የአቶ ዳዊት ገ/ሔር ቤት በአሸዋ ላይ ወይስ በዓለት?

(ስሉሥ ወልደሂወት)

“ማንም የቆመ የሚመስለው ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠነቀቅ”! መጽሓፍ ቅዱስ

የሰው ልጅ ፍላጎት ሁሌ የሚያድግና የማይሟላ በመሆኑ የለውጥ ጥያቄን ለመመለስ ሁሌም ሰለተሻለ አማራጭ፣ ስለተሻለ ዘዴ ወይም ስትራቴጂ ማሰቡና መነጋገሩ ተገቢና ጤናማ መሆኑ የማይታበል እውነት ነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ዘንድ የተቀደሰና ከነቀፋና ትችት የፀዳ የፖሊሲ አቋም ወይም የፖሊሲ አፈፃፀም የማይኖር መሆኑም እንደዚሁ። ዜጐች በግልም ይሁን በተደራጀ መልኩ በነፃነትና ከማንኛውም ተጽእኖ በጸዳ መልኩ የፖሊሲ አማራጮችን መተቸችና የመልካም አስተዳደር ግድፈቶችን ነቅሶ ማውጣት የሚችሉበት ሁኔታ ከተፈጠረ ያ ማህበረሰብ የታደለ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የፖለቲካ መሪዎች በዓቅም ውስንነት፣ በግንዛቤ እጥረት፣ የግል ፍለጎት በማሰቀደም ወይም በቅንነት እጦት ምክንያት የሕዝቦችን ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው። በመሆኑም የፖሊሲ አማራጮችንና የአፈፃፀም ግድፈቶችን ከመተቸት ባላፈ ፖሊሲውን ለማስፈፀም ሃላፊነት የወሰዱ የፖሊቲካ ድርጅቶች አመራር፣ ውስጣዊ ድርጅታዊ ህይወትና የአመራሩ የግል ማንነት ሳይቀር አብጠርጥሮ ማወቅና መተቸት በሰለጠነው ዓለም የተለመደና ውጤታማ የሆነ የዲሞክራሲ ባህል ነው፡፡

ከሰሞኑ አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር የተባሉ ዜጋ በተለየ ሁኔታ በህወሓትና ህወሓት በሚመራው የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የልማትና መልካም አስተዳደር ፖሊዎችና አፈጻጸም ላይ የሰላ ትችት በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ፡፡ የአቶ ዳዊት ትችት ከግል ገጠመኝና ትዝብት በመነሳት በአጠቃላይ በስርዓቱ፣ ስርዓቱ በቆመባቸው ምሰሶችና የማስፈፀምያ ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎች እንደዚሁም የድርጅቱና የድርጅቱ አመራር ዓቅምና ህዝባዊነት ላይ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ቀደም ብዬ እንዳልኩት ከፖሊሲ የተሻለ ፖሊሲ፣ ከተሻለው ፖሊሲ እጅግ የተሻለ ፖሊሲ መኖሩ የማይቀር ስለሆነ፤ አቶ ዳዊት ስለተሻለ አመራር፣ ስለተሻለ አፈፃፀም ቢናገሩ እንደዜጋ ስለአዩትና ስለሰሙት ጉዳይ ስሜታቸውና ሃሳባቸውን ቢገልጹ ቅር የሚያሰኝ እንዳልሆነ፤ ይልቁንም እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ የፀና እምነት አለኝ፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ውስጥ ልማት የለም፣ መልካም አስተዳደር የለም ማለት የእውነታና የማስረጃ ጉዳይ ስለሆነ እንከራከርበታለን፡፡ አለ የሚል ወገን ማስረጃውን ያቀርባል። የለም የሚለው ደግሞ እንደዚሁ። አፈጻጸም ብቻ ሳይሆን፤ የፖሊሲ አማራጭ በተመለከተም ያው ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የመንግስት የልማት፣ የዲሞክራሲና የሰላም ፖሊሲዎች በተለየ ሁኔታ ትግራይ ውስጥ አይሰሩም ብሎ በንድፈ ሃሳብና በተግባር ደረጃ መከራከር ብሎም አማራጭ ማቅረብ ችግር ያለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሌላው የክልሉ መንግስትና አመራር የትግራይ ህዝብ በመልካም አስተደድርና ልማት ዙሪያ ማግኘት የሚገባውን እንዲያገኝ፣ መድርስ ያለበት ጋ እንዲደርስ አድረጓል ወይስ ኣላደረጉም? የሚሉት ጥያቄዎች ሊነሱና ክረክር ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንደሆኑ አምናለሁ። አንድ ዜጋ በግለሰብ ደረጃ አማራጭ ማቅረብ ላይጠበቅበት ይችላል፡፡ ሆኖም አቶ ዳዊት ስርአቱን ከመንቀፍ አልፈው የተሻሉ ያሏቸው አማራጮችም ያቀረቡ በመሆኑ አማራጭ ሃሳቦቹ ወደፊት የሚያዩ ናቸው ወይስ ወደኋላ የሚል ጥያቄ በማንሳት ትዝበቴን በሚከተለው መንገድ አቀረባለሁ። የቶ ዳዊት የፖሊሲና ትግበራ ትችት በትግራይ ላይ ያተኮረ በመሆኑ የኔም ፅሑፍ የሚያተኩረው በዚያው ጉዳይ ላይ ነው፡፡Map - Ethiopia, Tigrai

የትግራይ ህዝብ ቅን፣ ስራ ወዳድ፣ ነፃነት ወዳድ፣ ፍትህ ወዳድ ለክብሩና ነጻነቱ ውድ ዋጋ የከፈለ ትልቅ ህዝብ ስለሆነ፤ አሁን ካለው የተሻለና የበለጠ ሁሉ የሚገባው ህዝብ ነው፡፡ በመሆኑም ለትግራይ ህዝብ የተሻለውን ለሚመኝ ሰው ታላቅ ክብር ይገባዋል፡፡ የትግራይ ህዝብ አሁን ካለው በላይ የሚገባው ህዝብ መሆኑ የማይቀበል ካለ ያ ሰው የህዝቡ ጠላት ነው ብል እውነት ነው። ለትግራይ ሕዝብ ያላቸው ክብርና ፍቅር ደጋግመው የገለፁት አቶ ዳዊት ከህወሓትና አሁን ካለው የመንግስት ፖሊሲ የተሻለው የፖሊሲ አመራጭ እንዳለ ከመጠቆም አልቦዘኑም። ሰለሆነም የአቶ ዳዊት የፖሊሲ አማራጮች ምንድናቸው? እሳቸው ያቀረቡዋቸው የፖሊሲ አማራጮች በሶስት ጉዳዩች ከፍሎ ማየቱ ተገቢ ሆኖ ተይቶኛል። ከዚህ ቀጥሎ የምተቻቸው የአቶ ዳዊት የፖሊሲ አመራጮች፣ ለዓይጋ ፎረም፣ ለአሜሪካ ድምጽና ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጧቸው ቃለመጠየቆች በተደጋጋሚ የገለጹዋቸው በመሆኑ የአፍ ወለምታና ስሜት ወለድ እንዳልሆኑ ይልቁኑም ተቺው በሚገባ አጥንተውና አስበው ያቀረቧች ሰለሆኑ የጸኑ አቋሞቻቸው ናቸው በዬ አምኛለሁ። ሰለሆነም ነው አስተያየቴ ለመጻፍ የተነሳሳሁት።

የአቶ ዳዊት የሰላም ፖሊሲ አማራጭ

የትግራይ ህዝብ መሰረታዊ አጀንዳዎችና የዘመናት የትግል ዓለማዎች አንዱ የሰላም አጀንዳ አንዱ ነው። ምክንያቱ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው። ሰላም እሳቸውም እንዳሉት የውስጥና የውጭ ሰላም የሚያጠቃልል ሲሆን፤ ከአእምሮ ስጋት ነፃ መሆንና ጦርነትና ግጭት የሌለበት ሁነታን ያመለክታል፡፡ አቶ ዳዊት በአሁኑ ወቅት የትግራይ ህዝብ ሰላም የለውም፤ የሚኖረው በስጋት ነው። በመሆኑም ሰላም ያስፈልገዋል ያሉን ሲሆን፤ የትግራይ ህዝብ ሰላም እንደሌለው ለማመልከት ማስረጃም አቅርቧል። ማስረጃቸውም በጃንሆይ ዘመን ቀበሌና የቀበሌ ጥበቃ አልነበረም፡፡ ኗዋሪዎች በየቀበሌው አይፈተሹም ነበር። አሁን ግን በየቀበሌውና መስሪያ ቤቱ ይፈተሻሉ የሚል ነው፡፡ በጃንሆይ ወቅት ዜጎች ይፈተሹ ነበር ወይስ አይፈተሹም ነበር የሚል ጥያቄ ወደ ጎን ትተን? እሳቸው ይበጃል ወደአሉት የሰላም አመራጭ እንለፍ። አቶ ዳዊት ለህዝቡ ያቀረቡት የሰላም አማራጭ በጃንሆይ ዘመን የነበረው ዓይነት ሰላም ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ ሰላም የነበረው በጃንሆይ /በአፄ ሃይለስላሴ) ዘመን መንግስት ብቻ ነው ይሉናል፡፡ በመሆኑም እንደምታው የትግራይ ህዝብ በዘመነ ጃንሆይ የነበረው አይነት ሰላም ሊያገኝ ይገባል ነው፡፡ ህዝብ እኩልነቱ ሳይረጋገጥ፣ በሃገሩ እንደ ባእድ ተቆጥሮ ግፍና በደል ሲደርስበት፣ በቋንቋውና ባህሉ፣ እምነቱ መሳለቂያ ሆኖ ምን ዓይነት ሰላም ሊኖረው ይችላል የሚልውን ንደፈ ሃሳባዊና ተግባራዊ ጥያቄ ወደ ጎን ትተን በወቀቱ የነበሩትን አንዳንድ ሁኔታዎች እንመለከት።

ዘመነ ጃንሆይ የትግራይ ህዝብ ያፈራውን ሃብት በየመንገዱ በሽፍቶችና ወንበዴዎች የሚዘረፍበት ወቅት ነበር። ከዚያም አልፎ ያፈራውን ጥሪት፣ ያፈራውን ሃብት በጭቃሹሞች፣ ጉልተኞችና የፊውዳል ስርአቱ ሆድ አደሮች ይነጠቅ የነበረበት ወቅት ነበር። ለሰላምና መረጋጋት መነሻ የሆኑትን በራስ ቋንቋ መናገር፣ በራስ ባህል የመኩራትና የመማር ቀረቶ፤ ትግርኛ በመናገሩ የሚዘለፍበትና በንጉስ ነገስት ፊት ሳይቀር ትግሬ ገዳይ ብለው ለሸለሉና ለፎከሩ ሽልማት ይስጥበት የነበረ ወቅት ነበር። የትግራይ ህዝበ ፍትህን ፍላጋ አዲስ አበባ ድርስ የሚመጣበትና ተገዶ በማይገባው ቋንቋ የሚዳኝበት ወቅት ነብር። አንድ ህዝብ በማንነቱና እሱነቱ የሚሰጋ ከሆነ ምን ዓይነት የስነልቦና ሰላም ሊኖረው ይችላል? ይህ ጥያቄ ከአቶ ዳዊት በስተቀር ማንም ሰው ሊመልሰው የሚችል ያለ አይመስለኝም። ያ ወቅት የመሬት ፖሊሲው ፍትሃዊ አይደለም፣ አከባቢያችን በራሳችን እናስተዳደር ብሎ የጠየቀውና የጋሻ መሬት ፖሊሲ የተቃወመው የትግራይ ህዝብ በተውሶ አውሮፕላኖች በዋና ከተማው፣ በገበያ ቀን በቦምብ የተጨፈጨፈበት ወቅት ነበር። ያ ወቅት ለትግራይ ህዝብ የሰላም ወቅት ነበር ማለታቸው ሳያንስ የዛ ዘመን ሰላም አሁንም እንዲመጣ መመኘታቸውና ያን ለማሳካት ቆርጠው መነሳታች የገለጹት አቶ ዳዊት፤ አቅጣጫቸው ወዴት ነው የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አድርጐኛል፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ረገድ በአቶ ዳዊት አመለካከት የትግራይ ህዝብ ዘውዳዊው ስርአት ለመገርሰስ ያደረገው ትግል ከሰላም አጀንዳነት አንጻር እርባና ቢስ ነበር ብሎ ወደ መደምደም የሚያደርስ መሆኑም ልብ ይሏል። ምክንያቱ ሰላም እያለው ስለሰላም የህይወት መስዋእትነት ከፍሎኣልና።

የአቶ ዳዊት የዲሞክራሲና ስርዓት አማራጭ

የትግራይ ህዝብ በጽናት ከታገለላቻው መሰረታዊ ዓላማዎች የዲሞከራሲ ስርዓትና የዲሞክራሲ ስርዓት ሌላ ገጽታ የሆነውን መልካም አስተዳደር ዋናዎቹ ናቸው። አሁንም አቶ ዳዊት ትግራይ ውስጥ የዲሞክራሲ ስረዓትና መልካም አስተዳደር እንደሌለ ህወሓትና ፖሊሲው ዲሞክራሲ ማምጣት እንደማይችሉ ክፉኛ ተችተዋል፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት የትግራይ ህዝብ አሁን ካለው መልካም አስተዳደር የተሻለ መልካም አሰተዳደር፣ አሁን ካለው ሰብአዊ ክብር በላይ ክብር የሚገባው ህዝብ እንደሆነ አምናለው፡፡ አቶ ዳዊት ከዲሞከራሲ ስርአትና መልካም እሰተዳደር አንጻር ለህዝቡ የተሻለ ነገር ይገባዋል ማለታቸውን መተቸት አልችልም። ምክንያቱ ስለሚገባው።

ሆኖም የአቶ ዳዊት አማራጭ ምንድ ነው? ለእሳቸው የተሻለው የዲሞክራሲ ስርዓት አማራጭ አሁንም የጃንሆይ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ጃንሆይ እሳቸው ምርጥ ዘር የእግዚአብሔር ልእኩ ሲሆኑ፣ ሌላ ዜጋ የትግራይን ህዝብ ጨምሮ የሳቸው አገልጋይና ንብርት ተደረጎ ይቆጠር እንደነበር የሚያከራክር አይደለም። ከዚያ እልፎ የትግራይ ህዝብ በቋንቋና ማንንነቱ ምክንያት ብሄራዊ ጭቆና ይደርስበት ነበር። የትግራይ ተወላጅ ሴቶች ከብሄራዊ መደባዊ ጭቆና ባሻገር በሴትነታቻው ከሰው በታች ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። የትግራይ ተወላጅ ሙስሊሞች ከመደባዊና ብሄራዊ ጭቆና በተጨማሪ ሃይማኖታዊ ጭቆና ይደርስባቸው ነበር። ያ ዘመን የትግራይ ህዝብ እንደ ሌላው ዜጋ ፍትህን በስጦታና በዘውዳዊ ስርአት ችሮታ የሚለገስለት እንጂ የተፈጥሮ መብቱ ተደርጎ የሚቆጠር አልነበረም። የትግራይ ህዝብ በገዛ ጉዳዩ ላይ ቃል የማይተነፍስበት ወቅት ነበር። የትግራይ ህዝብ በቋንቋው የማይዳኝበትና ከዚያ አልፎም በማንነቱ እንዲሸማቀቅ የሚደረግበት ወቅት ነበር። አቶ ዳዊት ለትግራይ ህዝ የሚመኙለትና የተሻለ ነው ያሉት የዲሞክራሲ ዘመን በትንሹ ይህንን ይመስላል። እሳቸው የአባቴ የቅስቀሳ ንግግር ነው ያሉትን የዘውዳዊው ስርአት የምርጫ ቅስቀሳ ይዘት ምን እደሆነ ባላውቅም የወንድና ሴት እኩልነትን፣ የሃይማኖቶች እኩልነትን የዜጐች እኩልነትን፣ ቋንቋዎችና ባህሎች ሁሉ እኩልትን አረጋግጣለሁ። የትግራይ ህዝብ በቋንቋው እንዲጽፍ እንዲዳኝ አደርጋለሁ እንደማይል ግን ማረጋገጥ ይቻላል። በመሆኑም አሁንም የአቶ ዳዊት አቅጣጫ መዴት ነው ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ከአቶ ዳዊት የዲሞክራሲ ስርአት አማራጭ አንጻር የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲን ለማስፈን ያደረገው ተጋድሎ እረባና ቢስ ብቻ ሳይሆን አክሳሪ ነብር። ምክንያቱ የህይወት መስዋእትነት የከፈለው የነበረውን ዲሞክራሲ ለማጣት ነውና። አቶ ዳዊት ዜጎች በሙሉ የተግባቡበትን የጕለተኛውን ስርአት ጸረ ዲሞክራሲያዊነት ለምን ተመኙ?

የአቶ ዳዊት የልማት አማራጭ

የትግራይ ህዝብ የትግሉ መሰረታዊ ከሆኑ ዓላማዎች አንዱ ዘላቂና ፍትሃዊ ልማት ነው፡፡ ልማት ሲባል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ አሁንም የትግራይ ህዝብ አሁን ካለውና ካገኘው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት የተሻለ እንደሚገባው የሚያከራክር አይሆንም። የትግራይ የህዝብ የልማት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ተመልሷል ብሎ የሚከራከር ካለ ራሱን ይመርምር ከማለት ሌላ አልልም፡፡ በመሆኑም አቶ ዳዊት የትግራይ ህዝብ በተሻለ ሁኔታ ሊማር፣ ሊታከምና ሊበለፅግ ይገባል ማለታቸውን አልቃወምም፡፡ አማራጩ ምን አይነት አማራጭ ነው ብሎ መጠየቁ ግን ተገቢ ነው። ለአቶ ዳዊት አሁንም የልማት አማራጩ የጃንሆይ አማራጭ ነው፡፡ አቶ ዳዊት ቢያንስ የጃንሆይን የትምህርትና የጤና ፖሊሲና የተሻለ አማራጭ እንደሆነ አቅርቧል። በጃንሆይ ጊዜ የትግራይ ህዝብ ወተት እየጠጣ ይማር ነበር፤ ሲታመም የሚታከምበት የተደራጀ የጤና ተቋም ነበረው ብሏል። በጃንሆይ ጊዜ የተሻሉ መሃንዲሶች፣ የተሻሉ ኢኮኖሚስቶችና ሃኪሞች ነበሩ ይላሉ፡፡ የጃንሆይ መሃንዲሶች የገነቧቸው የትግራይ ድልድዩች፣ መንገዶች፣ ትምህርት ቤቶች ሆስፒታሎች ዩኒቨርሲቲዎች የትኖቹ ናቸው? የተኛው የአስተዳደር ህነጻ ገነቡ? የተኛው የትግራይ ህዝብ ነበር ወተት እየጠጣ የተማረው? የንጉሱ ኢኮኖሚስቶች የትሄደው ነው የትግራይ ህዝብ አሰቃቂ በሆነው መንገድ በረሃብ ያለቀው? የትግራይ ህዝብ በልዩ ልዩ በሽታዎች ሲያልቅ ሃኪሞቹ የት ሄደው ይሆን? የአቶ ዳዊት ሃሳብ መጽሃፉ “የሌለ ነገር አይቆጠርም” ከሚለው እውነታ ጋር የሚጋጭና ያልነበረው እንደነበረ የሚቆጥር መሆኑ ያስገርማል፡፡ አቶ ዳዊት ያለንን አሳጥተው ያልነበርን እንደ ነበርን እንድንቆጥር የፈለጉት ለምን ይሆን?

አቶ ዳዊት እንደዜጋ የመሰላቸውን አማራጭ ማቅረባቸው መብታቸው ነው። ሆኖም ለትግራይ ህዝብ የፊውዳል ስርዓት አማራጭን እንደ ተሻለ አመራጭ፤ የፀረ ህዝብ የአስተዳደር ስርዓትን እንደ ዲሞክራሲያዊ ስረዓት መምረጣቸው ግን የቆሙበት መሰረት ጤናማ እንዳልሆነ፤ የተሻለውን ነገን የሚጠቁምና በዲሞክራሲ ስርዓት ማእቀፍ ውስጥ ያለና ከተሻለው የተሻለ አማራጭ ሳይሆን የትግራይ ህዝበ ወደ ተፋውና ወደ ኋላ ቀሩ የዘውድ ስርዓት ለመመለስ የሚሞክር ስለሆነ << ማንም የቆመ የሚመስለው ቢኖር እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ>> በሚለው የታላቁ መፅሐፍ ምክርን አቶ ዳዊት የቆሙበትን እዲፈትሹ በማሳሰብ፤ ለመሪዎቻችን ደግሞ የአገልጋይነት መንፈስ፣ የሚሰማ ጆሮ፣ የሚያይ ዓይንና የሚራራ ልብ እንዲሰጣቸው እመኛለሁ። (በቀጣይ አቶ ዳዊት ስለ ደርግ ስርዓት ባለቸው አቋም ላይ ያለኝን አስተያየት በቀጣይ አቀርባለሁ።)

*********

Guest Author

more recommended stories