ETV እንዴት ተሰናበተን? EBCን እንዴት እንቀበለው?

(በቴዎድሮስ ገ/ዓምላክ)

እ.ኤ.አ በ1964 ዓ.ም የመጀመርያውን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ሊያበስረን የተበሰረው ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ – ኢቲቪ እነሆ የስያሜ ለውጥ አድርጎ EBC በሚል አዲስ ስያሜ የቀድሞውን ስርጭት ቀጥሏል፡፡ የስያሜ ለውጥ ለማድረግ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት እና በአጠቃላይ በማንነት ለውጥ ዙርያ አዲሱ ኢቢሲ ምን አይነት መልክ እንደሚኖረው ድርጅቱ ሁኔታውን የገለፀበት አጋጣሚ ባይኖርም እራሱን በአዲስ መልክ ለመቀየርም ሆነ ኮርፖሬሽን ለመባል የሚያስችሉ ምክንያቶችን ግን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በስሱ ጠቅሰን እንለፍ ከተባለ፡-

ምክንያት 1- ውህደት

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና የኢትዮጵያ ሬድዮ በ1995 እ.ኤ.አ ጋብቻ መፈፀማቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ውህደት በራሳቸው ሁለት ህጋዊ ሰውነት ባላቸው ድርጅቶች መካከል የተደረገ በመሆኑ ወደ ኮርፖሬሽን ማደግ የሚያስችል አደረጃጀት ይሰጣቸዋል፡፡ ሆኖም ድርጅቶቹ  የኤጀንሲነት ሚናን ይዘው መዋሃድ ስለመረጡ፣ እስከዛሬ ድረስ በኤጀንሲ አደረጃጀት ረግተው ቆዩ፡፡

ምክንያት 2- በአዲስ መልክ ብቅ ለማለት

ኢቲቪ ለዓመታት ያለስያሜ ለውጥ በንጉሱ ጊዜ ንጉሱን መስሎ፣ በወታደሩ ዘመን ወታደሩን መስሎ እና በኢህአዴግ ዘመን አህአዴግን መስሎ መኖሩ እንደ አንድ የሚዲያ ተቋም ሲገመገም በራሱ ፈገግ ያሰኛል፡፡ ንጉሱን ሲያንቆለጳጵስ በነበረበት አፉ መልሶ ሲፈጠፍጥ፣ ደርግን “በለው እርገጠው!” ሲል በነበረው ልሳኑ፣ እነሆ ደርግን የሲኦል እቁብተኛ አድርጎ ሲስልልን፤ አሁን ደግሞ ባለተራውን ማወደስ ይዟል፡፡ ከዚህ አንፃር የስም ለውጥ ካስፈለገውም እንደውም ዘግይቷል፡፡

ምክንያት 3- አዲስ ማንነት ለመፍጠር

በርግጥ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢሬቴድን ወደ ኮርፖሬሽን ማሳደግ ሲመለከት የነበረው ልዩ ኮሚቴ፤ ኤጀንሲው ወደ ኮርፖሬሽን እንዲያድግ ካስፈለገበት አንኳር ምክንያት ውስጥ አዲስ ማንነት ለመፍጠር የሚል ግልፅ ነጥብ ባያስቀምጥም፣ አዲስ ማንነት ግን ያስፈልገዋል፡፡ ይህ አዲስ ማንነት ከሚያቀርበው ይዘት፣ የአቀራረብ መንገድ፣ ጥራት እና አጠቃላይ የድርጅቱን ማንነት በበጎ ጎን ሊገነቡ ከሚችሉ ነጥቦች አንፃር ሊቃኝ ይገባዋል፡፡ ይዘት ሲባል በርካቶች የቀድሞ ኢቲቪ ካለው ታሪክ አንፃር ምንም አይነት መንግስታዊ ለውጥ ሳይኖር እንዴት የይዘት ለውጥ ሊያደርግ ይችላል? የሚል ጥያቄ ሊፈጥርባቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን ትክክለኛ ህዝባዊ ማንነት እንዲኖረው ከተፈለገ፣ ተራ ልሳናዊ ብዕሩን አስቀምጦ፣ ከፍ ወዳለ የህዝብ ልዕልና ባህሪ ማደግ አለበት፡፡

ለዚህም ማንንም መስደብ ወይም ማንቋሸሽ አልያም መደገፍ አይጠበቅበትም፡፡ ከፈለገም የልማታዊ መንግስት ሚዲያ ባህሪን መላበስም መብቱ ነው፤ ሆኖም በልማታዊ መንግስት ሚዲያ ባህሪ ውስጥ ሊተቹ፣ ሊታረሙ አልያም ሊጋለጡ የሚገባቸው ህፀፆች እንደሌሉ ማሰብ እና ማድረግ ግን ከባዱ ስህተት ነው፡፡ የትኛውም አይነት አቋም ቢኖረውም ሚዲያ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህ ሚዲያ መምሰል መጀመር አለበት፡፡ አሁን ድርጅቱ እየሄደበት ያለው አካሄድ፣  ህዝብ በተለያየ ሁኔታ ከሚደርሰው ሌሎች መረጃዎች አንፃር ደረጃው ሲለካ በጣም የራቀ ይሆንና ኮርፖሬሽኑ ሊመታው ያሰበውን ግብ እንዳያሳካ ያደርገዋል፡፡

ከጥራት፣ ከአቀራረብ እና ከሌሎች የኮርፖሬሽኑን ገፅታ ሊገነቡ ከሚችሉ ተግባራት አኳያም እንዲሁ ሳይንሳዊ በሆነ መለኪያ የሚገመገም ወጥ የሆነ አካሄድ ሊተገበር ይገባዋል፡፡ ስለ ጥራት ስናወራ የምስል ጥራት አልያም የድምፅ ጥራት ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ጥራት አጠቃላይ እንደኮርፖሬሽን የሚገለፅ ፅንሰሃሳብ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከስቱዲዮ አደረጃጀት፣ ከምስል እና ከድምፅ ጥራት፣ ከኮርፖሬት ከለር፣ ከፕሮግራም አቅራቢዎች አለባበስ፣ ከምንጠቀመው ግራፊክስ፣ ከምንጠቀመው  ቴክስት፣ ከፎንት መረጣ፣ የፕሮግራም መግቢያ እና መውጪያ አኒሜሽኖች፣ የፕሮግራም ሎጎዎች (የእሁድ መዝናኛን ሎጎ በባለሙያ ቅኝት ላስተዋለ፣ የኢቲቪን ብሔራዊነት ለመጠራጠር ደቂቃም ሲበዛ ነው) እና ሌሎችም፡፡

ከላይ በምክንያትነት የጠቀስናቸው ነጥቦች ኢቲቪ ስሙን ለመቀየር ምክንያት መሆን የሚችል በቂ ማሳያ በመሆናቸው ድርጅቱ ወደ ስም ለውጥ መግባቱ እንደ አንድ በጎ ጎን ልናይለት የሚገባ ውሳኔ ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን ከስም ለውጥ ጋር ተያይዞ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮችን ድርጅቱ ትኩረት ሰጥቶ ሰርቷቸዋል ወይ? የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው፡፡ ምናልባት ድርጅቱ የቤት ስራውን መስራቱን ወይም አለመስራቱን ከዚህ ቀጥሎ የምናነሳቸው ነጥቦች አንድ ድርጅት በለውጥ ሂደት ሊከተላቸው የሚገቡ ቁምነገሮችን ማሳየት የሚችሉ በመሆናቸው አዲሱን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን ለመገምገምና ፍርድም ለመስጠት አመቺ ያደርገዋል፡፡ ነጥቦቹ ኢቢሲ እስካሁን እስካሳየን የለውጥ ደረጃ ድረስ ያሉት ብቻ ናቸው፡፡

1ኛ – እራስን ‘በትዝታ’

ለውጥ ሲታሰብ ማንኛውም ድርጅት የድርጅቱን የቀደመ ታሪክ በጥልቀት ማየት፣ አላማ አድርጎ የተነሳበትን ጉዳዮች መዳሰስ እንዲሁም አላማውን ለማሳካት ሲከተላቸው የነበሩ ስልቶችን መቃኘት የመጀመሪያው ተግባሩ ነው፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ስለድርጅቱ በዋናነት የሚመለከታቸው አመራሮች ውስጣዊ የሆነ መተማመን እና ስለነበረው ማንነት ግልፅ አቋም መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ተግባር ሲከናወን በቀጣይ እንደድርጅት ለምን እንደመጣ እና ምን የተለየ ነገር እንደሚሰጥ መረዳት ያስችላል፤ ያኔ ይህ ስራው ላይ መንፀባረቅ ይጀምራል፡፡

ከዚህ አንፃር አዲሱ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ምን ያህል ጥናት አካሂዷል፣ አላካሄደም እንዲሁም በድርጅቱ ታሪክ ላይ የተደረሰ አቋም መኖር ወይም አለመኖሩን የገለፀው ነገር ባለመኖሩ በጉዳዩ ዙርያ ሰፊ ነገር ለመሰንዘር አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ሆኖም “ለውጡ ምን አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ብቅ ብሏል?” ከሚል ካየነው የኢቲቪ የለውጥ ደረጃ ከስም እና ከሎጎ የዘለለ ስላለመሆኑ አገባቡ በተወሰነ ደረጃ ይጠቁማል፡፡ አገባቡ እንዴት ይህን ሊጠቁም ይችላል? ከተባለም ኢቢሲን እንደ አንድ አዲስ ምርት እንየው እና መልሱን እናገኘዋለን፡፡

አዲስ ምርት ወይም ነባር ምርት በአዲስ መልክ ወደ ገበያው ሲቀላቀል ቅድመ ፕሮሞሽን ሊሰራለት ይገባል፡፡ ኢቢሲም ለዓመታት ሲገለገልበት የነበረበትን የቀድሞ ስያሜ ያስጣለው ጉዳይ ተብራርቶ አዲስ ነገር እንድንጠብቅ ቅድመ ፕሮሞሽን ሊካሄድ እንዲሁም አዲስ እና ሙሉ የፓኬጅ ለውጥ ካለም ይፋዊ የሆነ የትውውቅ ፕሮግራም(launching program) ሊካሄድ በተገባው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሌሎችም የቅድመ ፕሮሞሽን ስልቶች እና በመጀመሪያ የምርት ወቅት እንደሚደረገው ጠንካራ(aggressive) የሆነ ተከታታይ ፕሮሞሽን በስፋት እና በተለያየ ስልት መከናወን ይገባል፡፡ የኢቢሲ አገባብ ግን ከዚህ የተለየ ነው፤ ሽምቅ አገባቡ እንደው እንደቀልድ ዘው የሚሉት አይነት ነው፡፡ ይህ የሚጠቁመው አመራሮቹ እና የሚመለከታቸው አካላት ለውጡ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ በቅጡ አልተረዱም አልያም ለውጥ ከነጭራሹ የለም፡፡

2ኛ – ሌሎች ስለኛ ምን ያስባሉ?

ሌሎች ስለ ቀድሞው ኢቲቪ ምን ያስባሉ? ተመልካቾቼ እንዴት ነው የሚያዩኝ? በዘርፉ ያሉ መሰል ተቋማት እኔን እንዴት ነው የሚያዩኝ?

አዲስ ነገር ይዘን ለመምጣት አስፈላጊ መሆኑን እና አለመሆኑን ትክክለኛ ምላሽ የምናገኝባቸው ጥያቄዎች እኒህ ናቸው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለነዚህ በቂ ምላሽ ከሰበሰበ በኋላ ወደምን መለወጥ እና እንዴት መለወጥ እንደሚገባው አቅጣጫ ያገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር አዲሱ ኮርፖሬሽን በቂ ጥናት በመሰብሰብ በውጤቱ መሰረት አዳዲስ ለውጦችን የሚያሳየን ከሆነ እንግዲህ በቀጣይነት የምናየው ይሆናል፡፡ ሆኖም ወደ ለውጥ የገባነው “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እና ዲያስፖራዎች” ለኢቲቪ ያላቸውን ልዩ ፍቅር፣ ከልብ የመነጨ አክብሮት እና ድጋፍ ተመርኩዘን ከሆነ አሁንም ኢቢሲ “የአንዳንዶች” መሆኑ ይቀጥላል፡፡

3ኛ – ተመሳሳይ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን በአግባቡ ማጥናት

“እኔን መሰል ድርጅቶች ምን መልክ አላቸው?” ብሎ ጥናት ማካሄድ ያለንበትን ደረጃ ለማወቅ ሁነኛ መንገድ ነው፡፡ በርግጥ ኢቲቪ በሀገር ውስጥ ከሚሰራጩ ጣቢያዎች ሊማር የሚችልበት አጋጣሚ መጥበቡ “እኔ ማነኝ?” የሚለውን ምስል እንዳይረዳ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ ሆኖም ለመማር ኢትዮጵያዊ መሰል ድርጅቶችን መፈለግ የግድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሌሎች በርካታ ጣቢያዎች ብዙ ሊያስተምሩት በተገባ ነበር፡፡ በዚህ ደረጃ ኢቲቪን ሲኮርጅ ብናየውም ቢያንስ ጎበዝ ኮራጅ ልንለው የምንችልበት አንድ አጋጣሚ መጥቀስ ግን አስቸጋሪ ነው፡፡

4ኛ – አንተን ሊገልፅ የሚችል ሎጎ፣ ታግላይን፣ ከለር፣ እና ሌሎች ተያያዥ ነገሮች መፍጠር

ይህ ክፍል አንድ ተቋም ከሌሎች ልዩ የሚያደርገውን የራሱ የሆነ ማንነት(Own Identity) የሚፈጥርበት ነው፡፡ እንግዲህ ኢቢሲን እስካሁን እስካየነው ድረስ እዚህ ቦታ ላይ ደርሷል፡፡ አዲሱ ኢቲቪ – ኢቢሲ በሚል በነጭ በተፃፈ የእንግሊዘኛ ፊደል፣ በቀይ ባክግራውንድ ለተመልካች በቀኝ እይታ አዲስ ሎጎ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ የኢቲቪ ለውጥ ከጥርጣሬ በላይ ምናልባት እንደማረጋገጫ በሚቆጠር መልኩ ባዶ ለውጥ መሆኑን ማሳያው ይህ ሎጎ እና ተከትሎት የመጣው ግንጥል አኒሜሽን ናቸው፡፡ አቀማመጡ፣ ሎጎው በስክሪን ላይ የተሰጠው መጠን፣ የፎንት እና የባክግራውንድ የቀለም ምርጫ እንዲሁም አጠቃላይ ሳቢነቱ በጣም ደካማ ነው፡፡

የባክግራውንድ ቀለም ምርጫ – ቀይ

ኢቲቪ ምንም እንኳን በሚዲያ ቢዝነስ ላይ የከረመ ቢሆንም ድርጅቱ የሚገለፅበት ቋሚ ቀለም (corporate colour) የለውም፡፡ ሆኖም በብዛት ሰማያዊ ቀለም የሚገለፅበት የዜና ስቱዲዮ እንዲሁም ቀይ ቡኒ የሚታይበት የፕሮግራም ስቱዲዮዎች መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለረዥም ጊዜ እንደ ድርጅቱ መለያ የምትታወቀው ምስል ቀይ ቀለም ያላት ናት፡፡ ይህ ድርጅቱ ወጥ የሆነ የራሴ የሚለው ቀለም የሌለው መሆኑ የሚያሳይ ሲሆን አሁን በሎጎ ቀለምነት የተጠቀመው የቀለም ምርጫ፣ ከነባሮቹ የኢቲቪ ቀይ ቀለም የተለየ የቀይ ቤት መሆኑ አሁንም በድርጅቱ ገፅታ ላይ ወጥ የሆነ ምስል አለመፈጠሩን ማሳያ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በቀጣይነት ጣቢያው ለሚያሳየው የቀለማት ድንብርብሮሽ እንደ ምክንያት ሆኖ ይቀጥላል፡፡

በዚህ አዲስ ለውጥ ኢቢሲ አጠቃላይ ድርጅቱ የሚገለፅበትን ቀለም ወይም ቀለማት ወስኖ ሊመጣ በተገባው ነበር፡፡ የቀለም ውህደትን በተመለከተ ድርጅቱ በብዛት ሲጠቀም የነበረው ሁለቱ ቀለማት ማለትም ደማቅ ቀይ እና ደማቅ ሰማያዊ ቀለማት ያላቸው የስነልቦና ተፅእኖ ከግምት ውስጥ ያልተካተተ ሲሆን ሁለቱም በጣም ጠንካራ እይታ ያላቸው መሆኑ የኮርፖሬት ቀለም ውህደትን ያልተከተሉ ያደርጋቸዋል፡፡ (በብዛት የሚመከረው ምርጫ አንድ ደማቅ ቀለም ከአንድ ሳሳ ብሎ ከሚታይ ቀለም ጋር ሲዋሃድ ነበር፡፡ ቢቢሲ ቀይ፤ አልጀዚራ ብርቱካናማ ዋና መለያቸው በማድረግ ይታወቃሉ፡፡)

ማራኪነት

ከዚህ አንፃር ኢቢሲ ሦስት ምርጫዎች ነበሩት፡፡ የመጀመሪያው ሙሉ ለሙሉ አለም አቀፍ ይዘት ያለው ሎጎ መፍጠር ሲሆን ሁለተኛው ሙሉ ለሙሉ ሀገራዊ ይዘት የሚንፀባረቅበት ሎጎ ነው፣ በሦስተኝነት ዓለም አቀፍ ባህሪን ከአገርኛ ጣእም ጋር የደባለቀ ማራኪ ሎጎ መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ቅኝት አዲሱን ሎጎ ለማጫረት ባወጣው መስፈርት ውስጥ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት የሚያንፀባርቅ የሚል አንድ መስፈርት ተቀምጦ እንደነበርም ይታወቃል፡፡ አዲሱ ሎጎ ግን ኢቲቪ ለግል ተጫራቾች ያወጣውን መስፈርት ሁሉ ጥሶ የቀረበ ግንጥል እና ምንም አይነት ትርጓሜ ለመስጠት የሚከብድ ነው፡፡ በርግጥ ድርጅቱ ያወጣውን ጨረታ ሙሉ ለሙሉ ሰርዞ በውስጥ ዲዛይነሮች ማሰራቱ በራሱ ኢቲቪ ከነበረው መልክ ያልራቀ ኢቢሲን ለማየት አንድ ምክንያት ነው፡፡ በጨረታው ከተሳተፉ ድርጅቶች ውስጥ አንድ ሁለት ተጫራቾች ያቀረቡትን የሎጎ ምርጫ ለማየት አጋጣሚ አግኝቻለሁ፡፡ እኒህ ሎጎዎችን ማየት ኢቢሲ አሁን ይዞ የቀረበውን ሎጎ የመረጠበትን በቂ ምክንያት ለመረዳት ይበልጥ አዳጋች ያደርገዋል፡፡ በቂ ትርጓሜን ከበቂ ማራኪነት እና ዘመናዊነት ጋር አጣምረው የያዙ አርማዎችን አይቻለሁ፡፡  ተጫራች ድርጅቶች ያቀረቧቸውን ሎጎዎች  በጋራ ሆነው ለህዝብ የሚያሳዩበት አጋጣሚ ቢገኝ አልያም በማህበራዊ ድረገፅ ላይ ቢያሰፍሩት ሰዎች ሁኔታውን ለመመዘን ይችሉ ነበር፡፡

በድርጅቱ  የዲዛይን ባለሙያዎች ስራው እንዲሰራ መደረጉ በራሱ ስህተት ነው ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ሆኖም የዲዛይን ባለሙያዎቹ የዲዛይን እውቀት ደረጃቸው ምን ድረስ ነው? ድርጅቱስ እራሱን ብራንድ ለማድረግ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ የዲዛይን እና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎቻቸው አጠቃላይ የኮሙኒኬሽን እውቀት ደረጃስ የት ድረስ ነው? የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር በውስጥ ያሉ ዲዛይነሮች ሳይንሱ የደረሰበትን የዲዛይን እድገት በአግባቡ ያውቃሉ ማለት ድፍረት ይሆናል፡፡ ምናልባት ባላቸው እውቀት ላይ ለዚህ ስራ ሌላ ተጨማሪ አማካሪ አካል ቢመደብላቸው፣ ከዲዛይን ባሻገር ያለ ሙሉ የኮሙኒኬሽን እውቀትን ተረድተው የተሻለ ነገር ሊፈጥሩ ይችሉ ነበር፡፡ ሙሉ ለሙሉ ትችት እንዳይሆን ምናልባት ይህን አዲሱን ሎጎ ቀለል ብሎ ከመታየት አንፃር (ሲምፕሊሲቲ) ጥሩ ነው ልንለው እንችላለን፡፡ እሱም ከማራኪ ውስንነቱ ጋር፡፡

ታግ ላይን

ኢቲቪ ለረዥም ጊዜ በአእምሯችን ውስጥ እንዲሰርፅ የሚያደርግ እራሱን የሚገልፅበት ወጥ የሆነ አጭር መግለጫ (ታግ ላይን) የለውም፡፡ በብዛት ወቅቶችን ሲመስል ነው የምናየው፡፡ ደስ ያለው ወቅት “ለኢትዮጵያ ህዳሴ እንተጋለን!” ብሎ እኛ ተመልካቾች በቀላሉ የማይገለፅልን ትጋቱን በግድ ሊያሳምነን ይሞክራል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ “እሩቅ ለማደር እሩቅ አስባ እየተጋች ያለች ሀገር” የሚል መፈክር ከዜና አንባቢዎች ጀርባ በፅሁፍ እንዲሁም በዜና አንባቢዎች ጭምር በተደጋጋሚ ሲያስነግር ይሰማል፡፡ ይህ በድርጅቱ ወጥ የሆነ እራስን መግለፅ የሚችል አቋም እንደሌለ ማሳያ ነው፡፡ ጐበዝ! የያዝነው እኮ ብሔራዊ ሚዲያ ነው!! እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የተጠና ስልት ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ሌሎች በሚዲያ አስተዳደር የት እንደደረሱ እንመልከት! ድርጅቱ በዚህ አዲስ ስያሜውን እና ሎጎውን በማስተዋወቅ ሂደት ወቅት የተጠና አብሮ የሚሄድ ታግላይን ይዞ ብቅ ማለት ይገባው ነበር፡፡

አሁንም ይህን ለማድረግ አልረፈደም፡፡ ሚዲያው ሊያሳካ የሚፈልገውን ወይም “እኔ እንዲህ ነኝ” ብሎ የሚያምንበትን በአጭር ቃላት አጣፍጦ መፍጠር ይኖርበታል፡፡ (እንተጋለንም ከሆነ ይቻላል፡፡)

እንደማጠቃለያ

ሚዲያው ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት ተቋም ነው፡፡ እንደ መንግስትም እንደ ህዝብም ልሳን፣ ሀገር በማነፅ ሂደት በርካታ ስራዎች ወድቀውበታል፡፡ ሀገሪቷ መድረስ የምትፈልግበት ደረጃን የማገዝ፣ የህዝቦች ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግንኙነት እንዲዳብር፣ ለነብሱ፣ ለጭንቅላቱ እና ለሰውነቱ ጭምር የሚጠቅሙ መረጃዎችን በተለያየ እና በእጅጉ በተጠና ስልት የማቅረብ አካሄድ መሄድ መጀመር አለበት፡፡

የእድሜውን ያህል ያልበሰለ አቀራረብ፣ ጥራዝ የነጠቀ እውቀት የሚስተዋልበት፣ አሰልቺ እና የማይስብ ማንነት ይዞ መቀጠሉ፣ አንድም ድርጅቱ እንደ ራዕይ ካስቀመጠው ቦታ ላይ ለመድረስ በዚህ የ “ቀንድ አውጣ” አካሄዱ ዘመናት ቢሰጡት የማይደርስ ሲሆን በተጨማሪም ህብረተሰቡ ሌሎች አማራጮች የሚያገኝበት ሁኔታ እየሠፋ መምጣቱ የማይቀር በመሆኑ የኢቢሲ ሚና ለነ ‘ሰው ለሰው’ እና ‘ቤቶች’ ድራማ ብቻ ከመሆን ያልዘለለ ሆኖ ይቀራል፡፡

**********
Source: አዲስ አድማስ፣ ጳጉሜን 03/2006

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories