በመጪው ምርጫ ከፖለቲከኞቻችን፣ ከፖለቲካቸው እና ከህዝቡ ምን ይጠበቃል?

ዘንድሮ ምርጫ አለ፡፡ዘንደሮም የተለያዩ የፖለቲካ ሃሳቦች እና አመለካከቶች በህብረተሰቡ ዘንድ ይስተናገዳሉ፡፡ በምርጫው ንቁ ተሳታፊ መሆን የሚፈልገውም፣ ከዳር ሆኖ የነገሮችን አካሄድ መቃኘት የሚያስበውም ፣ ስለ ነገሮች ደንታ የሌለውም የህብረተሰብ ክፍል ሁሉ በዚህ የወቅቱ የፖለቲካ ድባብ ውሥጥ መግባቱ አይቀርም፡፡

በምርጫ ጊዜ ታዲያ መስተዎል ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ምርጫ አለ፡፡ ፓለቲካ አለ፡፡ ደግሞ ሀገር አለ ፣ ህዝብ አለ ፣ ኑሮ አለ ፣ህይወት አለ፡፡ አንዱ አንዱን አጣፍቶ መሄድ የለበትም ፡፡ ሁሉም አብሮ መሄድ አብሮ መቀጠል አለባቸው፡፡ ከባለፉት ተሞክሮዎቻችን ( አሉታዊም ሆኑ አዎንታዊ) እንደ አስተዋይ ሰው ትምህርት ወስደን ነገሮችን በትክክለኛው አቅጣጫ ማስኬድ አለብን፡፡ ታዲያ ለዚህ ከፖለቲከኞቻችን ፣ ከፖለቲካቸው እና ከህዝቡ የሚጠበቅ ሃላፊነት አለ፡፡

አንደኛው የሃላፊነት አቅጣጫ በፖለቲከኞቻችን እና በፖለቲካቸው ህዝብ የማክበር ደረጃ ይለካል፡፡ ህዝብ የሚያንጓጥጥ፣ ህዝብን የሚያጣጥል ፣ የህዝብን የዜግነት ክብር የሚነካ የፖለቲከኞች እና የፖለቲካ አካሄድ በአጭሩ እና በግልፅ ስናስቀምጠው ዲሞክራሲያዊ አይደለም ! ስለሆነም የፖለቲከኞቻችን እና የፖለቲካቸው እንቅስቃሴ አጠቃላይ የሀገሪቱን ብሔር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦችን የሚያከብር ፣ በህዝቦች መካከል መቃቃርን የማይፈጥር ፣ በህዝቦች ዘንድ ያለን የአብሮ የመኖር ባህልን የማያደፈርስ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲከኞች ለጊዜያዊ የፓለቲካ ትርፍ ብለው የኃላ ኃላ ሊያበርዱት የማይችሉትን እሳት ጭረው ለራስ ደህንነት መስጋት እንዳይመጣ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ከወዲሁ በኃላፊነት ሊቃኝ ይገባዋል፡፡Image - Ballot box

በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ፖለቲከኞቻችን እና ፖለቲካቸው የሀገርን ሉአላዊነት ፣ ሰላም እና የእድገት ጉዞ የማይነካ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ውድድር እና ተወዳዳሪ በበዛበት አለም አንድ የማንሸሸው ግልፅ እውነት አለ፡፡ ለእኛ እንደ እኛ እና ከእኛ በላይ የሚያስብልን የለም! አስባለሁ የሚልም ካለ እውነትነቱን ብንፈትሽ በእኛ ጉዳይ ሽፋን የሚቀርብ የግል አጀንዳ እና ጥቅም ተይዞ እንደሆነ እንደ ኢትዮጵያዊ ፣ አፍሪካዊ እና “የሶስተኛ አለም ” ዜጋ ማወቅ እና ማስተዋል አለብን ፡፡ ይህን ባለመረዳት ወይም የራስ ጥቅምን ለማግኘት ተብሎ ከማናቸውም ሃይሎች ጋር የሚደረግ የፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ቁርኝት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የሀገርን ሉአላዊነት አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ እንዲህ ያለ አካሄድ ከተጠያቂነት እና ከታሪክ ተወቃሽነት አያመልጥም ፡፡ ስለዚህ ፖለቲከኞቻችን በማስተዋል እና በኃላፊነት ፖለቲካዊ ግንኙነቶቻቸውን ከወዲሁ ሊፈትሹ ይገባል፡፡ሌላው ከፖለቲከኞች፣ ከፖለቲካው እና ከህዝቡ የሚጠበቀው ነገር ደግሞ ምርጫን ጨምሮ አጠቃለይ የዲሞክራሲያዊ ስርዐት ግንባታ ሁልጊዜ ሂደት መሆኑን ማስተዋል ነው፡፡ በምርጫ ጊዜ ከየትኛውም ወገን እንከን ሊገኝ ይችላል፡፡ ማንኛውም ወገን ደግሞ ራሱን ሙሉ በሙሉ ዲሞክራሲያዊ አድርጎ ሊያቀርብ አይችልም፡፡ ይህ ከዕውነታ የራቀ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ዕውነታ ነው ተብሎ ዲሞክራሲያዊ ያልሆኑ አካሄዶች በዝምታ መስተናገድ የለባቸውም ፡፡ እንዲሁም ደግሞ በ “ድንቄም ዲሞክራሲ” እና “ ከእኛ ወዲያ ዲሞክራሲ ላሳር” አመለካከት እጅን አጣጥፎ ያለቀለት የዲሞክራሲ ስርዐትን አንድ ቀን አስኪመጣ መጠባበቅም ትክክለኛ አቋም አይደለም፡፡ ነገር ግን የዲሞክራሲያዊ ስርዐት ግንባታን የሚያሰናክሉ ሁኔታዎችን በአመለካከት እና በአሠራሮች መስተካከል እንደሚለወጡ ተስተውሎ አዳዲስ ሃሳቦችን እና አሰራሮችን ፈትሾ ለመተግበር ራስን ዝግጁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ማለት የዲሞክራሲ ስርዐት በሁሉም ተሳትፎ እና በማያቋርጥ ጥረት የሚዳብር እንጂ በአንድ ጊዜ ፍፁም ሆኖ የሚገኝ አይደለም ማለት ነው፡፡

በመጨረሻ ሳይገለፅ መታለፍ የሌለበት ነገር በዚህ ወቅት ከህዝቡ የሚጠበቀው ከባድ ሃላፊነት ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአለማችን የእለት ተዕለት ዜና ምንጭ በሆኑ ሀገሮች የምናየው የሀገር ሉአላዊነት መደፈር፣ በህዝብ መካከል ያለ የአብሮ የመኖር እሴት መደፍረስ ፣ የሰላም እና የመረጋጋት ማታጣት ብሎም የዜጎች ሕይወት መጥፋት አደጋ ከፖለቲከኞች የፖለቲካ አመለካከቶች እና አካሄዶች የመነጩ እንደሆኑ መስተዋል አለበት፡፡ ስለዚህ በዚህ የምርጫ ወቅት ህዝቡ ከስሜታዊነት እና ከስማ በለው በፀዳ አመለካከት የፖለቲከኞች የፖለቲካ አካሄድ ሀገርን እና ኑሮን ወዴትኛው አቅጣጫ እንደሚመራ የማስተዋል እና የመለየት እጅግ በጣም ትልቅ ሃላፊነት አለበት፡፡

እንግዲህ የተጠቀሱትን ሃላፊነቶችን በመረዳት መተግበር መጪው የምርጫ ጊዜ የሀገራችን የሰላም እና የዕድገት ጉዞ ተያይዞም የህዝቡም ኑሮ እና ህይወት አደጋ ውስጥ ሳይገባ የዲሞክረሲያዊ ስርዐት ግንባታችንን አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲራመድ ያደርጋል፡፡ ስለዚህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የየራሱን የሃላፊነት ድርሻ ለመወጣት ይንቃ ፣ ይትጋ !

********

Tazabi Yehuneta (Pen name)

more recommended stories