አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን የምንፈርጀው ከሕገ-መንግሥቱ ተነስተን ነው

(እውነቱ ብላታ ደበላ – የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳይ ጽ/ቤት ሚኒስትር ደኤታ)

[የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል እዚህ፤ ሁለተኛውን ክፍል እዚህ ያንብቡ]

3.በሀገራችን የአክራሪነት/ጽንፈኝነት አመለካ ከትም ተግባርም የለም፣ መንግሥት ለፖለቲካው መጠቀሚያ ይሆናል በሚል የፈጠረው አጀንዳ ነው በሚል የቀረቡ ጥያቄዎችና ሃሳቦችን በተመለከተ፤

አክራሪነት/ጽንፈኝነት ብሎም አሸባሪነት የአገራችን፣ የአህጉራችንና የዓለም አቀፍ ስጋት ሆኖ የብዙ ሰላማዊ ዜጐችን ሕይወት በሚቀጥፍበትና የንብረት ውድመት እያስከተለ ባለበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ በምንገኝበት ወቅት መንግሥት ይህንን ያመጣው ለፖለቲካ ፍጀታ ነው የሚለው አቀራረብ የግለሰቦቹንና የቡድኖችን ማንነት ከምንም በላይ በገሃድ የሚያሳይ ነው፡፡ አክራሪነት/ጽንፈኝነት በአገራችን የለም እያሉ መረባቸውን ለመዘርጋት በቂ ጊዜ እንዲያገኙና ከቁጥጥር በላይ ሆነው ሰላማችንና ልማታችንን በማወክ ህልውናችንን ለመፈታተን የሚያቀርቡት ማደናገሪያ ነው፡፡ ከጎረቤት አገሮች ጀምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሰው ሕይወት እንደቅጠል ሲረግፍ እያዩ አላየንም ይላሉ፡፡ በእስያ፣ በአውሮፓ አሜሪካ ወዘተ በየወቅቱ የሚፈጠረውን ቀውስና እልቂት በጆሯቸው እየሰሙ አላዳመጥንም ይላሉ፡፡ በአገራችን የሃይማኖት ነፃነትን፣ እኩልነትንና መንግሥትና ሃይማኖትን የሚለያየውን ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ ሲጣስ እያዩና እየሰሙ ይህንን ጉዳይ አንናገርም ይላሉ፡፡ስለዚህም ድብቅ ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ እውነታውን አናይም፣ አንሰማም፣ አንናገርም በሚል አገራዊ ክሕደት ይፈጽማሉ፡፡

በመጀመሪያ ለሕዝባችን ግልጽ የምናደርገው ጉዳይ መንግሥት አክራሪነት/ፅንፈኝነትን የሚፈርጀው ከየትኛውም ሃይማኖት ተነስቶ እንዳልሆነ መታወቅ መቻል አለበት፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሃይማኖቶችና እምነቶች የአክራሪነት/ ጽንፈኝነት ምንጭ ስላልሆኑ ነው፡፡ መንግሥት አክራሪ ነትንና ጽንፈኝነትን የሚፈርጀው ከሕገ-መንግሥታችን ከተቀመጡ ሦስቱ የሃይማኖትና እምነት ነፃነት ድንጋጌ መርሆዎች ተነስቶ ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶችም ከቅዱሳን መጻሕፍቶቻቸው በመነሳት የሚያስቀምጡት አፈራረጅ እንደሚኖር ግልጽ ነው፡፡

3.1.በሕገ-መንግሥታችን የሃይማኖትና እምነት ነፃነት በአንቀጽ 27 ተደንግጓል፡፡ ስለዚህ ከሕገ-መንግሥታችን ተነስተን ይህንን የሃይማኖትና እምነት ነፃነት በተግባር ለመናድ መንቀሳቀስ አክራሪነት/ ፅንፈኝነት ነው፡፡

ይህም በሀገራችን በግልጽ እየታየ ያለ ውሎ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት የእኔን ሃይማኖት/ሴክት ካልተከተልክ በስተቀር አማኝ አይደለህም በሚል ማስፈራራትና አካላዊ ጥቃት ማድረስ፣ ግድያ መፈጸም፣ የእምነት ተቋማትን ማፍረስ/ማቃጠል፣ መቃብሮችን ማውደም፣ የሌላውን ሃይማኖት ማንቋሸሽ እና ማብጠልጠል፣ ዜጎች በያዙት ሃይማኖት ምክንያት ማሸማቀቅ፣ በኃይል ሃይማኖታቸውንና እምነታቸውን ለማስቀየር መንቀሳቀስ ወዘተ… በአገራችን የተከሰቱ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ይህን ነባራዊ ክስተት የለም በሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ አካላት ሲኖሩ ራሳቸው ይህንን እኩይ ድርጊት የፈጸሙ፤ የሚደግፉና የተባበሩ ብቻ ናቸው፡፡

3.2.በሕገ-መንግሥታችን የሃይማኖትና እምነት እኩልነት በአንቀጽ 25 ተደንግጓል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ከሕገ-መንግሥቱ የእኩልነት መብት ድንጋጌ በመነሳት አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን ሲፈርጅ በሃይማኖት ሽፋን ይህንን የእኩልነት መብት በተግባር ለመናድ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ማለቱ ነው፡፡

ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት የሃይማኖታችንን ክብር፣ ሞገስ፣ ታሪክና ጥቅም ቀንሷል፣ ሀገሪቱ የአንድ ሃይማኖት አገር እንጂ ሌሎችን አይመለከታቸውም፣ ከእኛ ሃይማኖት በስተቀር ሌሎች አገራቸው ሌላ በመሆኑ እኩል እውቅና ሊሰጥ አይገባም፣ የአማኝ ቁጥር ለማነጻጸር የመሞከር የተሳሳተ አመለካከት፣ አንዳንድ የመልካም አስተዳደር ግድፈቶች በመንግሥት መዋቅራችን ሲፈጠሩም አሁንም ሃይማኖቶች እኩል አይደሉም ወዘተ… ብሎ በማደናገር የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በተጨባጭ በሕገ-መንግሥት እውቅና ያገኘውን የሃይማኖቶች እኩልነት የሚንድ ተግባር በመሆኑ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ልንታገለው የሚገባ ፀረ-ዴሞክራሲና ፅንፈኛ የሆነ አስተሳሰብና ተግባር ነው፡፡ ይህንን አመለካከትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የለም በሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ አካላት ራሳቸው ዋነኞቹ የፀረ-ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ተሸካሚና ድርጊት ፈጻሚዎች ናቸው፡፡ ሰው በሰብዕናው እኩል ከሆነ የሚከተለው የራሱ አመለካከትና እኩልነት መከበር ሲገባው ሃይማኖቶችን  በ2ኛና በ3ኛ ደረጃ ፈርጀው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡እነዚህን ሃይማኖቶች የሚከተሉ ሕዝቦች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የሚክድና ሃይማኖት ተከታዩ ኅብረተሰባችን በከፍተኛ የጋራ መስተጋብር በሠላም አብሮ የኖረ መሆኑን የሚዘነጋ ነው፡፡

3.3.መንግሥት ሦስተኛው አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን ሲፈርጅ በሕገ-መንግሥቱ ከተቀመጠው አንቀጽ 11 ተነስቶ ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ መንግሥትና ሃይማኖት መለያየትን በግልጽ አስቀምጧል፡፡ መንግሥታዊ ሃይማኖት ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት ለመመስረት በተግባር መንቀሳቀስ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ነው፡፡

መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት እንደማይኖርና መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ እንደማይገባ በሕገ-መንግሥታችን በማያሻማ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡ ከዚህ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ ተነስተን መንግሥታዊ ሃይማኖት ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት ለመመስረት የሚደረግ ተግባራዊ እንቅስቃሴ  በአክራሪነትና ጽንፈኝነት የሚፈረጅ ነው፡፡ ለአብነት ያህል አሁንም እንዳለፈው ዘመን መንግሥታዊ ሃይማኖትን እውን እናደርጋለን በሚል የሚንቀሳቀሱ መኖራቸው፣ ሌሎች ደግሞ መንግሥታዊ ሃይማኖት የመመስረት ጊዜው የእኛ ነው ብለው የሚንቀሳቀሱ አካላት መፈጠራቸው በሌላ መልኩ ደግሞ አሁንም ያው የድሮው ነው የተለወጠ ነገር የለም ብለው የሚንቀሳቀሱና መንግሥትና ሃይማኖት እንዳልተለያየ አድርገው የሚሰብኩ መኖራቸው የአክራሪነትና ጽንፈኝነት ጉልህ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ አመለካከቶች በሌላ መልኩ ከትምክህትና ጠባብነት የሚመነጩና አገርንና ሕዝብን የሚንዱ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ በሃይማኖት ተቋማት ሥር በተደራጁ የወጣት ማህበራትን እንደምሽግ የሚጠቀሙ ግለሰቦችና ቡድኖች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸወ፡፡ ይህ አመለካከትና ተግባር በጊዜ ሂደት ወደ አሸባሪነት የሚሸጋገር እንደሆነም በአገራችንም ጭምር እያየነው ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባ ጉዳይ ሃይማኖት በራሱ የሰላም ምንጭ እንጂ የአክሪነትና ፅንፈኝነት ባህሪ የለውም፡፡ የሃይማኖት ተከታዮችም የዘወትር ጸሎታቸውና ፍላጎታቸው መንግሥታዊ ሃይማኖት ወይም ሃይማኖታዊ መንግሥት መመስረት ሳይሆን ሰላምና ልማት ነው፡፡ ነገር ግን ሃይማኖትን መሣሪያ አድርገው የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚጥሩ እንዳሉ በሀገራችንም በዚህ መንገድ የብዙ ሰዎች ሕይወት እንደጠፋ፣ አካል እንደጎደለ፣  መስጊዶችና ቤተክርስቲያኖች እንደተቃጠሉ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡

እንደ መንግሥት አክራሪነት/ፅንፈኝነት ስንል እነዚህን ሦስቱን ሕገ- መንግሥታዊ ሃይማኖት ነክ የዴሞክራሲ መርሆዎችን በሚጻረር መንገድ በተጨባጭ መንቀሳቀስን ማለታችን ነው፡፡ አክራሪነት/ጽንፈኝነት የሌላውን ህልውና የማይቀበልና፣ አብሮ በሰላም መኖርን እንደ ስጋት የሚወስድ፣ ብዝሃነትን የማይቀበል፣ ተማምኖ/ተከባብሮና ተደማምጦ መኖር የሚባል ነገር የማያስተናግድ አስተሳሰብና ተግባር ነው፡፡ እነዚህን ሦስቱን ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎች በገሐድ እየጣሱ በሌላ በኩል በአገራችን አክራሪነት/ ጽንፈኝነት የለም፤ ለፖለቲካ ፍጆታ መንግሥት የፈጠረው አጀንዳ ነው የሚሉ አካላት ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-ልማትና ፀረ-ዴሞክራሲ የሆነውን ድርጊቶቻቸውን ለመደበቅ የሚያደርጉት ማደናገሪያ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ንጹሐን ዜጎቻችንን በአክራሪነትና ጽንፈኝነት የመመልመልና የማስፋፋት ዕቅዳቸውን ለማሳካት መንግሥትንና ሕዝባችን የማዘናጋትና ጊዜ የመግዛት ዘመቻና ማደናገሪያ እንደሆነ በግልጽ ሊያዝ የሚገባ ነው፡፡

በሌላ በኩል አክራሪነትና ጽንፈኝነትን ቅዱሳን መጻሕፍትና የሃይማኖት አባቶችም ከአስተምህሮዎቻቸው እየተነሱ የሚያወግዙት አመለካከትና ተግባር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ አክራሪነትና ጽንፈኝነት የአገራችን ተጨባጭ ችግርና ወቅታዊ ስጋት መሆኑን በመገንዘብ ለመመከት መረባረብ ይጠበቅብናል፡፡

4. በትምህርት ተቋም እንዲተገበር የወጣው የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያ የትምህርት ተቋሙን ማህበረሰብና ተማሪዎችን የሃይማኖትንና የእምነት ነፃነት የሚጋፋ ነው በሚል የቀረቡ  ጥያቄዎችና ሃሳቦችን በተመለከተ፤

ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወጣው መመሪያ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲከናወንና ተቋማቱ የልህቀትና ምርምር ማዕከል እንዲሆኑ ታስቦ የተሰራ ሥራ ነው፡፡ መመሪያው በምንም መልኩ የዜጎችን የእምነት ነፃነት የሚጋፋ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከመመሪያው አንጻር የትምህርት ቤት ማኅበረሰብና ተማሪዎችን ጨምሮ በግላቸው እምነታቸውን ተግባራዊ ማድረግን ይፈቅዳል፡፡ የመማር ማስተማሩን ሂደት እስካላወከ ድረስ ማለት ነው፡፡ በቡድን የሚደረግ ፀሎት ግን በመጀመሪያ ደረጃ በተቋሙ ውስጥ ጤናማ ያልሆነ የሃይማኖት ተከታዮች ውድድር የሚፈጥርና የመማር ማስተማሩን ሥራ የሚያውክ ይሆናል፡፡ በመቀጠል ለሁሉም ሃይማኖት የሚሆን የፀሎት ቦታ ይሰጥ ተብሎ ቢታሰብ እንኳ በትምህርት ተቋማት ግቢ ውስጥ የማይቻልና የማይታሰብ በመሆኑ ነው፡፡ ከአንድ ሺ በላይ የተመዘገቡ የሃይማኖት ተቋማት በትምህርት ተቋማት ግቢ ውስጥ የቡድን አምልኮ ቦታ ጥያቄ ቢያቀርቡ ለዚህ የሚሆን ቦታ ማግኘቱም እጅግ አዳጋች ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ዋናው ጉዳይ በሕገ-መንግሥታችን አንቀጽ 90/2 ትምህርት ከማናቸውም የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የባህል ተፅእኖዎች ነፃ ሆኖ መሰጠት ይገባዋል የሚለውን ድንጋጌ የሚጥስም ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ በግላቸው በተቋሙ ውስጥ የአምልኮ ሥርዓታቸውን እንዳያከናውኑ መመሪያው ገደብ አላስቀመጠም፡፡ በቡድን የሚፈጸሙ የአምልኮ ሥርዓቶችን በሚመለከት በአቅራቢያቸው በሚገኝ በሚመለከታቸው የእምነት ተቋም ሄደው በቡድን ማምለክ ይችላሉ፡፡

ከአለባበስ አንጻርም እንደዚሁ መመሪያው የከለከለው ማንነትን በግልጽ ለመለየት የማያስችል አለባበስን ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለትምህርት ተቋማቱና ማኅበረሰቡ ሰላምና ደህንነት ሲባል ነው፡፡ ይህም በተለይ ማንነትን በግልጽ ለማወቅ የማያስችል አለባበስን የሚመለከት እንጂ ሌሎች ሃይማኖታዊ አለባበስን የሚያካትት አይደለም፡፡ ሙሉ በሙሉ ፊትን የሚሸፈኑ አለባበሶች መከልከላቸው ከሃይማኖታዊ ግዴታዎች ጋር የሚቃረን አይደለም፡፡ ከአለባበስ አኳያ ሃይማኖታዊ ግዴታ የሌለባቸው መሆኑም ከሃይማኖት አባቶችም ጭምር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ማንነትን ለመለየት የማያስቸግር አለባበስ በትምህርት ተቋም አልተከለከለም፡፡ በሌላ በኩል ይህ መመሪያ የወጣው ለትምህርት ተቋማት እንጂ ሌሎችን ስፍራዎች የሚመለከት አይደለም፡፡

ከአመጋገብ አንጻርም እንደዚሁ ማንኛውም ተማሪ የሌላውን መብት እስካልተጋፋ ድረስ በግሉ ፀልዮ መመገብ አልተከለከለም፡፡ ነገር ግን በትምህርት ተቋማት የቡድን ጸሎት ጤናማ ላልሆነ ውድድር የሚጋብዝና አሁንም የሌላውን መብት የሚጋፋ ስለሆነ መመሪያው ይከለክላል፡፡ እንዲያውም ከዚህ አንጻር አቅም በፈቀደ መጠን  መንግሥት ለሙስሊም ሆነ ለክርስቲያን ተማሪዎች በተለየ ሁኔታ ምግብ እንዲዘጋጅ ፈቅዷል፡፡ ይህ መንግሥት ምን ያህል የእምነት ነፃነትን ለማክበር የሄደበትን ርቀት የሚያሳይ ነው፡፡

ለማጠቃለል አክራሪውና ጽንፈኛው ኃይል ይህንን ሰላማዊ መማር ማስተማር ለማሳካት የተነደፈውን መመሪያ ለራሱ ርካሽ ጥቅምና ፍጆታ ሲጠቀምበት ይታያል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ተቋም የሚገኘው አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ተማሪ በመሆኑና ተማሪዎች ደግሞ ወጣቶች በመሆናቸው በዚህ አካባቢ ውጥረት ቢፈጠር ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል ስሌት ነው፡፡ ሕዝብን በማደናገርና የነገን አገር ተረካቢ ትውልድ ጥራትና ብቃት ባለው ትምህርት እንዲገነባ ሰላም ወሳኝ ግብአት ነው፡፡ አገርን እንወዳለን እያሉ አገርን የሚያፈርስ ማደናገሪያ መርጨት ከዜጋ የሚጠበቅ አይደለም፡፡

አክራሪዎችና ጽንፈኞች በተማሪዎች ዘንድ ሃይማኖታዊ ይሁንታን በማግኘት ዓላማቸውን ለማስፋፋት የሚያደርጉት ጥረት ነወ፡፡ የትምህርት ተቋማት ማኅበረሰባችን የአምልኮ፣ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያ ሠላማዊ የመማር ማስተማርን ተልዕኮ የሚያስፈጽም እንጂ የእምነት ነፃነትን የሚገድብ እንዳልሆነ አውቀው ከማደናገሪያ መልዕክቶች ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ተቋማት የሚልኩት ሰላምና ደኅንነታቸው ተረጋግጦ ሀገራቸውንና ቤተሰባቸውን የሚጠቅም እውቀት እንዲገበዩላቸው ለማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም የአክራሪዎችና ጽንፈኞችን ድብቅ ዓላማ በማክሸፍ የትምህርት ተቋሞቻችን አገር ተረካቢ ዜጋን ለማፍራት መረባረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

*********

* ይህ ጽሑፍ መጀመሪያ የታተመው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ‹‹መንግሥታዊ ሃይማኖት፤ ሃይማኖታዊ መንግሥትም አይኖርም – መንግሥት አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን የሚፈርጀው ከሕገ-መንግሥቱ መርሆች ነው -›› በሚል ርዕስ ነው፡፡

Ewnetu Bilata Debela is a Special Assistant to the Prime Minister. Previously, he served as State Minister of Government Communication Affairs Office and a senior official at the Ministry of Federal Affairs. Ewenetu studied Chemistry in Bahir dar University, Political Science at Addis Ababa Univercity and Economics at Civil Service University. He occasionally writes on HornAffairs.

more recommended stories