ጣታችን ወደ ራሳችን እንቀስር! – ደሀን እናቱም ኣትወደዉም

የኢኮኖሚ ችግር ሲፈጠር ስደተኛዉን ኢላማ ኣድርጎ ጥቃት መሰንዘር በደቡብ ኣፍሪካ ብቻ የታየ ችግር ኣይደለም። ግሪክ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ሩስያ እና በብዙ ኣገሮች የታየ የተለመደ ክስተት ነው። ህንዳውያን በግሪክ ጎዳና ለመንቀሳቀስ ኣዳጋች እየሆነባቸው እንደሆነ ሁሉ ሞስኮም ኣሁን የውጭ ዜጋ እንደልቡ እማይንቀሳቀስባት ከተማ ሁናለች፤ ለምን ቢባል የኢኮኖሚ ችግር።በነዚህ ኣገሮች ከፈተኛ የፀረ ስደተኛ ጥቃትም እሚፈፀምባቸው ኣገሮች እየሆኑ ነው:: ይሄ ነገር ከዘር እና ከጥቁረት እያገናኙ ደቡብ ኣፍሪካውያንን የቀኝ ገዢዎች ንድፈ ሃሳቦች እየተጠቀሙ “ድሮስ ጥቁር….ለነፃነት ኣቅም ያልደረስ እንስሳ” ምናምን እያሉ የትምክህት ቃል መሰንዘር የጉዳዩን ትክክለኛ ገፅታ ኣለመረዳትን ነው እሚያሳየው።

የኢኮኖሚ ችግር ወደ ፖለቲካዊና የፀጥታ ችግር እንደሚቀየር ሳይታለም የተፈታ ሃቅ ነው። በሩዋንዳም በሌሎች ኣገራትም የታየው ይህ ነው። እንዲህ ኣይነት ሁኔታ ለሰነፍ ፖለቲከኞች ጥሩ ኣጋጣሚ ይፍጥራል፤ የሰነፍ ፖለቲካ ደግሞ ቀላል ግን ኣውዳሚ ስለሆነ ዉጤቱ ኣሁን ደቡብ ኣፍሪካ ላይ እያየን ያለነው ኣይነት እልቂት ያስከትላል።ኣንዱን በማስወገድ “መፍትሄ” ለመሻት መጣር ነው የሰነፍ ፖለቲካ ማለት።ለዚህ መዋቅራዊ መደላድል እሚፈጥረው ግን የኢኮኖሚ ችግር ነው። ሁቱዎች ቱትሲዎች ላይ ገጀራቸውን ከማሳረፋቸው በፊት የዋጋ ንረት እና ስራ ኣጥነት ሂወታቸው ላይ ገጀራዉን ኣሳርፎ ነበር። ይህ ቀቢፀ ተስፋነት ሰለፍ ፖለቲከኞች ተመቻቸው እና ዘርን ለማጥፋት ተጠቀሙበት። ደቡብ ኣፍሪካ ላይ እየተፈፀመ ያለ ነገርም ከጄኔቲክ ሳይሆን ከኢኮኖምያዊ ሁኔታ መመሰቃቀል እሚመነጭ ነገር ነው።

የደቡብ ኣፍሪካ ለየት እሚያደርገው የኣፓርታይድ ስርኣት በፖለቲካው ረገድ “ሲገረሰስ” የኢኮኖሚው ሁናቴ በነጮች እንደተያዘ እንዲቀጥል መፈቀዱ ነው። ማንዴላ ከዚ ዉጪ ኣማራጭ ነበረው ወይ? የሚለው መከራከር ይቻላል:: ማንዴላ እሚመራው ፓርቲ ያመጣው ሰላም ዘላቂ የሆነ ስላም ሳይሆን ጦርነት ኣለመኖርን እሚያመላክት ሰላም ነው (Negative Peace እሚባለው) በኢኮኖምያዊ እርምጃ ያልተደገፈ ሰላም የዉሸት ሰላም ነው። ኣቶ መለስ ዜናዊ እንዲህ ኣይነት ሰላም የኪራይ ሰብሳቢዎች ሰላም (Rental Peace) ይለው እንደነበር ኣሌክስ ዲዋል ይናገራል። ትክክልም ይመስለኛል።Photo - South African xenophobic mob

ኢትዮጵያዊያን እና ሌሎች ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ነገር ኢኮኖምያዊ ድቀት፣ ድንቁርና እና ኃላ-ቀርነት ተደማምረው የፈጠሩት ተስፋ መቁረጥ ያስከተለው ኣሳዛኝ ክስተት ነው። ይህን በዜጎቻችን እየደረሰ ያለው ነገር ለድርጅታዊ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማዋል መንቀሳቀስ ሌላ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ “ፖለቲከኛነትን” ነው እሚያሳየው። ለኔ ትምህርቱ ኣንድ እና ኣንድ ነው፤ የኢኮኖሚ የጀርባ ኣጥንቱ የተወሰኑ ሞላጫዎችን ብቻ ደግፎ የሚንቀሳቀስ ማህበረሰብ ኣወቃቀሩ ለሰላምም ለዴሞክራሲም ጠንቅ መሆኑ ነው። ብዙ ድሃና ድንቆሮ ተይዞ ዘላቂ ሰላም ብሎ ነገር የለም።

እምናየው እና እምንሰማው ነገር በርግጥ ያበግናል፤ ይሁን እንጂ ኣሁንም ዋና ጠላታችን የራሳችን ድህነት ነው።በየቦታው ላለመበተን ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ነው ቁልፍ መፍትሄው፤ ኢኮኖሚ ኢኮኖሚ ኣትበሉ መናገርያ ማይክራፎን እና ያራት ኪሎ ወንበር ብቻ ይሰጠን እንጂ ዳቦ ኣያስፈልግም እምትሉ ባለ-ዳቦ እና ባለ-በርገር “ፖለቲከኞች” ኣንድ ማወቅ ያለባቹህ ነገር ቢኖር ያ ደቡብ ኣፍሪካ ያለው ዜጋችን ማይክራፎን እና ያራት ኪሎ ወንበር ሳይሆን ዳቦ ፍለጋ ነው እዛ ድረስ የሄደው። እናም ኣገራችን ማይክራፎንም ዳቦም እንዲኖራት ጠንካራ እና ፍትሃዊ ኢኮኖሚ ያስፈልጋታል።

መዋቅራዊ መፍትሄው ኣገራችንን ማሳደግ ነው። ዘላቂ መፍትሄ ላይ እናተኩር፤ ክስተቶችን እየጠበቁ “የልዩ” ተቆርቛሪነት ካባ በመልበስ ኣርበኛ ለመሆን መሞከር ኣሁንም ሌላ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ “ኣክቲቪስት” መሆንን ስለሆነና ይህም እርባና ቢስ ስለሆነ የራሳችን ልማት ለማፋጠን ኣርቀን ብናስብ ይሻላል እላለሁ። ለጥ ብለው ኣለም ሲቀድመን ተኝተው ከርመው ችግር ሲመጣ እንደሞፎከር ኣስጠሊታ ነገር የለም።ይቺ ግዝያዊ እና የሳምንት ኣርበኝነነት ማንንም ኣትጠቅምም። የችግሩ መሰረታዊ መንስኤ መረዳት ነው ጠቃሚው ነገር::

ዜጎቻችንን ለማዳን ተጨባጭ መፍትሄ ለማግኘት እየተረባረቡ ላሉ ሁሉም ማመስገን እፈልጋለሁ።የደቡብ ኣፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ እና ኣደባባይ ወጥተው ድርጊቱን የተቃወሙ የደርባን ከተማ ነዋሪዎች ኣፍሪካዊ ወንድማማችነትን በግዝያዊ ችግሮች መሸርሸር እንደሌለበት ላሳዩት ኣጋርነት ክብር ይገባቸዋል። የኣፍሪካ በጎ ነገር መዘገብ ዳገት እሚሆንባቸው የምዕራባውያን ሚድያ እይታችንን ሸራርፎ ኣፍሪካዊ ወንድሞቻችን እንዳንጠላ መጠንቀቅ ኣለብን።

ሆኖም ኣሁንም ጣታችን ወደ ራሳችን እንቀስር፤ ራሳችንን ዉብ እና ዉድ እናድርግ… ዘላቂ መፍትሄው ይህ ነውና! ደሀን እናቱም ኣትወደዉም ኣይደል ብሂሉ?

*******

more recommended stories