የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በ160 ሺህ ብር ተካሰሱ

(አዲስ አድማስ)

የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት፣ በገንዘብ ምዝበራና በአሰራር ግድፈት የጠረጠራቸው አምስት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ክስ መመስረቱን የአዲስ አድማስ ምንጮች ገለፁ፡፡ ለፓርቲው ዲሲፕሊን ኮሚቴ ክስ የቀረበባቸው የስራ አስፈፃሚ አባላት፡- የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፣ የቀድሞው የፓርቲው ም/ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ፣የቀድሞው የፋይናንስ ሃላፊ አቶ ወሮታው ዋሴ፣ የቀድሞው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊና በኋላም የጥናትና ስትራቴጂ ሃላፊ የነበሩት ኢ/ር ጌታነህ ባልቻና የፋይናንስና የድርጅት ጉዳይ ፀሐፊና የብሔራዊ ም/ቤት አባል የሆኑት ወ/ሪት ወይንሸት ሞላ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

ባለፈው ህዳር ወር መግቢያ ላይ በፓርቲው ውስጥ ስለገንዘብ ብክነትና አሰራር ብልሹነት መወራት ሲጀምር ብሔራዊ ም/ቤቱ ሶስት አባላት ያሉት አጣሪ ኮሚቴ ማቋቋሙን የጠቀሱት ምንጮች፤ ኮሚቴው ለ45 ቀናት ምርመራ በማካሄድ ባለ 48 ገፅ ሪፖርት ማቅረቡ ተጠቁሟል፡፡ ግለሰቦቹ በሰላማዊ ሰልፍ፣ በክልል ጉዞዎች፣ በብድር መልክ፣ ደረሰኞችን ህጋዊ በማስመሰልና ከተለያዩ ቦታዎች ፓርቲውን ለመደገፍ ከሚገባ ገንዘብ ላይ ከ160 ሺህ ብር በላይ መዝብረዋል ያሉት ምንጮች፤ ብዙ ጽ/ቤቶች ለሌሉት አዲስ ፓርቲ ገንዘቡ በጣም ብዙ ቀዳዳ የሚሸፍን ነው ብለዋል፡፡

Logo - semayawi party, Ethiopia

“ገንዘቡ ብዙ ባይሆን እንኳን ነገ አገርን እመራለሁ ብሎ በተነሳ ፓርቲ አመራሮቹ ይህን ያህል ማጭበርበር መፈፀሙ ያሳምማል” ብለዋል፤ አንድ አባል በሰጡት አስተያየት፡፡ አጣሪ ኮሚቴው ያወጣው ሪፖርት፣ ክስና ሰነድ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ግለሰቦች የደረሳቸው ሲሆን በምዝበራው ከተጠረጠሩት መካከል የጥናትና ስትራቴጂ ሃላፊ የነበሩት ኢ/ር ጌታነህ ባልቻ፤ የተባለው ገንዘብ መባከኑን አምነው፣ የሚደርስባቸውን ገንዘብ ለፓርቲው ለመመለስ ቃል እንደገቡ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

“የግፍ ግፍ የሚሆነው ሲታገሉ ለታሰሩ የፓርቲው አመራሮች ከውጭ የተላከውን ገንዘብ ሳይቀር መመዝበራቸው ነው” ያሉት ምንጮቹ፤ የፓርቲው ሊቀመንበርም ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ለ18 ቀናት ከቢሮው ጠፍተው ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በየካፍቴሪያው ሲሰበሰቡ እንደነበር ተናግረዋል። ሰሞኑን የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ በአስቸኳይ ይጠራ መባሉን በመስማታቸው መጥተው ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት፣ በስራ ላይ እንዳሉ ለማስመሰል ሞክረዋል ያሉት ምንጮች፤ “ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በጐንደርና ኦሮሚያ በተነሳው ሁከት ዙሪያ አንድም ቀን ለሚዲያ መግለጫ አለመስጠታቸው ስራቸው ላይ እንዳልነበሩ ያሳያል” ብለዋል፡፡

ስለገንዘብ ምዝበራው የጠየቅናቸው የቀድሞው የፓርቲ ም/ሊቀመንበር አቶ ስለሺ ፈይሳ፤ ጉዳዩ በዲሲፕሊን ኮሚቴ መያዙን ጠቁመው፣ በግለሰቦች የእርስ በእርስ ግጭት የመጣ ስም ማጥፋት እንጂ እሳቸው በጉዳዩ እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ወይንሸት ሞላ በበኩላቸው፤ ጉዳዩ ተራ አሉባልታ መሆኑን ጠቁመው የዲሲፕሊን ኮሚቴው የሚወስነውን እየጠበቁ እንደሆነ ገልፀዋል። ተናግረዋል፡፡ የቀድሞው የፋይናንስ ሃላፊ አቶ ወረታው ዋሴም በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፣ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

የፓርቲው ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ እንደሻው እምሻው ደግሞ በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግረናቸው በአጣሪ ኮሚቴው የቀረበው ሪፖርት የገንዘብ ምዝበራው መፈፀሙን ያመለክታል ያሉ ሲሆን፤ ጉዳዩ በዲሲፕሊን ኮሚቴው ጥብቅ ክትትል የተደረገበት ነው ብለዋል፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡
*********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories