የሁከቱ መንስኤ – ማስተር ፕላኑ? ጸረ ሰላም ኃይሎች? ወይስ…?

አምስትም ሰው ይሙት አስር አሊያም 50 ይሁን 60 ባሳላፍናቸው ሳምንታት በኦሮሚያ ከተሞች በተነሳው ሁከት ህይወታቸውን ያጡት ወገኖቻችን ጉዳይ እጅግ አሳዝኖኛል፡፡ ለአገራችንም ሌላ ጥቁር ጠባሳ ጥሎብን አልፏል፡፡ ነገሩን ከሟቾች ወገን ሆነን ስናስበው ደግሞ ኃዘኑ ዛሬ አይደለም ነገም ስለመብረዱ እጠራጠራለሁ፡፡

ለዚህ ሁሉ አደጋ መንስኤው ማን ነው? ተጠያቂወስ ማን ሊሆን ነው? በእኔ እምነት መንግስት ይሄንን ጥያቄ ጊዜ ሰጥቶ ሊያስብበትና መልሱንም ሊፈልግ ይገባዋል፡፡ በዚህ ስራም የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማት አባቶችም ሊካተቱበት የግድ ነው፡፡ አለበለዚያ ነገሩን ከስሩ ፈልፍሎ ማውጣት ቢቻል እንኳን የመንግስት ተሿሚዎች ሪፖርት ስለሚሆን በሁሉም ዘንድ ተአማኒነትን ላያገኝ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ጉዳዩን ሳያጣሩ ሸፋፍኖ ለማልበስ ጥረት የሚደረግ ከሆነ ሌላ የጥፋት ፈንጅ ቀብሮ ማለፍ ይሆናል፡፡

ቀደም ብሎም በተመሳሳይ በማስተር ፕላኑ ሰበብ በተነሳው ሁከትና ረብሻ 9 ሰዎች ሞተው ነገሩ ተለባብሶ ቀረ፡፡ ይሄውና አሁንም መልሶ አገርሽቶ ካምናው በላቀ ሁኔታ ሁለትና ሶስት እጥፍ የሰው ህይወት ተቀጥፏል፡፡ ንብረት ወድሟል፡፡ አሁንም እንደ ቀደመው ጊዜ ክስተቱን አለባብሶ በደፈናው “ጸረ ሰላም ኃይሎች” ተብሎ ሊታለፍ ታስቦ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም በሚቀጥለው አመትም ሁከቱ ላለመነሳቱ ምንም ዋስትና የለምና፡፡

ስለሆነም መንግስት ጉዳዩን ከወዲሁ ሊያስብበትና በግልፅ የችግሩን መስንስኤ የሚያጣራ አካል ሊያቋቁም ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡ ከዚህ ምክረ ሀሳቤ ስመለስ ግን ነገሩን በወፍ በረር በመጥቀስ የችግሩን ምክንያት አረዳዴንና መፍትሄ የምለውን ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡

በእኔ እምነት ለችግሩ ዋናው መንስኤ ማስተር ፕላኑ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በየትኛውም አለም የልማት እቅድና ፕላን ለግጭት መንስኤ ሲሆን ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ስለዚህ ማስተር ፕላኑ ገፊ ምክንያት ወይንም በእንግሊዘኛው /immediate cause/ ሊሆን ይችላል እንጂ መሰረታዊ ምክንያት አይደለም እላለሁ፡፡

Photo - Oromo protests - Shewa zone

እንግዲያውስ መሰረታዊው ምክንያት ምንድነው?

በእኔ እምነት የህዝቡ ቁጣ መሰረታዊ ምክንያቱ የተለያየ ነው ቢባል እንኳን የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው ስለ ማስተር ፕላኑ በቂ ግንዛቤ አለመፈጠሩ ብሎም ከዚህ ቀደም በልማትም ይሁን በሌላ ምክንያት የእርሻ መሬታቸውን ለቅቀው የተነሱ ሰዎች ዛሬ ያሉበት ሁኔታ ነው፡፡

እንደሚታወቀው አገራችን በገባችበት ፈጣን የኢኮኖሚ ልማት ሳቢያ አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን በዙሪያዋ ያሉና ሌሎች ከተሞችም መሬት በገፍ የሚፈልጉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይሀ መሬት ደግሞ ቀድሞ በአርሶ አደሮች የተያዘ ነው፡፡ ስለሆነም አርሶ አደሮቹ ለልማት ሲባል መሬታቸውን መልቀቃቸው አልቀረም፡፡

ጥያቄው ያለውም እዚህ ላይ ነው፡፡ አርሶ አደሩ መሬቱን እንዲለቅ ሲደረግ መጀመሪያ በእርሱ መሬት ሊካሄድ ስለታሰበው ልማት እንዲያምንበት ተደርጓል ወይ? አምኖበታል ከተባለም ለመሬቱ የሚሰጠው ካሳ መልሶ ሊያቋቁመው የሚችል መሆን አለመሆኑስ ተፈትሿል? ይሄ አንድ እውነታ ነው፡፡

በመቀጠልም አርሶ አደሩ ከመሬቱ ሲነሳ በቀጣይ ለእሱና ለቤተሰቡ ህይወት ምን ታስቧል? ይሄም መመለስ ያለበት ሌላ እውነታ ነው፡፡ መሬቱን ወስዶ 60 እና 70 ሺህ ብር ብቻ ሰጥቶ ያለምንም ምትክ ቦታ ሂድ ማለት ለጊዜው የተሳካ ስራ የተሰራ ሊያስመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ውሎ አድሮ ያ አርሶ አደር ገንዘቡን ሲጨርስ ቤተሰቦቹን ይዞ ልመና እንደሚወጣ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም መሬት ከማረስ ከብት ከማገድ የዘለለ ልምድና እውቀት የሌለው አርሶ አደር ቢዘያ 70 እና 80 ሺህ ብር ምን አይነት ስራ ሰርቶ ቤተሰቡን ሊያኖር ይችላል? ያውም ልባም አርሶ አደር ከሆነ ማለት ነው፡፡ አለበለዚያማ እንዳየነው በየመሸታቤቱ ገንዘቡን ረጭቶ ባዶ እጁን ነው የሚቀረው፡፡

ስለዚህ የእነዚህን አርሶ አደሮች እጣ ፋንታ የተመለከተ ሌላ ባለመሬት ዛሬ ድንገት ከመሬት ተነስቶ መንግስት መሬትህ ለልማት ይፈለጋልና ካሳ እንካ ቢባል ይቀበላል? በጭራሽ፡፡ እንደ እከሌ ልሆን ነው እንዴ በሚል በጭራሽ በጄ አይልም፡፡ በተቃራኒው ቀድመው ለልማት የተነሱ አርሶ አደሮች በተሰጣቸው ካሳ ህይወታቸው ከቀድሞው ይልቅ ተለውጦ መንግስትም በአግባቡ አቋቁሟቸው ቢመለከት እነሱ ተነስተው በተከናወነው ልማት ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎችን ቢያይ ኖሮ አዲስ ተነሾቹ ያለማንም ጎትጓች መሬታቸውን ለልማት ማስረከባቸው አይቀርም ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ለመልሶ ልማት የተነሱ ያረጁ አካባቢ ነዋሪዎች የተሻለ መኖሪያና አከባቢ ስላገኙ የሌላ አካባ ነዋሪዎችን ለምን በእኛ አካባቢ ኮንዶሚኒየም አይሰራም? ለምን እኛስ እንደ ልደታ አራት ኪሎ አካባቢ ነዋሪዎች እድሉ አይሰጠንም? ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በአርሶአደሩ አካባቢ ያለው እውነታ ግን ከዚህ ለቅል ነው፡፡ በቂ ግንዛቤ ስለማይፈጠር፣ ተነሺዎችንም ለማቋቋም ስራ ስለማይሰራ ወዘተ ወዘተ አርሶ አደሩ በመሬቱ የመጣ ሁሉ በአይኑ የመጣ አድርጎ ይቆጥርና አንገቱን ለቢላዋ ደረቱን ለጥይት ይሰጣል፡፡

አምናም ሆነ ዘንድሮ በኦሮሚያ ከተሞች የሆነው ይሄው ነው፡፡ የመንግስት ተሿሚዎች በተለይ የኦህዴድ ሰዎች ስለማስተር ፕላኑ ጠቃሚነት ሙሉ እምነት ካለቸውና ነገ መልሶ አርሶአደሩን የሚጠቅም ከሆነ ስለምን ህዝቡን በግልጽነት ማወያየት ተሳናቸው? ነው ይንስ ሰሞኑን በአንዳንድ ሚዲያዎች ላይ እንደተደመጠው “ጊዜ አጥተን ህዝቡን ሳናወያየው ቀርተን ነው” የሚለው ምላሽ የመንግስትም አቋም ነው ብልን እንውሰድ? ይሄ ስህተት ነው፡፡ በጭራሽ ከተፈጠረው ችግር አንጻር ምክንያት ተደርጎ ሊቀርብም የማይገባው ምላሽ ነው፡፡

አምና “ማስተር ፕላኑ ቀርቷል” ተብሎ ቃል የተገባለትን ህዝብ “ጊዜ አጥሮናል” በሚል ሰንካላ ምክንያት ድንገት እቅዱን ለማስቀጠል መንቀሳቀስ ፍጹም ወደር የሌላው ስህተት ነው፡፡ በቀጣይም ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት እንዲያጣ የሚያደርግ ተግባር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ነገ መንግስት አንድ ነገር ቢናገር ማነው የሚያምነው? ማንስ ነው አበጀህ የሚለው? ማንም፡፡ ስለሆነም ያለፈው አለፈ፡፡ የሆነውም ሆነ፡፡ በቀጣይ ስለሚሆነው ግን ቁጭ ብሎ ማሰብ ከመንግስት የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

“ግርግር ለሌባ ይመቻል” እንዲሉ የተፈጠረውን ሁከት ጸረ ሰለም ኃይሎች አባብሰው የራሳቸውን አጀንዳ ማለትም መንግስትን በኃይል የመቀየር ፍላጎት ለማስፈጸም ተንቀሳቅሰውበታል፡፡ ይሄ ደግሞ ዝም ብዬ የምለው ሳይሆን የአሸባሪዎቹ ግንቦት ሰባትም ይሁን ኦነግና ሌሎች መግለጫዎች ያሉት ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሩን የቀሰቀሱት እነሱ ናቸው ብሎ መውሰድ ወደ ውስጥ አለማየትን ያስከትላል፡፡ የችግሩ ዋነኛ ምክንያት ሹመኞቹ ናቸው፡፡

እንዴት? ቢባል መልሱ አምና ቀርቷል ብለው ቃል የገቡትን ማስተር ፕላን ዘንድሮ ያለምንም ህዝባዊ ውይይት ለመተግበር መንቀሳቀሳቸው ነው፡፡ ይሄ ግን ፕላኑን ለመተግበር የመንቀሳቀስን ያህል ቀላል እንዳልሆነ ለሳምንታት የተፈጸመው ክስተት አሳይቶን አልፏል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ሳይቀር በጀት የመደበለት መስሪያቤት ተቋቁሞ ሲያበቃ መልሶ ማስተር ፕላኑ ይተገበራል የተባለው ውሸት ነው፣ ተቋቁሟል የተባለው መስሪያቤትም በህገወጦች የተቋቋመ ነው፣ አጣርተን እርምጃ እንወስዳለን፣ ማስተር ፕላኑ ቀርቷል…. የሚሉና ያረፈዱ መግለጫዎችን ሲነገሩ ታዝበናል፡፡

አንድ መታወቅ ያለበት እውነት አለ፡፡ ዛሬ ህዝቡ ከመንግስት መገናኛ ብዙኃን ቀድሞ ሄዷል፡፡ ስለዚህ እንደ 1980ዎቹ እና 90ዎቹ በቴሌቪዥን አሊያም በጋዜጣ ከሚሰጥ መግለጫ ይልቅ ሰው በፌስቡክና መሰል ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ጥገኛ ሆኗል፡፡ እምነቱንም በዚያ አድርጓል፡፡ በሌላ አነጋገር እያንዳነዱ ሰው ጋዜጠኛ ሆኗል፡፡ ያገኘኘውን መረጃና ማስረጃ ሁሉ በፌስቡክ ገጹ እየለቀቀ የመገናኛ ብዙኃንን ዘገባዎች ማሳጣት ከጀመረ አመታት ተቆጥሯል፡፡ ስለዚህ ከቀድሞው አስተሳሰብ ያልተላቀቀ ሹመኛና መገናኛ ብዙኃን ካለ ይሄን እውነት ይረዳ፡፡ የሰሞኑ ክስተት ያሳየንም ይሄንኑ ነው፡፡

ከዚህ ሂደት የምንረዳው የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከህዝቡ መቅደም አለመቻላቸውን ነው፡፡ ህዝቡ መንግስትን ቀድሞታል፡፡ ይሄንን የተነጠቀውን የቀዳሚነት መንበር ማሰከበር ከተፈለገ አሁንም ይሁን ወደፊት ግልጽ አሰራር ይስፈን፡፡ ህዝቡ በሁሉም የልማት እቅድ ይመንበት፡፡ ህዝብን ለምርጫ ሰሞን መሰብሰብ ያብቃ፡፡ አንዲት የምርጫ ዘመን ዋዜማ በሆነች አመት ላይ ሰብስቦ አራት አመት መበተን ጣጣውን እያየነው ነው፡፡ በጸረ ሰላም ኃይሎች እያሳበቡ የራስን የውስጥን ድክመት ማለባበስም የትም አያደርስም፡፡ ሌባ እኮ የሚገባው እንኳንስ ክፍቱን የተተወ ቤት አግኝቶ ይቅርና በብዙ ነገሮች የተዘጋንም ቤት ሰብሮ ነው፡፡ ስለዚህ ሜዳ ላይ የበተነውን ህዝብ ጸረ ሰላም ኃይሎች አግኝተው በደካማ ጎኑ ገብተው ቢቀሰቅሱትና አደባባይ ቢያስወጡት በእኔ እምነት ጥፋቱ የእነሱ ሊሆን አይችልም፡፡ ጥፋቱ የራሱ የህዝቡ መሪ ሜዳ ላይ በታኙ አካል ብቻ ነው፡፡

**********

Areaya Getachew (MA) is a public relations expert at a foreign embassy. He studied second degree at Addis Ababa University and was deputy editor in-chief of Addis Zemen newspaper.

more recommended stories