የ2007 የኢትዮጵያ ምርጫ ተጠናቆ ሙሉ ውጤቱ ይፋ ከሆነ እነሆ ሳምንታት አለፉ። የምርጫው ሂደት ያስነሳው የፖለቲካ ትኩሳትና አቧራ በርዶ ፤ የምርጫው ተዋናዮች ግርግርና አስረሽ ምቺው ሰክኖ ምርጫ 2007 ከሰበር ዜናነት ወደ ታሪክ ማህደርነት የሚተላለፍበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። የዚህን ምርጫ ታሪካዊ አንድምታና በታሪክ መዝገብ ውስጥ የሚኖረው ስፍራ በታሪክና ሶሻል ሳይንስ ተመራማሪዎች ወደፊት የሚለካ ሲሆን ይህ ጽሁፍ የዚህን ምርጫ ሁለት ለየት ያሉ ባህርያት ላይ ትኩረት በመስጠት ለመቃኝትና ለመዳሰስ ይሞክራል።

በመጀመሪያ ይህን ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች የተለየ የሚያደርገው ለምርጫ የወጣው ህዝብ ብዛት (turn out) ሲሆን ከተመዘገበው 36.8 ሚሊየን ህዝብ 34.8 ሚሊየን ህዝብ በነቂስ ወጥቶ በምርጫው ተሳትፏል። በዚህም በኢትዮጵያ ታሪክ ታላቁ ቀጥተኛና ነጻ የሆነ ህዝባዊ ተሳትፎ የታየበት የፖለቲካ ክስተት ያደርገዋል። ይህን መሰል ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የታየበት ምርጫ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በብዙ አገሮች ከሚታዩት የህዝብ የምርጫ ተሳትፎዎች ጋር ሲንጻጸር ከፍተኛ አሃዝ ከተመዘገበባቸው አንዱ የሚያደርገው ሲሆን ይህም የምርጫውን የዲምክራሲያዊ መሰረት ያሰፋ፤ ፉክክራዊ ባህርይውን ያጎለበትና ለተአማኒነቱንም ዋስትና እንዲኖረው ካደረጉት ምክንያቶች እንደ አንዱ ሆኖ ሊጠቅስ የሚያስችል ነው።

ከሁሉ በላይ ግን ለምርጫ ከወጣው የህዝብ ቁጥር አሃዝ ጀርባ ያለው ዋናው ቁምነገርና ይህንን ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በይዘት የተለየ የሚያደርገው ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤትነት መብቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋትና በጥልቀት እየተረዳ መምጣቱ የተንጸባረቀበት፤ ለዲሞክራሲ ስርአት ያለው ፍላጎትና ቁርጠኝነት እየሰፋና እየጎለበት መምጣቱን በግብር ያረጋገጠበት ምርጫ መሆኑን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫን የማይገሰስና የማይቀለበስ ቋሚ ባህሉ አድርጎት የተቀበለውና ከራሱ ጋር ያዋሃደው መሆኑን በቁጥር ብዛቱ ሪፈረንደም የሰጠበት ወይም (critical mass) ደረጃ ላይ መድረሱን ያረጋገጠበት ምርጫ ነበር።

ምርጫ እንደ ዲሞክራሲያዊ ባህል ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ይቅር ሲሉት የሚቀር፤ ይሁን ሲሉት የሚሆን የፖለቲከኞች ችሮታ ሳይሆን ለምንጊዜም የተተከለ የህዝቡ ባህላዊ ሃብት ሆኖ የተረጋገጠበት ምርጫ ሆኖ አልፏል። የምርጫ ስርአት የኢትዮጵያ ህዝብ የፖለቲካ ባህልና ወግ እየሆነ እንደማንኛውም ማህበራዊና ሃይማኖታዊ ባህሎችና ወጎች የኢትዮጵያ ህዝብ የባህል ቅርስ አካል እየሆነ መምጣቱን የተነበበበትም ምርጫ ነበር ።

ሌላው ሁለተኛው የ2007 ምርጫ መለያ ባህሪ ምናልባትም ከወደፊት ምርጫዎች በፍጹም የተለየ የሚያደርገው ለምርጫ ከተሳተፈው ህዝብ ገዥው ፓርቲ ከአጋሮቹ ጋር አብዛኛውን ድምጽ በማግኘት ሙሉ በሙሉ የምክር ቢት መቀመጫዎችን መቆጣጠሩ ነው። የዚህን ምርጫ የገዥው ፓርቲ የ100% አሸናፊነት ውጤት ትክክለኛ ምክንያት በሚገባ ለመርዳት ከአሃዞች ጀርባ ያለውን እውነታ መምርመር ያስፈልጋል። ይህም የምርጫው ዋና ባለቤትና ተዋናይ የሆነውን የኢትዮጵያን ህዝብ ለምን በዚህ መልክ ድምጹን እንደሰጠ መመርምርና መተንተን ግድ ይሆናል።

ተቃዋሚ ወገኖች ለሽንፈታቸው ተያዥ ለማግኘት በሚያደርጉት ሩጫ በጠቅላላ የምርጫው ሂደት ተአማኒንት ላይ የሚሰንዝሩት ጭፍን ክስና ውንጀላ አብዛኛው ውሃ የማይቋጥርና መሰረተ ቢስ መሆኑ ቢታወቅም፤ ያቀርቧቸው የምርጫው ሂደት ግድፈቶችና አቤቱታዎች በተጨባጭ ተከስተዋል ቢባልና በአግባቡም አልተዳኙም ቢባል እንኳን በምንም መልኩ የጠቅላላ ምርጫውን ሂደት ፍትሃዊነት የሚያፋልስና ተአማኒነቱን የሚሽር ክብደትና ዋጋ ያላቸው ምክንያቶች ሆነው አልተገኙም ። አይደሉምም። በመሆኑም የገዢው ፓርቲ በ100% ያሸነፈው በሸፍጥ ነው ወይም የህዝቡን እጅ ጠምዝዞና አስገድዶ ነው የሚለው፤ ተሸናፊዎቹ ለቁስላቸው ማገሚያ የሚጠቀሙበት ፈጠራ ከመሆን አልፎ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የአለም ማህበረሰብ ቦታ የሚሰጠው ምክንያት ሆኖ አልተገኘም።Photo - EPRDF supporters march - 2010

በየትኛውም አገር በምርጫ ሂደት ላይ ከመስመር የወጡ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችል ሁሉ ለጋው የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ምርጫ ሂደትም ተመሳሳይ ክስተት ሊኖርበት እንደሚችል ማንም የሚገምተውና የሚጠብቀው ነው። ዋናው ጉዳይና ሊተኮርበት የሚገባው ነጥብ የችግሮቹ መከሰት ሳይሆን ችግሮችን ለመፍታት ተጠንቶ የተቀመጠ የመፍቻ ስርአት መኖር አለመኖሩና ይህንንም በውቅቱ የሚያስፈጽም ብቃት ያለው አካል መቀመጡ ላይ ነው። የምርጫው ሂደት እንዳረጋገጥውና እስካሁን ያሉት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ምርጫ ቦርድ ያለ ብዙ ስንክሳር ሚናውን በብቃት የተወጣ መሆኑንና የምርጫ ሂደት አተገባብረ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀላጠፈና እየተሻሻለ መምጣቱን በቀላሉ ማረጋገጥ ይቻላል። በዚህም ምርጫ ቦርዱ በተከታታይ ባካሄዳቸው ምርጫዎች ያካበተው ልምድና ተሞክሮ ብቃቱንና ቅልጥፍናውን እንዳጠናከርውም አስመስክሯል።

ከላይ እንደተነሳው ምርጫው ፍትሃዊና ነጻ ከሆነና የምርጫውን አጠቃላይ ሂደትም ሆነ ውጤቱን የሚያፋልሱ ችግሮች ያልታዩበት መሆኑ ከተረጋገጠ ለምን የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአደግን በሙሉ ልቡ ተቀበሎ ያለ አንዳች ተቀናቃኝ መረጠው የሚለውን ጥያቄ መመርመር ተገቢ ይሆናል ። ወይም ለምን የኢትዮጵያ ህዝብ ተቃዋሚዎችን አንቅሮ ተፋቸው ብሎ መጠየቅም ይቻላል። የምርጫው ውጤት ተቃዋሚዎችን እንደ ኮረንቲ የነዘራቸውና እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ሁሉ ኢህአደግንም ያደናገርውና 100% ድል ያልተመቸው መሆኑ በገሃድ የታየ ነው።

ለዚህም ጥያቄ መልስ በዚህ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ አጀንዳ ምን ነበር? በህዝቡ ውስጥ የሚጉላሉና የህዝቡን ቀልብና ስሜት የሳቡ ዋና ዋና ጉዳዮችና ጥያቄዎች ምን ነበሩ? በእነዚህስ ጉዳዮችና ጥያቄዎች ላይ ኢሃደግ ምን አይነት ተግባራዊ ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል? ተቃዋሚዎችስ ምን አይነት አቋም ሲያራምዱ ነበር? የሚለውን ማንሳት ግዴታ ይሆናል። ምክንያቱም ህክምናውና የሃኪሙ አይነት የሚመረጠው በወቅቱ ካጋጠመው የህመም አይነት በመንሳት እንደመሆኑ ህዝብም ተመራጮችን የሚመርጠው በወቅታዊ ችግሮቹ አይነት ላይ ተንተርሶ በመሆኑ ነው።

ምርጫ በሚካሄድባቸው አገራት እንደሚታየው በእያንዳንዱ የምርጫ ኡደት የምርጫውን ውጤት የሚወስኑ በ መራጩ ህዝብ ዘንድ የወቅቱ ዋንኛና ቀዳሚ የሚባሉ ጉዳዮች ይኖራሉ። በአንድ የምርጫ ውቅት ኢኮኖሚና ስራ አጥነት ሊሆን ይችላል፤ በሌላ ጊዜ ጊዜ ደግሞ የመብትና ማህበራዊ ጉዳይ፤ ሌላ ጊዜ የሰላምና የጦርነት አወዛጋቢ አለም አቀፍ ጉዳይ ሊሆን ይችላል …ወዘተ ። የምርጫውንም ውጤት የሚወስነው ለውድድር የቀርቡት ተፎካካሪዎች ህዝቡ ወቅታዊ ናቸው ብሎ ባቀረባቸው የወቅቱ አጀንዳዎች ላይ የሚይዙት አቋምና በሚያቀርቡት መፍትሄ ሃሳብ ነው። አብዛኛው ህዝብ የተቀበለውን አጀንዳ የሚያራምድ እጩ ምርጫውን የማሸንፍ እድሉ ከፍ ይላል። በተቃራኒው የህዝብን ፍላጎትና ስሜት የማያንጸባርቅ ወይም ወቅቱ ያልሆነ አጀንዳ ላይ ያተኮረ የማሸነፍ እድሉ የመነመነ ይሆናል።

በአገራችንም በዚህ የምርጫ ወቅት ህዝቡ ዘንድ የሚነሱ በርካታ ችግሮችና ጉዳዮች ነበሩ። ከእነዚህም መሃል፦ ሰላምና ደህንነት፤ ልማትና እድገት፤ የመልካም አስተዳደር መዛባት፤ የሰብአዊ መብት አያያዝ፤ የዲሞክራሲ ምህዳር ጥበት፤የሃብት ክፍፍል መዛባት … ወዘተ እንደ ዋና ሆነው ሊዘረዘሩ ይችላሉ። ይሁንና የዘንድሮውን ምርጫ ውጤት የወሰኑት ግን የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ናቸው ማለት ይቻላል።

