በረከት ስምዖን በባህርዳር የፍትህና ጸጥታ ዘርፍ ስልጠና እየመሩ ነው

በኢትዮጵያ እየተፈጠረ የመጣውን በመረጃ የዳበረ ህብረተሰብ ለመምራት በእውቀትና ክህሎት የበለጸገ አመራር በዘላቂነት ማፍራት ወሳኝ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር አማካሪ ሚኒስትር አስታወቁ።

በአማራ ክልል በመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ በባህርዳር ከተማ እየተሰጠ ያለውን ስልጠና በመከታተል ላይ የሚገኙ የፍትህና ጸጥታ አካላት በታላቁ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ህዳሴ ግድብ፣ በዳኞች ነጻነት፣ በምርጫና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ላነሱት ጥያቄ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር አማካሪ ሚኒስትር በረከት ስምኦን እንደገለጹት፤ በፌዴራልና በየደረጃው በሚገኙ መስሪያ ቤቶች በፍትሃዊነትና ውጤታማነት ላይ ያተኮረ ሳይንሳዊ አመራር መፍጠር የሀገሪቱን ህዳሴ ለማረጋገጥ ያግዛል።

መንግሥት ከዝቅተኛ ጀምሮ የመካከለኛና ከፍተኛ አመራሩን አቅም መገንባት የሚያስችል የረጅም፣ የአጭርና የመድረክ ላይ ስልጠና ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም ባለፉት አስር ዓመታት ሀገሪቱ በእምርታ እየተጓዘችና ስራዎቹም በእጅጉ እየሰፉ በመምጣታቸው ብቃትና ክህሎት ያለው አመራር በየደረጃው መፍጠር የመንግስትና የድርጅት ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገሪቱን እድገት ማስቀጠል የሚችል አመራር በስፋት ለማፍራት ለሰው ሃይል ልማት ትኩረት በመስጠት መንግስት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱ እድገት በሚጠይቀው መጠን የአመራሩን አቅም ለመገንባት በተደረገው ጥረት በሀገር ደረጃ የተነደፈውን ፖሊሲና ስትራቴጂ በአግባቡ በመፈጸምና በማስፈጸም በኩል አመራሩ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል።

በዚህም መላ ህዝቡን በማሳተፍ የመፈጸም ስትራቴጂ እውን በመሆኑ በትምህርት፣ በግብርና፣በመሰረተ ልማትና ሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን አስታውቀዋል።

በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ በተፈጠረው ያልተማከለ አስተዳደር እያንዳንዱ ማህበረሰብ ራስን በራስ የማስተዳደር የስልጣን ባለቤት በመሆኑ በየደረጃው የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካ ውጤት እንዲመጣ ማስቻሉን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በራሷና በህዝቦቿ ሙሉ አቅም የምትገነባው የህዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት 40 በመቶ መጠናቀቁን ጠቁመው አንዳንድ ሀይሎች የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ ጥረት ቢያደርጉም በታቀደው መሰረት ስራው እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ 72 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በመያዝ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት የምስራቅ አፍሪካን የኃይል ትስስር ማጠናከር በሚያስችል ሁኔታ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።

የዳኞች ነጻነት የተረጋገጠው በህገ መንግስቱ በመሆኑ በሚቀርብላቸው ማስረጃ በመመስረት ፍርድ ቤቶች በመንግስት ላይ ጭምር ትክክለኛ ብይን እየሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል።

መንግሥት በያዝነው ዓመት የሚካሄደው ምርጫ ውጤት ምንም ይሁን ምን በዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ በመስራት ላይ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ሆኖም በቀለም አብዮት በጎዳና ላይ ነውጥ ሊፈጥሩ የሚችሉ ኃይሎች በመኖራቸው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትና ህብረተሰቡ ነቅቶ በመጠበቅ የስልጣን ሽግግሩ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲዘልቅ የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ተሾመ ተፈራና ኢንስፔክተር እንግዳው ሆዴነው እንደገለጹት ለተነሱ ጥያቄዎች ተገቢ ማብራሪያና በማስረጃ የተደገፈ ምላሽ በማግኘታቸው ግንዛቤያቸውን ማሳደግ ችለዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች ባነሷቸው ሀሳቦች ላይ ተመርኩዞ በተሰጠው ማብራሪያና በተካሄደው ውይይት ስለወቅታዊው የሀገሪቱ ሁኔታ እውቀታቸው ማደጉንም አስታውቀዋል።

በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ያለው የፍትህና ጸጥታ ዘርፍ ስልጠና እስከ መስከረም 14/2007 እንደሚቀጥል ከወጣው መርሃ ግብር መረዳት ተችሏል።
********
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን ‹‹በእውቀትና ክህሎት የበለጸገ አመራር የማፍራቱ ጥረት መጠናከር አለበት›› በሚል ርዕስ፡፡

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories