የህዳሴ ግድብ ላይ ለሚካሄደው ጥናት የሦስትዮሽ ኮሚቴ ተቋቋመ

(ካሳዬ ወልዴ)

ኢትዮጵያ ፤ ግብጽና ሱዳን ፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ሁለት ጥናቶችን የሚያካሂደውን አለማቀፍ አማካሪ ድርጅት የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ አቋቋሙ ።

ኮሚቴው በአንድ ወር ውስጥም አለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቱን ይመርጣል ።

አማካሪ ድርጅቱ ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አያያዝና አለቃቀቅ ላይ እንዲሁም በታችኛው ተፋሰስ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ ላይ ነው ጥናቶችን የሚያደርገው ።

በዚህም ላይ የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች ዛሬ የስምምነት ፊርማቸውን አኑረዋል።

የባለሙያዎቹ ቡድን ከአንድ አመት ጥናት በኋላ የኢትዮጵያ ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የጎላ ጉዳት አያደርስም ካለ በኋላ ፤ የግድቡ ውሃ አያያዝና አለቃቀቅ እንዲሁም በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ እንዲጠና ምክረ ሀሳብ ቢያቀርብም ፤ በሶሰት የካርቱም የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች የተደረገው ስብሰባ ጥናቱን ማስጀመር አልቻለም ነበር ።

ነሀሴ ላይ በአራተኛው የካርቱም ስብሰባ ላይ የተደረሰው ስምምነት ግን ጥናቱን ለማስጀመር መንገድ ከፍቷል ።

ሁለቱ ጥናቶች በሶስቱ ሀገራት የብሄራዊ የባለሙያዎች ምክር ቤት ተወካዮች የሚመራ ሲሆን፥ ምክር ቤቶቹ ከሶስቱም ሀገራት አራት አራት ሀገራት የተወከሉበትን ኮሚቴም አቋቁመዋል።

በዚህም መሰረተ የግብጾቹን ባለሙያዎች ፕሮፌሰር አሽራፍ ኤል አሻል ፤ የሱዳኖቹን ፕሮፌሰር ሰይፈዲን ሀማድ አብደላ እንዲሁም የኢትዮጵያን ባለሙያዎች ኢንጂነር ጌድዮን አስፋው ይመሩታል ።

ኢንጂነር ጌድዮን እንደሚሉት 12 አባላት ያሉት ኮሚቴ በቀጣይ ሁለት ጥናቶችን የሚሰራ አለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት የመቅጠር ስራ ይሰራል ።

ሶስቱም ሀገራት ሶሰት ሶስት አለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶችን በእጩነት ያቀቡና ከዘጠኙ ድርጅቶች አሸናፊው የሚመረጥ ሲሆን፥ የአለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቱ ክፍያም በሶስቱ ሀገራት የሚሸፈን ይሆናል ።

ድርጅቱ በታችኛው ተፋሰስ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ ላይ ጥናት ማድረግ ያስፈለገው፥ ከዚህ ቀደም በዚህ ላይ የተጠኑት ጥናቶች በሁለተኛ ደረጃ መረጃ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው ።

የሀይድሮሎጂ ሲሙሌሽን ሞዴል ላይ የሚደረገው ጥናት የኢትዮጵያን ግድብ የውሃ አያያዝና አለቃቀቅ ምን ይሁን የሚለው ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ ይህም ኢትዮጵያ ግድቡን ሰርታ ስትጨርስ በታችኛው የተፋሱ ሀገራት በበጋና በክረምት ወቅት ተጽእኖው ምን ይመስላል የሚለውን ለመለየት ያስችላል ።

ግድቡ ሀይል ለማመንጨት በ16 ተርባይኖች እንደመጠቀሙ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የተጽእኖ ትንታኔን መሰረት አድርጎ ፤ ምን ያህል ተርባይኖች በአንዴ ውሃ ይልቀቁ፣ ምን ያህሎቹ ተርባይኖች ለምን ያክል ጊዜ ውሃ ይያዙ ፣ የሚሉትን ጥያቄዎች ከወቅቶች አንጻር በመነሳት ምክረ ሀሳብ ያቀርባል ።

የሚቀጠረው አማካሪ ድርጅት በቅድሚያ ላለፉት ሀያ አመታት ተመሳሳይ ስራዎችን በመስራት ያለውን ልምድ እንደሚፈተሽ እና በተለይም እንዲህ አይነት ስራዎች በሰራባቸው ጊዜያት የነበሩት ስነ ምግባሮችም እንደሚጣሩ ነው ኢንጂነር ጌድዮን የገለፁት።

ጥናቱ ሳይንሳዊ ስለሚሆን ለተሳሳተ ውጤት በሩ ጠባብ መሆኑን እንዲሁም ይህ ጥናት ኢትዮጵያ ግድቡን ስትሰራ የውሃ አጠቃቀሟ ላይ ምክረ ሀሳብን ለማቅረብ የሚረዳ እንጂ፤ የሚደረገው ጥናት የግድቡ ግንባታ ይቀጥል ወይስ አይቀጥል ከሚለው ጉዳይ ጋር ምንም አያገናኘውም ነው ብለዋል ኢንጂነር ጌድዮን ።
*********
ምንጭ፡- ፋና፣ መስከረም 12፣ 2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories