ዕለቱ 9ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን እና የሕገ-መንግስታችን 20ኛ የልደት በዓል የሚከበርበት ህዳር 29፤ ቦታው ደግሞ ለዚሁ በዓል ተብሎ በፍጥነት እንዲደርስ የተደረገው የአሶሳ ከተማ ስቴድየም ነው፡፡

የኢ.ፌ.ድሪ ጠቅላላ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፣ የፌደሬሽን እና የሕዝብ ተወካዮችን ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎች፣የጎረቤት ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስቴሮች፣ የውጭና የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች፣ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የባህል ቡድኖች…ብቻ ምን አለፋችሁ ኢትዮጵያ በስቴድየሙ ከትማለች፡፡

በዓሉ ሰፊ፣ ደማቅና ብዙ ሊባልለት የሚገባ ነበር፡ ስለዚህ ሌላው በይደር ይቆየንና ለዛሬ አንድን ለየት ያለ ክስተት መርጨ ላውጋችሁ።

NNPD Constitution day mishap 6 

ለበዓሉ ከታቀዱት ትርኢቶች አንዱ፣ ለ26 ቀናት ሀገሪቱን በመዞር ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 204 ሚልዮን ብር የሰበሰበው እና ከታላቁ መሪ ለኢትዮጲያ ብሔር ብሔረሰቦች የተበረከተው የህዳሴ ግድብ ዋንጫ፣ ግድቡንም በአሉንም ወደምታስተናግደው የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ዋና ከተማ መግባት ነበር፡፡ ዋንጫው ወደ አሶሳ ስቴድየም እንዲገባ የታሰበውም ለየት ባለ መንገድ ነበር፤ በሄሊኮፕተር ከሰማይ።

በእርግጥ ይህ ለየት ያለ አቀራረብ የታሰበለትን በአሉን የማድመቅ ግብ መትቷል ፡፡ ግቡን የመታው ግን አዘጋጆቹ ባሰቡት መንገድ አልነበረም። ታሪኩ እንዲህ ነዉ።

አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፡ የሚመራውን ቡድን በመያዝ የስቴድየሙን መሀል ከተቆጣጠረ የቡድኑን 26 ቀን ሀገር አቀፍ ጉዞ በሰፊው መተረክ ከመጀመሩ ነበር ዋንጫውን ያዘው የመከላከያ ሄልኮፕተር በድንገት ከተፍ ያለው፡፡

ሄልኮፕተሩ ወደ ሜዳው መሀል ጉዞውን ቀጥሏል፤ ሰራዊት ፍቅሬም ትረካዉን። ሄሊኮፕተሩ ወደ መሀል እስኪደርስ የተነቃነቀ ሰው አልነበረም፣ ቀጥሎ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የገመተ የነበረም አይመስል። ልክ ሄልኮፕተሩ ሜዳው መሀል ደርሶ ከፍታ መቀነስ ሲጀምር ነበር ከእርሱ በፍጥነት መራቅና ከሚያስነሳው ሃይለኛ የአቧራ ማዕበል ማምለጥ እንደሚገባ ለሁሉም ግልጽ የሆነው ፡፡

ከዚያማ በሜዳው መሀል እና ዙሪያ ቆመው የነበሩት የኪነጥበብ እና ሚዲያ ባለሙያዎች በቀረባቸው አቅጣጫ ያደረጉት ሽሽት በትረቡን ለተቀመጠው ታዳሚ አዝናኝ ትርኢት ሆኖ ነበር ፡፡ ማዝናናቱ ግን ብዙም አልቆየ።

ሄልኮፕተሩ ወደ ታች መውረድ ቀጠለ፣ በስቴድየሙ ከሚገኘው ውስጥም ከሄልኮፕተሩ ቁጣ የሚያመልጥ አንድስ እንኳን እንደማይኖር ታየ፡፡ መላው ታዳሚ ፊቱን ከአቧራ ማዕበል ለማትረፍ ከመጣርና ሄልኮፕተሩ ዋንጫውን አውርዶ እስኪሄድ በትግስት ከመጠበቅ ውጭ አማራጭ አልነበረውም ፡፡ (እዚህ ጋር “መላው ታዳሚ” ስል ጠቅላያችንንና ክብርት ባለቤታቸውን ጨምሮ መሆኑ እየተስተዋለ)

premier Hailemariam NNPD Constitution day mishap 3

እንግዲህ ይህ ሁሉ የሆነው በሁለት ደቂቃ ከ23 ሰከንድ ውስጥ ነው። የአቧራውን ድብደባ የቀመሰ ሰው አግኝታችሁ ከ23 ደቂቃ እንደማያንስ ምሎ ተገዝቶ ቢነግራችሁ ግን አይግረማችሁ፣ ቀላል አቧራ አልነበረም። የእናንተው ዘጋቢ ገና በጊዜ ስትራቴጅክ የሆነ ቦታ መርጦ፣ ገዥ መሬት ይዞ እና ደረቱን ለአቧራ ማዕበል ሰጥቶ ነው ይህንን ታሪካዊ ትዕይንት ለእናንተ በምስል ያስቀረላችሁ፡፡ (ይህን መስመር መልሼ ሳነበው ስለመሀመድ አሚን የማወራ መሰለኝ እኮ) ወደ አቆምኩበት ልመለስ።

መቼም አያልቅ የለም የነውጠኛው ሄልኮፕተር ስራም አለቀ፡ ዋንጫውም ከሥር በሚጠባበቁት ሶስት ሰዎች እጅ ገባ። ሄልኮፕተሩም መላ ሜዳውን እንደ ምግብ ጠረጴዛ አጽድቶ፤ ታዳሚውን አቧራ አልብሶ ስቴድየሙን ለቀቀ። ከዚያማ የኪነ-ጥበብና የሙዲያ ባለሙያዎች ወደ ቦታቸው በመመለስ ታዳሚውም ልብሱን በማራገፍና ከአይኑ ውስጥ አቧራ በማውጣት ላይ ተሰማራ (ጠቅላያችን አይናቸውን ከአቧራ ሲያጸዱ የሚያሳይ ምስል የእለቱ ምርጥ ዘጋቢ በነበረችው የሬድዬ ጋዜጠኛ ሰላም ተሾመ ቀርቦላችኋል) ፡፡

እዚህ ጋር የሄልኮፕተሩ አብራሪ እየፈጠረ ያለውን ረብሻ ተገንዝቦ ወደታች ዝቅ ማለቱን ለምን አላቆመም? የዝግጅቱ አካል የነበሩ የመከላከያ ሰዎችስ ሄልኮፕተሩ ከህዝቡ መካከል ሲወርድ ሊፈጠር የሚችለውን ሁከት እንዴት መገመት ተሳናቸው? “ወታደር” እንደነበር በኩራት የነገረን አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬስ ሁኔታውን ገምቶ ቡድኑን ለምን በግዜ ከሜዳው አላራቀም? እና መሰል ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል። ይሄ ግምገማ ለዝግጅቱ አዘጋጆች የቤት ስራ ይሁንና ወደ በአሉ እንመለስ።

ከሁሉ የሚገርም የነበረው የሄልኮፕተሩ የስቴዲየም ላይ ነውጥ የበዐል ዝግጅቱን ማድመቁ ነበር። እንዴት?

የአቧራ ማዕበሉ በእረጃጅም ንግግሮችና በማስ ስፖርት ትዕይንቱ ተፋዞ የነበረውን ታዳሚ ያነቃቃ እና ፈገግታን ያላበሰ ሆነና አረፈው። ከተከታዩ ያማረ የብሔር ብሔረሰቦች የባህልና አልባሳት ትዕይንት ጋር ተደምሮ ከአቧራው በኋላ የነበረው የበዐሉ ድባብ ከአቧራው በፊት ከነበረው ይልቅ የደመቀ ሆኖ ነበር፡፡

the mood after the NNPD Constitution day mishap

የበዐሉ ትልቅነት እና የጋራችን መሆን በተለይ በተለይ ሄሊኮፕተሩ ያመጣው አቧራ ብቻ ሳይሆን የታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋንጫንም መሆኑ ለድምቀቱ መጨመር በምክንያት ሊቀርብ የሚችል አንድ መላምት ይመስለኛል፡፡ ዓላማዬ እናንተን ማውጋት እንጂ ትንታኔ ባለመሆኑ ብቸኛውን የፎቶ እና የቪድዮ ማስታወሻ በመጋበዝ ልሰናበታችሁ።

በኢትዮ ቴሌኮም ምርጥ የአገልግሎት አሰጣጥ ምክንያት ከቦታው በጊዜው ለማለት ብዘገየም ከመቅረት ይሻላልና እንኳን ለ20ኛው የሕገ-መንግስታችን የልደት በዓል አደረሳችሁ እላለሁ፡፡

———–

Video

*******

Fetsum Berhane is an Ethiopian resident, economist researcher and a blogger on HornAffairs.

more recommended stories