በክፍል አንድ ፅሑፌ (አጀንዳ ኤርትራ | ላለፈው ክረምት ቤት አይሠራም!) አቶ ገብሩ አስራት የህወሓት አመራር በትጥቅ ትግሉ ጊዜ በኤርትራ ጥያቄ ላይ በወሰዳቸው አቋሞች ላይ ያቀረቡዋቸውን ትችቶች በማስመልከት አንድ ሁለት ብያለሁ። ለዛሬም በሁለቱ ሀገራት በቅርቡ ስለተካሄደው ጦርነት ላይ በሰነዘሩዋቸው ነቀፌታዎች ዙሪያ የምለው አለኝ። ሁለተኛው ለሉአላዊነት መደፈር ምክንያት ሆኖ የቀረበው ጉዳይ በኤርትራ ወራሪነት በቅርቡ ያደረግነውን ጦርነት የሚመለከት ነው። ይኸውም እሳቸው ሻዕቢያ ሊወረን እንደሚችል በተደጋጋሚ ሃሳብ ማቅረባቸውንና በመንግስት በኩል በተለይ ደግሞ በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሰላ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ውሎ አድሮ ግን የፈሩት ነገር መድረሱን ይነግሩናል። ሲያክሉም የመለስ ዜናዊ ተቃውሞ ተራ የትንታኔ ስሕተት ሳይሆን ለሳቸው(ለገብሩ አስራት) ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ሁሌ ለኤርትራ ያሳዩት ከነበረው “መቆርቆር” የሚመነጭ እንደሆነ ያብራራሉ። በሳቸው እምነት ለድርድር ያጠፋነውን ጊዜ አላስፈላጊና አጨራረሱም የኢትዮጵያን ጥቅም ያላስከበረ እንዲሁም መንግስት “ሻዕቢያን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ” የነበረውን እቅድ ጋር ፈፅሞ እንደማይጣጣም ነው። ባጠቃላይ መንግስት(ትችታቸው ባብዛኛው በመንግስትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ያጠነጠነ ነው) የኢትዮጵያን ጥቅሞች አሳልፎ መስጠቱን እንዲሁም በወቅቱ በነበረን የበላይነት የአሰብን ጉዳይ የመደራደሪያ ዋና ነጥብ ሆኖ አለመቅረቡ ትልቅ ስህተት እንደነበረ ጭምር አክለው ይከሳሉ። ወደ ዝርዝር ክሶቹ ከመግባቴ በፊት ከያኔው የሽግግር መንግስት ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ባህሪያት እንዲሁም ሀገሪቱ ከነበረችበት ኢኮኖሚያዊ ማጥ የሚመነጩ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች በሰራዊቱ ዝግጁነት ላይ ያስከተሉዋቸው ተፅእኖዎች ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

የያኔው የኢህአዴግ ሰራዊት ከሐምሌ 1 ቀን 1983 ዓ/ም የሽግግር መንግስቱ የመከላከያ ሃይል እንዲሆን ቻርተሩ ሲፈቀድ ሀገሪቱ የሰራዊቱን ደመወዝ እንኳ መክፈል የሚያስችል ዓቅም እንዳልነበራት ስለሆነም ሰራዊቱ ለአራት ተከታታይ ወራት ምንም ሳይከፈለው እንዲያገለግል መደረጉ ገብሩ አስራት አበክረው ያውቃሉ። ከዚሁ ሌላ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የታጠቀ ሃይል የነበራቸው የፖለቲካ ድርጅቶች የነበሩ ሲሆን ደርግ ሲወድቅ ካስመዘገቡት ቁጥር ውጪ ሌላ ሀይል መጨመር በህግ የማይፈቀድላቸው ነበር። ይህ ግዴታ የመከላከያ ሰራዊት ሃላፊነት የወሰደው የኢህአዴግ ሰራዊትንም የሚመለከት ነበር። ስለዚህ የሽግግር መንግስቱ ቻርተር የስልጣን ዘመን አብቅቶ በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት እስከተተካበት 1988 ዓ/ም መባቻ ድረስ የሰራዊቱን ቁጥር ለመጨመር የሚያስችል ህጋዊ መሰረት አልነበረም። ይልቁንስ በትጥቅ ትግሉ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸውና በአዲሱ የሰራዊት ግንባታ መመዘኛዎች(አብዛኛዎቹ አካላዊ)ሊያሟሉ ያልቻሉ ብዙ ታጋዮች በመቀነሳቸው ምክንያት ጦርነቱ በታወጀብን ጊዜ የሰራዊቱ ቁጥር ከሃምሳ ሺህ የማይበልጥ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ።Image - Gebru Asrat Book

የሰራዊቱ የዝግጁነት ችግር ግን የቁጥር ጉዳይ ብቻ አልነበረም። በአካል፣ በስነልቦና እንዲሁም በቴክኒክና ሎጂስቲክስ ረገድ ሲታይ ደርግን በጣለበት ጊዜ የነበረውን ያህል አቅምና ቅርፅ እንኳ አልነበረውም። አመዛኙ የጊዜው የመከላከያ ስትራተጂና የጠላት ትንተናም ከአጭር ጊዜ አኳያ ከውስጥ ሸማቂዎችና ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች የዘለለ ጠላት እንደማይገጥመን የሚያመላክት ነበር። ከረጅም ጊዜ አንፃር ደግሞ ኢትዮጵያ እያደገች ስትሄድና የተፈጥሮ ሃብቷ መጠቀም ስትጀምር ጥቅማቸው የሚጎዳባቸው ወይም የሚጎዳ የሚመስላቸው ወገኖች ብቅ ብቅ ሊሉ እንደሚችሉ ስለሆነም የዚሁ እድገትና ስጋት ነፀብራቅ የሆነ የሰራዊት ቁጥር፣ ዓይነትና ትጥቅ በቀጣይነት እየተገነባ እንደሚሄድ የሚያስረግጥ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም።

በፖለቲካው ረገድም የተለያዩ ፍላጎቶችንና ዓለማዎችን ያነገቡ የፖለቲካ ድርጅቶችን አቻችሎ በሽግግሩ መንግስት ማዕቀፍ እንዲቆዩ ለማድረግ ከፍተኛ ትእግስትና ብልሃት የሚጠይቅ ወቅት ነበር። በኤርትራ በኩልም ወደ ኢኮኖሚያዊ ቀጥሎም ፖለቲካዊ ትስስር ሊመሩን ይችላሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ስምምነቶችንና መቀራረቦችን ተደርጓል። ከስምምነቶቹ አንዱ ከኤርትራ ጊዜያዊ መንግስት ጋር የተደረገውን የጋራ የመከላከያ ቃልኪዳን ይገኝበታል። የዚሁ ቃልኪዳን ዓላማም ከአጭር ጊዜ አኳያ በገቺነትና ሁለቱ መንግስታት ውጫዊ አደጋዎች የሚያጋጥሟቸው ከሆነ ደግሞ ኢኮኖሚዎቻቸው በተናጠል ሊሸከሙዋቸው የማይችሉትን ሰራዊቶች መገንባት ሳያስፈልጋቸው በነበራቸው ሃይል በጋራ መመከት እንዲችሉ ታስቦ የተገባ ስምምነት ነበር። በዚሁ ስምምነታቸውም ለተወሰኑ ዓመታት ዘልቋል።

ከዚሁ መልካም የሚመስል ስምምነትና መስተጋብር ጀርባ ግን ብዙ የተተበተቡ ስንክሳሮች ነበሩ። በወደብ አጠቃቀም፣ በንግድ ግኑኝነት፣ ያልለየላቸው ኢኮኖሚያዊና የወሰን ጉዳዮች፣ እንዲሁም የሻዕቢያ ስውር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በዋንኛነት ይጠቀሳሉ። ሻዕቢያ ባህሪውን የሚመጥኑ እጅግ የወረዱ ስዉር ተንኮሎች ሲፈፅም በኢትዮጵያ በኩል የነበረው አያያዝ ለብዙ ሰዎች አስደሳች ነበረ ማለት አይቻልም። አስደሳች አይሁን እንጂ ስሕተት ለዛውም ለኤርትራ ከማዳላት የሚነሳ ስሕተት ግን አልነበረም። ይልቁንስ የሁለቱ ሀገራት ፍቺ ከመወሳሰቡ የተነሳ የተከሰተ ነባራዊ ችግር ነው ብዬ አምናለሁ። ፖለቲካዊ መፍትሔው በሪፈረንደም ይቋጭ እንጂ እልባት ያልተደረገባቸው የበዙ አጀንዳዎች ነበሩ። ለምሳሌ ገብሩ አስራት ካነሱዋቸው ነጥቦች ኢትዮጵያ “በጠ/ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ብቻ” ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሃብት በላይ የሆነ ብር ለኤርትራ መሰጠቱን አንዱ ነው። እሳቸውና ጓደኞቻቸው ምን ሲያቦኩ ያን ያህል ክብደት የነበረውን ጉዳይ ጠ/ሚኒስትሩ “ብቻቸው” እንዲወስኑ ፈቀዱ የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው ወደ ጎን ትተን ኢትዮጵያ ውስጥ ከነበረው ገንዘብ መጠን በላይ ኤርትራ ውስጥ ነበረ ማለታቸው ውሃ የማይቋጥር የተሳሳተ መረጃ ነው። እንደዛም ሆኖ ኤርትራና ኢትዮጵያ ይፋዊ የሃብት ክፍፍል አላደረጉም። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ስትዋሃድ የነበራትን ሃብትና ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ስትለያይ ሊኖራት የሚገባት ሃብት መጠን ያሰላው አካል የነበረ አይመሰለኝም። ጠ/ሚ መለስም ስለተጠቀሰው ገንዘብ ጉዳይ በወቅቱ ተጠይቀው በተደጋጋሚ ማብራሪያ መስጠታቸውን አስታውሳለሁ። አጠቃላይ የመልሶቻቸው መንፈስም በወቅቱ በኤርትራ በኩል የተነሳ የሃብት ድርሻ መከፋፈል ሐሳብም ሆነ ፍላጎት አለመኖሩን ነገር ግን የራሷውን ምንዛሪ እስክታትም ድረስ የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ እንድትጠቀም መደረጉን እንዲሁም ወደ አንድ ቢልዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ(የኤርትራን የጊዜው ሀገራዊ ምርት የሚመጥን) ለኤርትራ መሰጠቱ ተገቢ መሆኑን የሚያስረግጥ ነበር። የኋላ ኋላ ይህ ገንዘብ ኤርትራ የራሷን ናቅፋ ማሳተምዋ ተከትሎ ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሪ እንድትገዛት ጠይቃ አሉታዊ ምላሽ በማግኘቷ ለጦሩነቱ መጀመር እንደ አንዱ ግብአት ማገልገሉ ይታወቃል።

ሌላው በተደጋጋሚ ያነሱት ክስ ሻዕቢያ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ስውር ደባውን በሚፈፅም ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት አይቶ እንዳላየ ያልፈው ነበረ የሚለውን ነው። ይህ አባባል ከላይ ሲታይ እውነት ቢመስልም ውስጡ ሲመረመር ግን የሂደቱን ውስብስብነት ያልተረዳ ደካማ አመዛዘን ነው። ወቅቱ የኢትዮጵያውያን የወደቦች “አባዜ” ያልለየለትና ኢህአዴግ ላይ ከቅርብም ከሩቅም አክራሪው የግሉ ሚዲያ ጨምሮ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይደርስ የነበረበት ወቅት ነበር። የወቅቱ የኢህአዴግ መንግስትም ከምንም ነገር በላይ ኤርትራ ነፃ ሃገር በመሆኗ ምክንያት በወደቦች አጠቃቀም ላይ የጎደለብን ነገር እንደሌለ ለማሳየት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ከሻዕቢያ በኩል ተገቢ ያልሆኑ ባህሪያት ቢያነብም ይፋዊ ባልሆነ መንገድና ጥንቃቄ በተሞላበት አኳሃን ችግሮቹን ለመፍታት ከመጣሩም በላይ ግንኙትነቶች ከሚያባብሱ እርምጃዎች ለብዙ ጊዜ መቆጠቡን በተደጋጋሚ ገልፀዋል። ይህንን ተገቢ ያልሆነ ተፅዕኖ በውል የተረዳው ሻዕቢያም ኢትዮጵያን ከሁለት ወገኖች የተፈጠረውን እፍጋት ተገን በማድረግ ፍላጎቱን ያለ ከልካይ እንዲያተራምስ ከፍተኛ ጉጉት ሊያሳድር ቻለ። ኢትዮጵያውያን ለወድቦች የነበራቸው ያልተገባ ግምት ለሻዕቢያ ነውረኛ ባህሪያት መባባስ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል የሚል ግምት አለኝ።

ይህ ሁሉ ሆኖም ከኢትዮጵያ በኩል ለጦርነት መንስኤነት የሚያበቁ ምክንያቶች ነበሩ ማለት አይቻልም። ስለዚህ ጦርነቱ በመደበኛው አገላለፅ ኢምክንያታዊ(uncaused) የሚሉት ዓይነት ነው። በኔ አተያይ የችግሩ ምንጭ ሻዕቢያ ኤርትራን ነፃ ያወጣበት የትግል ሂደት ላይ የነበረው የተሳሳተ ግምገማና እስካሁን በዘለቀው መደበኛ ኢኮኖሚን የሚጠላ አካሄድ የወለደው ነው። በፖለቲካው ረገድ ሻዕቢያ ኤርትራ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም ነፃ እንዳወጣ ያምናል። የኢህአዴግ ተሳትፎ ሰልፍ ለማሳመር ከተደረገ መጠነኛ ሙከራ በላይ ተመልክቶት አያውቅም። እንዲያውም ኢህአዴግ ይዞት የነበረ ጥንካሬ ያህልም ቢሆን የሻዕቢያ ቀጥተኛ እጅ ያረፈበት እንደሆነ ያምን ነበር። ህወሓት/ኢህአዴግን በተሳሳተ አኳሃን ሲገመግም ሻዕቢያ የመጀመሪያው አይደለም። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የፖለቲካ ሃይሎች በተሳሳተ የህወሓት/ኢህአዴግ አገማገማቸው የተነሳ ተረት ሆነው ቀርቷል። ሻዕቢያ ግን ከራሱም ሆነ ከሌሎች ስህተት የሚማር ሃይል ሆኖ አልተገኘም። ከሱ ከአስር እጥፍ በላይ የሆነ የህዝብ ቁጥር፣ የመሬት ስፋት፣ በተነፃፃሪ የተሻለ ኢኮኖሚ እንዲሁም የውጭ ወረራን አሜን ብላ የማስተናገድ ታሪክ የሌላት ሀገር ለመውረር የበቃበት ምክንያትም ከዚህ ስር የሰደደ በሽታው በመነሳት ነው። የኢኮኖሚ አያያዙም ሲታይ ዱሮ ሳህል ውስጥ ከነበረው አሰራር ፈቅ ያለ አይደለም። እንዲያውም ይባስ ብሎ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርንም እንደ አንዱ የኢኮኖሚ ዘርፍ የሚመለከት ነውረኛ መንግስት ወጥቶታል። ስለሆነም ነው መደበኛና በመንግስታት መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት ችላ ብሎ በተለያዩ ሴራዎች መሳተፍ እንደተሻለ አማራጭ ውስዶ የኢትዮጵያን መንግስት ተደጋጋሚና ቅን ጥረቶችን ሊያመክን የቻለው።

እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ችግር የያኔው የኢህአዴግ አመራር (ገብሩን ጨምሮ) ሻዕቢያን “አውቀዋለሁ” የሚለውን ያህል የሚያውቀው እንዳልነበረ ነው። ሻዕቢያ ትዕቢተኛ የመሆኑን ያህል መሰረታዊ ጥቅሙን አንጥሮ መለየት የማይሳነው ሃይል ተደርጎ ነበረ የሚታየው። በተጨባጭ የሆነው ግን ግልባጩ ነው። ሻዕቢያ መሰረታዊ ጥቅሞቹን መለየት እስኪሳነው ድረስ የታወረና በፈቃደኝነቱ እራሱን ለማጥፋት የወሰነ ሃይል ሆኖ ተገኘ። ስለዚህ ጦርነቱን ለማስቀረት የሚቻልበት ሁኔታ ከነበረ ሻዕቢያ ኢትዮጵያ ላይ ያደርግ የነበረውን ማተራመስ እንዲቀጥል ዕድል በመስጠት ነው ሊሆን የሚችለው። ከሁኔታዎች ነባራዊነት አንፃር ጦርነቱ ያስከተለውን ጉዳት መቀነስ እንጂ ሰራዊት በማጠናከር ጦርነቱን ማስቀረት አይቻልም ነበር። ጦርነቱ ማስቀረት ባይቻልም ሁኔታዎች ሳይባባሱ በቁጥጥር ማስገባትም አስፈላጊና ተገቢ ነገር ነው። እዚህ ላይ ገብሩም መለስም የሚስማሙ ይመስለኛል። ነገር ግን ጦርነቱ ኢትዮጵያ በምትገነባው የሰራዊት ጥንካሬ ብቻ የሚቀር አልነበረም፤ ምክንያቱም ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ጥንካሬ ሊረዳ የሚችል ሃይል አልነበረምና።

ሰራዊቱ ከኢኮኖሚያዊ ነባራዊነት ውጪ በልዩ ትኩረት እንዲጠናከር ያልተደረገበት ምክንያትም ሌላ የተሰወረ ሴራ ስለነበረ ሳይሆን ሁለት አስቸጋሪ ጉዳዮችን ለማስታረቅ የተላለፈ የአጣብቂኝ ውሳኔ ውጤት ነው። ውሳኔውም ድህነትን በዋነኛ ጠላትነት ከሚፈርጀው የመለስ ዜናዊ ፍልስፍና ይመነጫል። በመለስ ፍልስፍና የሃገራችን የጥንካሬ ዳዴ ለዘመናት በይደር የቆዩትን ውስጣዊ ቅራኔዎች ከመፍታት ይጀምራል። ድህነትን ካልተዋጋንና ውስጣዊ ቅራኔዎቻችንን መሆን በሚገባው መጠንና መልክ ካልፈታን ታሪክ፣ የሰራዊት ትጥቅና ስንቅ ሩቅ እንደማይወስዱን ከሚተነትነው ፍልስፍናቸው ይቀዳል። ኢኮኖሚም ሰራዊትም ጎን ለጎን መገንባት የሚያስችል አቅም ቢኖር ኖር ለመለስ ቀላሉ መንገድ ነበረ። ነገር ግን እነዚህ ሁለት የማይደጋገፉ ግቦች በድሃ ሀገር ውስጥ ለመፈፀም መምረጥ የግድ ይል ነበር። መለስ ደግሞ በረጅም ጊዜ ሂደት ሰራዊትንም ለመገነባትና ለማጠናከር የሚያስችለውን መንገድ መረጡ፤ ለኢኮኖሚው ልዩ ትኩረት በመስጠት። የመለስ “ድህንት እንግደል” ፍልስፍና ልክም ስህተትም ሊሆን ይችላል። መነሻው ግን ለኤርትራ ከማሰብ ሊሆን አይችልም። ይልቁንስ ለዘመናት ሰንቆ የያዘንን የድህነት ነቀርሳ በመጠኑ ለማስታገስ ብሎም ለማከም የተጠነሰሰ የጥልቅ ኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው። መለስን በስህተታቸው መውቀስና የእሳቤዎቻቸውን ተገቢነትና ቅንነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ለየቅል ናቸው። ገብሩ አስራት ከመለስ የተሻሉ ኢትዮጵያዊና አሳቢ የሚያደርጋቸው ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም።

ከጦርነቱ አይቀሬነት ቀጥሎ የሚነሳው ነጥብ “ጦርነቱ የት ይቁም?” የሚለው ሲሆን ጉዳዩ አሳሳቢና እንደ አመለካከታችን የሚለጠጥ ሆኖ ይታያል። “ባድመ ለኤርትራ መሰጠቷ ላይቀር ለምን ተዋጋን?” እስከማለት የሚደርሱ የፍርድ ቤት ውሳኔና የሉዓላዊነት ትርጉም ለመለየት የሚቸገሩ ሰዎች ተበራክቷል። የተዋጋነው በሰላማዊ መንገድ መፈታት የነበረባቸው አያሌና ውስብስብ ችግሮች በግዛት ይገባኛል ሰበብ በጉልበት እንዲከወን በቋመጠው ሻዕቢያ ምክንያት ነው። ገብሩ አስራትና የሳቸውን ሃሳብ የሚደግፉ ሰዎች የሚያራምዱት አቋም ግን በመሰረቱ ከኢትዮጵያ በኩል የጦርነቱ ግብ ያልነበረ አጀንዳ ነው። ጦርነቱ የሚያበቃው በሃይል የተያዙብንን ግዛቶች ስናስመልስና ሻዕቢያም ፍላጎቱ በአፈሙዝ ማረጋገጥ እንደማይችል በበቂ ሁኔታ ትምህርት ሲቅስም እንደሆነ በግልፅ ተቀምጧል። ይህ ግብ ተሳክቷል ወይስ አልተሳካም ብሎ ለማለት የራስ መከላከል ጦርነቱ ግቦች ጋር ከማነፃፀር ውጪ መደምደሚያ መድረስ የሚቻል አይመስለኝም። አስመራም ሆነ አሰብ የጦርነቱ ግቦች አልነበሩም። ስለዚህ እነዚህን ቦታዎች በተለየ ወይም ኤርትራን ባጠቃላይ ለመቆጣጠር የሚያስችል ግብ ከየት አመጡት? አንዳንድ ወገኖች እንደሚመፃደቁብን በምርጫችን ያካሄድነው ጦርነትም አይደለም። በኛ በኩል ውጊያው የመርህ ጉዳይ ነው፤ ማንም ቢሆን መሳሪያ ደግኖ እላያችን ላይ ፍላጎቱን አይጭንብንም። ይህ እንደማይሆን አረጋግጠናል። ቀጥሎ የሚመጣው ጉዳይ ግን ወደ ድርድርና ህግ እንጂ የኤርትራን ሉዓላዊነት ላይ ሳንካ ወደ መሆን አይደለም። የኤርትራን ነፃነት የተቀበልነው ጦርነቱን ለማስቀጠል አቅሙ ስላልነበረን አልነበረም፤ የመርህ ጉዳይ ስለሆነ እንጂ። ጉልበት ያለን በመሰለን ጊዜ መርሁን የምንጥስ ከሆነ ለሰላሳ ዓመታት ከናኙበት የጦርነት አባዜ ያስወገድናቸውን አጋንንት መልሶ መጥራት ይሆናል። ስለሆነም ጦርነቱ መቆም በነበረበት ቦታና ጊዜ ነው የቆመው። ለውሳኔው ትክክለኛነት ባሁኑ ጊዜ ያለውን የኤርትራ ሁኔታና የሰራዊታችንን ጥንካሬ መመልከት ይቻላል። ሌላው ትክክለኛ ማሳያ ሃገራችን በኢኮኖሚያዊ ገፅታዋ ተስፋ በሚስጥ ሁኔታ ላይ መገኘቷ ነው።

ባጠቃላይ የመለስ ለውስጣዊ ጥንካሬዎቻችን ልዩ ትኩረት የመስጠት ፍላጎትና እምነት በጦርነቱ ለከፈልነው ዋጋ ዋነኛ ምክንያት አይደለም። በገብሩ አስራትና(ጓደኞቻቸውን ጨምሮ) በመለስ መካከል የነበረው ልዩነት “ከጳጳሱ የተሻለ ካቶሊክ” እንዲሉ በኢትዮጵያዊነትና ከሃዲነት መካከል የተፈጠረ ልዩነት አይደለም። ጉዳዩ በአመራሩ መሀከል በቀደሙት መንግስታት ያየነውን ጠብ ጫሪ ሃገራዊነት ዳግም ማቆጥቆጡን የሚያሳይ ነው።የኤርትራን ሉአላዊነት መቀልበስ በየትኛውም መለኪያ ጥያቄ ውስጥ ሊግባ የሚችል እንዳልሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ነገር ግን ይህንኑ የኤርትራን ሉአላዊነት የማይቀበሉ የተወሰኑ ዛሮች አሁንም በሃገራችን ውስጥና በዲያስፖራው አከባቢ ይገኛሉ። ሌሎች የዋሃንም ከቅንነት የሚነሳ የወደብ ጭንቀት ስለተጠቁ ለንደዚሁ ዓይነት እብደት ጆሮ መስጠታቸው አልቀረም። ነገር ግን ነገሮችን ማምታታት ተገቢ አይደለም። ትግሉ በለመድነው የትምክህት ሀገራዊነትና በአዲሱ ስርዓት መካከል የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል መሆኑ መገንዘብ ያስፈልጋል። ስልጣን ለመያዝ እንደሚታገል ፖለቲከኛ ከያዙት አቋም የበለጠ ጠቃሚ የሆነ መንገድ መምረጥ ይችሉ ነበር። ደጋግመው እንዳነሱትም በመልካም አስተዳደር እጦትና በሙስና እየደረሱ ባሉ ችግሮች ላይ ተመስርተው ገዢ ፓርቲውን መገዳደር ቢችሉ ብዙ ደጋፊዎች ከጎናቸው ባሰለፉ ነበር። ይሁን እንጂ የትምክህቱ ጎራ መለያ በሆነ የተገቢነት(ሌጂትመሲ)ትግል ውስጥ ራሳቸውን በመዝፈቅ ለመዳከር ወሰኑ። ለዚሁ ምልክት ይሆን ዘንድ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ከውስጥ አዋቂነት የሚመነጭ ጦርነት ለመክፈት መረጡ። በተገቢነት(ሌጂትመሲ) በመመስረት የሚደረግ ትግል ግን ሀገሪቱ አንድ ክንድ እንኳ ሊያራምዳት አልቻለም፤ በባህሪውም ጨርሶ ያንን መፈፀም የሚችል አይደለም። ዋነኛ መገለጫውም ህገ-መንግስቱ የቆመላቸው መሰረታዊ ምሰሶዎችን አንድ በአንድ ማስወገድ ነው። የህወሓት ትግል ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ለማንገስ የሚያስችል ባህሪ እንዳልነበረው የትግሉ ውጤት የሆኑትን የቃልኪዳን ሰነዳችንና ተቋሞቻችንም ይህንን ተልዕኮ መፈፀም እንደማይቻላቸው መስበክ የውስጥ አዋቂነትን ጋሻ የተከናነበ የትምክህት ጥግ ነው። ይህንን መሰረታዊ ችግር ያልተገነዘበ ፖለቲከኛ ትውልድ የሚያስታውሰው ዱኳ ጥሎ ስለማለፉ እጠራጠራለሁ። በዚህ አጋጣሚ ከህወሓት አመራርነት ተነጥለው እንደ ገብሩ አስራት የትምክህት እልፍኝ ማድመቂያ ከመሆን የተቆጠቡት ገለሰቦች ባጠቃላይና ሁኔታውን ተገንዝበው ከዚህ ድራማ ራሳቸውን ያገለሉ ስየ አብርሃ ያለኝ አክብሮት ላቅ ያለ ነው።

ቸር ይግጠመን!!

***********

Teweldebrhan Kifle

more recommended stories