የIS ሂደት እና የኢትዮጽያ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ይጣጣም ይሆን?

 መግቢያ

የአሜሪካ መንግስት እ.አ.አ በ2009ዓ.ም በኢራቅ የሚገኘዉን አምባገነናዊ የሳዳም ሁሴን አገዛዝ ለማስወገድ ከሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ጋራ በመሆን ባካሄደው ወረራ የሳዳም ሁሴን አገዛዝን አስወግደው በፋንታው ጠንካራ የኢራቅ መንግስት ሳያቋቋሙና መልሶ ግንባታ ሳያካሄዱ በመቅረታቸው የእልቂቷ ምድረ-ኢራቅ እንዲትፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ በቀደምት የሰው ልጅ ስልጣኔ የምትታወቀው የባቢሎን ምድረ ኢራቅ በአሁኑ ወቅት በተቃራኒው ተሰልፋ ምድረ እልቂት፡ ምድረ ጦርነት፡ ምድረ ዱንቅርና ሆናለች፡፡ ቀድሞውም በሳዳም አገዛዝ ወቅት የነበረው የ”ሱኒ-ሺዓ” ፖሎቲካ ውጥረት በአከባቢያዊ ጎሳ ግጭት ላይ ተደምሮ የሀገሪቱ ስጋት የነበረ በመሆኑ ከአሜሪካና አጋሮቿ ወረራ ቡኋላ በፈራረሰችውና በመንግስት አልባዋ ምድረ ኢራቅ ነግሶና ግሎ የስንቱን ንጽሃን ዜጎች ህይወት በቀላሉ ቀጥፏል፡፡ ይህ አስከፊ ጦርነት መንግስት አልባ ሊባል የሚትችል ኢቅን በማምጣቱ እንደ IS አይነቱ ሰው-በላ አረመኔያዊ ቡዱን በሃማኖት ሽፋን እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ የሰሞኑ የአረብ አብዮት ተከትሎ በሶሪያ መንግስት ላይ የተነሳዉን ህዝባዊ አመጽ ከህዝብ በመንጠቅ የኢራንና ሺዓ አከባቢያዊ የበላይነትን ለማስቆም በሳዑዲ ዓረቢያና ኳታር የሚመራው የገልፍ አረብ ሱኒ ሀገራት ከአሜሪካ ጋር በመተባበር የበሽር አል-አሳድ አገዛዝን ለመገልበጥ ISን ጭምሮ የIS ገባር የሆኑ የተለያዩ ፅንፈኛ ቡዱኖችን አስታጥቋል፡፡ በዚህም IS በሰው ሀይል፡ በገንዘብ፡ በትጥቅና ሌሎች ወታደራዊ ሎጂስቲኮች በሚገባ ተደራጅቷል፡፡ ይህም የIS መቋቋም ጀርባ ማን እንዳለ ፍንጭ ሊሰጠን ይችላል፡፡

የIS ጉዞ

አልቃይዳን የማያስታውስ አለ? ኦሳማ ቢን ላዲንን የማያስታውስ አለ? የታሊባን ተዋጊዎችን የማያስታውስ አለ? የሴፕቴምበር 2001 የኒውዮርክ መንትያ ህንፃዎች ጥቃት የሚረሳ አለ? በዓለማችን ኣቻ ያልተገኘለት፡ አለ የተባለ ፖሎቲከኛ፡ ምሁር፡ የሃይማኖት ሊቅ የተጠበቡበት፡ የብዙ ሀገራት የውጭ ፖሊሲ ያስከለሰ፡ ስንትና ስንት ሀገር ያስፈረሰ፡ የስንቱን ንፁሃን ዜጎች ህይወት የቀጠፈ፡ ስንቱን አካለ ስንኩል ያደረገ፡ ሥነቱን ሜዳ ላይ የበተነ፡ ስንቱን ለስደትና ስቆቃ የዳረገ፡ በትርሊዮኖች የሚሰላ በጀት የተበጀተለት፡ ስንቱ እንደ አውሬ በየእስር ቤቱ የተወረወረበት፡ አለ የተባለ የስለላ ትክኖሎጂና ጠቢባን የተፈተኑበት፡ የተራቀቁ የዉትድርና ሎጂስቲኮች አገልግሎት ላይ የዋለበት የሽብር ክስተት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጅማሮ የተካሄደው ነው፡፡ በቀላሉ IS ማለት ይህን ሁሉ ክስተት ያስረሳ ነው፡፡ በቀላሉ IS ማለት የአሸባሪዎች ዕንቁ አል-ቃዒዳን ያስረሳ ነው፡፡ በቀላሉ IS ማለት በአንድ ወቅት ከ10 ዓመታት በላይ ዓለም በሙሉ ሲያድነው የነበረውን ኦሳማ ቢን ላደንን ያስረሳ ነው፡፡ ለIS የሴፕቴምበር 2001 መንትያ ህንፃዎች አይነቱ ጥቃት የዕቃ ዕቃ ጫወታ ነው፡፡ ለIS አል-ቃዒዳ ሰላማዊ ድርጅት ነው፡፡ ለIS ኦሳማ ቢን ላደን ተራ ግለሰብ ነው፡፡ የሚገርመው የIS ጉዞ ዕድሜ በአጭር ጊዜ ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ የIS አረመኔያዊ ክፉና ዘግናኝ ተግባር የማይቃወም ፍጡር ካለ እንኳን ሰዉ እንስሳም ሊሆን አይችልም፡፡Photo - Islamic State fighters

ሁሌም በጥቅም ግጭት ዉስጥ መዋኘት ምቾት የሚሰጣት የምድራችን ልዕለ ሀያሏ አሜሪካ ቀድሞ ተደግፍ የነበረችውን የሶሪያ በሽር አል-አሳድ መንግስት ተቃዋሚ ፅንፈኛ ሃይሎችን በማደራጀት የተቋቋመውን IS ለመቃወምም ሆነ ለመደብደብ የቀደመ አልነበረም፡፡ IS በኢራቅ የነበረው የ“ሱኒ-ሺዓ” ፖሎቲካ ሽኩቻ፡ በሶሪያ የነበረው ግጭት እና በአከባቢው የነበረውን “የአሜሪካ-ገልፍ አረብ ሀገራት-ኢራን” ሽኩቻ በጥቀሉ በተፈጠረው ክፍትት በመጠቀም ግዛቱን አስፋፍቷል፡፡ በተለይ ከገልፍ አረብ ሀገራት ሳዑዲ አረቢያን ጫምሮ፡ ከአሜሪካ፡ ከአውሮፓ፡ ከአውስትራሊያ፡ እና ከሰሜን አፍሪካ አረብ ሀገራት ሊቢያን ጫምሮ በደህንነት መስሪያ ቤታቸው በኩል ፍቃደኛ የሆኑ ዤጎቻቸውን በመመልመል በሳዑዲ አረቢያ እና ኳታር ስፖንሰርነት በማስቀጠር ከፍተኛ የሰው ሃይል ያለበትን የሶሪያ በሽር አል-አሳድ መንግስት ተቃዋሚ ፅንፈኛ ሃይሎችን እንዲቀላቀሉና የሶሪያ በሽር አል አሳድ መንግስትን እንዲፋለሙ ልኳቿል፡፡ በተለይ ሳዑዲ አረቢያ፡ ኳታር እና አሜሪካ እነዚህን ሃይሎች በገንዘባ፡ በወታደራዊ ሎጂስቲክ እና በወታደራዊ ስልጠና አቅማቸውን አዳብሯል፡፡ በዚህም ለIS ታላቅ ስጦታ አበርክቷል፡፡

IS በአጀማመሩ በኢራቅ በተቆጣጠረባቸው አከባቢዎች በተደጋጋሚ በሺዓ ሙስሊሞች፡ በገለልተኛ ሱኒዎች እና በአናሳዎቹ ያዚዲዝ ላይ አረመኔያዊ ክፉና ዘግናኝ ተግባሩን ፈፅሟል፡፡ በዚህ ወቅት ነበር አሜሪካ እና አጋሮቿ የIS አላማ ዓለምን በአጠቃላይ በአገዛዙ ሰር ለማስተዳደር የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ከተናጥል እርምጃ ይልቅ የተባበረ የአለምአቀፍ ብትር በቻ ከዓላማውና ከአረመኔያዊ ክፉና ዘግናኝ ተግባሩ በማለት IS ላይ አለምአቀፍ የፀረ-ሽብር ዘመቻ የከፈቱት፡፡ በIS ላይ ከጁን 13-2014 ጀምሮ ባለፉት 42ሳምንታት በአሜሪካ መሪነት በተከፈተው አለምአቀፍ የፀረ-ሽብር ዘመቻን (በኢራቅ፡ በሶሪያ፡ በሊብያ እና በናይጄሪያ) የተቀላቀሉ ከ60 በላይ ሀገራትና ተለያዩ ተዋጊ ቡድኖች፡

1. በኢራቅና ሶሪያ የዘመቱ (USA, Canada, Jordan, Morocco, UK)

2. በኢራቅ ብቻ የዘመቱ (Australia, Belgium, Denmark, France, Germany, Italy, Netherland, New Zealand, Norway, Portugal, Spain, Turkey)

3. በሶሪያ ብቻ የዘመቱ (Bahrain, Qatar, Saudi Arabia, United Arab Emirates)

4. ወታደራዊ ድጋፍ እየሰጡ ያሉ (Albania, Bosnia and Herzegovina, Bulgaria, Croatia, Czech Republic, Estonia, Greece, Hungary, Kuwait, Lebanon, Russia, Singapore)

5. ሰብዓዊ ድጋፍ እየሰጡ ያሉ (European Union, Austria, Ireland, Japan, Luxembourg, Poland, Russia, Slovakia, South Korea, Sweden, Switzerland)

6. የስለላ ድጋፍ (Israel)

7. በኢራን መሪነት የዘመቱ (Iran, Hezbollah)

8. በአሜሪካና አጋሮቿ ድጋፍ በኢራቅ ብቻ የዘመቱ (Iraq Government)

9. በኢራን ድጋፍ የዘመቱ የኢራቅ ሺዓ ሚሊሻዎች (Asa’ib Ahl al-Haq, Badr Organization, Kata’ib Hezbollah, Promised Day Brigade, Iraqi Kurdistan, Nineveh Plain Protection Units)

10. በአሜሪካና አጋሮቿ ድጋፍ በሶሪያ ብቻ የዘመቱ (Syrian Opposition)

11. በአሜሪካና አጋሮቿ እና በውጭ ኩርዶች ድጋፍ በሶሪያ ብቻ የዘመቱ (Syrian Kurdistan)

12. በተናጠል በሶሪያ ብቻ የዘመቱ (Local Syrian Guerillas)

13. በግብፅ መሪነት በሊቢያ የዘመቱ (Egypt, Libya, UAE)

14. በሲንዓይ፡ ግብፅ የዘመቱ (Egypt) እና

16. በናይጄሪያ መሪነት በቦኮ ሀራም (ISን በ2015 ተቀላቅሏል) የዘመቱ (Nigeria, Cameroon, Chad, Niger)

ናቸው፡፡

IS በኢራቅና ሶሪያ ብቻ በግምት መሰረት ከ20,000-31,500፡ በሊብያ ከ1,300-8,000 እና በናይጄሪያ ከ7,000-10,000 ወታደር አለው ተብሎ ይገመታል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 12,000 የሚሆኑት ከሌሎች ሀገራት ISን የተቀላቀሉ ሲሆን ከ12,000 ውስጥ ደገሞ 3,000 ከምዕራባውያን ሀገራት ISን የተቀላቀሉ ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ አብዛኛው የ IS ወታደራዊ መኮነኖችና የደህንነት አመራሮች በቀድሞ የኢራቅ ገዥ ባዝ ፓርቲ የተሾሙና በሳዳም ሁሴን አመራር ወቅት የደህንነትና ወታደራዊ ከፍተኛ እርከኖች ላይ የነበሩ ናቸው፡፡

በቴከከኖሎጂ አጠቃቀሙ አቻ ያልተገኘለትና በ2015 የአሜሪካ መዕከላዊ ሰርቨር በመጣስ Twitter & Youtube ሶሻል ሚዲያዎች መጠለፍ ጀርባ እሱ እንዳለ በሲ አይኤ የሚጠረጠረው ይህ አሸባር ቡድን የተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎችን እንደነ እና በመጠቀም ወጣቶቸን በእምነት ሽፋንና አርኪ ጥቅማ ጥቅሞችን በማቅረብ በመማለል መልምሎ ይቀጥራል፡፡ IS በተቆጣጠረባቸው ግዛቶች ከግብርና ቀረጥ፡ ከነዳጅ ሽያጭ፤ እና ከተለያዩ የአረብ ቱባ ቱጃሮች (በገንዘብም፡ በጦር መሳሪያ ግዥም) ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያገኛል ተብሎ ይታመናል፡፡

IS የተባለው ይህ አሸባሪ ቡድን 2አሜሪካዊ ጋዜጠኞች፣ 2አሜሪካዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኛ፡ 1አሜሪካዊ የነዳጅ ኩባንያ ሰራተኛ፡ 2ብርቲሽ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰራተኞች፡ 1የፈረንሳይ ጎብኚ፡ 1ጃፓናዊ ጋዜጠኛ፡ 1ጃፓናዊ ነጋዴ፡ 1ጆርዳናዊ አውሮፕላን አብራሪ፡ 21 የግብፅ ኮፕቲክ ክርስትያኖች እና 28 የኢትዮጽያ ቤተ ክርስትያን የመስቀሉ ተከታዮች አባላትን በአሰቃቂና አረመኔያዊ አኳኋን ቀጥፏል፡፡ በአጠቃላይም እስካሁን IS 6,365 ንፁሃን ዜጎች ተገድሏል፡፡ እስካሁን በIS ከተገደሉት 6,365 ንፁሃን ዜጎች ውስጥ ከ85% በላይ የእስልምና እምነት ተከታዮች ሲሆኑ ከነዚህም አብዛኛውን አሀዝ የሚይዙት ኢራቃውያንስሪያውያን ናቸው፡፡ ከ970,000 በላይ ንፁሃን ዜጎች ከኢራቅና ሶሪያ ብቻ ወደ ቱርክና ሌሎች ሀገራት ተሰዷል፡፡

IS እራሱን “አለማቀፍ እስላማዊ ኩለፋዕ” ብሎ መጥራቱ ድንበር የለሽ ያደርጓል፡፡ ይህን ይዘቱንም ቅርፅ ለማስያዝ ያመቸው ዘንድ ስትራቴጂካዊ ጥቃት በተለያዩ አከባቢዎች አድርሷል፡፡ በዚህም በአሜሪካ፡ ብርቲሽ፡ ፈረንሳይ፡ ጃፓን፡ ጆርዳን፡ ግብፅ፡ ናይጄሪያ፡ ኢትዮጽያ እና የሌሎች ሀገራት ኤጎችም ላይ በአሰቃቂና አረመኔያዊ ድርጊትን በመፈፀም በቪዲዮ በማሰራጫት የብዙሃንን ትኩረት አግኝቶ ወደ ዘመቻው እንዲቀላቀሉ አስገድዷቿል፡፡ 21 የግብፅ ኮፕቲክ ክርስትያኖችን የገደለበትን ቪዲዮ በለቀቀ በሰዓታት ውስጥ የግብፅ ጦር በሊቢያ ዘመቻውን በይፋ መቀላቀሉ ለሂህ እንደማሳያ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጫማሪም የጆርዳኑ ፐይሌትና የጃፓኖቹን ህይወት እንደቀጠፈ ሀገራቶቹ አለምአቀፍ የፀረ-ሽብር ዘመቻ እንዲቀላቀሉ አስገድዷቿል፡፡

የIS ሌላው ስትራቴጂ የአሸባሪነት ማዕረግ የያዙ ሌሎች ተቀናቃኝ ድርጅቶችን (እንደነ አል-ቃኢዳ፡ አል-ሸባብ፡ አል-ኑስራ እና ልሎችም) ከተቻለ በድርድር በስሩ ለመጠቅለል አልያም በአከባቢያቸው የሽብር ተግባርን በመፈፀም ጎልቶ በመታየት እነሱን በማሸማቀቅ የከበተ ልምድ ያላቸውን አመራሮችና አባላቶችን ከነገቢ ምንጫቸው ወደ ራሱ የሚመለምልበት ታክቲካዊ ስትራቴጂ ነው፡፡ በዚህም የፋይናንስ፡ የሰው ሃይልና የሞራል ጭማሪ አግኝቷል፡፡ ልምድ አልባው ቦኮ ሀራምን ስነ-ልቦና በቀላሉ በማጥቃት በስሩ መጠቅለሉ ለዚ እንደማሳያ ልሆን ይችላል፡፡

ኢትዮጽያ እና የፀረ-ሽብር ዘመቻዋ

ኢትዮጽያ በፀረ-ሽብር ዘመቻዋ ስኬት በዓለም ደረጃ ከሚመሰከርላቸው ውስጥ ምናልባት ብቸኛዋ ሀገር ናት፡፡ በሶማሊያ ምድር የዚያድ በሬ መንግስት መፈረሱን ተከትሎ ሀገሪቱ ለዘመናት እርስ በእርስ ጦርነት የሚትታመስ መንግስት አልባ ሀገር ሆና ቆይታለች፡፡ እርስ በእርስ ጦርነት በተዳከመ ሀገር፡ ለስደትና ለረሃብ በተጋለጠ ህዝብ መንግስት አልባ ሊባል ሀገር ውስጥ በቀላሉ መንገስ ጊዜ የማይፈጅባቸው በሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ፅንፈኛ አክራሪና አሸባሪ ሃይሎች (እንደነ አል-ሸባብና አል-ኢትሃድ) በሀገሪቱ ነግሶ ቆይቷል፡፡ ሆኖም የኢትዮጽያ መንግስትና ህዝብ በሶማሊያ ሰላም እንድሰፍን እና ጠንካራ ከአሸባርዎች የፀዳች ሶማሊያ እንድትፈጠር ከወገናቸው ከ ሶማሊያ ህዝብና መንግስት የቀረበላቸውን ጥያቄ በመቀበል እንዲሁም በነዚ አሸባር አካላት በኢትዮጽያ ላይ የታወጀውን የጅሃድ ጦርነት ተከትሎ በተለያዩ ወተደራዊና ፖሎቲካዊ ስልቶች ሶማሊያን ከአሸባሪ ሃይሎች ነፃ እንድትወጣና ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ መንግስት እንድኖራት ከመሰዋዕትነት በላይ ዋጋ ከፍሏል፡፡ እዚህ ጋር ሊረሳ የማይገባ ነገር ቢኖር ኢትዮጽያ በሶማሊያ ያደረገችው የፀረ-ሽብር ዘመቻ የበለጠ እንዲሳካ አለምአቀፍ ህብረተሰብ ከኢትዮጽያ መንግስትና ህዝብ ጎን በመሰለፍ የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል (በተለይ ልዕለ ሀያሏ አሜሪካየአፍሪካ ህበረት/ኢጋድ)፡፡

ኢትዮጽያ በሶማሊያ ያደረገችው የፀረ-ሽብር ዘመቻ ጣልቃ ገብነት ወይም ወረራ ሳይሆን የወገን ጥሪና የሀገር ልዕላዊነትን ከማስከበር ዓላም ባለፈ በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለውን ሁለንትናዊ ፈጣን ልማትና ዲሞክራሲ ማስቀጠል የሚቻለው ጎረቤት ሀገራት በሰላም ሲኖሩና የተረጋጋና ጠንካራ መንግስትና ሕዝብ ሲኖራቸው ብቻ እንደሆነ ስለታመነበት ነው፡፡ በዚህም በሱዳን፡ በጂቡቲና በሶማሊያ የኢትዮጽያ መንግስት አስፈላጊውን ፖሎቲካዊ፡ ኢኮኖሚያዊ፡ ወታደራዊና ማህበረሰባዊ የድጋፍ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጽያ በሶማሊያ ያደረገችው የፀረ-ሽብር ዘመቻ በአለም ደረጃ እንደምሳሌ ሊጠቀስ የቻለበት ምክንያት የኢትዮጽያ መንግስትና ህዝብ ምርጥ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነው (በተለይ በጎረቤት ሀገራት)፡፡ ይህም አብሮ የማደጋ ካለው ፅኑ ፍላጎትና ዓላማ የሚመነጭ በሰላም አምባሳደሮች በሆኑ መከላኪያ ሰራዊታችን እና በውጤታማ የፖሎቲካ አመራር በመታጀብ ጤናማ የህብረተሰብ ለህብረተሰብ ግኑኝነት መሰረት የተካሄደ የፀረ-ሽብር ዘመቻ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለቱ ህዝቦች በታሪክ አጋጣሚ ከነበራቸው የፖሎቲካ እና ወታደራዊ ተቃርኖ ምክንያት እናአሁን ያለው አለምአቀፍ የፖሎቲካ ሁኔታን በሚገባ የተገነዘበው የኢትዮጽያ መንግስት የአከባቢው ሀገራትን የዘመቻው አሳታፊ በማድረግ እና ይዘቱን ቀጠናዊ በማድረግ በሁለቱ ህዝቦች መካከልስር የሰደደ ጠንካራ ፖሎቲካዊ፡ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበረሰባዊ ግኑኝነት እንድፈጠር አድርጓል፡፡ በዚህም አል-ሸባብ ተዳክሞ በሞት አፋፍ ላይ ሲገኝ በሶማሊያ የተረጋጋ እና የተሻለ ሁሉን-አቀፍ መንግስት ተቋቋሟል፡፡

የኢትዮጽያ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ከሌሎች ሀገራት ፀረ-ሽብር ዘመቻ ጋር ሲነፃፀር

አሜሪካ የሚመረው የምዕራባውያን ፀረ-ሽብር ዘመቻ በአፍጋኒስታን፡ በፓኪስታን፡ በሊቢያ እና በኢራቅ ታይቷል፡፡ በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን ከ10ዓመታት በላይ የፈጀ የፀረ-ሽብር ዘመቻ በማድረግ የታሊባን መንግስትና አጋሩ አል-ቃኢዳን መበታተን ቢችሉም፤ ይህ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ምናልባት በዓለማችን አቻ ያልተገኘለት የብዙ ንፁሃን ዜጎች ህይወት የቀጠፈ፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎችን ለእንግልትና ለስደት የዳረገ፡ ብዙዎችን አካለ ጎዶሎ ያደረገ፡ በብዙዎች ላይ ሰባዓዊ መብት ጥሰት ያደረሰ፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናትና እናቶችን ለስቃይና ሞት የደረገ እና በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለስቆቃና እስራት የዳረገ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ነው፡፡ በዚህም ሳያበቃ የነበረውን መሰረተ ልማት፡ መኖሪያ ቤቶች፡ ሆስፒታሎች፡ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች የህዝብ ንብረቶችን ያወደመና ሀገራትን ያፈራረሰ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ነው፡፡

ከታሊባን ውድቀት ወዲህም ሁሉን ያላቀፈና በሃይማኖት ሴክት የተከፋፈለ እና ሙሰኛ የፖሎቲካና የመንግስት አደረጃጀት በመፍጠር መንግስት አልባ ሊባል የሚችል አፍጋኒስታን መስርቷል፡፡ በኢራቅም ልክ እንደ አፍጋኒስታን ሁሉ ብዙ ህይወቶች ጠፍቷል፡፡ ብዙ ንብረቶች ወድሟል፡፡ ብዙዎች ለእንግልተና ስደት ተዳርጓል፡፡ ብዙዎች የሰባዓዊ መብት ጥሰት ደርሶባቿል፡፡ ብዙዎች ለስቃይና እስር ተዳርጓል፡፡ በኢራቅ አሁን አጀንዳችን የሆነውን IS የፈጠረ፡ በሱኒና ሺዓ መሀከል ውጥረትና ግጭትን የፈጠረ የፖሎቲካና የመንግስት አደረጃጀት በመመስረት ከሳዳም ሁሴን አገዛዝ የከፋ የጦርነት ምድር የሆነችው ኢራቅን ፈጥሯል፡፡ ሊቢያም እንዲሁ ከአፍጋኒስታንና ኢራቅ የተለየ ዕጣ ፋንት አልደረሳትም፡፡

በአጠቃላይ የምዕራባውያን የፀረ-ሽብር ዘመቻ ሽብር ከማጥፋት ይልቕ የሚፈለፍል፡ ችግረ ከማስወገድ ይልቅ ችግሮችን የሚፈጥር፡ ከሀገር ግንባታ ይልቅ ሀገር ማፈራረስ ላይ ያቶከረ፡ ህዝብን ከማስማማት ይልቅ የሚያጋጭና የሚከፋፍል፡ ህይወት የሚያድን ሳይሆን ተጫማሪ ህይወቶችን የሚቀጥፍ፡ ከወረደ የኑሮ ሁኔታ ወደ ዘቀጠ የኑሮ ሁኔታ የሚያሸጋግር እና ከሰላም ይልቅ እልቂትን የሚፈጥር ፀረ-ሽብር ዘመቻ ነው፡፡ ለዚህ መንሰዔ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ግን ወናው መንስዔ የራሳቸው የምዕራባውያን የጥፋት ፖሊሲ ነው፡፡

የፀረ-ሽብር ዘመቻ ከምዕራባውያን ባለፈም በተለያዩ ሀገራቶች ተካሄዷል፡፡ ናይጄሪያ በቦኮሀራም ላይ የሚታደርገው የፀረ-ሽብር ዘመቻ አንዱ ነው፡፡ በዚ ዘመቻ ቦኮሀራም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደከመ ይሄዳል ቢባልም በተቃራኒው ግን ግዛቱን እያስፋፋ የብዙ ሰዎችን ህይወት እየቀጠፈ፤ ሴት ተማሪዎችን እየጠለፈና የተለያዩ ከተሞች ላይ ፍንዳታ እያደረሰ ይገኛል፡፡ የአከባቢው ሀገራት ካሜሩንን ጫምሮ ዘመችውን ቢቀላቀሉትም እስከሁን ድረስ የረባ ውጤት ሊመጣ አልቻለም፡፡ የረባ ለውጥ ሊኖር የሚችለው የሀገሪቱ ፖሊሲ የረባ ሲሆን ብቻ ነው፡፡

ኬንያ፡ ኬንያ በግዛቷ ውስጥ እንደፈለጉ የሚዋኙትን አል-ሸባብና ተባባሪዎቹን አቅፋየፀረ አል-ሸባብ ዘመቻን መቀላቀሏ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ በዚህም ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ48 በላይ የሽብር ጥቃት አስተናግዳለች፡፡ በቅርቡ በጋሪሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የደረሰው የሽብር ጥቃት ያደረሰው እልቂትን ማየቱ በቂ ነው፡፡ በኬንያም ስር-ነቀል መንግስታዊ፡ አኮኖሚያዊና ፖሎቲካዊ አደረጃጀት ካልመጣ በስተቀር ይህ ነው ሊባል የሚችል ተጫባጭ ውጤት ይመጣል ብሎ አይታሰብም፡፡

ግብፅ፡ የሁስኒ ሙባረክ አምባገነናዊ አገዛዝን በአረብ አብዮት ቁንጮ አደባባይ “ተህሪር አደባባይ” ወጥቶ በመቃወም ካወረደ ቡኃላ በምትኩ የአክራሪዎች እና አሸባሪዎች መፈልፈያ ድርጅት የሆነውን ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲን በዲሞክራሲያዊ ሂደት የመረጠው የግብፅ ህዝብ በቀላሉ ከሽብርተኝነትና ከአሸባራዎች አደጋ ነፃ ይሆናል ብሎ ማሰብ የወሃነት ነው (ምንም እንኳ ከዓመት ቆይታ ቡኃላ ሙስሊም ወንድማማቾችወታደራዊ ክፍል ተገልብጦ ከመንግስትነት ቢወገድም)፡፡ ለዚህም በሀገሪቱ ከምንገዜውም በላይ እየደረሰ ያለውን የሽብር ጥቃቶች ከማየት ባለፈ የሲንዓ በረሃ የሽብረተኞች እንቅስቃሴን ማየቱ በቂ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳ IS 21 የግብፅ ኮፕቲክ ክርስትያኖችን የገደለበትን ቪዲዮ በለቀቀ በሰዓታት ውስጥ በሊቢያ ዘመቻውን በይፋ መቀላቀሏ ምን ያህል የምትጨብጠውን እንዳጣች ያሳያል-“የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም እንደሚባለው”፡፡

በአጠቃላይ በአፍጋኒስታን፡ በፓኪስታን፡ በሊቢያ፡ በኢራቅ፡ በናይጄሪያ፡ በኬንያ እና በግብፅ የታዩ አይነት ክስተቶች “ለምን በኢትዮጽያ ፀረ-ሽብር ዘመቻ ኣልታየም?” ወደሚለው እንድንሄድ ያስገድደናል፡፡ ፍርዱን ለናንተ አንባቢያን ልተወው ወሰንኩ፡፡ ስለዚህ የሰሞኑ IS በኢትዮጽያውያን ክርስትያኖች ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ በቪዲዮ መልቀቁን ተከትሎ ኢትዮጽያ አለማቀፍ የፀረ-ሽብር ዘመቻ እንዲትቀላቀል በርካታ ግፊቶች እየተደረገባት ይገኛል፡፡ ግፊቱ በአንድ በኩል ከሀገር ውስጥ የሚደረግ ሲሆን እንደ ዜጋ ለሞቱት ወገኖቹ ከመቆጨትና ከወገናዊ ፍቀር አኳያ ሊታይ የሚችል በመሆኑ በሂደት እየቀዘቀዘ ሊሄድ የሚችል ነው፡፡ በሌላ በኩል የግብፅ ዉትወታ ካለን ይህ ነዉ የማይባል ግኑኝነት እና ከአባይ ግድብ አንፃር ሊታይ የሚገባ ሲሆን በኢትዮጽያውያ ዘንድም ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በአሜሪካኖችና ምዕባውያን ዘንድ የሚሰጡ የሀዘን መግለጫዎች ይዘታቸው ግልፅ የሆነና ኢትዮጽያን ወደ አለማቀፍ የፀረ-ሽብር ዘመቻ እንዲትቀላቀል የሚጋብዙ ናቸው፡፡ ችግሩ የፋይናንስ አይደለም- እስፖነሰር በሽ ነውና፡፡ እነ አሜሪካን ጫምሮ የገልፍ ቱባ ቱጃር አረብ ሀገራት ለፈንዱ ዝግጁ ልሆኑ ይችላሉ፡፡ ችግሩ ግን ብዙ ነው፡፡

ኢትዮጽያ አለማቀፍ የፀረ-ሽብር ዘመቻ ትቀላቀላለች ወይ? ለሚለው ጥያቄ በIS ላይ ከጁን 13-2014 ጀምሮ ባለፉት 42ሳምንታት በአሜሪካ መሪነት በተከፈተው አለምአቀፍ የፀረ-ሽብር ዘመቻን (በኢራቅ፡ በሶሪያ፡ በሊብያ እና በናይጄሪያ) የተቀላቀሉ ከ60 በላይ ሀገራትና ተለያዩ ተዋጊ ቡድኖች በድምሩ ያመጡት ውጤት ሊጤን ይገባል፡፡ ዘመቻው የIS ይዞታን ማስለቀቅ ችሏል? ዘመቻው የIS ጉዞን መግታት ችሏል? ዘመቻው በድምሩ ምን ያህል ለውጥ አምጥቷል? እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎች ሊመለሱ ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዘመቻው የሀገሪቱን የባለፉት 21 ዓመታት ሁለንትናዊ ስኬት ሚስጥር የሆነውን ዋና ዋና መርሆች ታሪክ የማድረግ እድሉ ሰፊ መሆኑ አንዱ ችግር ነው፡፡ “ኢትዮጽያ አለማቀፍ የፀረ-ሽብር ዘመቻ ትቀላቀላለች ወይስ አትቀላቀልም?” የሚለው ጥያቄ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ እኔ ግን ጨረሰኩ፡፡

*******

Abdulbasit Abdusemed

more recommended stories