የቻይና ኤግዚም ባንክ ለመቐለ ወልዲያ ባቡር ፕሮጀክት ብድር ሊለቅ ነው

(ዮሐንስ አንበርብር)

የቻይና ኤክስፖርትና ኢምፖርት (ኤግዚም) ባንክ ለመቐለ ወልዲያ የባቡር ፕሮጀክት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሊለቅ ነው፡፡Photo - Addis Ababa light rail project

የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሚኒስቴሩ ከፍተኛ ኃላፊዎችና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጌታቸው በትሩ የተገኙበት ቡድን በቅርቡ ወደ ቻይና ሄዶ ባንኩ ባስጠናው የአዋጭነት ጥናት ላይ ማብራርያ አቅርበዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የአዋጭነት ጥናት በኢትዮጵያ በኩል ከዚህ ቀደም የተጠና ቢሆንም፣ የቻይናው ኤግዚም ባንክ በድጋሚ ኩባንያ ቀጥሮ የአዋጭነት ጥናት አስጠንቷል፡፡

ይህ የሆነበት ምክንያትም የቻይና መንግሥት በኢትዮጵያ የፖታሽ ማዕድንን ከማልማት ረገድ ይህ የባቡር ትራንስፖርት መስመር የሚኖረውን ጠቀሜታ አስረግጦ ለመረዳት እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በዚህም መሠረት በጥናቱ ላይ ለተነሱ ውስን ጥያቄዎች ማብራርያ እንደተሰጠና በቅርቡም ገንዘቡ ይለቀቃል ተብሎ እንደሚገመት ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

የመቐለ ወልዲያ ፕሮጀክት 268.2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ለፕሮጀክቱ ብድር ለማቅረብ ከኢትዮጵያ አቻቸው ጋር መግባባታቸው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እያደረጋቸው የሚገኙ ሦስት የባቡር ፕሮጀክቶች ማለትም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር፣ የአዲስ አበባ ሜኤሶና የሜኤሶ ድሬዳዋ ደወሌ የባቡር ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከቻይና በተገኘ ብድር በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡

ብቸኛው ከቻይና ውጪ በተገኘ ብድር ለመገንባት ዝግጁ የሆነው ፕሮጀክት የአዋሽ ወልዲያ የባቡር መስመር ሲሆን የሚገነባው ከአውሮፓ ባንኮች በተገኘ ብድር ነው፡፡ ይህም መስመር በቻይና ብድር ከሚገነባው የመቐለ ወልዲያ ፕሮጀክት ጋር የሚገናኝ ነው፡፡

********

ምንጭ፡- ሪፖርተር፣ ሕዳር 21-2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories