Sep 15 2014

ለግድቡ የገቢ ማሰባሰቢያ በዋለው የጽሁፍ መልእክት18 እድለኞች ሽልማታቸውን ተቀበሉ

(ለምለም መንግሥቱ)

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈትቤት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንበታ የገቢ ማሰባሰቢያ ባዘጋጀው አጭር የጽሁፍ መልእክት (ኤስ ኤም ኤስ) በመጀመሪያው ዙር18 ዕድለኞችን ሸለመ። ጽህፈትቤቱ ለተጨማሪ የገቢ ማሰባሰቢያ የሚያውለው ከኦቶሞቲቭ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ ኦፍ ኢትዮጵያ (አምቼ) በስጦታ ያገኘውን 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የጭነት መኪና ተረከበ፡፡ Ethiopia - Renaissance dam lottery car

ጽህፈትቤቱ ለግድቡ የገቢ ማሰባሰቢያ ከአንድ ሳምንት በፊት በጀመረው በአጭር የጽሁፍ መልእክት ሽልማት ተሳትፈው አሸናፊ ለሆኑ ዕድለኞች ትናንት በጽህፈትቤቱ ባዘጋጀው ልዩ ሥነስርአት 14 ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ባለ32 ኢንች ቴሌቪዥን እና 2 ላፕቶፖችን ለእድለኞች ሸልሟል፡፡ ከእድለኞቹ ተሸላሚዎች አብዛኛዎቹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቢሆኑም ከክልሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

ለዕድለኞቹ ሽልማቱን የሰጡት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ባደረጉት ንግግር መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የግድቡ ግንባታ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚያኮራ መሆኑን ገልጸው፤ የተጀመረው ድጋፍና መነሳሳት እስከማጠናቀቂያው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡በተለይም በአጭር የጽሁፍ መልእክት በጨዋታው እየተዝናኑ እድለኛ በመሆን የሚደረገው ድጋፍም መቀጠል እንዳለበት መልእክት አስተላልፈዋል።

ከእድለኞቹ መካከልም ባለ 32 ኢንች ቴሌቪዥን እድለኛ የሆነው ከጅማ ከተማ ታዳጊ መሐመድ አሚን የሱፍ፣ እና በተመሳሳይ የቴሌቪዥን ተሸላሚው ከትግራይ ክልል ወጣት ጌታቸው አሰፋ እና ከአዲስ አበባ ከተማ የላፕቶፕ ዕድለኛ የፖሊስ አባል ኃይሌ አበራ በየበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ድጋፉ ሁለት ዓላማዎችን የያዘ መሆኑ ብዙዎችን የሚያነሳሳ እንደሆነ አመልክተው፤ እድለኞች በመሆናቸውም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ ቀሪውንም ሽልማት የራሳቸው ለማድረግ መልእክታ ቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

በሥነስርአቱ ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀጳጳሳት ዘ አክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃ ይማኖት፤ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዶክተር ዋቅስዩም እዶሳ፤ በየበኩላቸው «ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ስሟን የሚያስነሳ፣ ዜጎችንም የሚያኮራና ከድህነት ውስጥ የሚያወጣ ታላቅ ትርጉም ያለው ሥራ የሆነውን የግድብ ሥራ ማጠናቀቅ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ተግባር ነው» ሲሉ አሳስበዋል። ለዚህ በጎ ተግባር ድጋፉን የማያደርግ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብለው እንደማይገምቱም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ጉባኤ ጽህፈት ቤትም በጽሁፍ መልእክቱን አስተላልፏል።

የኢትዮ ፍሎሪ ኢቲ ኃይላንድ ኩባንያና በኢትዮ ሆርቲ ቬር ኩባንያ ስም የኩባንያዎቹ ባለቤት አቶ ፀጋዬ አበበ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክርቤት ጽህፈትቤት ለሚያከናውነው ተግባር የሚውል የ200ሺ ብር ድጋፍ አድርገዋል። ቀደም ሲልም በየኩባንያዎቹ ስም በ5ሚሊዮንና በ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ቦንድ መግዛታቸውንም በዚሁ ወቅት ገልጸዋል። አርቲስት ዝና ብዙ ፀጋዬና ገነት ንጋቱ በየበኩላቸው የግድቡን ሥራ በስፍራው ተገኝተው መጎብኘታቸውንና ሥራው ለድጋፍ ይበልጥ መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩልም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ ከኦቶሞቲቭ ማኑፋክቸሪንግ ካምፓኒ ኦፍ ኢትዮጵያ ( አምቼ) በስጦታ ያገኘውን 1.4 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የጭነት መኪና ተረክቧል፡፡

ኢቬኮ ባለማቀዝቀዣ የጭነት መኪና በስጦታ ያበረከቱት የአምቼ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ዎልፍፒንግ ብሌዝገር እንደገለጹት፤ ኩባንያው ለተጀመረው ግድብ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደምም ኩባንያውና የኩባንያው ሠራተኞች የግማሽ ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዝተዋል፡፡

ኩባንያው ያበረከተውን ስጦታም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ በምስጋና ተቀብለው ለታለመለት ዓላማ እንደሚውልም ገልጸዋል።

********

ምንጭ፡ ከአዲስ ዘመን

0 Comments

ስለጽሑፉ ምን ይላሉ? አስተያየቶን ያካፍሉን፡፡