ኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት ኣባል ብትሆን የሚኖሩ ተገቢ ስጋቶች

ኢትዮጵያ የኣለም ንግድ ድርጅት (World Trade Organization – WTO) ኣባል ለመሆን ድርድር እያካሄደች እና እየተጋች እንደሆነ  በመንግስት በኩል በተለያየ ኣጋጣሚ ይገለፃል። ከኣባልነት የምትጠብቀው ድግም ከኣለም ገበያ ጋር ራሷን በማስተሳሰር የኢኮንሚ ጥቅም ለማግኘት እንደሆነ ይገለፃል። ኣንድ ኣገር የኣለም ንግድ ድርጅት ኣባል ለመሆን ደግሞ ሟሟላት የሚጠበቅበት ብዙ እና የተወሳሰቡ ሰንሰለታማ ቅድመ ሁኔታዎች የንግድ ድርጅቱ ኣስቀምጠዋል። ዋናዎቹን ቅድመ ሁኔታዎች ለመጥቀስ ያክል፡  

1፣ መንግስት ቢቻል ሁሉም ካልሆነ ደግሞ ኣብዛኞቹ የሚቆጣጠራቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ለግል ይዞታ እንዲያዞር ይጠየቃል፣ በተዘዋዋሪም በቀጥታም ግፊት ይደረግበታል።

2፣ ለኣባልነት የሚያመልክት መንግስት ሁሉ ኢኮኖሚውን እና ገበያውን ለኣባል ኣገራት ክፍት ያደረጋል።  

የዚህ ቅድመ ሁኔታ ኣቅጣጫ በኣጭሩ ግልፅ ለማድርግ መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ከዘበኝነት ያለፈ ሚና ሊኖረው ኣይገባም የሚለውን Britonwood የመሰረተው የገበያ ኣክራሪ (Neoliberal) ሃይሎች  ኣስተሳሰብ ማስፈፀም ነው። በመሆኑም የንግድ ድርጅቱ የምእራቡ ኣለም የንግድ ኩባኒያዎችን ዋነኛ የብዝበዛ ኣስፈፃሚ መሳሪያ በመሆን የተደራጀ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል። በበዝባዥነቱ እና በፀረ ዴሞክራሲያዊነቱም በብዙ ኣለም ኣቀፍ ድርጅቶችም ይወገዛል። ሰልፎችም ኣድማዎችም የወጣበታል።

Logo - World Trade Organization

ይህ እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሱት እና ያልጠቀሱት ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ኣሟልታ ስታበቃ እና ኣባል ስትሆን ጊዜ የንግድ ድርጅቱ ኣባል ኣገራት በሙሉ በኢትዮጵያ ገበያ እና የኢኮኖሚ ዘርፍ እንዲንቀሳቀሱ ለመፍቀድ ትገደዳለች። ይህ ማለት እንደ ዎልማርትን (Walmart) የመሳሰሉት ከኢትዮጵያ ሃብት በላይ እጅግ የገዘፈ የማንቀሳቀሻ ባጀት ያላቸው ካምፓኒዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ከመርፌ፣ ሻማ፣ ዳቦ፣ ቅጠል ሻይ፣ ሰላጣ፣ ሽንኩርት፣ ካልሲ እስከ መኪና እና ማሽኖች የመሳሰሉት በኣለም ዙሪያ የተመረቱ ምርቶች የመሸጥ መብት ኣላቸው ማለት ነው። ይህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ ውሽጥ ያሉት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚቀልቡ ትንንሽ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቆች የመወዳደር ኣቅም ስለሌላቸው በኣጭር ጊዜ ውስጥ ከጨዋታ ውጭ ይሆናል።

የኣለም የንግድ ድርጅቱ ኣባል ከሆንን እንደ IKEA የመሰሉ የቤት እቃዎች እና የህንፃ መሳሪያዎች በተነፃፃሪ በርካሽ ዋጋ የማቅረብ (ገበያውን እስኪቆጣጠሩ ድረስ) ኣቅም ያላቸው ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ የመግባት መብት ኣላቸው። ታዲያ ተወዳዳሪ ዋጋ ማቅረቡ ለጊዜው የተሻለ ቢመስልም ብጥቃቅን እና ትንንሽ ድርጅቶ ተቋቁመው ወንበር እና ኣልጋ እየሸጡ ብዙ ዜጋ የሚቀልቡ ኣገር በቀል ድርጅቶች ከገበያ ውጭ እንደሚሆኑ መዘንጋት የለበትም።

በተመሳሳይ የውጭ ባንኮች ወድ ኢትዮጵያ ቢገቡ ኣሁን ያሉት የመንግስትና የግል ባንኮቻችን በገንዘብ መጠን፣ በቴክኖሎጂ፣ እጀግ የረቀቀ የሰው ሃይል እና በተቋማዊ ብቃት ተወዳዳሪ ስለማይሆኑ በኣጭር ግዜ ውስጥ ተሽመድምደው ከገበያ ውጭ ይሆናሉ። ኪሳራው በባንኮቻችን (የግልም የመንግስትም) ብቻ ተወስኖ ኣይቀርም። ስራ ኣስኪያጆቹን ጨምሮ ሰራተኛውም ኣብዛኛው ከስራ የመፈናቀል እድሉ ሰፊ ነው።

ሁሉም ነገር ወደ ግል ይዞታ ቢዞርና እና መንግስትም የዘበኝነት ሚና ብቻ የሚጫወት ከሆነ ለውጭ ኩባኒያዎች የሚሸጡት የመንግስት የልማት ድርጅቶች በተለይም ኣገራዊ ፋይዳቸው ከፍ ያሉ ድርጅቶች ኪሳራቸው ቀላል ኣይሆንም። 13 ሺ ሰራተኛ የነበረው የሞሮኮ ቴሌኮም የፈረንሳይ ኩባኒያ ሲገዛው የሰራተኛው መጠን  በቴክኖሎጂ ተተክቶ ወደ ጥቂት መቶዎች እንደወረደ የሞሮኮ ሙሁራን ፅፈዋል ተችተዋል።

ትልቅ ኢክኖሚ ያላት ደቡብ ኣፍሪካ ከቻይና በሚጎርፈው ርካሽ የጨርቃ ጨርቅ ምርት ገበያዊ በመጥለቅለቁ 3 ግዙፍ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎቿን ለምዝጋት ተገዳለች። ውጤቱ ድግሞ ከ75 ሺ በላይ ስራተኛ ስራውን ለማጣት ምክንያት ሆነ። በደቡብ ኣፍሪካ ኣንድ ስራ በኣማካይ ኣራት የቤተሰብ ኣባላት ይቀልባል ተብሎ ይታሰባል። እንግዲህ 75 ሺ ሲባዛ በ4 ወደ 300,000 ሺ ሰው ሰለባ ሆኗል። ይህ ተመሳሳይ ጥፋት በቀጠናው በሚገኙ ኣገሮችም ተደግሞ ፋብሪካዎች ኣስዘግተዋል። ስዋዚላንድ፣ ማዳጋስካር፣ ሞሪሼስ ኬናያ እና በምእራብ ኣፍሪካ ደግሞ ጋና የዚህ ሰለባ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ።

በዚህ ወቅት ነበር የደቡብ ኣፍሪካ መንግስት ከእንቅልፉ የነቃው። ሁኔታው ኣሳሳቢ ስለሆነበት የቻይና ምንግስት ወኪሎችን በመጥራት “ርካሽ የጭርቅ ምርታቹ ገበያችን ብቻ ሳይሆን ፋብሪካችንም ጭምር ኣዘግቶ ዜጎቻችን ለረሃብ ኣጋልጧል። ስለዚህ ጭርቅ ለማስገባት ልናስቆማቹ ነው” ኣለዋቸው። የቻይና መንግስት መልስ እንደሚከተለው ነበር: “እናንተም እኛም የኣለም ንግድ ድርጀት ኣባል ነን። ኣባል ስንሆን የተስማማንባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ኣሉ። ገበያችን ለኣባል ኣገራት ክፍት ማድረግ ይጠበቅብናል። በዛ ህግ መሠረት እየተጫወትን እንገኛለን። እናንተም የመጫወት መብት ኣላቹ። ህግን መጣስ ግን በኣለም ንግድ ድርጅት ዘንድ ያስጠይቃቹሃል” ሲሉ መለሱላቸው። ድርድሩ ቀላል ባይሆንም እንዲህ እያለ ቀጥሎ የተወሰኑ መሻሻሎች እንዳመጣ ይነገራል። ያደረሰውን ጥፋት ግን ማዳን ኣልተቻለም።

ብዙ ተጨባጭ ኣብነቶች ማቅረብ ይቻላል። ኢትዮጵያ ባለችበት ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ የኣለም ንግድ ድርጅት ኣባል ከሆነች የኛም ከዚህ የተለየ ኣይሆንም። ኣገር በቀል ድርጅቶች ከገበያ ውጭ ይሆናሉ፣ የኣገሪቱ ኢንዱስትሪ እና ኢኮኖሚ በውጭ ሃይሎች ተፅእኖ ይወድቃል፣ ስራ ኣጥነት በሰፊው ይነግሳል (በተለይም ብዙ ቁጥር ያለውን ያልተማረው)፣ የሚኖረው ኣማራጭ እጅግ በጣም ትንሽ ነው፣ ተስፋ መቁረጥ ይበዛል፣ ሂወትን ለማቆየት ወንጀልም ጭምር ይበራከታል፣ መፈናቀል ስደትም እንደዚሁ። ከዚህ ሁሉ የተረፈ ደግሞ ከይትኛውም ኣቅጣጫ የሚመጣለት የነውጥ ግብዣ ለመቀበል ዝግጁ ይሆናል። ኣደጋው በዚህ ኣያበቃም! ስራ ኣጥነት ዞሮ ዞሮ የኣገር ሽክም ብቻ ሳይሆን ስራ ኣጥ በበዛበት ሁኔታ ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ ኣይቻልም። 

ታዲያ ኢትዮጵያ በዚህ ኣይነት ኣሰቃቂ ጨዋታ ውስጥ ለመግባት ምን ያጣድፋታል? ኣገሪቱ ከላይ የተጠቀሱት ፈተናዎችን የመቋቋም መዋቅራዊ፣ ተቋማዊ እና ሰብኣዊ ኣቅም ኣላት? በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባለሱቆቻችን እና ተጠቃሚ ዜጎች በኣንድ ምናልባትም 200 ሰው መቅጠር በሚችለው ግዙፍ ኩባኒያ እንዳይተኩ ለመከላከል ምን ዋስትና ተይዟል? ለኣገሪቱ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዋስትና የሚሁነውን ኣገር በቀሉ ባለ ሃብት በተለይም ብዙ ስራ የመፍጠር ኣቅም ያላቸው ዘርፎችን ለማጠናከር እና ተወዳዳሪ የማድረግ ስራስ የጊዜውን ፍጥነት እና የሁኔታዎችን መለዋወጥ የሚመጥን ተጨባጭ ነገር እየተሰራ ይሆን? ጥቃቅን እና ኣነስተኛስ ድርጅትችስ ካሉበት ደረጃ ወደ ተሻለ ኣምራችነት ለማሸጋገር እና ተወዳዳሪ የመድረግ ሁኔታስ?

ሌላው ግልፅነት የሚሳፈልገው ጉዳይ ቢኖር ገዢው ፓርቲ የሚከተለውን ሪኦተ ኣለም እና በተግባር እየሄደበት ያለውን መንገድ ይሆናል። ለመሆኑ “ልማታዊ መንግስት” የሆነውን ኢህኣደግ የኒዮ ሊበራል ዋና ሞተር የሆነው የኣለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ሲወስን የልማታዊ መንግስት ሪኦተለም ወሳኝ የሆኑት መርሆዎችን ድምጥማጣቸው ጠፍተው የኣገሪቱ ፖለቲካል ኢኮኖሚ በኒዮሊበራል ቅኝት እንደሚተካ በቂ ግንዛቤ ተይዞ ይሆን? ወይስ ኣገር ውስጥ ሌላ ከኣገር ውጭ ሌላ ኣስተሳሰብ ተይዞ የማይታረቁትን ማስታረቅ ይቻላል?

 እነዚህን የመሳሰሉት ጉዳዮች የኣገሪቱን መፃኢ እድል የሚወስኑ በመሆናቸው የመንግስት ፖሊሲ ተመራማሪዎች፣ ፀሃፊዎች፣ ኣስፈፃሚዎች እና ሙሁራን ሊነጋገሩበት እና ሊፈትሹት የሚገባ ነው እንላለን። ኢህኣደግም በዚህ ጉዳይ ላይ በቂ የሚባል ጊዜ ቢያጠፋ ይመከራል።  

ቸር ይግጠመን !

*********

ገብረ ሥላሴ ኣርኣያ ኣብ ሃገራዊን ዞባዊን ከምኡውን ዓለም ለኻዊ ፖለቲካ ጉዳያት ዝከታተል፣ ኣብዝኾነ ፖለቲካዊ ውዳበ ዘይነጥፍ ውልቀ ሰብ እዩ። ንሃናፃይ ሪኢቶ ኣብ [email protected]

more recommended stories