የፖለቲካ ወይስ የአዕምሮ ምስቅልቅል? – የዶ/ር መረራ ጉዲና መጽሐፍ ዳሰሳ

(ሽመልስ አብዲሳ)

የመጽሐፍ ርዕስ፡- ‹‹የኢትየጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች – ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ››
ደራሲ፡- ዶ/ር መረራ ጉዲና
የተታተመበት ዘመን፡- ነሐሴ 2ዐዐ5
የመጽሐፍ ግምገማ፡- በሽመልስ አብዲሳ

መግቢያ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የሕትመት ብርሃን እያዩ ለአንባቢያን እየቀረቡ ያሉትን መሰል ሥራዎች በአንፃራዊ ብዛታቸውና ብዝህነታቸ ለታሪክ ‘ለፖለቲካ ሳይንስና ለሥነፅሁፍ ተመራማሪዎች ዓይነተኛ የጥናት ርዕስና ግብአት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይሰማኛል፡፡ ከእድሜ ባለፀግነቱ ጋር ለታሪክና ለትውልድ የሚጠቅም የሕይወት ልምድ አለን የሚሉ ዜጎች ከአገር ውስጥም ከውጭም የሕይወት ታሪካቸውን ለሕዝብ እያደረሱ ነው፡፡ እዚህ ላይ የንባብ ልምድ ‘የአንባቢው ፍላጎትና የፀሐፍያን ብቃትም ከፍ እያለ መምጣቱን ከሚያሳዩ ምልክቶች አንዱ ‹‹Tower in the Sky›› የተሰኘው የሕይወት ተፈራ በእንግሊዘኛ የቀረበ መፅሀፍ ነው፡፡

‹‹የኢትየጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች – ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ›› በሚል ርዕስ፣ ‹‹የሚበላውን ያጣ ሕዝብ መሪውን ይበላል›› በሚል ትዕምርተ-ጥቅስ ታጅቦ በነሐሴ 2ዐዐ5 ዓ.ም ለንባብ የበቃው የዶ/ር መረራ ጉዲና መጽሐፍ ላይ ምልከታ ለማቅረብ ስነሳ ሁለት የዳሰሳ ሥልቶች ከፊቴ ተደቀኑ፡፡ የመጀመሪያው መጽሐፉን በቴክስትነቱ ማለትም በራሱ ብቻ የቆመ ወጥ የፅሁፍ ውጤትነቱ ተረድቼው በውስጡ ባነሳቸው ወይም ሊያነሳቸው እየተገባ በዘለላቸው ጉዳዮች ላይ ብቻ ተወስኘ መቃኘት ሲሆን ሌላኛው ይህን መጽሐፍ በመረዳት ረገድ ተጨማሪ ትርጓሜ ለማግኘት መጽሐፉን ከሌሎች ጽሑፎች ጋር በማነፃፅር ማቅረብ የሚለው ነው፡፡ ይህን የንፅፅር ምልከታ ሳስብም እንደገና ሁለት የማነፃፀሪያ አማራጮች ታዩኝ፡፡ አንድም ዶ/ር መረራ ቀደም ሲል ካሳተሟቸው መጻሕፍት ጋር ካልሆነም በሌሎች ደራሲያን ከተፃፉት በይዘትም በቅርፅም ተመሳሳይ ከሆኑ የሕይወት ትዝታዎች ጋር ማወዳደር ይሆንና የንፅፅር ምልከታው የራሱ የሆኑ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም በተለይ ለዚህ መሰሉ ውይይት ጉዳዮች የበለጡ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡Dr Merera Gudina book

የዚህን መፅሀፍ ዶ/ር መረራ ራሳቸው ከዚህ በፊት ካሳተሟቸው መፅሐፍ ከአንዱ ጋር ቢቀርብ ተነፃፃሪዎቹ ፅሁፎች በዘውግ (Genre – ዣንራር) የማይጣጣሙ ይሆናሉ፡፡ Academic ጽሑፉና “የሕይወት ትዝታ” ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቀል የሚሉት አይነት ነው፡፡ የዶ/ር መረራን መጽሐፍ በሌሎች ደራሱያን ተፅፈው ከቀረቡ መሰል የሕይወት ትዝታ (Autobiograhy) መፅሐፍት ጋር ለማነፃፀር ደግሞ የመረጣ ሥራው ውስብስብ ይሆናል፡፡ በዘመን ‘ በቦታ’ በይዘትና በቅርፅ የሚቀርበውን መፅሐፍ የመምረጫ መሥፈርቱ ከአስማሚነቱ ይልቅ አከራካሪነቱ ስለሚያይል ጉዞውን ትቶ በአካሄድ ላይ ፀጉር ስንጠቃ መንገድ አያሳጥርምና የዚህን መፅሐፍ ወጥ ፅሁፍነት በመረዳት የምልከታዩን ሥልት በዚህ ላይ ብቻ እወሥናለሁ፡፡

ሆኖም ወደ መፅሐፉ ይዘት ስንገባ ፅሁፉ ያነሳቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ለመስጠት ጊዜ ስለማይበቃኝ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ለማተኮር እገደዳለሁ፡፡ ከወዲሁ አድማጮቼን ለማሳሰብ የሚፈልገው የስነ ፅሁፍ ሀያሲ አለመሆኔንና አስተያየቴ ፖለቲካዊ በሆኑና በተለይ ደግሞ በወቅቱ ፖለቲካ ላይ እመረኮዝና የማጠነጥን ይሆናል፡፡ መፅሐፉ 12 ምዕራፎችና 264 ገፆች ሲኖረው የመጀመሪያዎቹ 4 ምዕራፎች የህይወት፣ የት/ቤት፣ የፖለቲካ ትግልና የንጉሳዊ ስርዓቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ከምዕራፍ 5 እስከ 7 የ1966ቱን አብዮት እና ድህረ አብዮት ሁኔታዎችና የእስር ቤት ቆይታና የአዲስ ሕይወት ጉዞኣቸውን ያሳዩበት ነው፡፡ ከምዕራፍ 8 እስከ 12 አዲስ የፖለቲካ ህይወታቸውን፣ የ1997ቱን ምርጫ፣ የዲያስፖራ ፖለቲካ፣ የ2002 ምርጫና መደምደሚያ የያዘ ነው፡፡ ምልከታዩ በጥቃቅንና ዝርዝር መረጃዎች ተጠምዶ እንዳይወሳሰብ አንኳርና መሠረታዊ የጭብጥ እና የቀረፃ ጉዳዩች ዙሪያ ላይ በማጠንጠን በሁለት ክፍሎች ተዘጋጅቷል፡፡ የመጀመሪው የመፅሐፉን ፋይዳ የምዳስስበት ሲሆን ሁለተኛው ፅሁፉ ያለበትን እንከኖች የምጠቁምበት ይሆናል በመሆኑ በጥንካሬው እጀምራለሁ፡፡

ጥንካሬዎቹ

መፅሀፉን ዋጋ ከሚሰጡት ጥንካሬዎቹ የመጀመሪያው በታሪክ ውስጥ የግለሰብ ሚና ያለውን ሥፍራ ጠቋሚ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ እንደሚታወቀው ዘንድሮ የ196ዐ ዓ.ም አብዮት 4ዐ ዓመት ይሞላዋል፡፡ ዛሬ ላይ ሆነን ትላንትን እንዴት እንዳለፈ መፈተሽ ነገን ለማሣየት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ረገድ #የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች$ ከተባለው የዶ/ር መረራ መፅሀፍ መታተም የምናገኛቸውን አንኳር ቁምነገሮች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄን ይሁን ለጥቂት ቦግ ብሎ በተደራጁ የወታደሮች ቡድን የተጠለፈውን የኢትዮጵያ አብዮት በተመለከተ በርካታ ጥናቶች በተለያዩ ቋንቋዎች ለንባብ በቅተዋል፡፡ የአብዛኛዎቹ ጽሁፎች የትንተና ምሰሶ የፖለቲካ ድርጅትና መንግስታዊ መዋቅር በመሆኑ ‘ በተማሪዎች ንቅናቄ በኢትዮጵያ አብዮትና ከዚያም በኃላ ባሉ አብይ የፖለቲካ ሂደቶች ውስጥ ዋና ተዋናይ ስለነበሩና ስለሆኑ ሰዎች ግላዊ ሕይወት ፤ ማለትም ትውልድና እድገታቸውን ‘ሕልማቸውን ‘ ምኞታቸውን ‘ደስታቸውን ‘ሀዘናቸውን ‘ ጥላቻቸውን ‘ተስፋቸውን ‘ሥጋታቸውን ‘ ድካማቸውን ‘ብርታታቸውን የፈለግነውን ያህል ልናገኝ አልቻልንም ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ ሁኔታ በመቀየር ላይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ የዶ/ር መረራ መጽሐፉን በዚህ አውድ ስፈትሸው ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ የኢትዮጵያ አብዩትና በተለይም በመ.ኢ.ኦ.ን ‘ኦብኮ’ ሕብረት በኃላም መድረክ ተብለው ለሚታወቁ የፖለቲካ ድርጅቶች ለሚያጠኑ አጥኚዎች ሆነ መላው አንባቢ ትወና ያለተዋንያን እንደማይኖር ሁሉ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ያለአንቀሳቃሽ ግለሰብ አይታሰብምና ስለነዚህ ፖለቲከኞች ሕይወት ያለን እውቀት እንዲጨምር ስላደረገ ይህ መጽሐጽ እንኳን ታተመ እላለሁ፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲና የኦሮሞ ርለቲከኛ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ፖለቲካ ከተቀሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፖለቲካ ጋር ያለው ዝምድና አሊያም ባዕድነትን በተመለከተ በመፀሐፋቸው በግልፅ በቀጥተኝነት አቋማቸውን አስቀምጠዋል፡፡ የኦሮሞ ፖለቲካ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፖለቲካ ጋር ያለውን ዝምድና ወይም ባዕድነትን በተመለከተ ዘመናትን ያስቆጠረ ክርከር መካሄዱና አሁንም በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የተሰወገ አይደለም፡፡ በእኔ አረዳድ የዝምድናው መሠረት ሆነ የባዕድቱ ግድግዳ አመጣጥ በጥሞና ለመረደት በዋናነት ንቁ ፖለቲከኞቹና ፋናወጊዎቹ የመጡበትን ማህበዊ ዳራ /Social Background/ ማጥናቱ የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ በኦሮሞ ዘመናዊ ፖለቲካ አነሳስ ላይ የመልከአ ምድር/ Geopolitics/ የተጫወተው ሚና በቀላሉ እንደማይታይ በ196ዐዎች በባሌ ‘ በሐረርጌ ‘ በሸዋና በወለጋ ያቆጠቆጡት የኦሮሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በኃላ ኃላ ወደየሰበት ማዕከላቸው መጠቅለላቸው ማሳያ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ዶ/ር መረራ በመፅሀፋቸው እንዳስረዱት የኦሮሞ ፖለቲካን ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር ስላለው ዝምድና ጉዳይ ሲመለስ ዶ/ር መረራ ኦሮሚያና ኢትዮጵያ የተሰኘውን የባዕድነት የአመለካከት መሥመር መሠረተቢስነት ከታሪክ እያጣቀሱ እና ራሳቸውም የኖሩበትንም እያስታወሱ የመደብ ትንተናን ተጠቅመው አስረድተዋል፡፡ የአንድ ሰው ተሪክ ቢሆንም ይህ መሰሉ መፅሐፍ ቋሚ ምሰክር የሚሆኑ ሀቆች በመያዙ በዚህ ረገድ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው እላለሁ፡፡

በነገራችን ላይ ዶ/ር መረራ ይህን በማድረጋቸው ውጣ ውረድ በበዛው በሕይወት ዘመናቸው # ጠላትነትን ያተረፉት$ በመፃሀፋቸው እንደሚነግሩን ከኦሮሞ ፅንፍ ብሔረተኞች ነው፡፡ እዚህ ላይ በኦሮሞ ፅንፍ ፖለቲከኞች ዘንድ ያለው ስለኢትዮጵያ መሥማተ ያለመፈለግ ስሜት ‘ ከከተሜነት መስፋፋት ጋር በህዝቦች መሥተጋብር ወቅት ሊያጋጥም ከሚችል የባህል ምች ( Culture shock) ራሳቸውን ለማዳን ግላዊና የቡድን ስብዕናና ማንነትን በመገንባት የሥነልቦና ልዩ ዞን ከመፍጠር ባሻገር ለህዝባቸው ጥቅምና መብት መከበር አንዳችም ፋይዳ እንደሌለው መፅሀፉ የበለጠ እንድንገነዘብ ይረዳናል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ሰለ ጥቅም ኢትዮጵያ እንጂ ስለዝርዝር ህዝቦቿና ብሔረሰቦቿ በተለይም ስለ ኦሮሞ ፖለቲካ መነጋገር ቅቡልነት ያለው መሠረታዊ ጉዳይ ሳይሆን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ሴራ አድርገው ለሚያዩትም በአንዳድ የዶ/ር መረራ መፅሀፍ ይዟል፡፡ ፀሐፊውና ሌሎች ሚሊዮኖች ኖረው ያጋጠማቸውን የግፍ ኑሮ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ አራማጆች በስዕለ ሕሊናቸው የፈጠሩት ምናብ ነው ማለት ለሚዳዳቸውም ከእውነት ጋር መታረቅ የሚችሉበትን እድል አስፍቶላቸዋል ማለት እችላለሁ፡፡ በዚህ ገረድ ፀሐፊው የአካዳሚክ እውቀትና ሙያቸው ከፖለቲካ ልምዳቸውም ጋር ተጣምሮ ያመኑበትንና የኖሩበትን የኦሮሞ ፖለቲካ ምንነት በግልፅና በልበ ሙሉነት የቀረቡበት በመሆኑ በብሔር ጥያቄ አፈታት ላይ በአቋም መዋዠቅ ለሚሰቃዩ ራሳቸውን እንዲመረምሩ አጋጣሚውን የሚፈጥር ፅሁፍ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ›› የተሰኘው ይህ የዶ/ር መረራ መፅሀፍ ከያዛቸው አበይት ቁም ነገሮች አንዱ የፖለቲካ አመለካከታቸውንና አቋማቸውን ከግብ ለማድረስ የተከተሉትን ሰላማዋ የትግል ሥልት በማያሻማ መልኩ በግልፅ ማስቀመጣቻውና ከሳቸው በተቃራኒ የተንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ድርጅቶች በተከተሉት የትግል መስመር ምክንያት በጃቸው ገብቶ የነበረውን መልካም አጋጣሚና እድል እንዴት እዳመለጣቸው ማሳየት መቻላቸው ነው፡፡ በተለይ የ1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው የፖርላማ መግባት ያለመግባት ክርክር እና በተለይ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፖርቲ የውስጥ የስልጣን ፍትጊያ እና ሌሎችም ተያያዥ ውጣ ውረዶች የድርጅት አቅምና የአመራር ንቃት ውስንነት ውጤት እንደሆነ አሳየተውናል፡፡ ይህ መሰሉ አስተያየትና ትችት የመንግስት ተቃዋሚ ሆኖ በሌላው ተቃዋሚ ላይ የእርምት አስተያየት መሰንዘር በበጎ በማይታይበት ዘመንና ቦታ የዶ/ር መረራ መፅሀፍ ፈርቀዳጅ ነው በይባልም ለዚህ መሰሉ የመተራረም ባህል መዳበር የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል ብዩ አምናለሁ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የመፅሐፉ ይዘት ግላዊ ፐርሰናል በመሆኑ አንባቢያን እንድያስቡና በዶ/ር መረራ ህይወት ውስጥ እንዲመለከቱ በማድረጋቸው ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ በልጅነት ህይወታቸው ያሰለፉት ውጣ ውረድና የነበራቸው ጽናት አስተማሪና የትላንትናዋ ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስል ወደፊት ለማሳየት ሞክሯል፡፡

በተጨማሪ በአንድ በኩል የፖለቲካ መሪነት ሀላፊነት በሌላ በኩል በአካዳሚክ ተወጥረው ሳሉ ባለቸው ጥቂት ጊዜ በህይወታቸው የነበራቸውን ተሞክሮ ለማካፈል ይህ መፅሐፍ በመፃፋቸው አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ ሌላው አንኳር ነው ባይባልም የዶ/ር መረራ መፅሀፍ እንደፖርላማ እና እንደምርጫ ቅስቀሳ ንግግራቸው በቀልድና በፌዝ የታጀበ በመሆኑ አንባቢ ሳይሰላች ዘና ብሎ እንዲያነብ የራሱን አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ሳልጠቅስ አላልፍም፡፡

እንከኖች

1. የሁሉ ነገር ቀጣይነት

በኔ እይታ በአጠቃላይ መፅሐፉን ስንቃኝ “It’s the narrative of political continuity” ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህንን ለመግለጽ አዳጋች ቢሆንም በተቻለ መጠን አጠር አድርጎ ለማስቀመጥ ሙከራ አደርጋለሁ፡፡ የመፅሐፉ የስበት ማዕከላዊ ሆኖ ያገኘሁት የኢትዮጵያ የ40 አመት የፖለቲካ ሂደት መሠረታዊ ለውጥ ያልታየበትና እንዲሁም ወሳኝ ተብለው የተቀመጡ ተግዳሮቶች በቀጣይነት አሁንም እንዳዚሁ የሚቀርብ ትረካ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በሌላ አነጋገር ፀሐፊው ለአብነት በሚያነሳቸው በሁሉም በምዕራፎች ላይ ተመሳሳይና ቀጣይነት እንዳላቸውና መሰረታዊ በህሪያቸው አሁንም ቀጣይነት እንዳለውና አሁን እንዳልተፈቱና ደራሲው ደግሞ ይህንን ለመቅረፍ በግልም ሆነ በተደረጃ ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ነግረውናል፡፡ የእሳቸው ግላዊ ጣልቃ ገቢነት እንደተጠበቀ ሆኖ የፅሑፉ መዋቅራዊ ችግር በላይ በመሆኑም የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሂደት ስር ነቀል ምእራፎችን ያሰለፈ ቢሆንም እሳቸው በተቀራኒው ቀጣይነት ብቻ ለማጎላት የቀረቧቸው ክርክሮች በኔ ግምት አጥጋቢና የተሳኩ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ለዚህም ለአብነት ያህል የሚከተለውን “counter argument” ነጥቦች ከራሳቸው መፅሐፍ እያጣቀስኩ ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ በኔ እድሜ ውስጥ በተከሰቱ ለውጦች ላይ በማነጣጠር ማየት ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለው፡፡

ሀ. የ1966ቱ ለውጥ
የተማሪው ትግል፣ የገበሬ፣ የከተማ ነዋሪና የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ባደረጉት መራራ ትግል መሰረቱ የተገዘገዘውን ንጉሳዊ ስርኣት በተሻለ መልኩ ተደረጅቶ የነበረው ደርግ ስርኣቱን አፍርሶ በወታደራዊ መንግስት በመተካት ትግሉን ቢያጨናግፍም የመጡ ለውጦች አሉ፡፡ ስለደረግ በነበረው ትግል ውስጥ ዶ/ር መረራም ምስክርነት እንደሰጡት የመደብ ጉዳይ አንዱ ወሳኝ ነጥብ ነበር፡፡ ለዚህም መሰረት የሆነው መሬት በጥቂት መደቦች እጅ የነበረውን አፍርሶ መሬት ላራሹ አድርጓል፡፡ ነገር ግን በመሬቱ ላይ ምን ያህል ይጠቀማል የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ስለዚህም በዚህ ታሪካዊ ምእራፍ ያልተመለሱ የብሄር ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች እንደተጠበቁ ሆናው ኢትዮጵያ ውስጥ መሬት ኢኮኖሚ፣ ፖላቲካና ማህበረዊ እንዲሁም ሁሉ ነገር የሆነው ከሞላ ጎደል “address” ተደርጓል ማለት ይቻላል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ሳይሆን አንድ የፖለቲካ x!ኮኖሚ ምእራፍ የተሸጋገርንበት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ለ. የ1983ቱ ለውጥ
ዶ/ር መረራ በመፅሐፋቸው ውስጥ የብሄር ጥያቄዎችን ውሃ ቸልሰውበት እንዳለፉት ሳይሆን ትልቅ መሰረታዊ ችግር ነበር፡፡ እሳቸው ራሳቸው እንደጠቀሱት ለራሳቸው ጉዳይ ፍርድ ቤት ሄደው አንድ ተከሳሽ በማይሰማው ቋንቋ የሞት ፍርድ ሲፈረድበት አስተርጓሚው የተሳሰተ ትርጉም ሰጥተውት ወደ ሞት የሚሄደው ሰውዬ በደስታ እጅ ነስቶ እንደወጣ ገልፀውልናል፡፡ ይህ ችግር መሰረቱ ሰፊና ለብዙ ትግሎች መሰረት የሆነ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመሃከላቸው ለረጅም ዘመናት ግንኙነት ቢኖራቸውም ግንኙነቶቻቸው ግን ኢ-ሰብኣዊ ኢ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ፍትሓዊ ነበር፡፡ በዚህ መሃል የነበሩትን መልካም ግንኙነቶችን ማበልፀግና ህiፆቹን ማረም አስፈላጊ ነበር፡፡ ይህንንም ለማድረግ በ1987 በፀደቀው ህገ መንግስት መሰረታዊ መፍትሄ እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ በዚህም አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምእራፍ የተሸጋገርንበት ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሐ. መሰረታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጦች
በዶ/ር መረራ መፅሐፍ ውስጥ በተለያየ መልኩ ስገለፅ የነበረው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚዊና ማህበራዊ ችግሮች ከህገ መንግስቱ በመነጩ ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎች የኢትዮጵያ ጠላት የሆነውን ድህነትና ኋላቀርነትን እየተፈቱ ይገኛሉ፡፡
* በትምህርት ከጥቂቶች መብት ወደ ሁሉም ተደራሽነት ከሺዎች ወደ 23 ሚሊዮን ተሸጋግሯል፡፡
* በጤና በመደብ ህክምና ቀርቶ እስከ ቀበሌ ተዳርሷል፡፡
* በንጹህ መጠጥ ውሃ ከከተማ መብትነት ብቻ ሰብሮ ወጥቶ ገጠሪቷን ኢትዮጵያ በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡
* የመኪና መንገድ ለማግኘት ከአንድ ከሁለት ቀን እግር ጉዞ ወደ 20ና 30 ደቂቃ በአማካኝ ወርዶል፡፡
* ገጠሩ የችጋር ማእከል ሳይሆን የልማት ማእከል ሆኗል፣ እና ወዘተ ሽግግሮች ከነውስንነታቸው ሊሳኩ ችለዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ግን በየመፅሐፉ ክፍል ሁሉ አሁንም ቢሆን እያሉ የችግር አቀንቃኝ የሆኑበትን ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ያሉትን ችግሮች ካሉት ለውጦች እውነታን ለምን ማየት እንዳቃታቸው ለኔ እንቆቅልሽ ነው፡፡ እሳቸው ontologically የአእምሮአቸው አቀማመጥ መሰረታዊ ችግር እንደለበት ያሳያል፡፡ እውነታን ለመቀበልና ለማስተናገድ ዝግጁ እንዳልሆኑና ሁሌም ጨለማ’ ጥፋት እልቂት’ ሰቆቃ እንጂ ለውጥ የማይታያቸው መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ባህሪያቸው አንድ ፊልም ያስተውሰኛል፡፡ ጋሊሊዮ ጋሊሊ በግኝቱ በዳረገው ኮፐርካል አብዮት መሬት በፀሃይ ዛቢያ ትዞራለች በሚለው ላይ ተከሶ ሞት ሲፈረድበት ፈራጆቹን ቄሶች ለማስረዳት ቴሌስኮፑን እንዲመለከቱ ሲጠይቃቸው ካየን ልንፈርድብህ አንችልም እኛንም ቢያሳምነን ብለው እምቢ ያሉትን ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡

2. የሐሳብ ግርድፍነት

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዋች$ ለአንባቢ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ‘እይታዎችንና አስተያየቶች ያካተተ መፅሀፍ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ከዘውዳዊ ሥርዓት ጀምሮ እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ አንባቢያን ሊማሩባቸው የሚችሉ የሕይወት ልምዶች ተጠቅሰዋል፡፡ ይሁንና ዶ/ር መረራ ካላቸው የፖለቲካ ሳይንስ እውቀትና ሰፊ የምርምር ልምድ አንፃር መፅሀፉ የፖለቲካ ትንተና ውስንነት ይታይበታል፡፡ በርግጥ መፅሀፉ የሕይወት ትዝታ የቀረበበት ነው፡፡ የሕይወት ተዝታውም በዋናነት ፖለቲካዊ ነውና እግረመንገድ የሚጠቀሱ ፅንሰ ሀሳቦች አልጠፉም፡፡

ከነዚህ ፅንሰ ሀሳቦች ዋነኛው ራሱ የፖለቲካ ምስቅልቅል$ ምንነት ነው፡፡ የፖለቲካ ምስቅልቅል ምንድነው? በምንስ ይገለፃል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይህ ምስቅልቅል መቼ ጀመረ? ሂደቱ እንዴት ነው? አሁንስ; እነዚህና ሌሎችም መልስ የሚሹ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ካልን ፅንሰ ሀሳብ ከግል ስሜትና ከግል አስተያትነት ያላለፈ በምናብ የተፈጠረ በተጨባጭ ሁነትነት የማይታወቅ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሌላው በመፅሀፉ የተነተና ውስንነት የታየበት ርዕስ ጉዳይ፤ ከ1966 ዓ.ም አብዮት ማግስት ጀምሮ ብቅ ብቅ ስላሉት አገር አቀፋዊና የብሄር ድርጅቶች ስምና ግለሰቦችን ከመጥቀስ ባለፈ ድርጅቶቹ ቡድኖችና ግለሰቦቹ በዓላማ በፖለቲካ አቋምና የትግል ሥልት በኩል ያላቸውን ተመሳሳይነት ልዩነት እግረመንገዳቸውን ( በግርጌ ማስታወሻነት እንኳን) ሊያስቀምጡልን ይገባ ነበር ብሎ አምናለሁ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ፀሐፊው ተቋማትን የፖለቲካ ንቁ ተሳታፊዎችን መንግስታትን ምንነትና ባህርይ ሲገልፅ የአቃላይነትን ( Reductionist) እይታ ማዘውተራቸውም ሊወሳ የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
ለምሳሌ በመፅሀፋቸው መደምደሚያ ላይ ዶ/ር መረራ እንዲህ ይላሉ፡፡

‹‹አብዛኛው የትግራይ ልሒቃን ሥልጣን ወይም ሞት$ ብሎ ሥልጣን ላይ የሙጥኝ እስካለ ድረስ አብዛኛው የአማራ ልሂቃን በአፄዎች ዘመን የነበረውን የበላይነትን መልሼ አገኛለሁ ብሎ የሚገፋውን የሕልም ፖለቲካ እስካለተወ ድረስ ፤ ብዙሃኑ የኦሮሞ ልሂቃን ኦሮሚያን ለብቻ የመውጣቱን (ነፃ ይመስለኛል) ሕልም እስካለተወ ድረስ ሀገራችን ከአደጋ ቀጠና የምትወጣ አይመስለኝም››፡፡

ከዚህ አረዳድ አራት አጠቃላይ ድምዳሜዎች ማውጣት ይቻላል፡፡
1. ሀገራችን የአደጋ ቀጠና ውስጥ ናት
2. አብዛኛው የትግራይ ልሂቃን ሥልጣን ወይም ሞት$ ብሏል
3. አብዛኛው የአማራ ልሂቃን የአፄውን ዘመን ለመመለስ ያስባል እና
4. ብዙሀኑ የኦሮሞ ልሂቃን ኦሮሚያን ለብቻ ነፃ የማውጣት ሕልም ውስጥ ነው፡፡

ለነዚህ ድምዳሜዎች ደጋፊ የሆኑ ሳይንሳዊ መሠረት ያላቸው ማስረጃዎች አልቀረቡም፡፡ ‹‹ሀገራችን የአደጋ ቀጠና ውስጥ ናት›› የሚለው ከ2ዐ ዓመታት በፊት ጀምሮም እስካሁን የቀጠለ የተቃውሞ እህል ውሃ ስላልሆነ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

የሽግግር መንግስት ሲመሰረትም የአባይ ግድብ መሠረት ሲጣልም የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ላለመቀበል የሚደረገው ‹‹አይኔን ግንባር ያርገው›› እና ‹‹የዝንጀሮ ጆሮ ይስጠኛ›› ፀሎት አንድ ብሬሽት በተባለ ፀሐፊ ተውኔት የተደረሰ ትያትር አስታወሰኝ፡፡ የጋሊሊዮ ጋሊሊ ከሳሽ ቀሳውስት ቴሌስኮኘ እንዲያዩና ስለመሬት ሁነት እንዲረዱ ሲጋበዙ እንዳሉት ቴሌስኮፑን አይተን እውነቱን ካወቅን እንዴት አድርገን ጋሊሊዮ ጋሊሊ ላይ ሞት እንፈርድበታለን ብለው ግባዣውን ሳይቀበሉት ይቀራሉ፡፡ እናም አለማየትም አለማመንም እጅግ ምርጥ የተባለው መርህ ነው የተቃውሞ ቅድመ ሁኔታው አገሪቱን አደጋ ውስጥ እንደለች አድርጎ ማሰብ ነው፡፡

ፈላስፋው ኒቼ እንደማለው ሀሰት ማለት ያልሆነ ንግግር እንደሆነ ማውራት አይደለም እንደውም ይሄ ቀላል ሀሰት ሊባል ይችላል፡፡ ካልን ሀሰት የሚታየው ውሸት እፊታችን የተደነቀነውን ለማየት እና እውቅና ለመስጠበት ያለመፈለግ ነው ይለናል፡፡

አብዛኛውን የትግራይ’ የአማራና የኦሮሞ ልሂቃን በቅድመ ተከተል በመፍቀሬ ስልጣን ‘ በአፄ ናፋቂነትና በጠባብነት ብቻ መረዳት የአቃላይነት (Reductions) እይታ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህ ድምዳሜ በኢምፒሪካል (Empirical) ማስረጃ ተደግፎ ቢቀርብ ይመረጣል፡፡ ይህም ሆኖ ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በኢህአፖ’በመኢሶን’በኢህአዴግና በሌሎችም የፖለቲካ ድርጅቶች ስር ሕይወታቸውን የገበሩ አፍላ የወጣትነት ጊዜያቸውን መሥዋዕት ያደረጉና ለህዝቦች እኩልነተና ፍትህ ሲሉ የታገሉና በመታገል ላይ ያሉ ዜጎች ዶ/ር መረራ በመፅሀፋቸው ባዘጋጁት ሶስት ከረጢት ውስጥ የማይገቡና ሊገቡ የማይችሉ የተጠቀሱት ብሔሮች ተወላጅ የሆኑ ልሂቃን እንደነበሩና እንዳሉ መረሳት የለበትም፡፡ እነዚህ ከረጢቶች ውስጥ የማይገቡት ጥቂት ናቸው ከተባለም ኢምፒሪካል ማስረጃ ማቅረብ የማይታለፍ የቤት ስራ ነው፡፡ አለበለዚያ የትግራይ ‘ የአማራና የኦሮማ ልሂቃን እንዲህና እንዲህ ናቸው ማለት ከስቴሪዮታኘነት የዘለለ ተርጓሜ ሊሆን አይችልም::

