Book Review: የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ

(ታምራት ኃይሌ)The Case of the Socialist Witchdoctor

ርዕስ፡- የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ
ደራሲ፡- ሀማ ቱማ
ተርጓሚ፡- ሕይወት ታደሰ
አጭር፡- ሥነ ጽሁፋዊ ምልከታ
ገምጋሚ፡- ታምራት ኃይሌ

የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ The case of the Socialist Witchdoctor የ 22 አጫጭር ትረካዎች መድብል ሲሆን ትረካዎቹ በሁለት ክፍል ተለይተው ቀርበዋል፡፡ በክፍል አንድ አድራሻቸውን ፍርድ ቤት ያደረጉና በክስ መዝገቦች፤ በክርክሮች፤ በጥፋተኝነት ና በቅጣት ውሳኔዎች ላይ የተመሰረቱ አስራ አንድ ትረካዎች እናገኛለን፡፡ ትረካዎቹ አንድም አስራአንድም ናቸው፡፡ አንድነታቸውንም አስራአንድነታቸውንም በኋላ እመለስበታለሁ፡፡

በክፍል ሁለት እንደዚሁ አስራ አንድ ትረካዎች እናገኛለን፡፡ እንደመጀመሪያው በአንድ ቦታ የሚከናወኑ አይደሉም፡፡ ስለዚህ እነዚህን አንድም አስራ አንድም ናቸው ማለት ባይቻልም ፍጹም አይመሳሰሉም ደግሞ ማለት አይቻልም፡፡ በግድ አንድ ለማድረግ ሳይሆን፤ እንቅልፍ በሚያሳጣ ጸጉር ስንጠቃም ለመለያየት ሳይሆን በዚህ በሁለተኛው ክፍል ውስጥ ከተዘረዘሩት ትረካዎች መካከል በአንደኛው ማለትም “በሽብር ሚዛን አስር” መግቢያ ላይ የምናገኘው ኃይለ ቃል የቀሩትን ትረካዎች የጋራ ፍሬ ነገር በማስረዳት ረገድ ለጥቅስ የሚበቃ ይመስላል፡፡ እንዲህ ይላል፡፡

ትረካ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመራጭ የጊዜ ማሳለፊያ ቢሆንም፤አሁንም ጥቂት ተጠራጣሪዎች ከሰማኒያ በመቶ በላይ መሀይም ባለበት አገር ውስጥ ድሮም ሌላ አማራጭ ሊኖር አይችልም በማለት ይናገራሉ፡፡ ለማንኛውም በዕድሜ የገፉ ሰዎች የተካኑበት ትረካ በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ሁኔታ እንደተለወጠ የማይስማማ የለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ አሰቃቂዎቹና አስገራሚዎቹ ታሪኮች የሚተረኩት በሽማግሌና ባልተማሩ ሰዎች ሳይሆን በተማሩ ወጣት ካድሬዎችና መገናኛ ብዙሀን ተብሎ በሚጠራው አካል ነው፡፡በድሮ ጊዜ በአጠቃላይ ታሪኮች ለዘብ ያሉና ልጆችን ለማስፈራራት ያህል መጠነኛ ምትሀታዊ ጉዳዮች ያሉባቸው ነበሩ፡፡ ስለሚያወሩ ጥንቸሎች፤ስለሸረኛ ጦጣዎች ስለታላላቅ አናብስት፤ስለተንኮለኛ ጅቦች፤ የተለመደውን አጭበርባሪ እባብ ሳንረሳ በአጠቃላይ ጉዳት አልባ ታሪኮች ነበሩ፡፡

አሁን አሁን ግን አብዮቱ ምስጋና ይግባውና ታሪኮቹ ስለሰዎች ሲሆኑ ፈጣሪ የሚባል ከተጠቀሰ ያው ሰማያዊውን አምላክ የተኩትን እኚያን ምድራዊ ጥበበኛ ሰው ለመግለጽ ነው ማለት ነው፡፡ እሳቸውም ስማቸው የተባረከ ይሁን ሊቀመንበር ተብለው ይጠራሉ::(263)

ከአብዮት በኋላ ትረካ ተቀየረ ማለት ተያይዞ ሌላም ነገር ተቀይሯል ማለት ነው፡፡ ለውጡ ምን አይነት ነው አንድ ጥያቄ ነው፡፡ አለዋወጡ እንዴት ነው ደግሞ ሌላ፡፡ በዚህ የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ መድብል ሁለተኛው ክፍል ውስጥ የምናነባቸው አስራ አንድ ታሪኮች፤ በአብዮት ምክንያት ስለምናገኛቸው አዳዲስ አልፎ አልፎም እንግዳ የኅላዌ ሁኔታዎች(existential situations) ይነግሩናል፡፡ አያይዘውም እስከ አብዮቱ ዋዜማ የነበሩት የቀድሞ ኅላዌ ሁኔታዎች ምሰሶና ማገር የነበሩት ሕግጋት፤ ደንብ፤ ባህል፤ትውፊት፤ ነውር፤ የሙያ ስነ ምግባር ወዘተ፤ የአገልግሎት ዘመናቸው እንዳበቃ በአስደንጋጭ መልኩ ይተርኩልናል፡፡

የአብዮተኞች ሕልም በተለያዩ ምክንያቶች(ባለመታደል ወይ ባለመታገል ሊሆን ይችላል) ወደ ቅዠት የተቀየሩ እንደሆነ አዲሱና እንግዳው የኅላዌ ሁኔታ አስፈሪም አስደንጋጭም ይሆናል፡፡ የአብዮት ህልም ቅዠት ሲሆን የሰው ልጅ በተፈጥሮ አምባገነንነት ምክንያት ሳይሆን፤ በራሱ ውዴታና ግዴታ ከሞትና ከጥፋት ጋር በየቅጽበቱ ይፋጠጣል፡፡ በሁለተኛው የመድብሉ ክፍል ውስጥ የምናገኛቸው የበቀል፤የክህደት፡ የክፋት፡የጭካኔ፤ የተስፋ መቁረጥ ና የሰቀቀን ታሪኮች የአዲሱ ኅላዌ ሁኔታ መገለጫዎች ናቸው፡፡ እዚህ ላይ በቀል፤ክህደት፡ ክፋት፤ጭካኔ ተስፋ መቁረጥ ና ሰቀቀን በሰው ልጆች ህይወት ውስጥ ያሉ፤የነበሩና የሚኖሩ ናቸው ሊባል ይችላል፡፡ ለክርክር ማጠናከሪያም የተለመዱት የአቤልና የቃየል፤የኢየሱሰና የይሁዳ፤ የነብዩ መሀመድና የቁራይሽ አሳዳጆቻቸው ታሪክ በምሳሌነት ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ መጽሀፍ እንደምናነበው በቀል፤ክህደት፡ ክፋት፤ጭካኔ ተስፋ መቁረጥ ና ሰቀቀን ሰብሰብ ብለው፤እንደውም ተደራጅተው የምናገኛቸው የአብዮት ሕልም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ቅዠት ሲቀየር በሚፈጠረው አዲስ የኅላዌ ሁኔታ ውስጥ በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም አብዮት የሰው ልጅ ሕይወት ናሙና ነው ማለት ይቻላል፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ሰርቶ ማሳያ!

ሰብሰብ ብለው የምናገኛቸው እነዚህን የሰው ልጅ ክፉ ዕጣ ፈንታዎች ብቻ አይደለም፡፡ ከድርሰቱ ይዘት ሌላ ቅርጹም ራሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ አጫጭር የሆኑት ትረካዎች ቀልብ የሚስቡት ትንግርታዊ አጋጣሚዎች ተደራጅተው ታጭቀው ስለቀረቡ ይመስላል፡፡ ባለታሪኮቹ ብዙ ጊዜ ባልጠበቁትና በጠበቁት ሁኔታም ጭምር የቅርብ ሰዎቻቸው ዕጣ ፈንታ ይከተላቸዋል፤ ወይም ይከተሉታል፡፡ ድንገት በውድቅት በትንሳኤ ዋዜማ በህመምተኛ ቤት ዘው ያለ ሽምቅ ተዋጊ፤ሆስፒታል የቁስለኞችን ህይወት ታድጎ ለሌላ ዙር ግርፊያና ግድያ የሚያቀብል ሀኪም፤ የገዛ ልጆቹና ወዳጆቹ የአብዮት ዘመን ተቃርኖአዊ አሰላለፍ ውስጥ የገቡበት አባት ወዘተ፡፡ በትረካዎቹ ውስጥ ባለታሪኮቹ አፍንጫቸው ስር ባለው ጉድ ወይም እድል በመታጠራቸው ትልሞቹ ተለዋዋጭ፤ ያልተጠበቁና ወይም የሚጠበቁ ቢሆኑ እንኳን የሚቆረቁሩ ፍጻሜ አዝለዋል፡፡ በደፈናው በሁለተኛው ክፍል የተካተቱት አስራ አንድ ትረካዎች በአብዛኛው ጠላት ከሩቅ አይመጣም ይሉናል፡፡ ሰው ለሰውም ይላሉ፡፡ በዚህ መጽሀፍ የኢትዮጵያ ማህበራዊ ስነ ልቦና ሰብሰብ ተደርጎ ተጠርዟል፡፡

በሁለተኛው ክፍል ከተተረኩት አጫጭር ልቦለዶች አንዳንዶቹ ታሪክ ቀመስ ወይም በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን የሚጠቁሙ ምልክቶች ስላሉ፤ በፈጠራ ድርሰት ውስጥ በምናባዊነት ምክንያት አንድ ደራሲ ለወትሮ ይጎናጸፋቸው የነበሩ የደራሲ ልዩ ፈቃዶች(poetic licenses) መወሰናቸው አልቀረም፡፡ ትረካ ከሕይወት ቢቀዳም ካንድ ታሪካዊ ግለሰብ ገጠመኝ በቀጥታ ሲገለበጥ፤ በዚያ ላይ ደግሞ ኋላ ላይ እንደማወሳው የትረካዎቹ ዘውግ ፖለቲካዊ ሥላቅ ሲሆን ወጎቹ አከራካሪ ሆነው ስነ ምግባራዊም፤ ፖለቲካዊም ጥያቄ ሊቀርብባቸው ይችላሉ፡፡ እናም በእውን የነበሩ ሰዎችን ገጠመኝ የትረካው አካል በማድረጉ ድርሰቱ ለምን ዓላማ ተዘጋጀ የሚል ጥያቄ ሊነሳበት ይችላል፡፡

በመጀመሪያ ክፍል ስላሉት አንድም አስራ አንድም ትረካዎች እንመለስ፡፡ አንድ ያደረጋቸው መቸቱ ፍርድ ቤት መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይ ዝምድናቸው በትረካዎቹ ዘውግ ምክንያት ነው፡፡ ሁሉም ሥላቅ ናቸው፡፡ የፖለቲካ ሥላቅ! ያስቃሉ፤ ያዝናናሉ፡፡ ሥላቅ ከኮሜዲ በምን ይለያል? ጥያቄው ይሄ ነው፡፡ አስቂኝ ጥበባዊ ስራዎች ግባቸው ብዙ ጊዜ መነዝነዝ ሳይሆን ዘና ማድረግ ነው፡፡ ሥላቅ ግን ከሳቁ መልእክቱ ይበልጥብኛል ይላል፡፡ መሳለቂያው ግለሰብ፤መሳለቂያው ቡድን፤መሳለቂያው ተቋም፤ መሳለቂያው መንግስት ሊሆን ይችላል ብቻ መሳለቂያው በአድራጎቱ እና በጉራው መሀል ያለው ጭልጥ ያለ እፍረተ ቢስነት ታዛቢን ስለሚያናድድ መሳለቂያውን በአሽሙር፤ በቅኔ፤በሽሙጥ በማሳነስ እስከዶቃ ማሰሪያው ልክ ልኩን በመንገር እንዲታረም ማድረግ ነው፡፡ ታዲያ ሥላቅ ውስጥ ሳቅን ምን አመጣው ከተባለ፤ ማሽላ እያረረ ይስቃል ይላል ሀበሻ!

ሥላቅ በሰው ልጅ ነባራዊ ሁኔታዎች እና ኀሊናዊ ሁኔታዎች መካከል እርቅ ሳይኖር ሲቀር እንደሚከሰት ፈላስፎቹ ይነግሩናል፡፡ እሳት በሌለበት ጭስ እንዳይጨስ፤ ጉድለት በሌለበትም ሥላቅ የለም ሊባል ይችላል፡፡ ስለዚህ ከያንዳንዱ ፖለቲካዊ ሥላቅ በስተጀርባ ፖለቲካዊ ጉድለት አለ፡፡ በሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ የፖለቲካ ሥላቁ የሚጀምረው የደርግ መንግስት ነጻ እርምጃን ገንዘቡ በማድረግ የሽብርና የጭካኔ የተመሰከረለት ባለንብረት ሆኖ ሲያበቃ ፍርድ ቤት ያማረው፤ ሞራላዊ ፕሮፓጋንዳም የዳዳው ጊዜ ነው፡፡ አስራ አንዱ የክስ መዝገቦች፤አስራ አንዱ ክርክሮች፤ አስራ አንዱ ቅጣቶች አስራ አንዱ ትረካዎች የሚነግሩን ባለዲሞትፎር ድሮም ችሎት እንደማያምርበት ነው፡፡ ዳኛ አይተንፍሱ ሙጬ የጦር ሰራዊት ሻለቃ ነው፤ ከኦጋዴን መድፈኛ ክፍለ ጦር በሊቀመንበሩ ፍላጎት በቀጥታ በአንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ችሎት ላይ ተሰይሟል፡፡ ሥዩመ እግዚኣብሄር በሌለበት ያው ሥዩመ መድፍ ነው እየሰራ ያለው፤ሥዩመ ሕዝብ ገና ሩቅ ይመስላል፡፡ አቃቤ ህጉ ሲቪል ሲሆን፤ ተከላካይ ጠበቃው የጦር ሰራዊት መቶ አለቃ ነው፡፡ በትረካዎቹ መሳለቂያው ባብዛኛው የደርግ መንግስት ነው፡፡ የሰራውን ሰርቶ ሲያበቃ ያም ያነሰ ይመስል መድፍ ሥለተያዘ ብቻ ሊደረስበት በማይቻለው ሞራላዊ ማማ ላይ ለመውጣት የሚያደርገው ሙከራ ዋጋ ቢስ እንደሆነ፤ መዘባበቻም እንደሆነ፤ መታረምም እንዳለበት ታሪኮቹ ያስረዱናል፡፡

አስራ አንዱን ትረካዎች የፍርድ ቤት መቼትና የፖለቲካ ስላቅ ቢያዛምዳቸውም የየራሳቸው የኋላ ታሪክና ዕጣ ፈንታ ያላቸው አስራ አንድ ባለታሪኮች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ ቀበሌ ደጃፍ ባለማወቅ መሽናት ልክ በቤተ እምነት አካባቢ እንደመጸዳዳት ነውርም ወንጀልም ሆኖ ይተረካል፡፡ እንዲሁም አንድ ጀብደኛ ገራፊ የተገራፊዎቹ ቁጥር በማነሱ ብስጭት ገብቶት የፈጸመው ወንጀል ይነገረናል፤ የገራፊው ብስጭት ምሉዕ ይሆን ዘንድ ቅጣቱ የሱን ደንበኞች ቁጥር(ተገራፊዎቹን) ማሳነስ ነው! ለገራፊው ከዚህ በላይ ቅጣት የለምና ይቆረቁረዋል፤ያሳብደዋል፡፡ ምነው ቢባል በዘመኑ አዲስና እንግዳ የኅላዌ ሁኔታዎች(existential situations) ተፈጥረዋል፡፡ ሺህ ጊዜ እንግዳ የኅላዌ ሁኔታዎች ቢፈጠሩም ትረካዎቹ ግነት አያጣቸውም፡፡ ነገር ግን ግነት አንዱ የስላቅ ዘዴ ነውና እንታገሰዋለን፡፡ ግነት አላማው ጉድለቱን ማሳየት በዚያውም ሳቅ ማጫር እንጂ ጉድለቱን ማስፋት አይደለም፡፡

ደራሲው ሀማ ቱማ በዚህ የፖለቲካ ሥላቅ ትረካዎቹ በአብዮቱ ማግስት ስለተፈጠሩት የፖለቲካ ጉድለቶች ሲያሳየን እንደ ዲሞትፎር፤ እንደ መድፍ፤ እንደ ብር ሁሉ ቋንቋ ፤ትረካና ሞራል ኃይል ያላቸው መሳሪያዎች እንደሆኑ ያመላክተናል፡፡ ሚሼል ፎኮ የተባለ የሀያኛው ክፍለ ዘመን የፈረንሳይ ሊቅ ኃይል የትም ቦታ አለ፤እናም አደገኛ ነው ይላል፡፡ የእሱን እይታ ስንተረጉመው ኃይል በቤተመንግስት፤በጦር ካምፕ እና በባንክ ቤት ታጭቆ የመሰብሰቡን ያህል ሰው ባለበት ሁሉ ደግሞ ዘርዘር ብሎ ይገኛል፡፡ ቋንቋና ትረካ፤ ትረካና ሞራል እንዲሁም ሥላቅ በቀላሉ የሚታዩ ኃይል አይደሉም፡፡ እነዚህ የተቃውሞ መሳሪያ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ አብዮት የተለኮሰው ነባራዊና ሕሊናዊ ሁኔታ የተሟላ ጊዜ ነው ይላሉ አብዮተኞቹ፡፡ ለኅሊናዊው ሁኔታ መፈጠር የተማሪዎች እንቅስቃሴ ወሳኝ ቦታ ነበረው፡፡ ተማሪ በመጀመሪያ እና በአብዛኛው የታገለው በጽሁፍ ነበር፤ በቋንቋ! የበታች ወታደሮች ደግሞ እድሜ ለስራ ድርሻቸው ስልጣንን በዲሞትፎር ወሰዱ፤ በዲሞትፎርም ጠበቁት፡፡ ትንቅንቁ ቀጠለ፡፡ ሁሉም ባለው አጠቃ፤ ተከላከለም፡፡ ውጤቱ የታወቀ ስልሆነ አልዘረዝረውም፡፡ መጀመሪያ ላይ የነበረው በቋንቋ፤ በጽሁፍ የመታገል ነገር በኋላ ላይም ያባራ አይመስልም፡፡ የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ በፖለቲካ ሥላቅ ስርአቱን ላይ ርእዮተ ዓለማዊና ሞራላዊ ጥቃት የሰነዘረ ይመስላል፡፡ በመጀመሪያ ቃል ነበር ይላል መጽሀፉ፤ በመሀልም በመጨረሻም ጭምር አለ እላለሁ እኔ፡፡

ወደ መደምደሚያዬ ስመጣ ደራሲው በዚህ መድብል ውስጥ ያሉትን ትረካዎች ለአንባቢ ሲያቀርብ በአብዮቱ ማግስት ከተደረጉት፤ ከተነገሩትና ከተሰሙት እልፍ አእላፍ እውነተኛ ገጠመኞች ተነስቶ ስለሆነ የታሪክ ችግር አልገጠመውም፡፡በአመዛኙ ተራኪው ሁሉን አወቅ ሆኖ በየትረካዎቹ መግቢያና መውጫ ላይ ትዝብት አዘል አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ ዘመኑም ነገሮች የሚለዋወጡበት፤የሚገለባበጡበት፤ እንደ መብረቅ ብልጭታ ድንገተኛ፤ እንደነጎድጉድ ማስገምገም አስበረጋጊ የሚባሉ ፈጣን ድርጊቶች የበዙበት በመሆኑ ምክንያት ይመስላል ሴራው ቀርፋፋ አይደለም፤ ገጸባህሪያቱ ሁለት አይነት ናቸው፡፡ ወይ ወደው ወይ ተገደው እዚያ አዲስና እንግዳ የኅላዌ ሁኔታ ውስጥ የገቡ በመሆናቸው አንድም ባይተዋር አለዚያም ንቁ ናቸው፡፡ ባይተዋርነታቸውም ሆነ ንቁ ተሳታፊነታቸው የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸው ላይ ብዙም ለውጥ ያለው አይመስልም፡፡ በገጸ ባህሪዎቹ የመጨረሻ ዕድል መሰረት ስንመዝነው ድርሰቶቹ አሳዛኝ ሥላቅ(Tragic Satire) ሆነው ይደምደማሉ፡፡ በማጠቃለያ ምን ልንማር እንችላለን? በኔ ግምት ተራኪው “ሁኔታዎች በተቀየሩ መጠን ያው በፊት እንደነበሩት ናቸው” የሚለውን የፈረንሳዮች አባባል በይፋ እንደማይቀበል በግልጽ ቢያሰፍርም(ገጽ 263)፤በቀል፤ክህደት፡ ክፋት፤ጭካኔ ተስፋ መቁረጥ እና ሰቀቀን በአብዮት ማግስት ሰብሰብ ከማለታቸው በቀር በፊትም የነበሩ በኋላም አሉ፡፡ በሥላቁ ውስጥ ያለው የሥርአት ጉድለትም፤እንከንም፤መንጠራራትም ከቀዳሚው ጊዜ ምንም ለውጥ የለውም፡፡

***********

Guest Author

more recommended stories