(አንተነህ አብርሃም)

የኢቢሲ 50ኛ ዓመት በዓል ሲከበር ከነበሩት ዝግጅቶች በአንዱ ብቻ ተካፋይ ነበርኩ፡፡ ይሄውም የፓናል ውይይት ነበር፡፡ በፓናል ውይይቱ ሁለት የጥናት ጽሁፎች በመኩሪያ መካሻና ዶ/ር ነገሪ ዶሪ ቀረቡ፡፡ አወያዩ አቶ ዘርሁን ተሾመ (ዜዶ) ነበሩ፡፡ ውይይቱ ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ዘግይቶ የተጀመረ መሆኑን ገለጹት አቶ ዘርይሁን ለጽሁፍ አቅራቢዎች በቂ የገለጻ ጊዜ ከሰጡ በኋላ መድረኩን ለውይይት ክፍት አደረጉት፡፡ ይሁንና ሰዓቱ ረፈደ አሉና ለተወያዩች ጥያቄና አስተያየት በአጫጭር ደቂቃና ሰከንድ የተገደበ እድል ሰጡ፡፡ የተገኘችውን ቀዳዳ አሟጦ መጠቀም የብልጥ ልጅ ወግ ነውና እኔን እድል አገኘሁ፡፡

አቶ ዘሪሁን እኔ አስተያየቴን ከመስጠቴ በፊት የነበሩትን ተናጋሪ እንደ ደሀ ቀብር ቶሎ በል እያሉ ያጣድፉ ያዙ፡፡ እኔም በውስጤ ሲወርድ ሲወጣ የቆየውን ሃዛብ እንደአመጣጡ ለማውረድና ለማዋዛት ጥድፊ አላመቸኝም፡፡ እውነቱን ለመናገር በዚ ሁኔታ ሃሳብ ከመስጠት መተው ይሻል ነበር፡፡ ምክንያቱን አንድ በጣም ትልቅ ተራራ የሚያክል ሃሳብ አብራርቶ ለመጨረስና ግንዛቤ ለማስረጽ ጊዜ የግድ ያስፈልግ ነበር፡፡ ለረጅም ዘመን ያለአስታዋሽ ሲደክሙ ለነበሩ የድርጅቱ ጋዜጠኞች አዲሱ አመራር ያደረገውን ማበረታቻና ሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች አንስቶ ለማብራራት እንኳን ከመድረክ ነበረው ጥድፊያ አመቺ አልነበረም፡፡ ስለሆነም በቀጥታ ወደ ገደለው ገባሁ፡፡

ዋናው ሃሳቤም የኢቢሲ ‹‹የብዝሃነትና የህዳሴ ድምጽ!›› “The voice of Diversity and Renaissance!” የሚለው መሪ ቃል (motto) ነበር፡፡

Image - Logo of EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation)

በቅድሚያ እኔ ከብዛሃነት ጋር ምንም ችግር የለብኝም፡፡ ብዛሃነትን እቀበላለሁ፤ አከብራለሁ፡፡ ብዝሃነት የብዙዎች፣ የተከፋፈሉ፣ የተለያዩና በአጠቃላይ አንድ ያልሆኑና ሊሆኑም የማይችሉ ነገር ግን ተከባብረው መኖር ግድ የሆነባቸው – ለምሳሌ የሃይማኖት፣ የጾታ፣ የቀለም፣ የቋንቋ፣ የብሄራዊ ማንነትና የአስተሳሰብና የፖለቲካ አመለካከትን የመሳሰሉ ልዩነቶች – ብዛሐነት ቢባሉና እነዚህን በእኩልነት ማስተናገድና የሁሉም ድምጽ ሆኖ መንቀሳቀሱ ከአንድ ሚዲያ የሚጠበቅና ተገቢም ነው ቢዬ አምናለሁ፡፡

ነገር ግን በአንድ ሃገር ላይ የሃገሩ ብሄራዊ ሚዲያ ብዝሃነትን pluralism ብሎ መተርጎም ትቶ ሌላ የክፋት ሃሳብ ያዘለ በሚመስል ሁኔታ Diversity እያለ ሲተረጎምና የጥፋት ስራ ሲሰራ አላዋቂነት ነው ብሎ ብቻ መውሰድ አይቻልም፡፡

Diversity ልዩነት፣ የተለያየ፣ የአቅጣጫ መለያየት እንደማለት ነው፡፡ ማንም ሃገር በገዛ ገንዘቡ ባቋቋመው ሚዲያ ልዩነትን፣ መለያየትንና መበታተንን በየቀኑ እየጠራ ሊያበረታታ አይችልም፡፡ ስለመለያየት ተደጋግሞ የሚነገረው ህዝብ ሁሌም እንዴት ሊለያይ እያለ ወደ መጥበብ ይጠጋል፡፡ በጋራ ጉዳዩች ላይ ያሰለፍነው ህዝብ ስለ ጎጥ ሳይሆን ስለ ታላቋ ሀገሩ ማሰብና ማሰላሰል ይጀምራል፡፡ የሀገራችን ህዝቦች በጋራ አብረው ለረጅም ዘመናት ከኖሩ በኋላ በየአቅጣጫው ወደ ጠባብነት መስመር መግባት ጀምረዋል፡፡ አንዱ ሌላውን በማየት ጎራ መለየት ይጀምራል፡፡ አንዱ የሌላውን ባለስልጣነት ብዛትና የሚገኙትን ጥቅማ ጥቅም በማሰላሰል በአካባቢያዊ የጠባብነት ልክፍት ውስጥ ይወድቃል፡፡

አለም በአሁኑ ሰዓት ስለግሎባላይዘሽንን ማዜም ጀምሯል፡፡ ድፍን አፍሪካም ድንበሮችን ያለገደብ ክፍት ለማድረግ ውይይት ይዟል፡፡ የተለያዩ ሃሳቦችና አመለካከቶች በአንድ ሀገር መኖራቸውን አምኖ መቀበል እህል ውሃ የማያሰኝ አማራጭ ሌለው ጉዳይ ነው፡፡ የብሄሮችንና የሃይማኖቶችን እንዲሁም የእያንዳንዱን ግለሰብ ሰብአዊ መብት ማክበርና ማስከበር አለም አቀፍ ግዴታ ነው፡፡ የብሄሮችን ልዩነት ማንም አስቦና ፈልጎ አላመጣውም፡፡ ማንም እቅድ አስቦበት ብሄርንና ህዝብን መፍጠር አይችልም፡፡ ህዝቦችንና ብሄሮችን በአንድነት ተሳስበውና ተፈቃቅረው እንዲኖሩ ማድረግ ይችላል፡፡ በህዝቦች መካከል ያሉትን ልዩነቶች እያጎላ ተለያይተው ብዙ እንዲሆኑም ልዩነቶቻቸው በማስፋት ወደጫፍ እንዲወጡና ከዚያም እንዲበታተኑ ማድረግ ሚዲያ አያቅተውም፡፡ ሚዲያ አንድ ሃገር መገንባትም ማፍረስም የሚችል መሳሪያ ስለመሆኑ መናገር ጉንጭ ማልፋት ነው፡፡

ጋዜጠኞችና ሚዲዎች አብዝተው ስለልማት ሲያወሩ ህዝቡ ወደ ልማት ይገባል፡፡ ጋዜጠኞች አብዝተው ስለጦርነት ካወሩ ጦረኞች በየመንደሩ ይበረክታሉ፡፡ ዋናው ግን ጥሪው ነው ይብዛም ይነስም ማንኛውን ሰው ቁጥሩ ይብዛም ይነስም ጥሪውን በአእምሮው የሚሸከም ባሪያ ይሆናል፡፡ የሰውን ልጅ ባህሪ መረዳት አለብን፡፡ በአንድ የህጻነት ት/ቤት ክፍል ውስጥ አንድ ተማሪ ‹‹ዉ! ዉ! ው!›› እያለ ቢያጉረመርም ሁሉም ተማሪ ወዲያው ‹‹ው! ዉ! ዉ!›› እያሉ ማጉረምረም ጀምራሉ፡፡ አንዱን ተማሪ አንስተው ‹‹ለምን ዉ! አልክ›› ብትሉት ምክንያቱን አያውቀውም፡፡

በአንድ ወቅት ከመቐለ በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ እየመጣሁ ከጎኔ ለተቀመጠው ተሳፋሪ ስለሰው ልጅ ባህሪ እነግረው ነበር፡፡ በመጨረሻ አውሮፕላናችን ለማረፍ ሲቃረብ ‹‹እዚህ አውሮፕላን ውስጥ ያለውን ሰው ሁሉ ላስጨብጭብ ወይ›› አልኩት፡፡ ‹‹እንዴት እንደማስጨበጭብ ታያለህ›› አልኩና ትንሽ እንዲጠብቀኝ ነገርኩት፡፡ አውሮፕላኑ ለማረፍ መሬቱን እንደረገጠ በጭብጨባ ቀወጥኩት ተሳፋሪው ሁሉ ምን ተፈጠረ ሳይል አውሮፕላኑን በጭብጨባ አናወጠው፡፡ ወዳጄም ወደ እኔ ዞሮ ላሳየሁት ችሎታ አድናቆቱን በፈገግታ ገለጸልኝ፡፡ ህዝብ ማለት የእንደዚህ አይነት ነገር ነጸብራቅ ነው፡፡ ፖለቲከኞች ህዝቡ ህዝቡ ይላሉ፡፡ ሃሳቡ ግን ሁል ጊዜ የእነሱ ነው፡፡ ህዝብ ሃሳብ ሊኖረው አይችልም ባይባልም የህዝብ ሃሳብ የሚመነጨው ከፖለቲከኞች ራስ ቅል ነው፡፡

ወደ ኢቢሲ ስንመለስ ኢቢሲ የጋራ ሃገራዊ መግባባትን በማስፈን አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ወደ መፍጠር ህገመንግስታዊ ራእይ መሸጋገር እንጂ ልዩነትን ማዜም የለበትም፡፡ እኛ ልዩነትን ስናወራ ሰዉ የታየው አንድነቱ አይደለም፡፡ እዛው ልዩነቱ ላይ ሚዳክር ህዝብ መፍጠር የለብንም፡፡ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብን ለመፍጠር ደግሞ ሞቶ መሆን ያለበት Diversity ሳይሆን Unity ነው፡፡ አንዳንድ ወዳጆች ዩኒቲን ፕሮሞት ማድረግ የተቃዋሚዎች ስራ ይመስላቸዋል፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ Renaissance የሚለው ቃል pluralism እና Diversity ኢቢሲ እንደሚለው ብዛሃነትን በውስጡ አቅፎ የያዘ ድልብ ቃልነው፡፡ ኢቢሲ የህዳሴ ድምጽ ብሎ ቢያቆም ምንም ችግር አልነበረውም፡፡ ኢቢሲ የህዝቦችን እኩልነት ካረጋገጠ በኋላ አንድ አድርጎ አስተሳስሮ ስለያዛቸውና ጉዳይና ወደፊት ራኢቸው ላይ ወደ ፊት አሻቅቦ በበልከት የሚችል ጣቢያ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡፡

**********
* አንተነህ አብርሀም የብሔራዊ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

 

Guest Author

more recommended stories