"ካላገዝከን ወዮልኽ!" ብሎ ትግል የለም

የፖለቲካ እንቅስቃሴ፣ ሰላማዊም የትጥቅም፣ በባህሪው ትብብርን ይጠይቃል። ሕብረተሰብ በማሳትፍ የሚደረግ የትብብር ሥራ ነውና። የኢትዮጵያ ገዥ ጥምር ድርጅት አንድ አካል የኾነው ህወሓት የፈር ቀዳጅነት ሚናውን ወስዶ የዛሬ አርባ ዓመት በትግራይ በረኻዎች የትጥቅ ትግል ጀምሮ በሚያካሂድበት ጊዜ፣ “ተወዲቡ ብጽንዓት ዝተቓለሰ ይዕወት” (ሲተረጎም፣ ተደራጅቶ በጽናት የታገለ ለድል ይበቃል) የሚል መፎክር ከአነገባቸው መፎክሮች አንዱ ነበር። በነገራችን ላይ የህዝብ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ኢህአዴግ እንደ መንግስት ሀገር ሲመራ የተከተለው ህዝብን አደራጅቶ እና አስትፎ የመስራት ባህልም ከዚኽ መፎክር የተወረሰ ሳይኾን አይቀርም። ለዚህም ነው ኢህአዴግ ነጥሮ በመውጣት በትጥቅ ትግሉም ሀገር በመምራቱም ወቅት ውጤታማ ሊኾን የበቃው።

አሁን በፖለቲካው ተደራጅተው ሳይደራጁም እየተንቀሳቀሱ ያሉ የተቃውሞ፣ ሕጋዊ የኾኑትም ያልኾኑትም በዋናነት የዚኽ የተባብሮ መስራት ድክመት ስላለባቸው ነው ለውጤት ያልበቁት። ሲጣመሩ፣ ሲቀናጁም ኾነ ሲያብሩ፣ የአብሮ መስራት ምክንያታቸው የመላው ህዝብ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በፖሊሲ፣ ስትራቴጂ እና ፖለቲካዊ ፕሮግራም ነጥሮ የወጣ ፖለቲካዊ አቋም ይዘው መስዋእት ለመክፈል ተዘጋጅተው ሳይኾን በጥላቻ እና የስልጣን ጥም ብቻ መሰረት አድርገው ነው ወደ አንድ የሚሰባሰቡት። በዚኽ አካሔድ ደግሞ ጠብ የሚለ ውጤት አላገኙም። በተለይ ለመስዋዕትነቱ የሚመርጡት ሌላ አካል እንዲኾንላቸው ይፈልጋሉ። እነሱ በአቋራጭ ስልጣን ላይ ለመፈናጠጥ እንዲያስችላቸው።

ከዚኽ አንጻር የሀገራችን ተቃዋሚዎች ትጥቅ ትግል አውጀው በሕገ ወጥ ድርጊት የተሰማሩት እና በስመ አክቲቪዝም የሚከትሏቸው (ሁለቱንም መንገድ የሚያጣቅሱ ቡድኖች) እንዲኹም በሰላማዊ ሕጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱት በተደጋጋሚ የመተባበር እና ለህዝብ መስዋዕት የመኾን መሰረታዊ ባህሪ ስለሚጎድላቸው እና የስልጣን ጥማቸው በአቋራጭ ማርካት ስላልቻሉ፣ ሌሎች አብረዋቸው ባለመታገላቸው ለውድቀታቸው እንደ ሰበብ ያስቀምጣሉ። የ “ካላገዛችሁን” አባዜ ላይ ይንጠላጠላሉ። አሁን አሁን እየወደቁ ያሉት ህዝብ ሊያግዛቸው እንዳልቻለ በመግለጽ በዚኽ ሊያግዛቸው የሚገደድ ህዝብ ላይ በግልጽ ዛቻ እና ስድብ ጭምር የታከለበት ድንፋታ እንደ አንድ የትግል ስልት ይዘው ብቅ ብለዋል።

እንደ ልምድ የሀገራችን ተቃዋሚዎች፣ ከኢህአዴግ በተለያዩ ምክንያት የተሰናበተን ሰው ቀርቦ አብሯቸው እንዲሰራ መማጸን ባህላቸው አድርገው ከቆዩ ሰንብተዋል። አሁን ግን ህዝብ እየተጠየቀ ነው። “ካላገዝከን ድል ልናደርግ አንችልም!” እያሉ ነው። ኢህአዴግን መደገፍ ብቻ ሳይኾን ካለ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ገለልተኛ ኾኖ የሚኖረው ህዝብ ሳይቀር ወደኛ ተቀላቅለኽ “ካላገዝከን” ወዮልኽ! እያሉት ነው።

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአንድ ወቅት ከምርጫ ጋር በተያያዘ በሰጠው ቃለ ምልልስ “የትግራይ ህዝብ መቶ በመቶ እየመረጠ ምን ዋጋ አለው። ትግራይ ምርጫ 100% ነው። ይህ ደግሞ ምርጫ ሊባል አይችልም።” በማለት ነበር የህዝቡ ምርጫ ስሕተት እንደኾነ ሊያስረዳ የሞከረው። ፕሮፌሰሩ በመቀጠል “የትግራይ ህዝብ ነጻ ሳይወጣ ሌላ ኢትዮጵያ ነጻ ይወጣል ማለት ደግሞ ዘበት ነው። ይኽ ጀግና ህዝብ ወያኔ ጠርንፎ ይዞታል።” በማለት ደግሞ ለ “ካላገዝከን” የትግራይን ህዝብ አጬት። ምርጫውን እንኳ ሳያከብሩለት ማለት ነው። በአክቲቪዝሙም በትጥቅ ትግሉም የፕሮፌሰሩ ደቀ መዛሙርት የኾኑት ደግሞ “የትግራይ ህዝብ ወያኔን ሙሉ በሙሉ ይደግፋል። ወያኔ የትግራይ ህዝብ ድጋፍ ባያገኝ ስልጣን ላይ አይቆይም ነበር። ስለዚህ ትግራይ ወያኔን ለመጣል ሊያግዘን ይገባል!” በሚል የካላገዛችሁን መፎክሩ ገፉበት።

በአንድ ወቅት በዲሲ ከተማ የሚኖር አንድ የሻዕቢያ ደጋፊ ኤርትራዊ ጋር እያወጋን “እነዚህ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች እናንተ ካላገዛችሁን ወያኔን አንጥለውም። ልታግዙን ይገባል ይላሉ። እኛ መስዋዕት እንድንከፍልላቸው ይፈልጋሉ። ትጥቅ ትግል ብለው አውጀው ሲያበቁ ነገር ግን መዋጋት አይፈልጉም። ፕሮፓጋንዳ ብቻ ይወዳሉ። እነሱ ዶላር አዋጥተው ሊሰጡን እኛ እንድንዋጋላቸው ነው የሚፈልጉት” ብሎኛል። ስልጣን በአቋራጭ ይሉታል ይኽ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ ከዚኽ የ”ካላገዛችሁን” ለቅሶ ጋር በተያያዘ ሄኖክ የሺጥላ የተባለ ገጣሚ የመፎክሩ ፊታውራሪ እንደኾነ ከወዳጄቼ ጽሑፎች ለመረዳት ችያለኹ። በለቅሶ የሚቀየር ነገር ያለ ይመስል። አንድን ህዝብ በጥላቻ ፖለቲካ ልፈፋ ቀን ተለሌት እየዘለፉ “ካላገዘን” ብሎ ነገር የለም። የጠላኸው ህዝብ ሊደግፍኽ አይችልምና። የፖለቲካ ትብብሩን የሚወደውን ቢደግፍበት ያተርፍበታል። እንዲሁም መሰረታዊ ጥላቻ የተጠናወተው የፖለቲካ ስብስብ ድጋፉን የሰጠ ህዝብ እስከዛሬ አላየንም።

መፍትሔው ከጥላቻ ፖለቲካ አዙሪት መውጣት ነው። “ካለገዛችሁን ነጻ አንወጣም” የሚባል ስሌተም አይሰራም። ተባብሮ መስራት ትግሉም ውጤቱም የጋራ ነው። መስዋዕትነቱም ፍሬውም እኩል። እየጠሉ የነጻነት ትግል ብሎ የለም። የፖለቲካ አክቲቪዝም መሰረቱ ጥላቻ ግቡ ደግሞ በአቋራጭ ስልጣን ከኾነ፣ ትብብሩ አይኖርም ድልም አይገኝም። ሰላም።

*********

Alula Solomon

more recommended stories