የአዲስ አበባ – ፊንፊኔ ዙሪያ እቅድን መቃወም ለምን?

(አዲስ – ከድሬዳዋ)

ድሮ ድሮ የአዲስአበባ ዙሪያ ገበሬዎች ራሳቸው መሬታቸውን እየሸጡ ነበር ከተማ የሚስፋፋው፡፡ ከ15 አመት ወዲህ ደግሞ መንግስት ካሳ እየከፈለ መሬታቸውን በሊዝ ለባለሀብት(ቤተሰሪ) ይሰጥ ነበር፡፡ በመጀመሪያዎቹ አመታት ታዲያ ለመሬቱ የሚከፈለው ክፍያ እዚህ ግባ የማይባል ስለነበር የብዙዎችን ህይወት ያበላሸ ነበር፡፡ በ1990ዎቹ አጋማሽ ካዛንቺስ ቶታል አካባቢ እዚህ ግበ የማይባል ካሳ ተሰትቶት የንግድ ተቋሙን የተነጠቀ ሰው ራሱን እንዳጠፋ መስማቴን አስታውሳለሁ፡፡ ቆይቶ የካሳው መጠንም በሽያጭ የሚገኘውን ያህል ባይሆንም መመሪያ ተዘጋጅቶለት የተሸለ መልክ እየያዘ እንደነበርም አስታውሳለሁ፡፡ እንዲያውም ለልማት የሚፈለግ ቦታ ላይ ተነሺ ሰዎች አስቀድሞ ከ2 አመት በፊት ሁሉ እየተነገራቸው ቅድመ ዝግጅት ያደርጉ እንደነበረና በዚህ መሀል የመሬት ካሳ የተቀበሉ ገበሬዎች መሬቱን በርካሽ ዋጋ አትርፎ መሸጥ ለሚፈልግ የከተማ ስግብግብ ሁለተኛ ዙር ሸጠውለት በፋራ ሙድ ጉድ እንዳደረጉት ሁሉ ሰምቻለሁ፡፡

አሁን ባለፈው አመት የአዲስአበባና አጎራባች የኦሮሚያ ወረዳዎች የተቀናጀ እቅድ ሲወጣ የኦሮሚያ ወረዳዎችን ወደአዲስአበባ የሚጠቀልል ነው በሚል ተቃውሞ ሲሰማ ነበር፡፡ መንግስት ደግሞ አዲስአበባና አጎራባች ወረዳዎች በመሰረተልማት፣ በተፋሰስ፣ እና በፕላን የተቀናጁ እንዲሆኑ እንጂ አንዱ ሌላውን እንዲውጥ የታሰበ ነገር የለም ነው የሚለው፡፡ በርግጥም ይህንን የሚያስተባብል ማስረጃ እስከዛሬ አላጋጠመኝም ፡፡ ማንም ተራ ሰው መገመት እንደሚችለው የአዲስአበባ ፕላን ላይ የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ቢኖር የዚያ አጎራባች የሆነ የኦሮሚያ ወረዳ በፕላኑ እዚያ አካባቢ የመኖሪያ ሰፈር ሳይሆን የቆሻሻ ማስወገጃ ቢያቅድ ተጠቃሚ ይሆናል፤ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ አጎራባች ወረዳዎቹ ከአዲስአበባ ጋር የተናበበ እቅድ ካላቸው ብቻ ነው፡፡ በግሌ ይሄንን ልቃወም የምችልበት ምክንያት የለም፡፡Photo - Addis Ababa area slum

በሌላ በኩል የተቀናጀ እቅድ መኖሩ በራሱ የኦሮሚያ ወረዳዎችን በአዲስአበባ ስር ባያደርግም አላማው ለአዲስአበባ መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር በመሆኑ ይህ ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ አሁን ባይሆን እንኳ ዘግይቶ ወረዳዎቹ በአዲስአበባ መዋጣቸው አይቀሬ ነው፤ በመሆኑም የተቀናጀውን ፕላን ከወዲሁ ልንቃወመው ይገባል የሚሉም አሉ፡፡ ይሔ እውነት አለው፡፡ ነገር ግን መኪና ያላቸው ሰዎች ማስተር ፕላኑ ከመውጣቱስ በፊት ኦሮሚያ ክልል መንግስት በሊዝ መሬት እየተጫረቱም ከግለሰቦች እየገዙም ባለመሬት እየሆኑ አይደለም ወይ፡፡ለገጣፎና ቡራዩ ቀርቶ 45 ኪሎሜትር ርቀት ደብረዘይት እየኖሩ አዲስአበባ የሚሰሩ የ60 ቁትር አውቶብስ ደንበኞች የትየለሌ አይደሉም ወይ፡፡ በሌላ አነጋገር ማስተርፕላኑ ኖረ አልኖረ አዲስአበባ ውስጥ የቤት ባለቤት ለመሆን ወይም ደህና ቤት ለመከራየት ከሚያስፈልገው ገንዘብ ይልቅ በአጎራባች የኦሮሚያ ከተሞች ቤት ገዝቶ/ተከራይቶ እየተመላለሱ መስራት የተሸለ አማራጭ እስከሆነ ድረስ ይህንኑ አማራጭ ሰዎች እንዳይከተሉ ማድረግ እንችላለን ወይ፡፡ የምንችል አይመስለኝም፡፡

እዚህ ጋ ከተለየ አቅጣጫ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ሊደግፉት የሚችሉት አንድ ነገር አለ፡፡ አሁን ትግራይ ክልል ወይም አማራ ክልል ያሏቸውን ኢንዱስትሪዎች ብዛት አንዲት የኦሮሚያ ሚጢጢ ከተማ (ለምሳሌ ሰበታ ወይም ዱከም)ሊኖራት ይችላል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው እነኚህ ከተሞች ልዩ የተፈጥሮ ሀብት ስላላቸው ወይም በአገልግሎት አሰጣጥ የተሸሉ ስለሆኑ ሳይሆን የሐገሪቱ ብቸኛ የኢኮኖሚ ማዕከል አዲስአበባ በመሆኗ እና ኢትዮጵያን ብሎ እየመጣ ያለው ኢንቨስትመንትም በአዲስአበባና አዲስአበባ ዙሪያ የታጠረ ስለሆነ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ከሸዋ ኦሮሚያ በስተቀር ሌላው የሀገሪቱ ክፍሎች የልማቱ ተጠቃሚ ከሚባሉ የበይ ተመልካች ቢባሉ የሚቀሉ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ፌደራል መንግስት አሁንም ከየትኛውም አካባቢ በላይ አዲስአበባ የኢኮኖሚ እና የፈጣን እድገቱ ማዕከል ሆና እንድትቀጥል እየተከተለ ያለው አቅጣጫ አዲስአበባና አካባቢዋ በፈጣን የለውጥ አዙሪት ውስጥ እንዲገቡ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገትን እንዲያስመዘግቡ(በየቀኑ ለውጥ የሚታይበት እጅግ ፈጣን እድገት)፣ እሱን ተከትሎም ይህ እድገት በሚታይባቸው አካባቢዎች የዴሞግራፊ ለውጥ እንዲመጣ እያደረገ ነው፡፡ አሁን ከአንዳንድ የኦሮሞ ብሔርተኞች የምሰማው ዬተቀናጀውን ማስተር ፕላን ተቃውሞ በዋናነት ይህንን የዴሞግራፊ ለውጥ ካለመፈለግ እንደሚመነጭ እገምታለሁ(ሌሎች እኔ ያላወቅኳቸው ምክንያቶች ሊኖሩ ቢችሉም)፡፡ የሀገሪቱ ሌሎች ክልሎች(አካባቢዎች ብል ይቀላልከሸዋ ውጪ ያሉ የኦሮሚያ ዞኖችንም ለማካተት) ደግሞ አሁን ሀገሪቱ እያስመዘገበችው ያለው ልማት ፍትሃዊ አለመሆኑን በመጥቀስ በአዲስአበባ ዙሪያ የታጠረውን ልማት በመቃወም ከጎናቸው ሊሰለፉ ይችላሉ፡፡ በርግጥም ባለሀብቶቻችን ሌላ አካባቢ በነፃ(ቢበዛ 1ሚሊዮን ባልሞላ ብር) ሊያገኙ የሚችሉትን 444ካሬ ሜትር መሬት አዲስአበባ ውስጥ በ300 ሚሊዮን እስከመግዛት የደረሱት ሌላ አካባቢ ልማት ስለሌለ ነው፡፡ እንጂ የኢንቬስተር ያለህ ለምትለውና የካፒታል እጥረት ለሚያሰቃያት ሀገራችን ሌላ ቦታ በነፃ ሊገኝ ለሚችል መሬት 300 ሚሊዮን ማፍሰስ ለስንት ሺ ሰው የስራ እድል ሊፈጥር የሚችል ፕሮጀክት ማቋቋሚያን እንደማቃጠል ነው፡፡ከዚህ አንፃር የአዲስአበባን መስፋፋት(የኢኮኖሚ ሞኖፖሊ ማሳያም ስለሆነ ሌሎች የሐገሪቱ አካባቢዎች ቢቃወሙት የሚገርም አይሆንም፡፡

እንደኔ አይነቱ ደግሞ ከልማታችን ፍትሀዊ ያለመሆን ባሻገር ከተሞች እንደአዲስአበባ ሲለጠጡ ነዋሪዎች በየቀኑ እስከ3 ሰዓት ጊዜያቸውን በጉዞ እንዲያሳልፉ፣ ማህበራዊ ትስስራቸው እንዲላላ፣ ወንጀል እንዲበራከት፣ ባህል እንዲሸረሸር፣ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው የዋጋ ውድነት እንዲኖርና ነዋሪዎቹ ኑሯቸውን በቀላሉ እንዳያሸንፉ . . . . .ወዘተ ስለሚያደርግ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተሞች ቢበዛ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪ እንዲኖራቸው መበረታታት የለበትም ብሎ የሚያስብ እና የአዲስአበባ መስፋፋትንም ከዚህ አንፃር የሚቃወም ይኖራል፡፡ ስለሆነም አዲስአበባን፣ ድሬዳዋን፣ኮምቦልቻና ሀዋሳን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የወጠነው የፌደራል መንግስት አዲስአበባና አካባቢዋን ለቀቅ አድርጎ ሌሎች የሐገሪቱ ከተሞች ላይ እንዲያተኩርና የልማቱ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ማበረታታት አለበት እላለሁ፡፡

ለተለያየ አላማ በጋራ መቆም ማለት እንዲህ ነው፡፡

********

አዲስ ከድሬዳዋ - Frm. journalist; currently communicator

more recommended stories