ያለ ፍላጎታችን ብሔር የተጫነብን ኢትዮዽያውያን አለን

(አቤንኤዘር ቢ. ይስኃቅ)

ኢህአዴግ ካመጣው ነገር አንዱ መታወቂያ ላይ ብሔርን ማስሞላት ነው። ነገር ግን እንደ ኢትዮዽያዊ ብቻ መታወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ምንም ምርጫ አላዘጋጀም። ያለ ፍላጎታቸው መታወቂያቸው ላይ የሆነ ብሔር እንዲሞሉ ይገደዳሉ። በእርግጥ አንዳንዶች በእነሱ ክልል/ከተማ እንደዚህ አይነት ነገር እንደሌለ ሲከራከሩ አይቻለው። በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ደግሞ ሁለቱም አይነት አሰራር አለ። አንዳንድ ከተሞች ሲጠይቁ አንድንዶቹ ደግሞ አይጠይቁም።

በራሴ ካጋጠመኝ ስነሳ የቀበሌ መታወቂያ ላወጣ ስሄድ ፎርም እየሞላው ሳለ “ብሔር” አለችኝ የቀበሌው ሰራተኛ እኔም ከተለያዩ ብሔሮች ነው የተወለድኩት ስለዚህ እኔ የዚህ ብሔር ልልሽ አልችልም ኢትዮዽያዊ ብለሽ ሙይው አልኳት። እሷም “እንደዚያ አይቻልም የግድ አንዱን ብሔር መምረጥ አለብህ” አለች። እሺ ከእናትና ከአባት ብሔር የትኛው ብሔር ነው የሚበልጠው? ስላት “እንደዚያማ ብሎ ነገር የለም ሁለቱም ዕኩል ናቸው” አለች። ጥሩ እንደዚያ ካልሽ ኢትዮዽያዊ ብለሽ መሙላት ወይም 50% የእናቴን 50% የአባቴን ብለሽ መጻፍ ካልሆነ በስላሽ የእናቴ/የአባቴን ማስቀመጥ አልኳት። በዚህ አልተስማማችም። “አይቻልም የግድ አንዱን ምረጥ አለብህ አለበለዚያ መታወቂያውን ማግኘት አትችልም” አለችኝ። ወደ በላይ አካል አቤት ብልም የሚሰማ ስለማይኖርና ያለ መታወቂያ መንቀሳቀስም ሆነ ሌላ ቦታ አገልግሎት ማግኘት ስለማልችል ያለፍላጎቴ በግድ አንዱን ብሔር መርጬ መታወቂያውን ወሰድኩኝ።Image - Ethiopia regions flags

እዚህ ጋር እንግዲህ ኢህአዴግ የራሱን ዓላማ ለማራመድ ሲል እኔን ያለፍላጎቴ በግዴታ አንድ ብሔርን ምረጥ እያለኝ ነው። መታወቂያ ለማግኘት ከፈለኩኝ ያልሆንኩትን አንዱን ብሔር መርጬ እንድኖር እያስገደደኝ ነው። ኢትዮዽያዊ ነኝ እያልኩት ካልሆነም የመጣሁባቸውን ብሔሮች በሙሉ እውቅና ሰጥተህ በመቀበል መታወቂያዬ ላይ አስፍራቸው ስለው እምቢ ብሎ በግድ አንተ “የዚህ ወይም የዚያ ብሔር አባል ነኝ” በል እያለ እያስገደደኝ ነበር።

ሌላ ተመሳሳይ ነገር ያጋጠመኝ ሥራ ለመቀጠር የሄድኩበት አንድ ቁልፍ የሆነ የፌደራል መስሪያ ቤት ነው። እዚያ መስሪያ ቤትም የሚቀጠሩ ሰዎች ወደዱም ጠሉም ብሔራቸውን መጻፍ አለባቸው። ከሁለት የተለያዩ ብሔሮችም ከተወለዱ የግድ አንዱን መርጠው የቅጥር ቅጹ ላይ መሙላት ይጠበቅባቸዋል። እንደ ዜጋ ሳይሆን እንደ ብሔር ነው የሚቀጥሩህ። የቱንም ያህል በተገቢው መንገድ ተወዳድረህ በብቃትህና በችሎታህ ለሥራ መደቡ ብቁ ብትሆንም። የግድ አንድ የብሔር ካባ ለብሰህ መሄድ አለብህ። የስራ መደቡ ከብሔር ጋር ምን ግንኙነት አለው? ብሔሬን ለምን ፈለጋችሁት? ብለህ ብትጠይቅ መልስ የሚሰጥ ሀላፊ የለም። ብቻ የመንግስት መመሪያ ነው ትባላለህ። ያ መስሪያ ቤት አሁን ያንንም ትቶ የኢህአዴግ አባላትን ከመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ሲመረቁ በቀጥታ ወይም ከሌላ መስሪያ ቤት በዝውውር መቅጠር ጀምሮአል።

ሥራ ለመቀጠር የግድ የአባትህን ወይም የእናትህን ብሔር ምረጥ ይሉሀል። አንተ ግን የእናትህ ወይም የአባትህ ብሔር ብቻ አባል አይደለህም። ወደ አያቶችህም ስትሄድ ሌላ ብሔር አለ። ነገር ግን ትክክል ሁን ወይም አትሁን ግድ የላቸውም ብቻ አንዱን ብሔር የቅጥር ፎርሙ ላይ እንድትሞላ ትገደዳለህ። ለእኔ አይነት ኢትዮዽያውያን ያልፈለግነውን ብሔር በግድ እንድንመርጥ እንገደዳለን። በኢህአዴግም መመሪያ አንድ ብሔር ይጫንብናል። ያልሆንከውን ነህ ማለትና ያለፍላጎትህ የሚደረግ ነገር ሁሉ በጫና የመጣ ነው። ኢህአዴግ የዘረጋው ሥርዓት አንዱ ችግር እንደ እኔ ከተለያዩ ብሔሮች ለተወለዱ ዜጎች የሚሆን ክልልም አልሰጣቸውም። ሥርዓትም አልዘረጋላቸውም። አዲስ አበባና ድረዳዋ በሥም ከየትኛም ብሔር አስተዳደር ነጻ ናቸው ቢባሉም በተግባር ግን በተለያዩ መንገዶች ወደ አንዱ ብሔር እንድትጠቃለል የሚጠይቁና የሚያደርጉ ናቸው። የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሲካሄድ የዜጎችን ብሔር፣ ሐይማኖትና ሌሎች ነገሮችን መጠየቅና መሙላት የተለመደና ተቀባይነት ያለው ነው። ነገር ግን የቀበሌ መታወቂያ ላይ ብሔር እንዲሞላ ማስገደድ ለምን አስፈለገ? ጥቅሙና አላማውስ ምንድነው? እስከዛሬስ ምን ጥቅም አስገኘ?

“ኢትዮዽያዊነት ተጭኖብን ነው እኛ ቅድሚያ በብሔራችን ነው የምንታወቀው” አላችሁ። ደህና መብታችሁንና ፍላጎታችሁን አከብርራላችኋለው። ኢትዮዽያ እንደዚህ አይነት ጥያቄ ላላቸው ሕዝቦቿም በኢህአዴግ የማስመለስና ለፖለቲካ ፍጆታ በሚውል መንገድ ሳይሆን በትክክል ምላሽ ሊኖራት ያስፈልጋል ብዬ አምናለው። ችግሩ ያለው እናንተ ሊሆንባችሁ ያልፈለጋችሁትን ነገር ሌሎች ላይ ለማድረግ መወሰናችሁና ማድርጋችሁ ነው። ለምን እኔ ላይ ብሔር ትጭኑብኛላችሁ? እኔ ከመጀመሪያውም ኢትዮዽያዊ ነኝ። ኢትዮዽያዊነትም አልተጫነብኝም። ስለዚህ ለምን እንደ ኢትዮዽያዊነቴ አትቀበሉኝም? ከላይ ያነሳዋቸው ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ ነው። ሌላም ይኖራል። ይሄ የአንድ ወይም የሁለት ዜጎች ጉዳይ አይደለም። እንደ እኔ አይነት ተመሳሳይ ጥያቄ ያላቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አሉ። ኢትዮዽያ “ማንነትቴ ብሔሬ ነው” ለሚሉ ብቻ ሳይሆን ማንነቴ ኢትዮዽያዊነቴ ነው ለምንልም ዜጎች ሀገራችን ስለሆነች የሁሉንም ጥያቄ ሊያስተናግድ የሚችል መንግስትና ሥርዓት ያስፈልገናል።

*******

Guest Author

more recommended stories