ይህን ፅሑፍ ለመፃፍ መንስኤ የሆነኝ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጱያ የታሪክና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ አንዳንድ የኪነጥበብ ሰዎችና የነሱ ‘ተከታይ’ አድናቂዎቻቸው የሚሰነዝሩት በስሜት የተሞላና በአብዛኛውም ከእዉነታ የራቀ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን (ያሉትም ያለፉትም) አዛብቶ የማቅረብ አባዜ በብዛት በማስተዋሌ ነው፡፡ የዚህ ቁንጮ ተዋናይ ደግሞ ቴዲ አፍሮ ሲሆን በዚህ ፅሑፍ የዚህ ታዋቂ አቀንቃኝ አጠቃላይ ይዘትና እርስ በርሱ የሚጋጭ ፖለቲካዊ ተምኔትና እና ታሪከ እንዲሁም ማህበራዊ አረዳድ ዙሪያ አንዳንድ ነጥቦች ለማንሳት ነው፡፡፡

ለመነሻ ይሆን ዘንድም አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል:: ከላይ እንደተጠቀሰው የቴዲ አፍሮ አተያይ እና አካሄድ (ገብቶዎቸውም ይሁን በጭፍን ፍቅር ሳይገባቸው) የሚያቀነቅኑ እና ሌት ተቀን የሚያወድሱ ብዙ ሰዎች ስላሉ እንደነ ቴዲ አፍሮዎች ስል ይህን ለማመልከት እንደሆነ አንባቢያን ታሳቢ እንድታደርጉ እጠይቃለሁ፡፡ የሰሞኑ እንደ ቴዲን ካልሆን እሚሉትንም ይጨምራል::

በዚህም መሠረት እውን ቴዲ አፍሮዎች ኢትዮጵያን፣ ህዝቦችዋንና እንዲሁም ያለፈው ታሪክዋ በቅጡ ያውቁታል? ወይስ እንዳለፉት አንዳንድ መንግስታት እና ሊሂቃን ኢትዮጵያን ሳያውቁ ኢትዮጵያን እንደመሩ ሰዎች ናቸው? እውንስ ቴዲ አፍሮዎች ለቀና እና ውስጠ-ፈንቅል ጥበብ ነው ወይስ ፖለቲካዊ መነሽዋረር ላናወዘው የ ስነጥበብ ገበያ ነው የሚሰሩት? በታሪክ እና ትላልቅ ፖለቲካዊ ትርጓሜዎች ዙሪያስ ድፍረት ነው ወይስ እውቀት ነው መንደርደሪያ ኃይል እየሆነ ያለው? በነዚህ ጥያቄዎች ዙሪያ ለመፃፍ እና ለመመራመር ብዙ ጊዜና ሰፊ የመወያያ መድረክ እንደሚፈልግ ስለገባኝ ለዛሬ ይሆነን ዘንድ ቴዲ አፍሮ ባገኘው አጋጣሚ ስለሚሰብከው ‘ፍቅር’ ‘ስርየት’ ‘ስንዋደድ’ እና ‘የፍቅር ጉዞዎች; የተወሰኑ ስራዎችን በማጣቀስ ለማየት እሞክራለሁ፡፡ የዚህ ሁሉ ቴዲ አፍሮዊ ግርታ ማሰሪያም ቴዲ አፍሮ ‘ፍቅር ያሸንፋል’ በማለት ይገልፀዋል፡፡

ግርማዊነትዎ እና ሼህ ማንደፍር

ቴዲ አፍሮ ‘የአፍሪካ አባት’ እያለ የሚያሞካሻቸውን አፄ ኃይለስላሴ ስም ሳይጠራ ወይም የዘውዳዊ መንግስት ባንዲራ ከጀርባዉ ሳይሰቅል፣ ይህ ሳይቻል ሲቀር ደግሞ በ LCD projector ምስላቸውን ሳያሳይ እና አፄ ኃይለስላሴን ሳያወድስ ያካሄደው ኮንሰርት አለ ለማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ያስተሰርያል ካወጣ ወዲህ ደግሞ ሼ መንደፍርን ከግርማዊነትዎ በተጨማሪ መዝፈንና ማንጐራጐር የተለመደ የቴዲ ኮንሰርቶች መገለጫዎች ናቸው፡፡

እኔም በግሌ ይህን እውነት እ.ፈ.አ 2ዐ13 ቴዲ አፍሮ በጀኔቫ ከተማ ባቀረበው ኮንሰርት በአይኔ በብረቱ ተመልክቻለሁ፡፡ በተራቀቀው የ Palexpo አዳራሽ የቴዲ ባንድ ከጀርባው በትልቅ ስክሪን የተለቀቀው የዘውዳዊው መንግስት ባንዲራ ሲሆን፣ ግርማዊነትዎን ሲዘፍን ደግሞ የንጉሱን የተለያየ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ፎቶዎች ሲታዩ ነበር፡፡ እንደተለመደው በመሃሉ ‘ፍቅር ያሸንፋል’ የምትለዋን መፈክር ትሁን ማስፈራሪያ ደጋግሞ ይላት ነበር፡፡ የኔን ጥያቄ ይበልጥ ያጦዘው ግን እዛው ኮንሰርት ላይ ሼ-መንደፍርን በስሜት ተሞልቶና ከጀርባው የክርስትና መስቀል እና የእስልምናን ሃይማኖት የምትወክለውን ምልክት ጐን ለጐን አድርጐ ስለሃይማኖት መቻቻልና አንደነት ሲዘፍን ነው፡፡ እዚህ ጋር አንባቢ ታዲያ ይህ ምን ችግር አለው ሊል ይችላል:: ደግሞም ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ ችግሩ የሚመነጨው መስቀል ያነገበና ዘውድ የደፋ አንበሳ በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ታጅቦ ያለው ባንዲራ በግላጭ የተሸከመው ፖለቲካዊ ትርጉም እና የ ሼ-መንደፍር ዘፈን በይዘትም በቅርፅም የሚጋጩና ፍጥረታቸውም የማይጣጣሙ መሆናቸው ለመገንዘብ ትንሽ ትንተና ሲካሄድ ነው፡፡

Photo - Teddy Afro
Photo – Teddy Afro

የዘውዳዊ መንግስትና የቴዲ አፍሮዎች የኢትዮጵያ ባንዲራ

አገራዊ ባንዲራ (ሰንደቅ አለማ) ማለት የአንድን ፖለቲካዊ ስርዓት አጠቃላይ ባህሪይና አወቃቀር ምልክታዊ ማሳያ ነው፡፡ ባንዲራ ጥልቅ የሆነ መሠረታዊ ነገሮችን የሚያሳይ የቆመላትን አገር ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እሴቶች፣ እምነቶች እና የወደፊት አቅጣጫን የሚያሳይ አርማ ነው፡፡ በዚህ አንፃር የዘውዳዊው መንግስት እና የቴዲ አፍሮዎች ባንዲራ ይዘቱና ትርጓሜውም ምንድነው? ባጭሩ ለማስቀመጥ ዘውድ የደፋው አንበሳ እና ያነገበው መስቀሉን እንመልከት፡፡

መስቀል ያነገበና ዘውድ የደፋው አንበሳ

ይህ በአጭሩ የሚነግረን ስልጣን የሚገኘው የሰለሞናዊ ስርወ መንግስት የአመራር ዘር በመሆን ሲሆን ይህም ዘር እግዝአብሄርን (የክርስቲያን ኦርቶዶክስ) ወክሎ ያለምንም ሀይ ባይነት ፍፁማዊ በሆነ መንገድ የተቀረውን ህዝብ የመግዛት (የማስተዳደር) ስልጣን ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ህዝቡም መሬቱም የንጉሱ ሲሆን ንጉስ ማለት ደግሞ ‘ዘእምነ ነገድ ይሁዳ’ ሲሆኑ በእግዜር የተመረጡ ምርጥ ናቸው፡፡ ቴዲም ግርማዊነትዎ በሚለው ዘፈኑ ይህን ትርጓሜ እንዳለ በመውሰድ የአፄ ኃይለስላሴን ሰማያዊ ሰብእና ባንዲራቸውን በማድረግ በቻ ሳይወሰን በግጥም ስንኞችን አንቆርቁሮታል፡፡

ዘውድ የደፋው ባለ መስቀል አንበሳ የነገሰባት ባንዲራ ባጭሩ ሰለሞናዊ የዘር ሀረግ ‘አላቸው’ ከሚባሉት በእግዜር ከተመረጡ ምርጥ ሴሞች (Semetic) ውጪ ያሉት እንደ ኦሮሞ፣ ኣፋር፣ ሶማሌ፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ እና የተቀሩ ብዙ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካዊ ስልጣን መብት እና ቅርበት እንደሌላቸው በህግ የደነገገ ስርዓት መገለጫ ባንዲራ ነው፡፡ ባለ ዘውድ ኣንበሳ ያነገባት መስቀል ደግሞ “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት” የሚል የገዢዎች መዝሙር ማሳያ እና ባንዲራዊ መገለጫ ናት፡፡ ይህ ደግሞ እስላሙ፣ ዋቄ ፌታው፣ ካቶሊኩ፣ ፕሮቴስታንቱ፣ ባህላዊ አምልኮ አማኙ እንዲሁም አላማኙም በስርዓቱ ቸርነት የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንጂ እኩል ኢትዮጵያዊ አይደሉም ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የዚህ ኃላቀር አስተሳሰብ ውጤት ደግሞ ሙስሊሞች በዓል ሲያከብሩ “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሙስሊሞች” እያሉ ዘገባ መስራት ነው፡፡

ባጭሩ መስቀል የተሸከመው ዘውድ የደፋ አንበሳ ቁንፅል፣ አፋኝ አግላይ እና በዳይ የሆነ የሃይማኖት፣ የስልጣንና የዘር የበላይነት መገለጫ ነው፡፡ ይህ የዘውዳዊ ስርዓት መጨቆኛ ባንዲራ አንጠልጥሎ መዞርና የውዳሴ ስንኞችን መደርደር መገለጫው ያደረገ ቴዲ አፍሮ ‘ፍቅር ያሸንፋል’ ‘ወደ ፍቅር ጉዞ’ ‘ሼ መንደፍር’ ሲል ምን ማለቱ ነው? ስለሚሰግድለት ባንዲራስ ሳይገባው ቀርቶ ነው?

ፍቅር የሚለው ቃል አሻሚና ድፍን ትርጉም ቢኖረውም ይህን አግላይ እና “ምርጦችን” ብቻ እንዲጠቅም የተሰራ እና የሰራ ዘሙዳዋ ባንዲራ ተይዞ ስለምን አይነት ፍቅር ነው እምንነጋገረው? የራሱን ዘውድና መስቀል መሸከም አቅቶት ከባንዲራነት ከብዙ ዓመታት የተሽቀነጠረ ሙት አንበሳን እየጐተቱ የምን ፍቅር የምን ስርየት ነው እሚወራው? ለኔ ይህ ድርጊት ኣንድም ኣለማወቅ ነው ኣንድም የ ፖለቲካ ገናዥነት ነው:: የ ፈረንጅ ገናዥ በ እንግሊዝኛ undertaker ይባላሉ ስራቸውም ሟችን ሽክ ኣድርገው በሂወት ያለ እስኪመስል ኣድርገው ለቀብር ማሰናዳት ነው:: ዞሮ ዞሮ ሙትን ማሳመር እንጂ ማዳን ኣይችሉም ፤ ልክ እንደ ቴዲ ኣፍሮዎቻችን::

አንዱን ሃይማኖትና የተወሰኑ ምርጥ ዘሮችን ፍፁማዊ የኢትዮጵያ ባለቤትነትና መብት የሚገልፅ ባንዲራ እያራገቡ ‘ሼ መንደፍርን መቀባጠር እንዴት ከአንድ ጤነኛ አእምሮ ሊመነጭ ይችላል? ይህን ስል ግን የቴዲ አፍሮ ተቃርኖዎች ለማሳየት እንጂ በሙሉ መንግስታዊ እና የተቀናጀ ሃይማኖታዊ ጭቆና ሰርም እያለን (እድሜ ለነዛ ደነዝ ዘውድ የደፋ ባለ መስቀል አምበሳ ተሸካሚዎች) ያለፈው እና አሁንም ያለው ማህበረሰባዊ መስተጋብራችን በአብዛኛው በ ‘ሼ-መንደፍር’ አይገልፅም ለማለት አይደለም:: ሳስበው ሳስበው ግን ግርማዊነትዎን እያቀነቀኑ በጐን ደግሞ ሼ-መንደፍር ማለት ሼም (shame) “እሚያስይዝ” ተግባር መስሎ ሰለተሰማኝ ነው፡፡ መድፈር የሚያመጣው ሼም፡፡ ቴዲ በተቃርኖ የተሞላ ዘፋኝ ነው።

የዴሞክራሲ አክቲቪስት ነኝ እያለ ከዘዉድ አማላኪነት መላቀቅ የተሳነው ወጣት ማየት ይዘገንናል።

********

more recommended stories