በእርግጥ አነሳሴ፣ በሀገራችን ያለውን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ሰሞኑን ኢትዮ-ቴሌኮም እየወሰዳቸው ባሉት እርምጃዎች ዙሪያ የዳሰሳ ፅሁፍ ለማቅረብ ነበር። የዓለም የቴሌኮምዩኒኬሽን ማህበር (ITU) በ2015 የፈረንጆች አመት ያወጣውን ሪፖርት በወፍ-በረር እያነበብኩ ነበር። የአለም ሀገራት በዘርፉ ያላቸውን የልማት ደረጃ ከሚያሳው ሰንጠረዥ ውስጥ ኢትዮጲያን ከላይ ወደ ታች እየወረድኩ ብፈልጋት አጣኋት። ፍለጋዬን ከታች ወደ ላይ አድረኩ። 167ኛ፡ ቻድ፣ 166ኛ፡ ኤርትራ፣ 165ኛ፡- …. “ውይ! የእኛው ጉድ! እዚህ ነሽ’ዴ፣ …እንዲህ የአለም ጭራ ያደረገሽ ድህነት ጠባሳ መቼ ይሆን የሚጠፋው?” ሪፖርቱን ማንበብ ቀጠልኩ።

ከዚያ ቀጥሎ ግን አይኔን ከ ሪፖርቱ አንድ ዓረፍተ ነገር ላይ መንቀል አቃተኝ – “በኢትዮጲያ ለዘርፉ እድገት ዋና ማነቆ የሆነው ‘ድህነት’ ሳይሆን መንግስት ነው።”

የዚህን ዓረፍተ ነገር ፅንሰ-ሃሳብ ለመረዳት…. መንግስት፣ ኢትዮ-ቴሌኮም፣ ማህበራዊ ድረገፆች፣ ስማርትፎኖች፣ የሞባይል ስልክ፣ የመስመር ስልክ፣ የወረቀት ሚስ-ኮል፣ ልፈፋ-ጥንታዊ ገመድ-አልባ ስልክ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ የምዕራባዊያን ሥልጣኔ… እያልኩ ማብሰልሰል ቀጠልኩ። በመጨረሻ፣ በሦስት ቀናት ውስጥ ሦስት ክፍለ ዘመን ወደኋላ ተጉዤ ከምዕራባዊያን የሥልጣኔ መሰረት ደረስኩ። አሁን ግን ወደ ዛሬ ዞሬ እየመጣሁ ስለሆነ፣ ለምን እግረ-መንገዴን በዙሪያዬ ያለውን እየነገርኳቸው አልመጣም?

አሁን የምገኝበት 18ኛው ክፍለ ዘመን ሕይወት እንደ ኩሬ ውሃ ዘገምተኛ ናት። የሰዎች ኑሮ በቦታና ግዜ ተፈጥሯዊ ገደቦች የተገደበ ነው። ወደ 19ኛው ክ.ዘመን አከባቢ ስደርስ፣ ቀድሞ በዝግመት የታጠረው ሕይወት በመካናይዜሽን (mechanization) ጉልበት እየፈጠነ መጣ። በእርግጥ በመካናይዜሽን ላይ የተመሰረተው የምዕራባዊያን ሥልጣኔ የቦታና ግዜ ተፈጥሯዊ ገደቦችን በማስወገድ ዝግመትን የመቀነስ ወይም ፍጥነትን የመጨመር አላማ አለው። ይህን፣ እኔ ያለሁበትን የ19ኛ ክ.ዘመን እና እናንተ ያላችሁበትን 21ኛ ክ.ዘመን ነባራዊ እውነታዎችን በንፅፅር በማየት መገንዘብ ይቻላል። ለምሳሌ፡- የእናንተ መብራት እዚህ ካለው ሻማ በተሸለ ረጅም ግዜ ያገለግላል፤ ሰፊ ቦታ ይዳረሳል፣ የእናንተ የማምረቻ መሣሪያ (machine) እዚህ ከሚሰራበት የሰው ጉልበት ብዙ እጥፍ በአጭር ግዜና ቦታ ያመርታል፣ የእናንተ መኪና እዚህ ካለው ፈረስ በአጭር ግዜ ረጅም ርቀት ይጓዛል፣ የእናንተ ሞባይል ስልክ እዚህ ካለው “ልፈፋ”በአጭር ግዜ ብዙ ቦታ መልዕክት ማስተላለፍ ይችላል፣ … ወዘተ። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው፣ የምዕራባዊያን ሥልጣኔ የመጨረሻ ውጤት “ፍጥነት” ነው።

Photo - smart phones

ፍጥነት (Speed) በተወሰነ የግዜ ሰዓት ውስጥ ያለን የቦታ ሽፋን (distance/time) ነው። የሰው-ልጅ ያሉበትን የቦታና የግዜ ተፈጥሯዊ ገደቦች ሙሉ-በሙሉ ማስወገድ አይችልም። ሆኖም ግን፣ ሥልጣኔ ያፈራቸውን አዳዲስ ፈጠራዎች እና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ ከቦታና ግዜ አንፃር ያሉበትን ውስንነቶች ለመቀነስ የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል። አሁን ከእናንተ ዘንድ የሚገኙ አዳዲስ ፈጠራዎች፣ ለውጦችና መሻሻሎች በሙሉ ቀድሞ እዚህ የነበረውን አዝጋሚ ሕይወት ለማፍጠን በሚደረግ ጥረት የተገኙ ናቸው። በአጠቃላይ፣ በዘመናዊ ሥልጣኔ የታዩት ለውጦችና መሻሻሎች የሰው ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚቀንሱ አዝጋሚ ነገሮችን ለመቀነስና ፍጥነትን ለመጨመር በተደረጉ ቀታይ ጥረቶች የተገኙ ናቸው።

የፍጥነት የመጨረሻ ግብ የሰው-ልጅ ያሉበትን ተፈጥሯዊ ገደቦች ሙሉ-በሙሉ በማስወገድ በሁሉም ግዜና ቦታ መገኘት መቻል ነው። በዚህም፣ ለዘላለም (Eternity) በሁሉም ቦታ መገኘት (Omnipresent) መቻል፣ ከፈጣሪ እኩል “ምሉእ ነፃነት” እንደ መጎናፀፍ ነው። ሥልጣኔ “የሰው-ልጅን ከፈጣሪ እኩል ምሉእ ነፃነት ሊያጎናፅፈው ይችላል” ብሎ በድፍረት መናገር ይከብዳል። ሆኖም ግን፣ “ነፃነት” (Liberty) የሥልጣኔ መነሻና መድረሻ፣ የሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ስለመሆኑ እርግጥ ነው። ነፃነት በራስ ምርጫና ፍላጎት መሰረት፣ በሁሉም ግዜና ቦታ መንቀሳቀስ መቻል ነው። ከዚህ በተቃራኒ፣ ዝግመት በራስ ምርጫና ፍላጎት የሚደረግ እንቅስቃሴን መግታት፣ የሥልጣኔ እንቅፋትና ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር ተፃሪሪ የሆነ ነገር ነው።

ከሥልጣኔ – ፍጥነት፣ ከፍጥነት – ነፃነት በፍጥነት እየሮጥኩ የ19ኛው ክ.ዘመን አጋማሽ ላይ ደርሼያለሁ። አሁን ካለሁበት የ150 ዓመታት ርቀት ላይ ሆኜ ደብዳቤ ከመላክ፣ በልፈፋ ዘዴ የድምፅ መልዕክት ወደ እናንተ መላክ እችላለሁ። በእርግጥ፣ ብዙዎቻችሁ አፄ ሚኒሊክ የመስመር ስልክ ወደ ሀገራችን ከማስገባታቸው በፊት “ልፈፋ” የሚባል “ገመድ-አልባ የድምፅ መልዕክት ማስተላለፊያ ዘዴ” እንደነበር የምታውቁ አይመስለኝም። ስለዚህ፣ እስኪ ስለ ልፈፋ ትንሽ ላጫውታችሁ።

አሁን የሰሜን ወሎ ተራራዎችን ቁልቁል እየተመለከትኳቸው ነው። በዚህ አከባቢ በስፋት አገልግሎት ላይ ይውል የነበረው ልፈፋ፣ በከፍተኛ የጩኸት ድምፅ መልዕክትን እየተቀባበሉ በማስተላለፍ ከታሰበለት ሰው ዘንድ እንዲደርስ የማድረግ ዘዴ ነው። ለምሳሌ፣ የአንድ የአከባቢው ነዋሪን ዜና ዕረፍት ሌላ አከባቢ ላለ ግለሰብ ለማድረስ ሲፈለግ፣ የመልዕክቱ ላኪ (ደዋዩ) በሰፈሩ ካለ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ይወጣና “እከሌ የተባለ ሰው ሞቷል ብለህ ለአያ እከሌ ንገር” ብሎ ከርቀት ላለ ሰው ጮሆ ይናገራል፣ መልዕክቱን የተቀበለው ግለሰብ’ም በተራው ለሌላ ከርቀት ላለ ሰው ይስተላልፋል። በዚህ መልኩ፣ በአካል ቢሆን ከአንድ ቀን በላይ የእግር ጉዞ ይወስድ የነበረን መልዕክት የልፈፋ ዘዴን በመጠቀም በሰዓታት ውስጥ ማስተላለፍ ይቻል ነበር።

ስለ ልፈፋ ልምዱን እንዲያካፍለኝ የጠየቅኩት አንድ የወልዲያ አከባቢ ተወላጅ፣ “በልፈፋ ዘዴ ከ50 – 60 ኪ.ሜ ርቀት ድረስ የድምፅ መልዕክት ማስተላለፍ እንደሚቻል ገልፆልኛል። ከዚህ በተጨማሪ፣ እንያንዳንዱ የሕብረተሰቡ አባል የሰማውን የድምፅ መልዕክት ተቀብሎ የማስተላለፍ ማህበራዊ ግዴታ ያለበት ሲሆን፣ ግዴታውን ያልተወጣ ግለሰብ በሀገር ሽማግሌዎች ይወቀሳል፥ ይቀጣል” ብሎኛል። ከዚህ አንፃር፣ ጥንታዊው የልፈፋ ዘዴ ከአሁኑ ኢትዮ-ቴሌኮም የተሻለ ተጠያቂነት እንደነበረበት መገመት አይሳናችሁም።

ይኸው ወደ ዛሬ እየገሰገስኩ ነው። ከ125 ዓመት በፊት ወደ ሀገራችን በገባው ዘመናዊ የስልክ ቴክኖሎጂ እያናገርኳችሁ ነው። በእርግጥ፣ከልፈፋ ዘዴ የሚለየው ዋና ነገር “ፍጥነት” ነው። ከግዜ አንፃር፣ በእግር ጉዞ ቀናት ይወስድ የነበረን ተግባር ልፈፋ ወደ ሰዓታት፣ የመስመር ስልክ ደግሞ ግዜውን ወደ ደቂቃና ሰኮንድ ዝቅ አድርጎታል። በተመሣሣይ፣ በአንድ አከባቢ ብቻ ውስን ከነበረው የልፈፋ ዘዴ አንፃር የመስመር ስልክ የድምፅ መልዕክትን በአለም ዙሪያ ማድረስ አስችሏል። የመልዕክቱ ፍጥነት ቢጨምርም፣ “በሁሉም ግዜና ቦታ መገኘት” ከሚለው የፍጥነት ግብ አንፃር ብዙ ይቀረዋል።

እንሆ እየገሰገስኩ መጥቼ 1990ቹ የመጀመሪያ አመታት ላይ ደርሼ፣ ለትምህርት ወደ ሐረር፣ ሃሮማያ ዩንቨርሲቲ ሄጄያለሁ። ከ1990 በፊት የጎረመሰ የነበረ በሙሉ፣ በጎረቤት ልጅ ወይም በወረቀት “ሚስ-ኮል” አድርጓል ወይም ተደርጎለታል። የመጀመሪያው “እንትና…ስልክ!” የሚል የጎረቤት ልጅ ድምፅ ነው። የወረቀት “ሚስ-ኮል” ደግሞ ምን አይነት ነው። የአንደኛ ዓመት የካምፓስ ተማሪ ሆኜ፣ አንድ ሁላችንም ዘወትር የምጎበኛት የማስታወቂያ ቦርድ እንደነበረች አስታውሳለሁ። ታዲያ፣ በዚያን ግዜ ስልክ የሚደወለው እንደ ዛሬ በፈለጉት ግዜና ቦታ አይደለም። በቅድሚያ ቤተሰብ በዩኒቨርሲቲው የስልክ ቁጥር ይደውልና “እከሌ የተባለውን ተማሪ ለማነጋገር ስለምፈልግ በዚህ ሰዓት ይቅረብልኝ” ብሎ ቀጠሮ ያስይዛል። በመቀጠል፣ የስልክ ኦፕሬተሯ “የስልክ ቀጠሮ ያላቸሁ ተማሪዎች” የሚል ማስታወቂያ ቦርዷ ላይ ትለጥፋለች። ወደ 5000 ለሚጠጋ ተማሪ የሚደወለው በሁለት የስልክ መስመሮች ስለነበረ በቀጠሮው ሰዓት የስልክ መስመሩን ማግኘት በራሱ እድል ይጠይቃል። ብዙው ተማሪ ከኦፕሬተሯ ዘንድ ሄዶ እድሉን እያማረረ ሲመለስ፣ ጥቂቶች ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አጭር ሰላምታና መልዕክት ይለዋወጣሉ።

የመስመር ስልክ ያለበት በዋናነት ከቦታ ሽፋን ጋር የተያያዘ ውስንነት ነው። ምክንያቱም፣ የመስመር ስልክ በዋናነት በመኖሪያ ቤት እና መስሪያ ቤት ውስጥ የተወሰነ ስለሆነ አገልግሎቱን በተፈለገው ግዜና ቦታ ማግኘት አይቻልም። ይህን ውስንነት ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት በመጀመሪያ የመንገድ ላይ ስልክ፣ ቀጥሎ ገመድ-አልባ የሳተላይት ስልክ፣ በመጨረሻም የሞባይል ስልክ ተፈጠረ። በተለይ የሞባይል ስልክ ከቦታ አንፃር የነበረውን ውስንነት በማስወገድ፣ ከድምፅ በተጨማሪ የፅሁፍ መልዕክትን በተፈለገው ቦታና ግዜ መለዋወጥ አስችሏል።

የሞባይል ስልክ ወደ ሀገራችን ኢትዮጲያ ከገባበት እ.ኢ.አ 1991 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አስር አመታት የድምፅና የፅሁፍ መልዕክት ማስተላለፊያ መሳሪያ ከመሆን ያለፈ ሚና አልነበረውም። ከዚያ ቀጥሎ ባሉት አመታት፣ በዋናነት የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት መሰጠት ከተጀመረ በኋላ ግን፣ የሞባይል አገልግሎቱ ከመልዕክት ማስተላለፊያነት ያለፈ ሆነ። በተለይ፣ የ”3G” እና “4G” ኔትዎርኮች መስፋፋት እና ዘመናዊ የሆኑ ስማርትፎኖች “Smartphones” መምጣት ቀድሞ የነበረውን አገልግሎት ፍጹም ቀይሮታል።

እስከ አሁን እንደ ነገርኳችሁ፣ ሥልጣኔ የሰው-ልጅ ያሉበትን ተፈጥሯዊ ውስንነቶች ለመቀነስ፣ በተግባራዊ እንቅስቃሴው ፍጥነትን ለማሳደግ የሚደረግ፣ በአጠቃላይ፣ ለነፃነት የሚደረግ ትግል ውጤት ነው። ከጥንታዊው የልፈፋ ዘዴ ተነስቶ ዘመናዊው ስማርትፎን ላይ ለመድረስ የተደረጉት ለውጦች፣ ፈጠራዎች እና መሻሻሎች የዚህ የማያቋርጥ ጥረት ውጤት ናቸው። ይህን የለውጥ ሂደት ለመግታት ወይም ለማዝገም የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ሙከራ ለሥልጣኔ እንቅፋት፣ የለውጥና መሻሻል ማነቆ ነው። እንዲህ፣ ከሰው-ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ተፃራሪ የሆነ ማንኛውም ተግባር “ዝግመት” ይባላል።

ይኸው ትላንት ላይ ደርሼያለሁ። አንድ ዘመናዊ ስማርትፎን’ም በእጄ ይዤያለሁ። ይህ ስልክ፣ እንደ አንድ ተንቀሳቃሽ የመልዕክት ማስተላለፊያ መሳሪያ መታየት የለበትም። ምክንያቱም፣ ለእኔ ይህ ስማርትፎን፡ “ኮምፒውተር፥ ፎቶ ካሜራ፥ ቪዲዮ ካሜራ፥ ፎቶ-ኮፒ፥ ስካነር ማሽን፥ ፋክስ ማሽን፥ ቴሌቪዥን፥ ሬድዮ፥ መፅሃፍት፥ ጋዜጣ፥ መፅኄት፣…የድምፅ፥ የፅሁፍ፥ የምስል፥ የዕቃ መላኪያና መቀበያ መሳሪያ፣ …የፅህፈት መሳሪያ፥ የሂሳብ መሳሪያ፥ የመጫዎቻ መሳሪያ፣ ቤተ-መፅሃፍት፣ ባንክ ቤት፥ መዝገብ ቤት፥ ትምህርት ቤት፥ ፍርድ-ቤት፣ … የትምህርት መሳሪያ፥ የመገናኛ መሳሪያ፣ የፖለቲካ መሳሪያ፥ የጦር መሳሪያ፣ …የስነ-ጥበብ መድረክ፥ የኢኮኖሚ መድረክ፥ የፖለቲካ መድረክ፥ ማህበራዊ መድረክ፥…ወዘተ በአንድነት የያዘ ሁለገብ መሳሪያ ነው። ሁሉንም ነገር በአንድ ቦታ ላይ ለማግኘት ወይም በሁሉም ቦታ በአንድ ግዜ ለመገኘት እንዲቻል የተፈጠረ ስለሆነ ስማርትፎን በራሱ “ፍጥነት” ነው።

ሃይ!…እንዴት ናችሁ! ዛሬ ላይ ደረስን! “በኢትዮጲያ ለዘርፉ እድገት ዋና ማነቆ የሆነው “ድህነት” ሳይሆን መንግስት ነው” ማለት፤ “ቴክኖሎጂ ፍጥነት፣…ፍጥነት ነፃነት፣ … መንግስት ዝግመት!” እንደማለት ነው!!!

***********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories