ኦሮምኛ ለፌደራል መንግስት – እንዴት?

(አዲስ ከድሬዳዋ)

በሶሻል ሚዲያ(በተለይ በፌስቡክ) ብዙ ጊዜ አስተማሪና ምክንያታዊ የሆኑ ፅሑፎችን በመፃፍ የሚታወቀው ዶክተር ብርሀነ መስቀል አበበ ሰኚ ሰሞኑን ከአማርኛ ጎን ለጎን ኦሮምኛም የፌደራል መንግስት፣ እንዲሁም የድሬዳዋ እና የአዲስአበባ አስተዳደሮች የስራ ቋንቋ እንዲሆን የሚጠይቁ ፅሑፎችን በተከታታይ እያወጣ ሰፊ ውይይትም እየተደረገ ነው፡፡ ሀሳቡንም በግሌ እደግፈዋለሁ፡፡ነገር ግን በምን መልኩ ነው የስራ ቋንቋ የሚሆነው , እንዲሁም በአተገባበር ሒደት ምን ሊያጋጥም ይችላል የሚለው ግን የታሰበበት አይመስልም፡፡

ኦሮምኛን የስራቋንቋ ይሁን ስንል የሀገሪቱ የቋንቋ አጠቃቀም ፖሊሲ ምን ይመስላል የሚለውን በጨረፍታ ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቋንቋ የላትም፡፡ በሀገሪቱ የሚነገሩ ቋንቋዎች ሁሉም እኩል ናቸው፡፡ በርካታ ወይም አነስተኛ ተናጋሪ ስላለው አንድ ህዝብ በአፍ መፍቻ ቋንቋው እንዳይማር፣ አገልግሎት እንዳገኝ፣ እንዳይዳኝ፣ . . . . አይከለከልም፡፡ሆኖም ከኢኮኖሚ አቅም እና የተማረ የሰው ሀይል ውስንነት ጋር ተያዞ በመማሪያነት እያገለገሉ ያሉ ቋንቋዎች ከ30 አይበልጡም(በርግጥ ይህ ከ90 ፐርሰንት በላይ ኢትዮጵያውያንን ይሸፍናል)፡ ስለዚህ ሁሉም ቋንቋ እኩል ከሆኑ አንድን ቋንቋ የፌደራል የስራ ቋንቋ አድርገህ ሁሉም ክልሎች በትምህርት ቤቶቻቸው እንዲስተምሩት፣ በጋራ መግባቢያነት እንዲጠቀሙት፣ . . ለመወሰን የተለየ መነሻ ያስፈልጋል፡፡በዚህ ረገድ አማርኛ በ ታሪክ አጋጣሚ በብዙ ቦታዎች በሁለተኛ ቋንቋነት፣ በጋራ መግባቢያነት ( lingua franca) ና በመንግስት ቋንቋነት ሲያገለግል ስለቆዬ በሚል መነሻ የፌደራሉ መንግስት የስራቋንቋ እንዲሆን በህገ መንግስቱ ተወስኗል፡፡Logo - Federal government of Ethiopia

ኦሮምኛስ ኦሮምኛ በሀገሪቱ በርካታ ተናጋሪዎች ያሉት ቋንቋ ነው፣ ሆኖም ቋንቋው ከኦሮሚያ ውጪ በሁለተኛ ቋንቋነት እምብዛም አገልግሎት አይሰጥም፣ ልክ እንደ ትግርኛና ሶማሊኛ ከክልሉ ውጪ የሚነገረው በክልሉ አጎራባች ወረዳዎች ብቻ ነው . . . . ከዚህ አንፃር ኦሮምኛን የፌደራል ቋንቋ እንዲሆን ወስነህ ትግሪኛን ወይም ሶማሊኛን አይሁኑ ለማለት የሚያበቃ መነሻ አለ ወይ?. . . .ማለትም ሶስቱም ቋንቋዎች ያላቸው ተናጋሪ ብዛት ምንም ያህል ይሁን ከክልላቸው ውጪ ለሌሎች ብሄሮች በሁለተኛ ቋንቋነት የሚሰጡት አገልግሎት ውስን እስከሆነ ድረስ እና በክልላቸውም ብሄራዊ ቋንቋ ሆነው እያገለገሉ እስከሆነ ድረስ ከክልላቸው አልፎ ሌሎች ክልሎችም በጋራ በሚገለገሉባቸው የፌደራል ተቋማት በስራ ቋንቋነት እንዲያገለግሉ መወሰን ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?

እኔ ኦሮምኛ የፌደራል መንግስት የስራቋንቋ እንዲሆን የምደግፈው ግን በአሁኑ ሰዓት እንደ አማርኛ በጋራ መግባቢያነት( lingua franca) ለሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ሊሰጥ በሚችለው አገልግሎት ሳይሆን ፡- 1ኛ. የኦሮሞ ህዝብ ካለው የቁጥር የበላይነት አንፃር በልዩ ሁኔታ ኦሮምኛ ከአማርኛ ጋር ተመሳሳይ ደረጃ(የፌደራል ቋንቋነት status) እንዲኖረው 2ኛ. ኦሮሚያ ያለው መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከሁሉም ክልሎች ጋር ስለሚጎራበትና ህዝቦቹም ከአብዛኛዎቹ የሐገሪቱ ህዝቦች ጋር በባህል፣ ሀይማኖት፣ ኢኮኖሚ . . .የተሳሰሩ በመሆናቸው ወደፊት ሐገሪቱ በኢኮኖሚ ይበልጥ እየተሳሰረች በሔደች ቁጥር ኦሮምኛም በጋራ መግባቢያነት( lingua franca) የሚያበረክተው አስተዋፅዖ እየጨመረ ይሔዳል በሚል ታሳቢ ነው

ኦሮምኛ የፌደራል ቋንቋ ይሁን ሲባል ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበት ሁለት አማራጮች አሉ፡፡

1ኛ የፌደራል ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ከአማርኛ በተጨማሪ በኦሮምኛም ጭምር እንዲሆን ማድረግ – በዚህ አማራጭ ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሌሎች የሐገሪቱ ብሄር ብሔረሰቦቸ ግን በነበረው ይቀጥላሉ፡፡ በዚህ አካሄድም ኦሮሞዎች ከክልላቸው ባሻገር በፌደራል ደረጃም በኦሮምኛ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉ ሲሆን ይህም የፌደራል መንግስትን የተወሰነ ወጪ ከሚያስወጣው በስተቀር በሌሎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም፡፡ ከአንድ በላይ ቋንቋ በሚነገርባቸው እንደ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች በጋራ መግባቢያነት የመረጡትን መጠቀም ይችላሉ፡፡

2ኛ. ሌላኛው አማራጭ ኦሮምኛ የፌደራል ቋንቋ ሲሆን ቋንቋው በፌደራል መስሪያ ቤቶች በስራ ቋንቋነት ከማገልገል ባሻገር ልክ እንደአማርኛ ሁሉ በሁሉም ክልሎች እንደ አንድ ትምህርት እንዲሰጥ፣ እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መግባቢያነት የአማርኛን ያህል ኦሮምኛንም እንዲጠቀምበት ማድረግ ነው፡፡ ይሔኛው አማራጭ ለተወሰኑ አስርተ አመታት ኦሮምኛን በማይናገሩ ክልሎች ላይ ጫና የሚፈጥር ሲሆን ሀሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ ከተተገበረ ግን ቋንቋው በሂደት ወደጋራ መግባቢያነት( lingua franca) እንዲያድግ እድል ይፈጥርለታል፡፡ ነገር ግን ይሔኛው አማራጭ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ክልሎች ከፈቀዱ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ተግባራዊነቱ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በቋንቋቸው አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም እንዲማሩት ስለሚገደዱ ነው፡፡ በእኔ ግምት የመጀመሪያው አማራጭ ለመተግበር የሚቀል ይመስለኛል፡፡ ሆኖም በሁለቱም አማራጮች ቋንቋው የፌደራል መንግስት የስራ ቋንቋ ሲሆን አንዳንድ ጠባቦች በቋንቋ አገልግሎት የማግኘት መብትን ከመጠቀም አልፈው መብታችሁን በኦሮምኛ ብቻ ጠይቁ፣ አማርኛ አትገልገሉ፣ኦሮምኛ ጭምር የማይችል ሰው በፌደራል አይቀጠር . . . አይነት ከፋፋይ እና የሌሎችን መብት የሚጋፉ አካሄዶችን እንዲከተሉ በር እንደሚከፍትላቸው ይታሰባል፡፡ በተረፈ ዶክተር ብርሀነ መስቀል ባቀረባቸው ዝርዝር ሀሳቦች ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ላቅርብ፡፡ 1. አማርኛ 29 ፐርሰንት ተናጋሪ አሉት ያልከው አማርኛን በአፍ መፍቻ ቋንቋነት የሚጠቀሙትን ብቻ የሚመለከት እንጂ አማርኛን በሁለተኛ ቋንቋነት የሚጠቀሙትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን አያካትትም፡፡ 2. አዲስአበባ እና ድሬዳዋ ኦሮሞን ያገለሉ ደሴቶች እንደሆኑ አድርጎ የገለፅውም ትክክለኛውን ምስል አያሳይም፡፡ በዝርዝር እንየው፡-

ድሬዳዋ የስራ ቋንቋዋ አማርኛ የሆነ አስተዳደር ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አገልግሎት የሚሰጠው በአማርኛ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ አማርኛ በማይናገሩ የገጠር ቀበሌዎች በመምህርነት፣ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛነት እና የግብርና ኤክስቴንሽን ሰራተኛነት፣ . . . . ለመስራት የሚቀጠሩ ባለሙያዎች በሙሉ ኦሮምኛ ወይም ሶማሊኛ እንዲችሉ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኦሮምኛ በስፋት በማይነገርባቸው የከተማዋ ሰፈሮች ተወልደው ያደጉና ቋንቋዉንም የማይችሉ ሆኖም አስተዳደሩ በግብርና ለ2 አመት አስተምሯቸው ከተመረቁ በኋላ ኦሮምኛ/ሶማሊኛ አትችሉም በሚል ከሌሎች ተነጥለው ሳይቀጠሩ በመቅረታቸው ቅሬታ ያላቸው ጓደኞች አሉኝ፡፡ ሌላው ከተሜ ኦሮሞ ግን ሙሉ በሙሉ አማርኛ መናገር የሚችል በመሆኑ በአማርኛ አገልግሎት መሰጠቱ ችግር የሚፈጥርበት አይመስለኝም፡፡ አልፎ አልፎ ቋንቋ የማይችሉ ቢመጡም ኦሮምኛ ወይም ሶማሊኛ የሚችል መንግስት ሰራተኛ በየክፍሉ ስለማይጠፋ ችግር ሆኖ አያውቅም፡፡ በሌላ በኩል ቋንቋ የማይችሉ ሰዎች አገልግሎት ሊያገኙ ከሚመጡባቸው ተቋማት መካከል የሆኑት የህክምና ተቋማት አስተዳደራዊ አገልግሎታቸውን በአማርኛ ያድርጉ እንጂ ለታካሚዎች በሚገባቸው ቋንቋ ነው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኘው፡፡ በዚህ ረገድ አንድ ምሳሌ ላቅርብ፤ የድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል አልጋ ይዘው ህክምና እያገኙ ካሉት ታካሚዎቹ አብዛኛዎቹ የምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች ናቸው፡፡ የፌደራል መንግስት እንዲያውም በድሬዳዋ በጀት የሚንቀሳቀሰው ሆስፒታል አብዛኛዎቹ ተገልጋዮች ከክልሉ ውጪ ያሉ ነዋሪዎች በመሆናቸው ድጎማ አደርጋለሁ ማለቱ ነው የሚነገረው፡፡

ትምህርትን በተመለከተም ኦሮምኛ በስፋት በሚነገርባቸው ሰፈሮችና የገጠር ቀበሌዎች የኦሮምኛ ትምህርት ቤቶች ናቸው አገልግሎት የሚሰጡት፡፡ በሀይስኩል ደረጃ ደግሞ በየሰፈሩ ራሱን የቻለ የኦሮምኛ ትምህርት ቤቶች ባይከፈቱም በየክፍሎቹ ግን የተወሰኑ ሴክሽኖች የኦሮምኛ ክፍሎች ናቸው፤ ለምሳሌ 30 የ9ኛ ክፍል ሴክሽኖች ቢኖሩ 5ቱ ወይም 6ቱ የኦሮምኛ ሴክሽኖች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የድሬዳዋ ነዋሪዎች በተለይ ሶማሊዎችና ኦሮሞዎች በሲቪል ሰርቪሱ ያላቸው ድርሻ በነዋሪነት ካላቸው ሬሾ ያነሰ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በአንድ በኩል በቀደሙት አመታት ከትምህርት ይልቅ ንግድ ወይም ግብርና ላይ ያተኩሩ ስለነበረ፣ በሌላ በኩል በሲቪል ሰርቪሱ ወር ጠብቆ በሚከፈል አነስተኛ ደሞዝ ለመስራት ባለመፈለግ ተሳትፎዋቸው አነስተኛ ነው፡፡ ይህንን የምልህ በአስተዳደሩ ካሉት 7600 ገደማ ሲቪል ሰርቫንቶች አብዛኞቹ ፅዳት፣ ተላላኪ፣ ጥበቃ፣ ሾፌር፣መዝገብ ቤት፣ሂሳብ ክፍል፣ . . . እና የመሳሰሉ ድጋፍ ሰጪ መደቦች ሲሆኑ የተሸለ ደሞዝ የሚከፈልባቸው ፕሮፌሽናል መደቦች ያላቸው ድርሻ ከጠቅላላው ሲቪል ሰርቪስ 10.41 ፐርሰንት ብቻ ነው፡፡ በዲግሪ የተመረቁ መምህራንንና የጤና ባለሙያዎችን ብንጨምራቸውም ከ20 ፐርሰንት አይበልጥም፡፡ አሁንም የስራ ማስታወቂያ ስታወጣ በአብዛናዎቹ የድጋፍ ሰጪ መደቦች ለመስራት የሚወዳደሩት ሌሎች ናቸው፡፡(ይህ ውክልና አዲስአበባና ሌሎች ክልሎችንም ይመለከታል)፡፡ ያም ሆኖ ከሲቪል ሰርቪሱ 3.86 ፐርሰንት ድርሻ ያለውና የድሬዳዋን ሁለንተናዊ አቅጣጫ የሚወስነው ተሹዋሚ 80 ፐርሰንቱ ኦሮሞና ሶማሌ ነው፡፡ ለዚያውም በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ቀድሞ የነበረውን አነስተኛ ውክልና ለማስተካከል በሌሎች ክልሎች በሜሪት የሚገኘው የመምሪያ ሀላፊነት/ሂደት መሪነት መደብ ሳይቀር ድሬዳዋ ውስጥ ግን በሹመት እንዲሆን በማድረግ በአመራር ረገድ የነበረው የአቅም ክፍተት እንዲጠብ እየተደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የድሬዳዋ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስ ከአብዛኛዎቹ ክልሎች አቻ ተቋማት የተሸለ የማስፈፀም አቅም ገንብቷል፡፡ ስለዚህ የአስተዳደሩ የስራ ቋንቋ አማርኛ በመሆኑ ከአስተዳደሩ አገልግሎቶች የተገለለ ማንም የለም፤ ኦሮምኛም በተደራቢነት የስራ ቋንቋ ይሁን ቢባል ባለቤትነትን ከማሳየት(ሲምቦሊክ ከመሆን) ባለፈ የተገለሉ ኦሮሞዎችን ተጠቃሚየሚያደርግ ነው የሚለው አገላለፅ ግን እውነታውን አያሳይም – ኦሮሞዎች ስላልተገለሉ፣ አሁንም የከተማዋ ዋና ባለቤቶች ስለሆኑ፡፡ በዚህ ረገድ ለጊዜው በበቂ ሁኔታ አልተወከልንም ሊሉ የሚችሉት አማራዎች እንጂ ኦሮሞዎች አይደሉም፡፡