በዘንድሮው ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀዳሚ ጉዳዩና አንገብጋቢ ችግሩ አድርጎ የወሰደው እንዳለፉት ጊዜያት ሁለቱን ጉዳዮች ነው። እነኚህም – አንደኛው ሰላምና ደህንነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ልማትና እድገት ነው።

ሰላምና ደህንነት

ሰላምና ደህንነት በአሁኑም የምርጫ ዙር ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቁ ጉዳይ የሚሆነበት ምክንያት አካባቢው የሽብርና የጦርነት አደጋ የሚያንዣብብበት በመሆኑ ለሰላሙና ለደህነነቱ ካለው ስጋት የመነጨ ነው። ጦርነት ለኢትዮጵያ ህዝብ ከታሪኩ ጋር አብሮ የተስፋ፤ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ ትውልዶችን ያመከነ፤ አገር ያቆረቆዘ መሆኑን በገፈት ቀማሽነት የሚያውቀው ነው። ያለፉት አምስትና አስር አመታት የአለም አቀፍ የፖለቲካ ሂደትና የአገር ውስጥ ሁኔታ ያስተማሩት ነገር፤ የሚኖርበት ቀጠና ከምንጊዜውም በላይ ለጦርነትና ለብጥብጥ እየተጋለጠ መምጣቱንና የተገኘውን ቀዳዳ በመጠቀም አንጻራዊ ሰላሙን ለመንጠቅ ለአንዲት ሰከንድ እንኳን ከማያመነቱ የውጭ ጠላቶችና የውስጥ አክራሪ አሸባሪዎች ጋር እንደተፋጠጠ ይገነዘባል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ከምንም በላይ አገሩ በርስ በርስ ጦርነት የምትታመስ ሶርያን እንድትሆን አይፈልግም። ወይም ቦኮሃራም አይነት አክራሪ ነፍሰ ገዳይ ድርጅት የሚፈንጭባት ናይጄሪያን እንድትሆን አይሻም። ወይም አልሸባብ ወጣ ገባ እያለ ገበያ የሚያፈነዳባት ተማሪዎችን የሚረሽንባት የተጋለጠች ኬኒያን እንድትሆን አይፈቅድም።

በዚህ ስጋት በተሞላበት ዘመንና ባልተረጋጋ የጂኦ ፖለቲካል ቀጠና የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንካራና አስተማማኝ አመራር መሻቱ ምክንያታዊ ነው። ቢያንስ ጦርንትና አመጽን የሚያወግዝ ከአሽባሪ ድርጅቶችና ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ንክኪ የሌለው ድርጅትና አመራር መሻቱም አግባብ ያለው ነው።

ኢህአደግ ይህን የኢትዮጵያ ህዝብ የህልውና ጥያቄ ለመመለስ ብቃት ያለው መሆኑን ካለፈው ምርጫ በኋላ ስልጣን በቆይባቸው አመታት በተግባር አስመስክሯል። በውጥረትና በሽብር በታፈነ ቀጠና ኢትዮጵያ የሰላም ደሴት ሆና እስካሁን መዝለቋ ትልቅ ስኬት ነበር። በዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ኢሃደግን በድጋሚ መምርጡ የሚጠበቅና ሳይታለም የተፈታ ጉዳይም ነበር።

በተቃራኒው ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰላሙና ደህነነቱ ያለውን ስጋት የሚንቁ፤ ዘውተር ጦርነት እንዲቀሰቀስና መንግስት በሃይል እንዲገረሰስ የሚመኙ ፤ ከምኞትም አልፈው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሚፍጨረጨሩ ድርጅቶች አንድም ወንበር ባያገኙ የሚያስደንቅ ሊሆን አይገባም። ህዝቡ ለሰላሙና ለደህንነቱ ያላቸውን ንቀትና ግዴለሽነት አይቶና ተገንዝቦ ድምጽም ፊትም ቢነሳቸው ተገቢና ትክክለኛ ፍርድ ይሆናል።

ጭንቅላታቸውን ውጭ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ቀዳሚ ፍላጎት ለመገዛትና ወቅታዊ ጥያቄውን ለማክበር ያልፈቀዱ፤ ሰላሙንና ጸጥታውን በተደጋጋሚ ለመፈታተን የሚቃጡትን ህዝቡ በድምጹ ቢቀጣቸው ምን ይገርማል?

የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉን ነገር ያያል ሁሉን ነገር ይሰማል። ሁሉንም ነገር ይረዳል። ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጉያ ሆነው በደልህን እኛ እናውቅልሃለን፤ ተረግጥሃል፤ ተጨቁንሃል፤ ተነስ የሚሉትንም እየታዘበ ይሰማቸዋል። እየሰማ ይታዘባቸዋል። ‘አገርህ ተሽጧል፤ ሃይማኖትህ ተደፍሯል፤ አንተም ሞተህ አልቀህ ቀባሪ ሳታጣ አሁኑኑ ተነስ ገርስስ ደምስስ’ የሚሉትን እየሰማ እንኚህ ሰዎች የትኛው አለም ላይ ነው የሚኖሩት ብሎ ይደነቃል። ከውቅያኖስ ባሻገር ጦር ሰብቀው፤ ጦርነት አውጅው ‘ባትዋጋ እንኳን በል እንገፍ እንገፍ ፤ ያባትህ ጋሻ ትኋኑ ይርገፍ’ ብለው ክተት የሚጠሩትንም ሰምቶ እነኚህ ስዎች እዛ ያሉበት አገር ምን አይነት መድሃኒት ነው የሚወስዱት ሲል ይጠይቃል።

በዲሞክራሲ እሴቶች እናምናለን ግን የጦርነት ኢ-ዲሞክራሲያዊ መንገድም ወደዚሁ መንግስተ-ስማያት ያደርሳል ብለው የሚሞግቱ ወገኖች ‘ከስጋው ጾመኛ ነኝ ከመረቁ ስጡኝ’ ያለውን ‘ጻድቅ’ ሰው ያስታውሳሉ። ኢትዮጵያዊ ደብተራ ጭንቅላት ብቻ ነው ባንድ እግር የሰላማዊ ትግል ዛፍ በሌላው ደግሞ የጦርነት ዛፍ ላይ ይወጣል ብሎ የሚያምን። የጥቁር አሜሪካኖቹ ቄስ ማርቲን ሉተር ኪንግና የሂንዱው ካህን ማህትመ ጋንዲ ይህን ሲሰሙ ከተጋደሙበት መገላባጣቸው አይቀርም። ‘ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’  ማለትስ ይሄም አይደል?

ተቃዋሚ ወገኖች ሊረዱት የሚገባ አንድ አብይ ቁምነገር አለ። ይኸውም ከምንም በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ብልህ፤ አስተዋይና አርቆ አሳቢ መሆኑን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነትና በፍቅር የሚያምን፤ የጥላቻ ፖለቲካን፤ ጦርነትና አመጽን የሚጠይፍ ኩሩና ሰላማዊ ህዝብ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋቸዋል። አበክረው ሊያጤኑት የሚገባቸው የኢትዮጵያ ህዝብ በህሊናው የሚምራ ጽኑ እምነትና ትግስት ያለው ህዝብ መሆኑን ነው። የረዥምና ዘላቂ ጥቅሙን ለይቶ መረዳት የሚችል በግልብልብና የግርግር ፖለቲካ የማይዋከብ የሰከነ ህዝብ መሆኑን ነው።

በሌላ አነጋገር በእነሱ ምናብ እንደሚስሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ተነስ ሲሉት የሚነሳ፤ ተቀመጥ ሲሉት የሚቀመጥ፤ ወደነዱት የሚነዳ መንጋ እንዳልሆነ መርዳት ይገባቸዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ሲረገጥና ሲበደል የማይገባው፤ አቅል የጎደለው መብቱንና ነጻነቱን ማስከበር የማይችል ወኔ ቢስ ፈሪ ህዝብም አይደለም።

ተቃዋሚ ክፍሎች አሁንም አሁንም፤ ደግሞ ደጋግሞ የሽንፈት ማቅ ከሚያከናንባቸው የውድቀት አዙሪት ማጥ ውስጥ ለመውጣት ከፈለጉ፤ የራሳቸውን አጀንዳ የኢትዮጵያ ህዝብ አጀንዳ እንደሆነ አድርገው ማሰብና ማመን ማቆም አለባቸው። ቆም ብለው አስተውለው ይህንን ስህተት ማረም ይጠበቅባቸዋል። የእነሱ አሳዛኝ ሽንፈት ለዲሞክራሲያዊ ሂደቱ እንቅፋት እየሆነ፤ አገሪቱን ብቻ ሳይሆን ኢሃደግንም ሳይቀር እያሳፈረ መጥቷልና።

ልማትና እድገት

እንደ ሰላሙና ደህንነቱ ሁሉ ለገጠሬውና ለከተሜው የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቁ አጀንዳውና ፍላጎቱ በቀን ተቀን ውሎው ኑሮውን ማሻሻልና ድህነትን ማሸነፍ ነው። በዚህ ረገድ በአሁኑ ሰአት በአገሪቱ እየታየ ያለው ፈጣን ልማትና እድገት ለዘመናት ከትውልድ ትውልድ በድህነት አረንቋ ሲማቅቅ ለነበረው ህዝብ ብሩህና አዲስ የተስፋ ጮራ የፈንጠቀ፤ የረሃብና የኋላቀርነት ተምሳሌት ለነበርች አገር በአለም መድረክ አዲስ ብሄራዊ ክብርና ኩራት እያጎናጸፋት ያለ በመሆኑ መላው ህዝብ በሙሉ ልቡ የተሰለፈበትናና ቀልቡን የሰጠው አጀንዳው ነው።

ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች በተለይም የህዳሴ ግድብ ህዝቡን ከጠረፍ እስከ ጠርፍ በማንቀሳቀስና በማሳተፍ ይህ ነው የማይባል የብሄራዊ የአንድነት ስሜትና፤ ለልማትና ለእድገት መነሳሳትን አቀጣጥሏል። ህዝቡ ከእለት ተእለት ኑሮው እየቆጠበ በሚያደርገው መዋጮና ወደር የለሽ ሁለ-ገብ ተሳትፎ ለልማትና እድገት የሚሰጠውን ቦታ በግልጽ አሳይቷል። ዋንኛ ጉዳዩም እንደሆነም አረጋግጧል።

በተለይ ካለፈው ምርጫ በኋላ የተጀመረው የህዳሴ ግድብ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለአገሩ እድገትና ብልጽግና ያለውን ምኞት፤ ተስፋና እምነት የቋጨበት የልማትና እድገት ታቦቱ ሆኗል። የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ህዝብ የማንነቱና በራስ የመተማመኑ መገለጫ፤ የእምቢ አሻፈረኝ ባይነቱ መንጸባረቂያ፤ የይቻላል መንፈሱ ማረጋገጫ፤ እንደ አይኑ ብሌን የሚንከባከበው ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን የሞራልና መንፈስ እሴቱ ነው።

ህዳሴ ግድብን ደግሞ ከኢሃደግ ለይቶ ማየት አይቻልም። ህዳሴ ግድብን ከዋናው የይቻላል መሪ ከመሃንዲሱ ከመለስ ዜናዊ ነጥሎ ማየት አይቻልም። በመሆኑም የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተጀመሩት የልማትና የእድገት ውጥኖች እንዲቀጥሉ ኢሃደግ ባሳየው ብቃት ህዝቡ ቢሸልመውና ድምጹን ቢያስታቅፈው ምክንያታዊና ተገቢ ነው።

በተቃራኒው የአገሪቱን ልማትና እድገት የሚክዱ፤ የሚያጣጥሉና ከዛም አልፈው እንቅፋት ለመሆን የሚጥሩትን ተቃዋሚ ድርጅቶች ህዝቡ መምረጥ ቀርቶ አንዲት ወንበር ቢከለክላቸው ምን ያስደንቃል። ለይስሙላ ልማት እንደግፋለን እያሉ ቦንድ እንዳይገዛ የሚቀሰቅሱትን፤ ለእድገትና ለልማት ያለውን ብሩህ ተስፋ የሚያጠቁሩብትን፤ ጥረቱን የሚያንቋሽሹበትንና ሞራሉን የሚፈታትኑትን ህዝቡ በድምጹ ቢቀጣቸው ምን ነውር አለው?

የኢሃደግ ብቁ ተቀናቃኝ ነኝ ብሎ የሚመጻደቀው ድርጅት መሪ የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት ወቅት የህዳሴ ግድብ መጀመርን አስመልክቶ – “የአባይን ጉዳይ ለአባይ ልጆች ተዉላቸው”  ሲል ተሳልቆ ነበር ። ታዲያ እንዲህ አይነቱን ራዕይ አልባና ህዝብ ከፋፋይ “ፖለቲከኛ” እሱንም ሆነ የሚመራውን ድርጅት እንዴት ህዝብ ሊመርጠው ይችላል? እንዴትስ አንድ ወንበር ሊቸረው ይገባል? ዶ/ር መራራ የፖለቲካ ስብእናውን በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ያጣው ይህን የተናገረ እለት ነበር ። በዚህ ምርጫም ህዝቡ እሱንም ድርጅቱንም – ሂድ! ወጊድ! – ቢለው አግባብ አለው።

ምርጫው ተስርቋል እያለ ሲደሰኩር ለምን የኢትዮጵያ ህዝብ እሱንና መሰል ተቃዋሚዎችን እንዳራቃቸውና በድምጹ እንደቀጣቸው እስካሁን የተከሰተለት አይመስልም። ዶ/ር መራራ በርግጥም የሁሉንም ተቃዋሚ ድርጅቶች ባህርይና ማንነት የሚገልጽ እውነተኛ ተወካይ (symbolic figure) ነው። power hungry but clueless; educated but oxymoron; pompous yet miserable.

ለማጠቃለል የዘንድሮው የ2007 ምርጫ ከምንጊዜውም በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የተሳተፈበት ብቻ ሳይሆን እንደ ማንኛውም ብሄራዊና ሃይማኖታዊ በአላት ህዝቡ በታላቅ መነሳሳትና ደስታ የዘከረው በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል።ይህም በመሆኑ፤ ምርጫ እንደ ዲሞክራሲያዊ ባህል በህብረተሰቡ ውስጥ የተዋሃደና መሰረት የያዘ ከነባር ባህሎች ጋር የተስተካከለ መሆኑን በተሳታፊው ቁጥሩ ብዛት የተረጋገጠበት ምርጫ ነበር።

በምርጫው ውጤትም ኢሃደግ እንደተጠበቀው ያሸነፈ ሲሆን ካለፈው ምርጫ በኋላ በነበሩት አምስት አመታት ባስመዘገበው ስኬታማ የአገር ደህንነትና የህዝብ ሰላም ጥበቃ እንዲሁም አመርቂ የልማትና የእድገት ውጥኖች በድጋሚ ሊመረጥ በቅቷል።

በተቃራኒው አለን ብቁ ነን የሚሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች በህዝቡ ወቅታዊ አጀንዳዎች ላይ ከህዝቡ የተለያየ ተጻራሪ አቋም በመያዛቸውና ከህዝብ ጋር በመጋጨታቸው ያለ አንዳች መቀመጫ በዝረራ ተሸንፈዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ህዝብ ለተቃዋሚዎች ያስተላለፈው መልእክት፦

ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ …… መሬት ትቀመጣለህ ! የሚል ነበር።

እግዚአብሄር አገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ

**********

Befekadu Wolde Gabriel - Ph.D. in agriculture, B.Sc in Sociology and graduate student (MPA master of public administration) at Franklin University - Ohio, and can be reached at [email protected].

more recommended stories