የሰለጠነ ውይይት እንጂ መነቋቆር ምን ሊረባን?

(አዲስ – ከድሬዳዋ ከተማ)

ባለፈው ‹‹በከተሞች ፎረም ያወዛገበው ‘ትግሬ’›› በሚል የፃፍኩትን አስተያየት ተከትሎ በርካቶች ብዙ አይነት መልሶችን ሰጥተውኛል፡፡

እውነት ለመናገር እኔ የጠበቅኩትና ያገኘሁት የተለያየ ነበር፡፡ አንዳንዴ እንደአክቲቪስት/ፕሮሞተር ስታወራ በማንኛውም መንገድ ቢሆን ያንተ ሐሳብ አሸናፊ የሚሆንበትን መንገድ ላይ ብቻ ታተኩራለህ፤ ይህ ደግሞ ምናልባት ሰከን ብለህ ስታስበው አሸናፊ እንዲሆን የምትታገልለት ሐሳብ ክፍተቶች ካሉት እነኛን ክፍተቶች ለማስተካከል ጥረት እንዳታደርግ ይልቁንም ተሸፋፍነው እንዲያልፉ እንድትሞክር ሊያደርግህ ይችላል፡፡ ሰሞኑን እንደዚህ አይነት ነገሮችን ነው ጎልተው ያየኋቸው፤ እንደ አክቲቪስት ጎራ ሳይለዩ ሐላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ነገሮችን ተንትኖ ያያሉ ብለህ የምታስባቸው አንዳንድ ሰዎች ጎራ ለይተው እናንተ እና እኛ ወደሚል አላስፈላጊ አቅጣጫ በማምራት ፅሑፌ አላማውን እንዲስት አድርገውታል፡፡

የሆነው ሆኖ እሰጥ አገባ ውስጥ ላለመግባት እና አጀንዳውን ለመቋጨት ያህል፡-

1. የአንድ ሐገር ዜጎች ሆነን፣ ከልጅነት እስከእውቀት የትግራይና ኤርትራ ዘር ያለባቸው ጓደኞች ጋር አድገን፣ ትግራይ የታሪካችን ማዕከል መሆኗ እየታወቀ፣ በትግራይ ጉዳይ እንደማያገባኝ፣ ባዕድ እንደሆንኩኝ፣ ባስ ሲልም የጠላትነት ስሜት ሁሉ እንዳለብኝ ልትነግሩኝ የፈለጋችሁ ሰዎች አልሰማችሁም፡፡ በትግራይ ጉዳይ እኔም ያገባኛል፡፡ የትግራይን ህዝብ ሳልሰድበው ሰድበሀል ብለህ ልታጣላኝ ስትሞክርም ዝም አልልህም፡፡

2. ትግሬ ስድብ አለመሆኑን በበርካታ መንገዶች አረጋግጠናል፡፡ ሆኖም ቃሉ እንዲቀየር የሚፈልጉ አክቲቪስቶች ለቃሉ ምንጭነት የበሬ ወለደ ታሪክ ከማውራት ጀምሮ(-እኛ የቋንቋው ተናጋሪዎች የማናውቀው-ተእግሬ ከሚል፤ ቃል የመጣ ነው የሚል የፈጠራ ታሪክ) ሌሎች ብሔሮችን ከሚመለከቱ እና ከበርካታ አመታት በፊት ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ታቡ ቃላት ጋር እያነፃፀሩ/እያቀላቀሉ ሲያቀርቡ አይተናል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ትግሬ አትበሉን ትግራይ ነው ስማችን ተብሎ እንደማይታወቅ እየታወቀ፣ ያለፉ ስርዓቶች ተገቢ ያልሆኑ ቃላት ተብለው ከ1960ዎቹ እስከ1980ዎቹ ሲነገሩ ከነበሩ ታቡ ቃላት ውስጥ ትግሬ እንዳልነበረ እየታወቀ ከሌሎች ታቡ ቃላት ጋር እያመሳሰሉ ማቅረብ ቅጥፈት/ አስመሳይነት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ምክንያታዊ የሰከነ ውይይት እንጂ ለማሸማቀቅ መሞከር እኔ ጋር ፋይዳ ስለሌለው ይህንን አካሔድ የምትከተሉ ሰዎች በከንቱ አትድከሙ፤ እየተቃወምኩ ያለሁት አንደኛው ነገር ህዝብን ያለጥፋቱ ማሸማቀቅ ተገቢ አይደለም ሲሆን አንዳንዶች ግን እኔን ራሴን ሊያሸማቅቁኝ እየሞከሩ ነው፡፡

3. በመሰረቱ አንድ ህዝብ መጠራት በማይፈልገው ስም መጠራት እንደሌለበት ግልፅ ነው፤ በተለያዩ አጋጣሚዎችም፣ በባለፈው ፅሑፌም በግልፅ ያንፀባረቅኩት ነገር ነው፡፡

እኔ ያለፈውን ፅሑፍ ስፅፍ ፡-

ሀ/ ትግሬ መባል የማይፈልጉ እንዳሉ ተረድቼ ፣ ነገር ግን ይህ የብዙሐኑን ስሜት የሚያንፀባርቅ ሳይሆን የተወሰኑ አክቲቪስቶች ስሜት እንደሆነ እና እነሱም ይህንን ስሜታቸውን ብዙሐኑ ላይ ሊጭኑበት እየሞከሩ እንዳሉ ግምት ይዤ ነው፡፡

ለ/ ትግሬ በትግራይ እንዲተካ እየተከተሉ ያሉት አካሔድም ትግሬ የሚለውን ቃል ወደስድብነት የሚቀይር፣ ትግሬ እያለ የሚጠራውን ሁሉ የሚያሸማቅቅ፣ የብሔሩን ተወላጆችም የተጠቂነት ስሜትን እንዲያዳብሩ የሚያደርግና ለሌሎች ብሔሮች በተለይም ለአማራው ጥላቻን እንዲያዳብር የሚያደርግ ስለሆነ ይህንን አካሔድ እንዲተው ለመጠየቅ ነበር፡፡

የጠበቅኩት ምላሽም፡-

ሀ/ ምናልባት ትግሬ መባል የማይፈልጉ ሰዎችን በተመለከተ በጥቂት አክቲቪስቶች ደረጃ ብቻ ሳይሆን በፓርቲ ደረጃ አቋም የተያዘበትና ለፖለቲካው ቅርብ የሆነ ሰው ሁሉ የተስማማበት ከሆነ መሳሳቴን ለመቀበል(ብዙሐኑ ህዝብ ጋር ግን ይህ ስሜት እንደሌለ አረጋግጫለሁ)፤

ለ/ እንዲሁም ትግሬ በሚለው ቃል ላይ የሚደረገው ዘመቻ ቢቻል እንዲቀር፣ ካልሆነም አሁን አንዳንዶች እየተከተሉ ባሉት ቃሉን ወደ የተከለከለ ስድብነት/ታቡነት የሚቀይር፣ አማራውን፣ ኦሮሞዉንእና ሌሎችንም ቃሉን የሚጠቀሙትን ሁሉ ጥፋተኛ የሚያደርግና ቃላቱን በመጠቀማቸውም እንዲሸማቀቁ የሚያደርግ ፣ የትግራይ ህዝብም የተሰደብኩ ስሜትን እንዲያዳብር የሚያደርግ መሆኑ ላይ ተግባብተን ሌላ አይነት አካሔድ እንዲከተሉ ማድረግ መቻል ነበር፡፡ በውስጥ መልዕክት ከተወሰኑ የኦሮሞና ትግራይ ተወላጆች ጋር በዚህ ረገድ የተግባባሁ ቢሆንም ፌስቡክ ላይ ግን አንዳንዶች ያዙኝ ልቀቁኝ ማለትን መርጠዋል- ይህ ደግሞ የሚጨምረውም የሚቀንሰውም ነገር የለም፡፡

4ኛ- የትግርኛና አማርኛ በአንዳንድ ቃላት ላይ ያላቸው የአነባበብ ልዩነት ሊከበር እንጂ የአንዱ በሌላው ላይ ሊጫን አይገባም፡፡ቴሌቪዥናችን የሁላችንም ስለሆነ ይህንን ቢያስተካክለው ጥሩ ነው፡፡ ‘ሀ’ በትግርኛና አማርኛ የተለያየ አነባበብ ነው ያላት፤ የትግርኛው ‘ሀ’ ከአማርኛው ‘ኸ’ ጋር ተመሳሳይ ነች፡፡ የአማርኛዋ ‘ሀ’ ግን ከ ’ሃ’ ጋር ነው ተመሳሳይነቷ፡፡ ይሔ ዘመናትን የተሻገረ ልዩነት ሊከበር ይገባዋል እንጂ አማርኛ ተሳስቷል ፣ወይም በፈለገው መልኩ መፃፍ መብቱ ነው ማለት ያለብን አይመስለኝም፡፡ግለሰቦች ቢሉም የመንግስት ሚዲያዎች ግን ይህንን አክብረው መስራት አለባቸው፡፡የአንድ ሰው ስም ያላግባብ በርሄ ተብሎ ሲፃፍ እንደነበር እየተቃወምን አሁን አማርኛ ላይ ይህንኑ ስም በርሀ ብሎ መፃፍ ለአማርኛ አነባበብ እውቅና አለመስጠት ነው፡፡

5ኛ- የቦታ ስሞችን በተመለከተ ንጉሰነገስቱ በዘመናቸው የበርካታ ቦታዎችን ስም የቀየሩ ሲሆን እነኚህ ቦታዎች አብዛኞቹ አሁን በቀድሞ ስማቸው እየተጠሩ ነው – ለምሳሌ ኦሮሚያ ውስጥ ደብረዘይት ወደ ቢሾፍቱ፣ አሰበ ተፈሪ ወደ ጭሮ፣ አማራ ክልልም ኮሶ በር ወደ እንጅባራ ፣ . . . ተመልሰዋል ፡፡ ይህንን እንደግፋለን፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት ከአማርኛ ጋር የተያያዙ ቃላት ሁሉ የማርያም ጠላት(ዴሞናይዝ) መደረግ አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ለምሳሌ ቃላቱ በየቋንቋቸው ህዝቡ በለመደው መልኩ መጠቀሙ ተገቢ ቢሆንም ከዚያ አልፎ አማርኛ ላይ ጂጂጋ በ ጂግጂጋ ፣ ጥቁር ውሀ በቢሻን ጉራቻ ፣ መቀሌ በመቐለ መቀየሩ ተገቢ አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ የሐገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች በኢትዮጵያ ስላሉ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ቋንቋዎቻቸው(ስለአማርኛና አማራም ጨምሮ)ያላቸውን ግንዛቤ አዎንታዊ እንዲሆን ነው ጥረት መደረግ ያለበት፤ ፍቅር ነው መሰበክ ያለበት፡፡ ቃላት/ስያሜዎች ሁልጊዜም የባለቤትነት አመላካቾች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ጉራጌ ውስጥ ታዋቂ የምንላቸው ቡታጂራና ወልቂጤ ከተሞች ኦሮምኛ ስም አላቸው ማለት የኦሮሚያ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አማራ ክልል ውስጥም ኦሮሚያ ውስጥ ካሉ የአማርኛ ስሞች የበለጠ አማራ ክልል ውስጥ በርካታ የኦሮምኛ የቦታ ስሞች አሉ፡፡ ከላይ እንደገለፅናቸው ሆን ተብሎ ስማቸው የተቀየረባቸውንና ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸውን ቃላት ወደቀድሞ ስማቸው ቢመለሱ ችግር የለውም/ተገቢም ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ በጅምላ ከአማርኛ ጋር የተያያዙትን ስያሜዎች ማጠልሸት ግን ተገቢም ሐላፊነት የሚሰማው አካሔድም አይደለም፡፡ይህንን አሁንም ወደፊትም እቃወማለሁ፡፡ አማርኛ ላይ ከባለቤቶቹ በከፊል ለየት ያለ አጠራር ያላቸው የቦታ ስሞችን በጅምላ የማውገዝ አካሔድ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ በሌሎችም የአለማችን ቋንቋዎች የሚስተዋል የቋንቋ ተፈጥሯዊ ባህሪይ እንጂ አንዳንዶች የአማራንና አማርኛን ስም ለማጥፋት እንደሚያወሩት ትምክህት/ንቀት የወለደው የአማርኛ ብቻ መገለጫ አይደለም፡፡ እባካችሁ ያላግባብ ጥላቻን አንዝራ፡፡ እዚህ ጋር ካስቀመጥኩት የተለየ ሐሳብ ያላቸው ሐሳባቸውን ቢያካፍሉኝ ደስ ይለኛል፡፡ አማራ እንደሌላው ኢትዮጵያዊ እኩል መብት የሌለው ይመስል የእነኚህ ቦታዎችን ስያሜ እንድቀይር የተደረግኩት ያለአግባብ ነው ብሎ በህጋዊ መንገድ የመጠየቅ መብት የለውም ብላችሁ የምታስቡና ይህንን በመጠየቄ ወደ ግል ስድብ የገባችሁ፣ ባስ ሲልም አማራን ለመስደብ እንደመልካም አጋጣሚ እየተጠቀማችሁ ያላችሁ ሰዎች አድቡልኝ፡፡

**********

አዲስ ከድሬዳዋ - Frm. journalist; currently communicator

more recommended stories