አዲስአበባን በተመለከተ የከተማ አስተዳደሩ እና በከተማዋ የሚገኙ የፌደራል መስሪያ ቤቶች ሲቪል ሰርቪስ ድሬዳዋ ላይ እንዳየነው አብዛኛዎቹ ድጋፍ ሰጪዎች በመሆናቸው አብዛኞቹ ተቀጣሪዎቹም የከተማዋ ነዋሪዎች መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ መቼም በፅዳት ለመቀጠር ከኦሮሚያ ወይም ደቡብ መጥቶ የሚወዳደር የለም፡፡ በዚህ የተነሳ በሁለቱም የፌደራል እና የአዲስአበባ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የአማራ ውክልና ከፍተኛነት ወደፊትም መቀጠሉ አይቀሬ ይመስለኛል(የከተማዋ 47 ፐርሰንት ነዋሪ አማራ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ ሆኖም አዲስ አበባ እንደ ድሬዳዋ ባለብዙ ቋንቋ ተናጋሪ ስላልሆነች(ከ80 ፐርሰንት በላይ ነዋሪዋ የአፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ ነው) አማርኛ ተናጋሪ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን አማርኛ ቋንቋ ካልቻሉ የመንግስት አገልግሎትን ብቻ ሳይሆን በግለሰቦቹ ህይወት ይበልጥ ወሳኝነት ያላቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችንም ማድረግ ከባድ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የከተማዋ ነዋሪ የሆነ አንድ ኦሮሞ መስሪያ ቤት ውስጥ በኦሮምኛ አገልግሎት ቢያገኝም እንኳ በማህበራዊ ህይወቱ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው አማርኛን እንዲናገር መገደዱ ስለማይቀር የከተማዋ ነዋሪ ሆኖ አማርኛ የማይችል ኦሮሞ አይኖርም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ስለሆነም የአዲስአበባ ነዋሪ ሆኖ አዲስአበባና ፌደራል መንግስት የስራ ቋንቋቸው አማርኛ በመሆኑ ተጎጂ እየሆነ ያለ የለም- አማርኛ የማይችል ስለሌለ፡፡ ድሬዳዋ ላይ እንዳለው በአዲስአበባ ኦሮምኛ ልክ እንደ አማርኛ የጋራ መግባቢያ ( lingua franca) ሆኖ በግብይትም፣ ማህበራዊ ግንኙነትም፣ ስራም፣ መዝናኛም . . . . .ወዘተ የሚያገለግል ቢሆን ኖሮ ኦሮምኛ ብቻ የሚናገር ሰው በከተማዋ ሌላ ቋንቋ መልመድ ሳያስፈልገው መኖር ይችል ነበር፡፡ ይህ ግን ኦሮምኛን በመንግስት መስሪያ ቤት የስራ ቋንቋ በማድረግ ብቻ የሚመጣ አይደለም- እጅግ ሰፊ ስራንና ረጂም ጊዜን ይፈልጋል፡፡

********

አዲስ ከድሬዳዋ - Frm. journalist; currently communicator

more recommended stories