አንድነት| እነበላይ ‘የምንጠራው ጠቅላላ ጉባኤ የለም’ ሲሉ – እነትዕግስቱ ለነገ ጉባኤውን ጠርተዋል

(ጥላሁን ካሳ)

በአቶ በላይ ፍቃዱ ቡድን የሚመራው የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትህ ፓርቲ/አንድነት/ ዛሬ በሰጠው መግለጫ የምጠራው ጠቅላላ ጉባኤ የለም አለ።

ጠቅላላ ጉባኤ አካሂጄ የፓርቲውን መሪ መርጫለሁ ሌላው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የከፈተብኝ ዘመቻ ነው ሲልም ነው የገለፀው።

ይህንንም የቦርዱን ዘመቻ ለመቃወም ለእሁድ ሰልፍ ጠርቻለው ብሏል። Belay Fekadu (left), Tigistu Awelu (right)

ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሁለት የተከፈሉት እና በእነ አቶ በላይ ፈቃዱ የሚመራው የአንድነት ቡድን ከነገ በስቲያ እሁድ አካሂደዋለሁ ያለውን ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄድ እንደማይችል ነው ዛሬ የገለፀው ።

የአስተዳደሩ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አሰግድ ጌታቸው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ቡድኑ ሰላማዊ ሰልፉን እንዳያካሂድ የተከለከለው ሰለማዊ ሰልፍ ሲካሄድ መሟላት ያለበትን አስፈላጊ ቅጽ ባለማሟላቱ ነው ብለዋል።

እንደ ሀላፊው ቅፁ የሚጠይቃቸው በሰልፉ ላይ የሚያዙ መፈክሮችን እና ሰልፉ ከየት ተነስቶ የት እንደሚጠናቀቅ የሚገልፁ መረጃዎችን ጨምሮ ሌሎች መሟላት የሚገባቸውን የሰላማዊ ሰልፍ ማካሄጃ መስፈርቶችን አላሟላም።

ከዚህ ቀደም መንግስት አስፈላጊውን የሰላማዊ ሰልፍ መመሪያዎች ተከትለው ለተንቀሳቀሱ ሰላማዊ ሰልፎችን የማካሄድ ፍቃድ መሰጠቱን የተናገሩት ሃላፊው፥ በእነ አቶ በላይ ፈቃዱ የሚመራው ቡድን የፊታችን እሁድ ለማካሄድ ያሰበው ሰላማዊ ሰልፍ ግን የወጣውን መመሪያ ያልተከተለ በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ የማይሰጠው መሆኑን ገልፀዋል።

ሌላኛውን የአንድነት ቡድን ወክላለው የሚሉ ግለሰቦች የእሁዱ ሰልፍ በአንድነት ፓርቲ ስም ሊካሄድ አይገባም ብለው በመቃወም ተፈራርመው ለአስተዳደሩ ማስገባታቸውንም ነው ሀላፊው የጠቆሙት።

ሌላኛውን የአንድነት ፓርቲ ቡድን በአሁን ወቅት በፕሬዚዳንትነት እየመሩ የሚገኙት አቶ ትእግስቱ አዎሎ በአቶ በላይ ፍቃዱ የሚመራው አንድነት የትኛው ህጋዊ መሰረት ኖሮት ነው ሰልፍ አካሂዳለሁ ያለው ሲሉ ይጠይቃሉ።

ትክክለኛው የአንድነት ፓርቲን የምመራው እኔ ነኝ የሚሉት አቶ ትእግስቱ አያይዘው ነገ ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራታቸውን ገልፀዋል።

በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ከመላው ሃገሪቱ የተውጣጡ ከ300 በላይ የሚሆኑ የፓርቲው አባላት በጉባኤው ላይ ይገኛሉም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የአንድነት ፓርቲ ከመከፋፈል ወደ አንድነት መጥቶ በጋራ ትክክለኛ የፓርቲው ውስጠ ደንብ መሰረት ምርጫ አካሂዱ በማለት ያስተላለፈውን መመሪያ በማክበር አቶ በላይ ፍቃዱን እንደራደር በማለት በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብላቸውም ሰሚ አጥተናል ብለዋል አቶ ትእግስቱ አዎሎ።

***********

ምንጭ፡- ፋና፣ ጥር 15-2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories