሥር-ነቀል ለውጥ ነው። በዚህ ረገድ፣ አብዛኞቹ ሀገራት “መካከለኛ ገቢ ያላቸው…” የሚለውን ማነቆ ማለፍ ሲሳናቸው፣ ደቡብ ኮሪያ ግን ይህን ገደብ አልፋ “ከበለፀጉ ሀገራት” ተርታ ለመሰለፍ በቅታለች። ከ29 ዓመት በፊት ለደቡብ ኮሪያ መሪዎች ከህዝቡ የቀረበላቸው ጥያቄ፣ አሁን ለደረሱበት የብልፅግና ደረጃ የመሆንና ያለመሆን ጥያቄ ነበር። በወቅቱ የነበሩት የሀገሪቱ መሪዎች የህዝቡን ጥያቄ በሚገባ ተረድተው ፈጣንና ተግባራዊ ምላሽ መስጠት በመቻላቸው የዛሬዋን የበለፀገች ደቡብ ኮሪያ መገንባት ችለዋል።

ማጠቃለያ
በ1987 በደቡብ ኮሪያ 3ኛው የለውጥ ማዕበል ሲነሳ የሀገሪቱ መንግስት ለችግሩ ምላሽ የሰጠው “June 29 Proposal” በመባል የሚታወቀው ሰነድ በማዘጋጀት ነው። ይህ ሰነድ ለህዝቡ ጥያቄ ቀጥተኛ እና ተግባራዊ የሆነ ምልሽ የሰጠ ሲሆን በውስጡ የሚከተሉትን ስምንት (8) ነጥቦችን የያዘ ነበር። (የፅንሰ-ሃሳብና የአውድ ልዩነት እንዳይፈጠር በሚል በእንግሊዘኛ የተፃፈውን እንዳለ ማቅረብ ይመረጣል።)

“the peaceful transition of government through a direct presidential election based on new constitution; fair election procedures; amnesty of a popular opposition leader Kim Dae·Jung and the restoration of his rights and the release of political prisoners; enhancement of human rights; freedom of speech and press; formation of local assembly and democratization of university administration; responsible and harmonious party politics; social purification for a healthy society

በ1987 ዓ.ም የደቡብ ኮሪያ መንግስት ከህዝቡ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የዘረዘራቸው ስምንት ነጥቦች፣ ያለ ምንም መዛነፍ፣ አሁን የኢትዮጲያ ህዝብ እያነሳቸው ካሉት ጥያቄዎች ጋር ተመሣሣይ ናቸው። ከ2013 (2006) ዓ.ም ጀምሮ ከህዝቡ እየተነሳ ያለው የለውጥ ጥያቄ እና በደቡብ ኮሪያ በ1987 ዓ.ም የተነሳው የህዝብ ጥያቄ ጋር ፍፁም ተመሳሳይ ነው። በሁለቱም ሀገራት የዴሞክራሲ ጥያቄ የተነሰው በመጀመሪያ ከዩንቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ሲሆን፣ በመቀጠል ወደ ብዙሃኑ የሀገሪቱ ሰርቶ-አደሮች እና አርሶ-አደሮች እየተስፋፋ ነው የሄደው። የደቡብ ኮሪያ መንግስት በወቅቱ የወሰደው እርምጃ፣ መንግስታዊ ሥርኣቱን ከአምባገነናዊነት ወደ ዴሞክራሲያዊነት ቀይሮታል፣ ሀገሪቱንም ከታዳጊነት ወደ ብልፅግና አሸጋግሯታል።

በአጠቃላይ፣ ግዜውና ቦታው የተለያየ ይሁን እንጂ፣ በደቡብ ኮሪያ ተነስቶ የነበረው የዴሞክራሲ ጥያቄ ዛሬ በኢትዮጲያ ተነስቷል። ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ከህዝቡ ለተነሱት ጥያቄዎች በተመሣሣይ ሁኔታ ምላሽ መስጠት ከቻለ ራሱን ወደ ዴሞክራሲያዊ መንግስት የማሸጋገር እድል ይኖረዋል። በእርግጥ “ደቡብ ኮሪያዎች የረገጡትን ድንጋይ መርገጥ…” ማለት ይኼ ነው። ደቡብ ኮሪያዎች ከደረሱበት የብልፅግና ደረጃ ላይ ለመድረስ እነሱ በድፍረት የወሰዷቸውን እርምጃዎች ለመውሰድ ቁርጠኝነት ይጠይቃል።

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories