የተክሌ በቀለ የትግል ጥሪ እና የአንድነት ፓርቲ ዕጣ

የፓርላማ አባሉና የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ /አንድነት/ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የሆኑት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ የልማት ሰራዊት ግንባታ ላይ እየተረባረብኩ ነው የሚለውን መንግስት ለመገዳደር የትግል ሰራዊት መገንባት እንደሚገባ ከአንድ ቀን በፊት እንዲህ ሲሉ በብሎጋቸው ላይ አስፍረው ነበር፡፡

“የሰላማዊ ትግል ሰራዊት እንዴት እንገንባ ለሚለው ጥያቄ አፋጣኝ ምለሽ ካልሰጠን በስተቀር መንግሰት በግልፅ እየደገፈ ያለው በጠብመንጃ ሊገዳደሩ የፈለጉትን ነው” ግርማ ሰይፉ

የአቶ ግርማ ሰይፉ ፅሁፍ የሚያስረዳው ተቃዋሚ ሃይሎች ተረባርበውና ተደጋግፈው ኢሕአዴግን ሊጥሉበት የሚገባው ጊዜ አሁን መሆኑን ነው፡፡ በአጭሩ የውስጥ ችግሮቻችንን አደፋፍነን የጋራ ጠላታችንን ኢሕአዴግን ገፍትረን እንጣለው ሲሉ ነው ጥሪያቸውን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ያስተላለፉት፡፡ የትግል አጋራቸው የሆኑት አቶ ተክሌ በቀለ ግን በሰዓታት ልዩነት ከትግል አቅጣጫ አንፃር የዚህ ተቃራኒ የሆነ ሌላ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ የአቶ ተክሌ ጥሪ ትግሉ ከውጭ ሃይሎች ጋር ሳይሆን በራሱ በአንድነት ውስጥ ካሉት ጋር መሆን አለበት የሚል ነው፡፡

የአንድነት የቀድሞው ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ተክሌ በቀለ በአንድነት ውስጥ ያሉ የስልጣን ሃይሎችን ለማፈራረስ ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ተክሌ ይህን የድጋፍ ጥሪ ያቀረቡት በአገሪቱ ላሉ ፓርቲዎች ነው፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበርን ከሚያክል ‘ትልቅ ስልጣን’ ሰሞኑን ከሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ያፈነገጡት አቶ ተክሌ በቀለ በፌስቡክ ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት በፓርቲው ውስጥ ስልጣን ይዘው ያሉ ሃይሎችን ህልም ቅዠት ማድረግ የሚቻለው የለውጥ ሃይሎች ሲተባበሩ ብቻ ነው፡፡ Andinet UDJ party leadership

የስልጣን ኃይሎች በኢትዮጵያችን በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን የመጨረሻቸዉ ይሆናል፡፡ ሌላ እድል ሊሰጣቸዉ አይገባም፤ በየፓርቲዎቹ ያላችሁት የለዉጥ ኃይሎች ተባበሩ፡፡ በዉስጣችን ያሉት የስልጣን ኃይሎች የፈጠሩትን ድንበር አፈራርሰን፤ ህልማቸዉን ቅዠት አድርገን ህዝባችንን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ እንዋሃድ፤ እንተባበር፡፡ተክሌ በቀለ

ይህ የአቶ ተክሌ የእንተባበር ጥሪ ምን ያህል ድጋፍ ያስገኝላቸዋል? በሚለው ላይ እስኪ የግል አስተያየቴን ልስጥ፡፡ በግልፅ አማርኛ ጥሪ የተደረገላቸው የለውጥ ሃይሎች እነ ተክሌ በቀለን በደጋፊዎቻቸው ሞራል ተሟሙቀውና ለኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው የተሳሳተ ዝቅተኛ ግምት ሰጥተው ከወረዱበት ወንበር ደጋግፈው ይመልሷቸዋል ወይስ ኢንጂነር ግዛቸው እንዳሸነፉ ይዘልቃሉ? ነው ጥያቄው፡፡

እኔ እንደማስበው የዚህን ትክክለኛ መልስ ለማወቅ ትንሽ ጊዜ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ ሆኖም ያሉትን ሁኔታዎች በግርድፉ መዳሰስ ይቻላል፡፡ የአቶ ተክሌን ጥሪ ተቀብለው ተፅዕኖ ሊያደርሱ የሚችሉት በራሱ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ያሉ አባሎች ናቸው፡፡ እነዚህ አባሎች አሁን ለሁለት መከፈላቸው ይታወቃል፡፡ ከፊሉ በስልጣን ላይ ያሉትን ኢንጂነር ግዛቸውን ሲደግፉ ገሚሶቹ ደግሞ እነ ተክሌ በቀለና በላይ ፍቃዱን የሚደግፉ ናቸው፡፡

በእነ ተክሌ ቡድን የተሰለፉት ለዚህ ጥሪ ቀና ምላሽ መስጠታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ግራ ገብቷቸው መሃል የሰፈሩትን ወደ በላይ እና ተክሌ በመሳብ፤ ካስፈለገም እንደተለመደው ግርግር በመፍጠርና ቢሮ በመስብር ወይም ኢንጂነር ግዛቸው ወደግቢው እንዳይገቡ በመከልከለል ጭምር የቁርጥ ቀን ውግንናቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ፡፡ በተለይ በፓርቲው ወጣት አባላት የተሻለ ተቀባይነት ያላቸውን እነ ዳንኤል ተፈራና የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን የያዘው ይህ ሰልፍ ለኢንጂነር ግዛቸው ስጋት መሆኑ አይቀርም፡፡

በአንፃሩ የኢንጅነሩ ደጋፊዎች ኢንጂነሩን ከማንኛውም አደጋ ለመታደግ አስፈላጊውን መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ እገምታለሁ፡፡ ኢንጂነር ግዛቸው ደግሞ ይህን ሰልፍ እንዴት መምራት እንደሚቻል አሳምረው ያውቁበታል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ‘መርህ ይከበር’ ወይም ‘ዝም አንልም’ የሚል መፈክር አንግበው ከፓርቲው ያፈነገጡ አባላት በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እየተመሩ ጥቃት ቢሰነዝሩም ተሸንፈው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡

ያኔ በጉልበት ፅ/ቤቱን የመቆጣጠር ጥረታቸው በኢንጂነሩ የመከላከል ስልት የከሸፈባቸው ወጣት የፓርቲው አባላት የተወሰኑት ሲበተኑ የተወሰኑት ሰማያዊ ፓርቲን አቋቁመው ይሄው እስካሁን ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን የእነ ተክሌ በቀለ ደጋፊዎች ለኢንጂነር ግዛቸው ስጋት መሆናቸው ባይቀርም ኢንጂነሩን አውርዶ ተክሌ በቀለን ወይም በላይ ፍቃዱን የማውጣት አቅም ይኖራቸዋል ብዬ አልገምትም፡፡

በራሱ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ካሉት የአመራር ለውጥ ፈላጊዎች ቀጥሎ የዚህ ጥሪ ቀዳሚ ተደራሽ የሚደረጉት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ አባላት መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድነትና መኢአድን ለማዋሃድ የተደረገው ጥረት ፍሬያማ አለመሆኑ ለእነ አቶ ተክሌ ማፈንገጥ እንደምክንያት ይቀርብ ስለነበር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ከአንድነት ጋር መዋሃድ የሚፈልጉ ነገር ግን ውህደቱ ለመክሸፉ ኢንጂነር ግዛቸው ተጠያቂ ናቸው ብለው የሚያምኑ የመኢአድ አባላት እንደተጠየቁት ድንበር አፈራርሰው፤ ህልምን ቅዠት ለማድረግ ድጋፋቸውን ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

እዚህ ላይ በምን መልኩ ድጋፍ ሊሰጡ ይችላሉ? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ እንደሚታወቀው የመኢአድ አባሎች አብዛኞቹ በእድሜ የገፉና ያለፈው ስርዓት ቅሪቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በዚህ ወቅት በአንድነት አመራሮች ላይ ግርግር ለመፍጠር ፍላጎቱም አቅሙም አይኖራቸውም፡፡ ይልቁንም ድጋፋቸው የኢንጂነር ግዛቸውን ስም አጥላልተው የደጋፊዎቻቸውን ቁጥር በማመናመንና በተወሰነ መልኩም በገንዘብ በመደገፍ ሊገለፅ ይችላል፡፡ መኢአድን ከቁንጮው ለተመለከተው ገንዘብ ጭንቁ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ለዚህ የሚሆን የተወሰነ ፈንድ ሊያስለቅቅ ይችላል፡፡ ቁንጮውን ታውቁታላችሁ ብዬ ነው፡፡ የእነዚህ ድጋፎች ድምር ውጤት ግን አቶ ተክሌን በሆያ ሆዬ ተወናብደው ወደለቀቁት ወንበር ይመልሳቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡

የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በመወሰን ረገድ የላቀ ሚና የሚጫወተው ፓርቲዎቹ በውጭ አገራት ካሉ የገንዘብ ምንጮቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች የገንዘብ ምንጫቸው ከአባላት የሚሰበስቡት መዋጮ ሳይሆን ከውጭ በህገ ወጥ መልኩ የሚፈስላቸው ዶላር በመሆኑ ውጭ ያሉ ፅንፈኛና አክራሪ ሃይሎች በርቀት መቆጣጠሪያ ሪሞት የውስጣቸውን ፖለቲካ እንዳሻቸው ይጠመዝዙታል፡፡ እንደ መድረኩ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ‹‹ዶላራችሁን እንጂ እጅ ጥምዘዛችሁን አልፈልግም›› የሚል ካለም የእጁን ያገኛል፡፡ መድረክን የመታውን ድርቅ የምናውቀው ነው፡፡ ቤታቸው ድረስ ይመጣ የነበረው የዲያስፖራ ዶላር አሁን አሜሪካና አውሮፓ ድረስ ሄደውም ባሰቡት ልክ ሊያገኙት አልቻሉም፡፡

ከዚህ አንፃር አንድነትም በተጨባጭ አጣብቂኝ ውስጥ የገባ ፓርቲ ሆኗል፡፡ አሁን በተፈጠረው የአመራር ክፍፍል ላይ የዲያስፖራው ድጋፍ ወደ አፈንጋጮቹ በላይ ፍቃዱና ተክሌ በቀለ በማጋደሉ እንደ ግርማ ካሳ ያሉ በውጭ የድጋፍ አስተባባሪዎች ለኢንጂነር ግዛቸው መራሹ አንድነት የገንዘብ ድጋፍ መስጠታቸውን እንደሚያቋርጡ በግልፅ አስታውቀዋል፡፡ በርግጥ አንድነት በኢኮኖሚ አቅማቸው ‘ትንንሽ’ የሆኑትን እነ በላይ ፍቃዱን፤ ተክሌ በቀለን፤ ዳንኤል ተፈራን፤ የመሳሰሉትን አርቆ የኢኮኖሚ አቅማቸው ግዙፍ የሆነውን ኢንጂነር ዘለቀ ረዲን አቅርቧል፡፡ ሆኖም ይህም ቢሆን ለጊዜው ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ መፍትሄ የሚያመጣለት አይመስልም፡፡ የዲያስፖራው የገንዘብ ምንጭ ከደረቀ ከፓርቲው የሚንጠባጠብላቸውን የሚጠብቁ አባላቶቹ እየራቁ መሄዳቸው የማይቀር ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከረጅም ጊዜ አኳያ ኢንጂነሩን ለብቻቸው አስቀርቶ ለተቃዋሚዎቻቸው እንዲንበረከኩ ያደርጋቸዋል፡፡ ስለሆነም ዋናው የኢንጂነር ግዛቸው ስጋት ይህ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

በጥቅሉ ሲታይ ግን ኢንጂነር ግዛቸው ከራሱ ከአንድነት፤ ከመኢአድና ከዲያስፓራው ደጋፊ የሚወነጨፉ ቀስቶች አሉባቸው፡፡ ይህን ተቋቁመው መንበረ ስልጣናቸውን ለማቆየት ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡ ግን ፈተና ሁሉ የሚወደቅበት አይደለም፡፡ እንደዚህ አይነት ሴራዎችን በሌላ ሴራ የማክሸፍ ልምዳቸው በዚህ ወቅትም ሊታደጋቸው የማይችልበት ምክንያት አይታየኝም፡፡ ይልቁንስ ኢንጂነሩ መውደቃቸው የማያጠራጥረው ከገዢው ፓርቲ ጋር በሚኖራቸው ትግል ነው፡፡ ኢንጂነሩ ሴራ በመሸረብና በማክሸፍ ያላቸውን ልምድ ያህል በፖለቲካው መድረክ ብስለት አይታይባቸውም፡፡ በ2002ቱ ምርጫ ገና የምርጫ ጣቢያዎች በር ከመከፈቱ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት ፓርቲያቸውን ነጥብ እንዳስጣሉት ማስታወሱ በቂ ነው፡፡ በውይይት ተከራክረው ለማሳመንም የተካኑ ወይም የታደሉ አይደሉም፡፡

ይህም ቢሆን አንድነት የቤት ስራውን ጨርሶ ለምርጫ ውድድር ከደረሰ ነው፡፡ እንግዲህ ምርጫው የቀረው ከአንድ አመት ያነሰ ጊዜ ነው፡፡ እጩዎችን ማዘጋጀትና ቅስቀሳ ማድረግን ጨምሮ ከወዲሁ በርካታ ስራዎች መፈፀም አለባቸው፡፡ አንድነት ግን በዚህ ሁኔታው ከቀጠለ ለ2007ቱ ምርጫ የሚደርስ አይመስልም፡፡ ስለሆነም በድረስ ድረስ የመንግስት ስልጣን ለማግኘት ምርጫ ውስጥ ገብተው ክፉኛ ከመዘረር መጀመሪያ የፓርቲ ሊቀመንበርነትን ስልጣንን አጥብቆ መያዝን ሊመርጡ ይችላሉ፡፡ ብብት ስር ያለውን አጥብቀው ሳይዙ ቆጥ ላይ መንጠራራት ሁለቱንም ሊያሳጣ እንደሚችል ጠንቅቀው ያዉቁታል፡፡

******

Kebede Kassa

more recommended stories