ሰማያዊ ፓርቲ አራት የምክር ቤት አባላትን አባረረ

(አዲስ አድማስ)

የሰማያዊ ፓርቲ ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰሞኑን ባደረገው ስብሰባ፤ ከፍተኛ የስነ – ስርዓት ጥሰት ፈፅመዋል ያላቸውን አራት የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ከፓርቲው አባረረ፡፡

የተባረሩት የብሔራዊ ም/ቤት አባላት፣ በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲው የቀድሞው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮናታን ተስፋዬ፣ አቶ ኢያስጴድ ተስፋዬ፣ አቶ ጋሻዬነህ ላቀና አቶ ዮናስ ከድር ናቸው ተብሏል፡፡

ፓርቲው በተባበሩት አባላት የስንብት ደብዳቤ ላይ የተባረሩበትን ምክንያት የጠቀሰ ሲሆን የቀድሞ አባላት የታሪክና የጎሳ ጥላቻ የሚቀሰቅስ የኢትዮጵያን ህዝብና የተለያዩ የሀገራችንን መንግስታት ታሪኮች የሚያጐድፍ፣ ለጥላቻ የሚያነሳሳና በህዝብ መካከል የባህል መከባበር እንዳይኖር የሚያደርግ… ፅሁፎችን በማህበራዊ ድረገፅ ላይ በማሰራጨታቸው ክስ ተመስርቶባቸው መባረራቸውን ያስረዳል፡፡Logo - Blue Party of Ethiopia

በተጨማሪም ተሰናባቾቹ የሰማያዊ ፓርቲን ደንብና ፕሮግራም በመጣስ፣ ስለፓርቲው ከማስረዳት ይልቅ ሌላ ቀደምት የፖለቲካ ተቋማትን ፕሮግራምና ደንብ በመደገፍ እንደሚያብራሩ ጠቅሶ፣ በአጠቃላይ ከፋፋይነት ያላቸውን ፅሁፎች አሰራጭተዋል ብሏል፡፡

ከፓርቲው ከተባረሩት መካከል አቶ ዮናስ ከድር፤ በማህበራዊ ድረ – ገፅ ላይ የአቶ ኢያስጴድንና አቶ ዮናታንን ሀሳብ የሚደግፉ ጽሑፎች በመለጠፍ በተለይም በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ላይ መሳለቃቸውንና፣ በባንዲራ ዙሪያ ከፋፋይ ፅሁፎችን ማውጣታቸው ተጠቁሟል፡፡

ተሰናባቾች በበኩላቸው፤ ምንም እንኳን የተከሰሱትና የተሰናበቱት ማህበራዊ ድረ – ገፅ ላይ ተሰራጨ በተባለ ፅሁፍ ቢሆንም ይህ ሽፋን እንጂ የተከሰሱበት ትክክለኛ ምክንያት እንዳልሆነ ጠቁመው፤ የፓርቲውን ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃልን ከቦታው ማስነሳት የሚፈልጉ አካላት እርሱን ስለደገፍንና አካሄዳቸውን ስለተቃወምን የሸረቡብን ሴራ ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

አቶ ኢያስጴድ በሰጡት አስተያየት፤ “ጉዳዩ ወደ ዲሲፒሊን ኮሚቴ የተመራው የማይመለከታቸው ግለሰብ በሰጡት ድምፅ በተፈጠረ ብልጫ ነው” ብለዋል፡፡ የፓርቲው የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን ሰብሳቢ አቶ አበራ ገብሩ በበኩላቸው፤ ድምፅ መስጠት አይገባውም የተባለው ግለሰብ ድምፅ ባይቆጠርም አቶ ኢያስጴድን ወደ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ለማቅረብ በቂ ድምፅ ተገኝቶ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

ከፓርቲው አባልነት የተሰናበቱት ግለሰቦች በ15 ቀናት ውስጥ ይግባኝ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ታውቋል፡፡
**************

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories