የዱር እንስሳትን አብዝቶ የሚወድ አንደ ሰው ነበር አሉ፡፡ ይህ ሰው ይሄንን ፍቅሩን የሚያስታግሰው ወደ እንስሳት መኖሪያ ፓርክ በመሄድ ነበር፡፡ እናም አንድ ቀን እንደለመደው ወደ አንድ የእንስሳት መጠለያ አመራ፡፡

በዚያ የእንስሳት ፓርክ ውስጥም አይኑ አንድ አስገራሚ ነገር ላይ ያርፋል። በጣም ትልቅና ግዙፍ ዝሆን በትንሽ ቀጭን ገመድ ታስሮ ቆሟል። ስላየው ነገር ተገርሞ የፓርኩን አስጎብኚ ጠየቀው “እንዴት ይህ ግዙፍ ዝሆን በቀጭን ገመድ ታስሮ ሊቆም ቻለ? ለምንስ ሊበጥሰው አይሞክርም?” ሲል ጠየቀው፡፡

አስጎብኚውም “ዝሆኑ ከህፃንነቱ ጀምሮ በዚህ ገመድ እየታሰረ ነው ያደገው፡፡ እርግጥ አንተም እንዳልከው በዛን ወቅት ሊበጥሰው ይሞክር ነበር፤ በቅጡ መጓዝ እንኳን ያልጀመረ ስለነበር ግን ሊበጥሰው አልቻለም። አሁን ግን እንደምታየው ዝሆኑ ግዙፍ ሆኗል፡፡ ትንሽ እርምጃ ወደፊት ቢጓዝ ይበጥሰዋል፤ ነገር ግን የአልችልም መንፈስ ውስጡ አብሮት ስለአደገ አይሞክረውም” አለው ይባላል።

የአገራችን የድህነት ታሪክም ከተረቱ ጋር ብዙ የሚያመሳስለው ነገሮች አሉት፡፡ ታላቅ ህዝብና አገር የነበርን እኛ አንድም እርስ በእርስ በመናቆር አንድም በሌላ በሌላ ምክንያቶች ከነበርንበት የታላቅነት ማማ ቁልቁል ተምዘግዝገን በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን ኖረናል፡፡ ይህንን የተሸከምነውን የድህነት ቀንበር አሽቀንጥረን ለመጣል እንደ ዝሆኑ ሁሉ የአልችልም መንፈስ ተጠናውቶን አመታት አስቆጥረናል፡፡

ዝሆኑ ካለው ጉልበት እና ሃይል ይልቅ ውስጡ የያዘው የአልችልም እምነት ገዝፎ እድሜ ልኩን ታስሮ እንዲኖር አድርጎታል። የእኛም የድህነት ታሪክ ተመሳሳይ ነው፡፡ አስሮ ከያዘን ድህነት ይልቅ ያለን እምቅ ሀብትና ብዝኃነት ብዙ ጊዜ ይልቃል፡፡ ነገር ግን ድህነትን አሜን ብለን ተቀብለን የማይነካ የማይናድም ጋራ አድርገነው ቁጭ ብለን ኖረናል፡፡ ምስጋና ለታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ይሁንና እነሆ የተሸከምነው ድህነት ካለን ሀብት አንጻር ኢምንት መሆኑን በተግባር አሳይተውን የድህነትን ጋራ መናድ ጀምረናል፡፡ አሁን እኛን አስሮ የያዘን የድህነት ገመድ ዝሆኑን አስሮ እንደያዘው ቀጭን ገመድ፣ እኛም እንደ አገር የዝሆኑን ያህል የገዘፍን መሆናችንን ተረድተናል፡፡ ስለሆነም ወደፊት ከመራመድ የሚመልሰን ይኖር ብዬ አላምንም፡፡ ነገሩ የነብርን ጅራት አይዙ…ነው፡፡

Photo - Grand Ethiopian Renaissance Dam, 2016. [Photo: Reuters/Tiksa Negeri]
Photo – Grand Ethiopian Renaissance Dam, 2016. [Photo: Reuters/Tiksa Negeri]

ሌላው የአንችልም መንፈስ ተብትቦ ይዞን በቁጭት ብቻ እንድንኖር አድርጎን የኖረው የአባይ ወንዝ ልማት ነው፡፡ ይሄን ወንዝ መገደብና ማልማት ያልተመኘ፣ ያልወጠነም መሪ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የአንችልም መንፈስ ከልማት ፍላጎቱ በላይ ልቆ ኖሮ ለዘመናት በህልምና በቁጭት ብቻ እንድንኖር ተገደናል፡፡ አሁንም ምስጋና ለታላቁ መሪያችን ይሁንና ያለን ሀብት አስሮ ከያዘን የድህነት ገመድ እንደሚልቅ በተግባር ግንባታውን አስጀምረው አሳይተውናል፡፡ ዛሬ የግድባችን ግንባታ ከግማሽ በላይ ተጠናቋል፡፡ የግድቡ ግንባታ ይፋ ሲሆን እዚህ ይደርሳል ብሎ ያመነ ሰው ይቅርታ ይደረግልኝና እጅግ አነስተኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እንደ እኔ አይነቱ ተራ ዜጋ አንድም በቀደመው የአንችልም መንፈስ ተመርቶ ወይንም ደግሞ በአካባቢው የውሃ ፖለቲካ ስጋት ገብቶት ግድቡ እዚህ አይደርስም ብሎ ቢያምን ቢናገርም በጀ ይባል ይሆን ይሆናል፡፡ ነገር ግን አገር እንመራለን ትውልድም እንቀርጻለን ከሚሉ ታላላቅ የፖለቲካ ሰዎችና ምሁራን አንደበት ግድቡ አይሳካም የሚል ተስፋ አስቆራጭ  ንግግር ማድመጥ፣ አቋማቸውንም መመልከት ያስተዛዝባል፡፡ የሆነው ግን ይኸው ነው፡፡

የግድቡ መጀመርን አስመልክቼ ከአራት አመት በፊት ያነጋገርኳቸው ፖለቲከኞችና ምሁራን በወቅቱ የሰጡኝን ምላሽ ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው እኔም ብቻ ሳልሆን እነሱንም የሚያሳቅቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ከአራት አመታት በፊት እነዚህ ኢትዮጵየዊያን ግድቡ የሚሳካ ፕሮጀክት አይደለም፡፡ በጭራሽ አይሳካም፡፡ በአስር አመት ውስጥ እንኳን አያልቅም፡፡ ወያኔ ዝም ብሎ ይሄንን የማይወጣውን ፕሮጀክት ከመጀመር ይልቅ በአባይ ላይ የተለያዩ አነስተኛ ግድቦችን ቢገነባ ይሻለው ነበር፡፡ የህዝቡን የዴሞክራሲ ጥያቄ ለማስቀየስ ሲባል ግድቡን መገንባት ተጀመረ እንጂ ታስቦበት የተጀመረ ፕሮጀክት አይደለም…ሌላም ሌላም፡፡

እናንት ምሁራንና ፖለቲከኞች ሆይ፣ ዛሬስ ግድቡ የሚሳካ አይመስላችሁም ይሆን? ወይንስ አሁንም በቀደመው አቋማችሁ ላይ ናችሁ? መቼም በእናንተ መንደር የአቋም ለውጥ ማድረግና መተጣጠፍ የተለመደ ስለሆነ አሁን ላይ የምትሉት ቀድሞ ካላችሁት የተለየ እንደሚሆን እምነቴ ነው፡፡

ለማንኛውም ግን አሁንም ጊዜው አልረፈደምና  ቢያንስ ቢያንስ እጃችሁን ወደ ኪሳችሁ ጨምሩና አሻራችሁን በግድቡ ላይ አኑሩ፡፡ ግደቡ እንደሆነ ማለቁ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ በኋላም የመጣነውን ያህል አይከብደንም፡፡ ስራው ቁልቁለት ነውና፡፡ እኛን የከበደን የእናንተ በአገር ጉዳይ ላይ ከመንግስት ጋር በጋራ የምትቆሙበት ቀን መቼ እንደሆነ ማወቁ ነው፡፡ ለመሆኑ ከአባይ ሌላ አንድ ሊያደርግ የሚችል ፕሮጀክት ወደፊት ይመጣ ይሆን? አይመስለኝም፡፡ ከመጣም እንደተባለው ከአባይ ያነሰ እንጂ ከአባይ የሚልቅ አይሆንም፡፡ ስለሆነም በትልቁ ፕሮጀክት ትልቅነታችሁን ካላሳያችሁ በትንንሾቹ ላይ ከመንግስት ጎን ብትቆሙ ትንሽ አሳቢዎች፣ ትንሽም አላሚዎች መሆናችሁን ከማሳበቅ ሌላ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡

እያልኩ ያለሁት ግልጽ ነው፡፡ ለምን መንግስትን ተቻችሁት አይደለም፡፡ ከቻላችሁ መንግስትን እስከ አንገቱ ድረስ ተቹልን፡፡ አቅም ካለ ማለቴ ነው፡፡ ነገር ግን በስመ ትችት መደገፍ እንጂ መተቸት የሌለባችሁን የአባይን ፕሮጀክት ለምን ተቃወማችሁት?  ለምንስ አይሳካም ስትሉ አሟረታችሁብን? ነው፡፡

መሆን የነበረበት እንዲህ ነበር፡፡

መንግስት ግድቡን መስራት ባይጀምርና ኢኮኖሚው አድጓል እያለ ቢናገር እናንተ ቀበል አድርጋችሁ “ኢኮኖሚው ካደገ የዘመናት የህዝብ ቁጭት የሆነውን አባይን ለምን መገደብ ተሳነህ?” ብትሉ እጅግ ትክክል ትሆኑ ነበር፡፡ ክርክራችሁም ውሃ የሚቋጥር ትችታችሁም ተገቢ ይሆን ነበር፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ግነ ትችቱና ክርክሩ የተገላቢጦች ሆኗል፡፡

የመብራት መቆራረጥና መጥፋት ችግርን አምርሮ የሚቃወም ሰው እንዴት ብሎ ለችግሩ የቀረበን አይነተኛ መፍትሄ ይቃወማል? ነገሩ ግራ የሚያጋበ አይነት ነው፡፡

ለማንኛውም አሁንም ከመቅረት ማርፈድ ይሻላልና ምንም ብትዘገዩም ከእነ አካቴው ከምትቀሩ ግድቡን የተቃወማችሁ የአገራችን ምሁራንና ፖለቲከኞች ህዝቡንና መንግስትን በጊዜ ይቅርታ ጠይቃችሁ ከጎናችን ሁኑ፡፡ መንግስትም በሆደ ሰፊነት ህዝቡም ቢሆን በአርቆ አሳቢነት ይቅር እንደሚሏችሁ እምነቴ ነው፡፡

**********

Areaya Getachew (MA) is a public relations expert at a foreign embassy. He studied second degree at Addis Ababa University and was deputy editor in-chief of Addis Zemen newspaper.

more recommended stories