ሰሞኑን በኦሮሚያ ከተሞች የተካሔዱ ተቃውሞዎች ብዙ ነገሮችን እንድናስብ ያደረጉ ነበሩ፡፡ እንቅስቃሴው የብዙ እናቶችን ቅስም የሰበረ እና እንባ ያራጨ፣ ከምርጫ 97 ወዲህ (በላይ) ለመጀመሪያ ጊዜ መንግስትን ያስደነገጠ፣ በሽኩቻ ይታወቁ የነበሩት የአማራና ኦሮሞ ኤሊቶች ተስማምተው የታዩበት፣ . . . . .ወዘተ ነበር፡፡

ይህ በብዙዎቻችን አዕምሮ ውስጥ በርካታ ሐሳቦችን ያመላለሰው ክስተት እኔ ከምንም በላይ ያየሁት መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ለአጭር ጊዜ ድጋፍ ላይ ብቻ አተኩረው እየሰሩ መሆናቸውንና በዚህም ብዙ ነገር እያበላሹ መሆኑን ነበር ያየሁት፡፡ ከእስከዛሬው ይልቅ የወደፊቱ ያሳስባል እኮ!!

እኔ እንደዚህ አስባለሁ፤

ኦሮሞ በሀገሪቱ ግንባር ቀደም ብሔር ሆኖ እያለ ኦሮሚያ እምብርት ላይ ያለችው አዲስአበባ ኦሮሞን እንደሌሎች ማይኖሪቲዎች አማርኛን እንዲለምዱ የምታስገድድ፣ የባዕድነት ስሜትን የምትፈጥር፣ 81 ፐርሰንት ነዋሪዋ ኦሮሞ ያልሆነባት መሆኗ ሲታሰብ፤ ክልሉም በሀገር አቀፍ ደረጃ ካለው ቁጥርና የኢኮኖሚ አቅም አንፃር ያለው ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም መሆን ካለበት(ከሌሎች አንፃርም ቢታይ) ዝቅተኛ መሆኑ፣ ቋንቋው ከአማርኛ በላይ ቀርቶ የአማርኛን ያህል እንኳ ለጋራ መግባቢያነት የማያገለግል መሆኑ፣ . . . . . ከሌሎች የቅርብ ጊዜ ታሪኮቻችን ጋር ተደማምሮ በእያንዳንዱ የኦሮሞ ብሔርተኛ ዘንድ የሚፈጥረው ስሜት ቀላል አይደለም፡፡

ይህንን ተቃርኖ(ፓራዶክስ) ማንንም ሳይጎረብጥ እንዲስተካከል ከመስራት ይልቅ ኦነግና ኦህዴድን ጨምሮ አብዛኛው ያገባኛል ባይ ለጊዜያዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያነት መጠቀምን ሲመርጡ ነው የሚስተዋለው፡፡ የፕሮፌሰር ላጲሶን ቃል ልዋስና ይህ አካሔድ የበላይነትም የበታችነትም የማይሰማውን ኦሮሞን የተጠቂነት ስሜት እንዲያዳብር ተፅዕኖ አሳድሮበታል፡፡

ኢኮኖሚውን ያየን እንደሆነም የሐገራችንን ግማሽ ሐብት የያዘችው ብቸኛዋ የሐገሪቱ የኢኮኖሚ ሜትሮፖሊስ አዲስአበባ ኦሮሚያ እምብርት ላይ የምትገኝ ከመሆኗ አንፃር በከተማዋ አቅራቢያ ያሉ ኦሮሞዎች ሁሉ ከሌሎቹ የሐገሪቱ አካባቢ ነዋሪዎች በተሸለ በስራ እድልና በከፍተኛ የመሬት ሊዝ ኪራይ(ሽያጭ) ዋጋ ተጠቃሚ ሊሆኑ ሲገባ ይህንን ተጠቃሚነታቸውን ግን መንግስት እየወሰደባቸው ነው፡፡ በዚህም አዲስአበባ ተነቅላ በሄደችልን ብለው የሚመኟት ከተማ ልትሆን በቅታለች፡፡

አሁን እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ከላይ የሚታዩትን ያህል ስስ አይደሉም፤ አሁን የምንፈተፍተውን ያህልም ቀላል መፍትሔ የላቸውም፡ የኦሮሞ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ሁሉ ከዚህ በፊት ተዘውትሮ እንደሚነገረው የአዲስአበባ ችግርና መፍትሔ ከብሔር አንፃር የሚተነተንና ሌላ ብሔርን (በተለይ አማራን) ተወቃሽ/ ተጠያቂ በማድረግ መፍትሔ የሚገኝለት አይደለም፡፡

የድሮውን እንተወውና አዲስአበባ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ፡-

– የህዝብ ቁጥሯ ከእጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡

– ኢኮኖሚዋ እስከ 10 እጥፍ አድጓል፡፡

– ከተቆረቆረችበት ዘመን ጀምሮ ባሉት 100 ዓመታት ካፈናቀለቻቸው በብዙ እጥፍ የበለጡ አርሶአደሮችን አፈናቅላለች፡፡

– ከተቆረቆችበት ዘመን ጀምሮ ባሉት 100 ዓመታት ከሳበቻቸው የሌላ ክልል (በተለይ የአማራና ደቡብ) ተወላጆች በላይ በርካቶችን አሁን ነዋሪዎቿ አድርጋቸዋለች፡፡ . . . . . . . ሌላም ሌላም!!

የዚህን መንስዔ በጥንቃቄ መረዳት መፍትሔውን ለመፈለግ ያስችለናል፡፡

Map - major Ethiopian cities

ይህ ኦሮሞን የሚያገልልና ሌሎች ብሔሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአፓርታይድ ስርዓት በመዘርጋት የመጣ አይደለም (በዚህ ረገድ የተበላሸ ነገር ካለ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን የሚመለከት እንጂ ብሔርን በጅምላ የሚመለከት ነገር ያለ አይመስለኝም)፡፡

ከላይ ስናየው ሌሎች ብሔሮች በተለይ የደቡብ አማራና ትግራይ ተወላጆች በስፋት ወደአዲስአበባ የሚጎርፉ ሲሆን ኦሮሞዎች ግን ለከተማዋ ካላቸው ቅርበት አንፃር ከሌሎች በላይ ከተማዋን መቀላቀል ሲገባቸው በተቃራኒው አፍንጫቸው ስር ላለችው አዲስአበባ ባይተዋር ሆነው መቅረታቸው ለምን የሚያስብል ነው፡፡ ከተማዋ አማርኛ ተናጋሪ መሆኗ የራሱ ተፅዕኖ ቢኖረውም ዋናው መንስዔ ግን ከራሱ ከኦሮሞ አንፃር ሚታይ ነው፡፡ ኦሮሞ በተለይ በአዲስአበባ ዙሪያ ያለው የሸዋ ኦሮሞ የሌሎቹን (የአማራ፣ ደቡብና ትግራይ) አርሶአደሮችን ያህል በድህነት ያለመጠቃቱ አንዱ መንስዔ ነው፡፡ አሁን ከአዲስአበባ የቤት ሰራተኞች ቢያንስ 75 ፐርሰንቱ አማሮች ናቸው፤ አብዛኞቹ ሊስትሮዎችና ሎተሪ አዟሪዎች ደቡቦች ናቸው፤ አብዛኞቹ የቀን ሰራተኞችም አማሮችና ደቡቦች ናቸው፡፡ ግን ደግሞ የእነሱን ያህል የተቸገረውን የሐረርጌ ኦሮሞ የተሸለ ኑሮ ፍለጋ ወደአዲስ ያለመጉረፉን ስናይ ደግሞ ባጠቃላይ አብዛኛው ኦሮሞ ከሌሎች አንፃር ተቸግሮ እንኳ የአባት ምድሩን መልቀቅ እንደሚከብደው ማየት እንችላለን (ግን ምቹ ሁኔታዎች ቢኖሩ የተሸለ ኑሮን የሚጠላ እንደሌለና በዚህ ረገድ ምቹ ሁኔታ እንደሌለ ሳንረሳ)፡፡

ዛሬ ከቁጥራቸው አንፃር ከአዲስአበባ ኢኮኖሚ ትልቅ ድርሻ ያላቸው ጉራጌዎችና ስልጤዎች ከተሜነትንና ንግድን እንዲለምዱ በንጉሱ ከተደረገላቸው ልዩ ድጋፍ ባሻገር የአብዛኞቹ ሀብት መሰረት ከትንሽ ነገር ተነስቶ ማደግ እንደሆነው ሁሉ ዛሬ አዲስአበባ ላይ ለእለት ጉርሳቸው የሚፍጨረጨሩት ከላ የዘረዘርኳቸው ለፍቶአዳሪዎች የነገ የአዲስአበባ መካከለኛ ገቢ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ነገ በጥቃቅንና አነስተኛ አደራጁን የሚሉት፣ የኮንዶሚኒዬም ቤት የሚጠይቁት፣ መሬት በሊዝ የሚጫረቱት እነኚህ ናቸው (ከነባሮቹ የአዲስአበባ ነዋሪዎችና ሀብት ይዘው ከሚመጡት የክልል ሰዎች ባሻገር)፡፡

በሌላ አነጋገር አዲስአበባ አሁን እየተከተለች ያለችው መንገድ ከተማዋ “”ወደፊትም”” ለኦሮሞ ባዕድ ሆና እንድትቀጥል የሚያደርጋት ነው፡፡

ምን ማድረግ ይሻላል/ይቻላል?

1.. አዲስአበባ ብቸኛ የኢኮኖሚ ማዕከል በመሆኗ የተፈጠረው ይህ ምስቅልቅል ለሌሎች ክልሎችም የኢንቨስትመንት ድርቅን አስከተለባቸው እንጂ አልጠቀማቸውም (ለምሳሌ የአማራ ክልል ከገበሬዎች መሬት ወስዶ ለአበባ ኢንቨስትመንት ካዘጋጀ በኋላ ኢንቨስተር በመጥፋቱ መሬቱ ከሁለት ያጣ እንደሆነ ሰምቼ ነበር)፡፡

ባለፉት አመታት የአዲስአበባ ኢኮኖሚ 10 እጥፍ ከሚያድግ 5 እጥፍ አድጎ ቀሪው ሀብት መቀሌ፣ ባህርዳር፣ ድሬዳዋ፣ ጅማና አዋሳ ላይ ኢንቨስት ቢደረግ ኖሮ ፤ በሌላ አነጋገር ባለፉት 24 አመታት አዲስአበባ ላይ ኢንቨስት ከተደረገው ገንዘብ ግማሹ 5ቱ ከተሞች ላይ በኢንቨስትመንት መልኩ ቢከፋፈል ኖሮ ሐገሪቱ ለራሷ 5 ተጨማሪ 5 የኢኮኖሚ ሜትሮፖሊሶች ይኖሯት ነበር፡፡ ባህርዳር ከተማ የአዲስአበባን ያህል ኢኮኖሚያዊ አቅም ቢኖራት ያለጥርጥር ከጎጃምና ጎንደር ወደአዲስአበባ የሚጎርፈው የተሸለ ኑሮ ፈላጊ ሁሉ ባህርዳርን ይመርጥ ነበር፡፡ ወላይታውም ዋና መዳረሻው ወላትኛ እያወራ ሊሰራ የሚችልባትን አዋሳን ያደርግ ነበር፡፡ አሁን ግን የአዲስአበባን 1/20ኛ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያለው ከተማ እንኳ መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡ በሌላ አነጋገር ከመላ ሐገሪቱ የሚፈጠር ኢኮኖሚያዊ ጫናን አዲስአበባ ብቻ እንድትሸከም የተደረገችበት ሁኔታ በየአካባቢያቸው ባሉ ከተሞች ይከፋፈል ነበር፡፡

2.. ሌላው መፍትሔ የአዲስአበባ ዙሪያ የኦሮሞ አርሶ አደር በአዲስአበባ የመገኘቱን “ሲሳይ” እንዲጠቀምበት እድሉን ማመቻቸት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አዲስአበባ የሐገሪቱ የቢዝነስ ማዕከል መሆኗን ተከትሎ የአዲስአበባና ዙሪያዋ መሬት ዋጋ ከሌሎች አካባቢዎች ሊወዳደር በማይችልበት ሁኔታ ከፍተኛ ዋጋ አለው፡፡ የመሬት ባለቤት የሆነው አርሶ አደርም ይህንን መሬት ማጣት ካለበት መሬቱ የሚያስገኝለትን ከፍተኛ ዋጋ አግኝቶ መሆን አለበት፡፡

በዚህ ረገድ መንግስት ሊያስቀር የሚችለው የተወሰነ ነገር ሊኖር መቻሉ ተቀባይነት ያለው ቢሆንም ለገበሬው የመሬቱን ትክክለኛ ዋጋ 1/10ኛ ገደማ ብቻ የሚከፈልበት አሰራር ግን መንግስት በልማት ስም ዘረፋ ነው ወይ የያዘው ያስብላል፡፡

3.. ከዚህ ጋር በተያያዘ አርሶ አደሮች በመሬታቸው ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችን በአክሲዮን በማደራጀትና አርሶ አደሮችም የአክሲዮኑ ባለድርሻ ሚሆኑበትን አሰራር በመከተል መንግስት እውነተኛ ግራዘመም ፖለቲካ አራማጅ መሆኑን ማረጋገት አለበት፡፡ አርሶአደሮችን አደራጅቶ ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲሰማሩ ማድረግንም እንደአማራጭ ማየት ተገቢ ነው፡፡ እስካሁን ለባለሀብቱ የሚፈልገውን መሬት መስጠት ላይ እንጂ በዚህ ምክንያት ኑሮው ስለሚቃወስበት ባለመሬት ብዙም አስበንበት እንደማናውቅ ተግባራችን ይናገራል፡፡ ይህንን ማድረግ ከቻልን የአዲስአበባን መስፋፋት ኦሮሞው ይፈልገው ነበር፡፡

ይህ አሰራር ኦሮምኛ ተናጋሪዎች የሚበዙባቸው ሰፈሮች እንዲበራከቱ ያደርጋል (በነገራችን ላይ በአዲስአበባ መስፋፋት የሚፈናቀለው ገበሬ የት ሄደ ለምትሉ ትክክለኛው መልስ የትም አልሔዱም፣ አሉ፣ ግን ከእነሱ ከ5 እጥፍ በላይ በሆኑ ሌሎች ነዋሪዎች ስለተዋጡ ልናያቸው አልቻልንም)፡፡ ኦሮምኛ ተናጋሪ የሚበዙባቸው ሰፈሮች በዙ ማለት ደግሞ አዲስአበባ ኦሮምኛንም መናገር የምትጀምርበትን መንገድ ተያያዘች ማለት ነው፤ መቼም ለስራ ወይም ለሌላ ጉዳይ ወደኦሮምኛ ተናጋሪ ሰፈሮች የሚሔድ ሰው ኦሮምኛ ስለመልመድ ማሰቡ አይቀርም፡፡ ይህ የተሸለ ኑሮ ፈላጊ የክልል ኦሮሞዎችንም ወደአዲስአበባ እንዲመጡ የሚያበረታታ ነው፡፡

በዚህ መልኩ የማንንም መብት ሳይጥሱ አዲስአበባ በሂደት ኦሮሞ ፍሬንድሊ ከተማ እንድትሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ የብሔር ተዋፅዖው ላይ ተዓምራዊ ለውጥ መጠበቅ ቢከብድም ለውጦች እንደሚኖሩ ግን እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡

4.. ከዚህ ውጪ በሂደት ነቀምቴ ወይም ጭሮ የአዲስአበባን ያህል እንኳ ባይሆን የአዲስአበባን ሩብ ወይም ግማሽ ያህል ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላቸው ከተሞች ቢሆኑ በሜኑዋቸው ውስጥ ላፊሶን ወይም ጨጨብሳን የሚያቀርቡ፣ የሸጎዬና ረገዳ ባህል ቤቶች የሞሉባቸው ፣ ሌሎችም አዲስአበባ የሌሏት እሴቶች ያሏቸው የ “ኦሮሚያ” ከተሞች እንዲሆኑ ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ከተሞቹ ሲስፋፉ የተሸለ ኑሮ ፍለጋ የሚመጡት የአቅራቢያ ከተማ ነዋሪዎችም ሆኑ በከተሞቹ የሚዋጡ የገጠር ቀበሌዎች ነዋሪዎች ኦሮሞዎች ስለሆኑ ከተሞቹ እየተስፋፉ በሂዱ ቁጥር የኦሮሞ ነዋሪያቸው ድርሻ በፐርሰንትም እየጨመረ መሔዱ አይቀሬ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ለኦሮሞ ብሔርተኛ ፓርቲ አዲስአበባን ኦሮሞ ኦሮሞ የምትሸት ከተማ ከማድረግ ይልቅ ሌሎች ኦሮምኛ ተናጋሪ የአዲስአበባ አቻ ከተሞችን መፍጠር ቀላል ነው፡፡ ልብ በሉ፤ አዲስአበባ በእኛ እድሜ ኢኮኖሚዋን በብዙ እጥፍ አሳድጋለች፤ ወደፊትም ከእስከዛሬው የበለጠ ብዙ እጥፍ ልታድግ ትችላለች፡፡ በሌላ አነጋገር ከእስከዛሬው የበለጠ ወደፊት ብዙ ለውጦች ይጠብቁናል፡፡ እነኚህ ለውጦች ምን አይነት መልክ ሊይዙ ይገባል የሚለው ላይ ማተኮር እና አቅጣጫ መቀየስ ያለብን ይመስለኛል፡፡ አዲስአበባ ብቸኛዋ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማዕከል፣እንዲሁም ከ15 ሚሊዮን በላይ ነዋሪ ያላት ሜጋ ሲቲ ልትሆን ትችላለች፡፡ እያንዳንዳቸው ከ3 ወይም 5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪ ያላቸውና የኢኮኖሚ ማዕከል የሆኑ ከ5 በላይ ከተሞች ያሏት ሐገር እንድትኖረንም ልናደርግ እንችላለን፡፡ ውሳኔው በእጃችን ነው!

*********

አዲስ ከድሬዳዋ - Frm. journalist; currently communicator

more recommended stories