3. ንፍገት

ዘንድሮ የ1966 ዓ.ም አብዮት 4ዐ ዓመት ይሞላዋል፡፡ በዚህ መጽሐፋቸው ፤ ዶ/ር መረራ ባለፉት 4ዐ ዓመት ያሳለፉት ዘመናት በገጠመኞቻቸው አማካኝነት ሊየሳዩን ሞክረዋል፡፡ በመጽሀፉ ሊያሳዮን እንደጣሩት
1. በምዕራብ ሸዋ በተለይ በአምቦና ቶኬ አከባቢ
2. በምስራቅ ወለጋ አርጆ ከተማ በ4ዐ ዓመታት ውስጥ ተያያዥና ተነፃፃሪ ሁነቶች ተስተናግደዋል፡፡

‹‹ምስቅልቅል›› ነው ባሉት በነዚህ ዓመታት የምዕራብ ሸዋ አምቦና ቶኬ አከባቢ የደርግን ጭፍጨፋ አስተናግዳለች፡፡ የምስራቅ ወለጋ አርጆም ኃይሌ ፊዳን እንደፈራች ተርከውልናል፡፡ አርጆ የተወለደው ኃይሌ ፊዳም ከእሰርና እንግልት በኃላ በግፍ እንደተገደለ ዶ/ር መረራ በአንፅኦት ተርከውልናል፡፡ እነ ዶ/ር ተረፈ ‘ዲማ ጉዲና’ ኃይሌ ፊዳና ሌሎችም ከተገደሉ ከጥቂት አስርት ዓመታት በኃላ ግን ፀሐፊው ለምርጫ ቅስቀሳ በአምቦና በአርጆ ከተማ ሲንቀሳቀሱ የዚያ የፈተናና ሰቆቃ ጊዜ ተቀይሮ የተስፋና የልበሙሉነት ስሜት ይሰማቸው እንደነበረ አልሸሸጉም፡፡ ለመሆኑ ፈተናና ሰቆቃውን ወደ ተስፋና ልበሙሉነት ምን ቀየረው; አርጆ ላይ የኃይሌ ፊዳን ወንድም ሲያዩና እን ዶ/ር ተረፈ ‘ ዲማ ጉዲናንና ሌሎችንም አስታውስው ከምር ለማልቀስ ያልቻሉት ምን አግኝተው ነው; የትግል ጓዶቻቸው እንደወጡ ቀርተው ሞታቸው ከንቱ ከፍያለ ደረጃ ለመድረስ ከታደሉት ጥቂቶች አንዱ መሆናቸውን ተገንዝበው ተሥፈኛና ልበሙሉ ባደረጋቸው በዚህ እድል ለመጠቀም ፤ የማንጓጠጥና የሽርደዳ ፍቅራቸውን የባለ ሥልጣናትንና በተቋማትን የማንቋሸሽ አምሮታቸውን ለነዶ/ር ተረፈ’ለዲማ ጉዲና ለይሌ ፊዳ ሞት ሲሉ ዋጥ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በዚህ ረገድ የሞቱት በአንዳንድ ሕያዋን ግላዊ ፍላጎት ሊካዱ እንደሚችሉ ተገንዝቤያለሁ፡፡

ዶ/ር መረራ በመፅሀፋቸው እንዳብራሩት ወደፖለቲካ የተሳቡበት መንገድና የተሳትፏቸው አይነተ ለሕዝባዊ ጉዳዮች ከመቆርቆር ለዚየም ምላሽ ለመሥጠት ከመሻት ይልቅ ከግል ገጠመኞቻቸው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይናገሩናል፡፡ ሁለት ምላሴ ላንሳ ከ1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ አብዮት መንግስት በታዘዘው የእድገት በህብረት የእውቀትና የስራ ዘመቻ ወቅት ዶ/ር መረራ ከተመደቡበት ዩብዶ ወለጋ የፍ/ቤት ክርክር አለኝ በሚል ሰበብ ወደ ትውልድ ቦታቸው ሄደዋል፡፡ የሄዱት ግን በአገርና በዘመድ ናፍቆት ተቸግረው አልነበረም፡፡ ገፅ59 ላይ እንዲህ ይላል ምክንያት ልጅ ሆኜ በቤተሰባቼ ላይ ግፍ ከሰሩብን ባላባቶች ጋር የቆየ ሂሳብ ለማወራረድ ነበር$ አብዮትን ለግላዊ ቂም በቀል መወጫ እየተጠቀሙበት ስለፍትህና ዲሞክራሲ ማውራት አብረው የሚሄዱ ነገሮች አይመሥሉኝም፡፡

ሌላው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ ሊመሠረቱ የቻሉበት ሁኔታ ነው፡፡ ራሳቸው ከሰጡን መረጃ እንደምንረዳው የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ የግል እልህ የወለደው ድርጅት ነው፡፡ ገፅ156 ላይ እንዲህ ሲሉ ፅፈዋል ጨርሶ ባልጠበቅኩበት መንገድና ጊዜ ወደ ፖለቲካ ፖርቲ የመፍጠሩ ስራ ያስገባኝ ኢህአዴግ ሳይሆን ‘የኦነግ ዘመዶቼ ናቸው$ ነገሩን ሲያብራሩም በገፅ 158 ላይ በኡረጂና ሰይፈ ነበልባል ያልጠበቅኩት የማዲያ ጦርነት ተከፈተብኝ እንዲያቆሙ ብለምንመ የሚሰማኝ ጠፋ$ የሚፃፈሙ መረራ ፖለቲካ አይገባውም ወንድሙን በደርግ አስገድሎ አገልግሏል የሚል ድረስ ነበር፡፡ ቀይ መስመር ያለፉትም ወንደሙን ቆሞ አስገድሎ የደርግ ኢሰፖ ሹመት ለውለታው አገኘ የሚለውን ሲጨምሩበት ነው ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ ኡርጂና ሰይፈ ነበልባል የሚዲያ ጦርነት ባይከፍቱ ኖሮስ ተብሎ ሊጠየቅ ይችላል መልሱን ለታሪክና ለፖለቲካ ሳይንስ አጥኜዎች ትቼዋለሁ፡፡

በ26ገፆች ያለምንም የውስጥ ፎቶግራፎችና መግለጫዎች የፖለቲካ የህይወት ተሞክሯቸውን ለአንባቢ ያቀርቡት ዶ/ር መረራ እጅግ በርካታ የሚባል ርዕስ ጉዳይ አሳተሙ፡፡ አንዳንዱን በዝርዝር ሌላውን በስሱ ሌውንም በስም በቻ በማንሳት ትክክል ነው ያሉትን ትዝታ አቅርበውልናል፡፡ ይህ የሕይወት ትዝታቸው የቃኙበት መፅፍ ቢሆንም ከህይወት ጉዞአቸው ጋር ተያያዥነት ያላቸው አንዳንድ ሊታለፉ የማይገባቸውን ፖለቲካዊ ርዕስ ጉዳዮች ዳስሰውልናል፡፡ ለምሳሌ ‹‹የኢትዮጵያ ዲያስፖራና የኢትዮጵያ ፖለቲካ›› ብለው ጉዳዩን ለምዕራፍ እንዲመጥን አድርገው ማቅረባቸው የሚመሰገን ነው፡፡ ነገር ግን እንደፖለቲካል ሳይንስ ምሁርነታቸው ሚዲያንና ፖለቲካን በተለይም ከ1997 ምርጫ ሂደትና ውጤት ጋር አያይዘው ይተነትኑልናል የሚል ጉጉበት ነበረኝ፡፡ በምርጫ ክርክር ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ተክለሰውነት እንዲገነቡ እና ሀ ብሎ ህዝቡ እንዲያውቃቸው የሚችሉበት እድል መፍጠራቸውና መድረክ ማመቻቸታቸውን ፤ የግል ጋዜጦች ደግሞ በተለይ በተቃዋሚዎች ውሳኔዎች ላይ ያሳደሩትን በጎም ይሁን ጎጂ ወይም ሌላ ተፅዕኖ አልዘረዘሩልንም፡፡ አብዛኛዎቹ የግል የሚዲያ በተቋማት (ኡርጂና ሰይፈ ነበልባልን ጨምሮ) በማንና ለምን አላማ ማስፈፀሚያ ይታተሙ እንደነበረ ከዶ/ር መረራ አይነቱ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የጥናት ውጤት እንኳን ባይሆን ትዝብትና አስተያየት በአጭር መግለጫ መልክ ይጠበቃል፡፡ የሚዲያና ፖለቲካ በመፅሀፍ አለመካተቱ የመፅሀፉ አብየ ድክመት ይመሥለኛል፡፡

ሌላው ትንታኔ ባይሰጥበት እንኳን ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ከሰላማዊ የትግል መሥመር ውጭ የኢትዮጵያውያንን ጥቅምና መብት እናስከብራለን የሚሉ ቡድኖች ኤርትራ የመቀመጥና የመመላለሳቸው ጉዳይ ነው፡፡ ኦነግና ከቅንጅት ወራሾች አንዱ የሆነው ግንቦት ሰባት (የአሰብ ያለህ እያለ ከመነታረኩ ጋር) ከአራት ኪሎው ፖርላማ ይልቅ አስመራ ቅርብ ሆኖ ማግኘታቸው የፖለቲካ ብስለት ይሁን ክስረት ሙያዊ ጥቆማ ቢሰጥበት መፅሀፉ ምሉዕ ይሆን ነበር፡፡ በመፅሐፋቸው ውስጥ ኢህአዴግ በምርጫ እሳቸውን ለማሻነፍ መብራት እንዳስገባ ያነሳሉ፡፡ ቆይ ዶ/ር መረራን የሚያስጨንቃቸው የቶኬ ኩታዬ ህዝብ ችግር መፈታት ነው ወይስ ምርጫ ማሸነፍ ነው፡፡ ችግሩ የሚታያቸው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በችግሩ ውስጥ ህዝብን በማቆየት የፖለቲካ ኣላማን ለማሳካት እንደ አማራጭ የወሰዱ ይመስለኛል፡፡

በ1997ቱ ምርጫ ዶ/ር መረራ ህዝቡጋ የነበሩትን ብሶቶች ተጠቅሞ የመጀመሪያውንም የመጨረሻውንም ድል ያገኙበትና በመፅሐፋቸው ውስጥ ራሳቸው ላይ እንደመሰከሩት የመረጣቸውን ህዝብ ድምፅ በመናቅ ቴሌቭዥንና ጠቅላይ ሚንስቴሩ በሚገኙበት ቀን ብቻ እንደሚሳተፉና ይይዙ የነበረው አቋማቸው ከህዝቡ እየነጠላቸው የመጣበት ወቅት ነበር፡፡

በ2002ቱ ምርጫ ዶ/ር መረራ አብዛኛዎቹን የሚጠቀሙበትን የህዝብ ብሶቶች ከመሰረቱ ስለተፈቱ እሳቸው እንደሚሉት እኔ” ለማሸነፍ መብራት አስገባ ይበሉ እንጂ ህዝቡ ለኢህአዴግ ድምፁን በመስጠት እሳቸውን ከዜሮ ፖለቲካ ድምር እንዲወጡ ያስተማረ ነበር፡፡

ሌላው በመፅሀፉ ከታዘብኳቸው የፀሐፊውን መንታ ምዘና ወይም double standard ነው፡፡ ገፅ 75 ላይ ዶ/ር መረራ እንዲህ ይላሉ ሙት ወቃሽም ላለመሆንም ጭምር ‘ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው የመንግስቱ ኃ/ማርያም ወዳጅ መንግስቱን መክሮታል የሚባለውም$ ኢህአፖ የሚባለው ድርጅት ኢትዮጵያን ለማጥፋት ስለተፈጠረ ያለርህራሄ አጥፋው ‘መኢሶን የሚባለው ድርጅት ደግሞ አድፍጦ ስለሚወጥህ አንተም አድፍጠህ ዋጠው የሚል ነበር ይባላል፡፡ ይህ ሰው ማነው; ዶ/ር መረራ ስሙን መጥቀስ አይፈልጉም፡፡ ምክንያቱም ሙት ወቃሽ ላለመሆን በመፅሀፋቸው መለስ ዜናዊን ሲያብጠለጥሉ ምን እያደረጉ ነው;

በመጨረሻም አንድ ተራ የሚመስል ግን ጥቅል የሥነ ልቦና ሁኔታን የሚግልፅ ጉዳይ ከመፅሀፉ ላንሳ፡፡ ገፅ 165 ላይ ዶ/ር መረራ እንዲህ ይላሉ ኢህአዴግ ማንን ለመጥቀም እንዳወጣው አላውቅም ፤ እኔ (የውጭ ትምህርቴን) ልጨርስ ሁለት ወራት ሲቀሩት እስክ ላንድ ክሩዝር ድረስ ተማሪዎች ከቀረጥ ነፃ የሆነ መኪና ማስገባት እንደሚችሉ አዲስ ፖሊሲ አወጣ፡፡ እኔም በሕይወቴ ለመግዛት የማላስበውን ቶዮታ ላንድ ክሩዘር መኪና ተበድሬ ጭምር ገዛሁ፡፡ በሀገር ውስጥ ከብዙ ተቃዋሚ መሪዎች የምሻለው በሱ ነው፡፡
መንግስት ለሥራው (ግዴታው ነውና) እውቅናውን ባየጠብቅም ‘የቀረጥ ነፃ ፖሊሲውም ለዜጎች ‘ ፖርላማውም በተለይ በ1997 በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲበዛ ክፍት የነበረው ማዲያም የተቋዋሚዎችን የፖለቲካ ተክለ ሰውነት ገንብቷል፡፡ የተቋዋሚ መሪዋች በሚሊዮኖች ዘንድ ስማቸው የታወቀው በሚያንቋሽሻቸውና በሚያጥላላቸው ተቋማት ድልድይነት ነው፡፡ ተሸጋሪዎች ሁሉ ድልድዩን ከጥቃት የመከላከል የሞራል ግዴታ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ መሻገሩን መፈለግና እዚያው በዚያው ድልድዩን አለመከላከል የዜሮ ድምር ፖለቲካ እንጅ ሌላ አይመሰለኝም፡፡

ደ/ር መረራ በመፅሀፋቸው የመኪና ከቀረጥ ነፃ የመሆኑን ፖሊሲ እንደዛ ሲያጣጥሉ መኪናዋን የሚገዙ (ተበድረው) በኩራት የሚያሽከረክሩም አይመስልም ይህ ነው የፖለቲካ ምስቅልቅል፡፡

4. ስሜታዊ ድምዳሜና ትርጓሜ

«የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የህይወቴ ትዝታዎች$ የተሰኘው የዶ/ር መረራ መፅሀፍ ካሉበት እንከኖች አንዱ በመፅሀፉ ያነሷቸውን ነጥቦች በስሜትና በአሰትያየት ሳይሆን በማስረጃ አስደግፈው ማቅብ አለመቻላቸው ነው፡፡ ዶ/ር መረራ የህይወት ተሞክሮኣቸው ብቻ ላይ ቆመው አጠቃላይ የአገር አቀፍ የፖለቲካ ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ለዚህም ምልከታዬ አንድ ሁለት ምሳሌ አቀርባለሁ፡፡

በገፅ 1ዐ8’132 እና በሌሎችም የፅሁፈ ክፍሎች ደጋግመው አንደሚያነሱት በወታደራዊ መንግስት ዘመን ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ እመቃ ተካሂዷል፡፡ ከራሳቸው’ ከትግል አጋሮቻቸውና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ልምድ በመነሳት የዘመኑን ግፍና ፍትህ አልባነት በመፅሀፋቸው ከሌሎች የህትመት ውጤቶች ከምናገኛቸው መረጃዎች ላይ ተጨማሪ ታሪኮችን አቅርበውልናል፡፡ የዘመኑን የሽብርና የሀይል እርምጃ በተመለከተ ቋሚ ምስክር የሆኑ ቁጥራቸው በቀላሉ የማይገመቱ የግፍ ገፈት ቀማሾች አሁንም በህይወት ስለሁኔታው ልዘረዝር አልሞክርም፡፡ ነገር ግን በወታደራዊ ዘመን የነበረውን የሽብርና የኃይል እርምጃ (Terror & violence) በተመለከተ አንድ ነጥብ ላንሳና ዶ/ር መረራ በመፅሀፋቸው ሥለፈፀሙት የክርከር ህፀፅ ልግለፅ፡፡

በወታደራዊ ዘመን የነበረ ሽብርና የኃይል እርምጃ ቀጥተኛ ሰለባ የሆኑት #የፖለቲካ እስረኞች እንደሆኑ ይታወቃል$ ሲወሰድ የነበረውም እርምጃ እውቅ የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች በሀገሪቱ ታሪክ ወደር የለሽ ወንጀል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ረገድ ኘሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‘ኘሮፌሰር ገብሬ ታቀኝ ‘ዶ/ር ጆን አቢንክ ተጠቃሽ የሆኑ ሳይንሳዊ ጥናቶች አካሂደዋል፡፡ እንደአጥኚዎቹ የምርምር ውጤት ከሆነ ወታደራዊው መንግስት በሰው ልጅ ሕይወት ላይ በወሰዳቸው እርምጃዎች ምህረት የለሽና ግፈኛ ነበር፡፡ ከሥነሰብ (Anthropological) አንፃር የነበረውን የሽብርና የኃይል እርምጃ የተነተኑት ዶ/ር ጆን አቢንክ The Impact of violence the Ethiopian Red Terror as a social phenomenon በተሰኘው ፁሁፋቸው በግልፅ እንዳስቀመጡት በፖለቲካ እስረኞችና ተጠርጣሪዎች ላይ የተወሰደው የሽብር የሀይል እርመጃ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ፤ የሥልጣን የአቤት ባይነት ቀሪና እንጥፍጣፊ እሴቶችን ሳይቀር ጨፍልቆ ግድያ ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘዬ እንዲሆን መሽጋገሪያ ድልድይ የፈጠረ ነበር፡፡ ጠቅለል ሲደረግ ጭፍጨፋ በወታደራዊው ዘመን በስተቀር (exception) አልነበረም ይልቁንም የዘመኑ ገዢ ሁነት (Rule) ነበር፡፡

የደ/ር መረራ መፅሀፍ ይህን የግፍ ዘመን ሲግለፅ መቋጫና ማሰሪያ ያደረጉት መደምደሚያቸው እና ትርጓሚያቸው (Interpretation) አሁንም ቢሆን$ በኢህአዴግ ዘመንም ቢሆን የፖለቲካ እሥረኞችን በተመለከተ የተሻለ ነገር የለም የሚል ነው፡፡ ይህን አይነት ትርጓሜ ሲሰሙ ግን በfact ላይ ፍርደ ገምድልነትን ፈፅመዋል፡፡ የዚህ ዘመን ገዢ ሁነትና (Rule) በሥተቀር (exception) የትኛው እንደሆነ አምታተውታል፡፡ የዚህ ዘመን ሁለት (Rule) ጭፍጨፋና ሬሳን በጥይት ዋጋ መቸብቸብ እንዳልሆነ መገንዘብ ኢህአዲግነትን አይጠይቅም ለማሥታወስ ያህል የዚህ ዘመን ገዢ ሁነት ቢዝነስ ሜኪንግ ነው፡፡

በወታደራዊ ዘመን ግፍ ምክንያት ከሞት ከግርፋት ከስደት ‘ከማህበራዊ መመሰቃቀል በተጨማሪ ሀገሪቷ ብዙ ነገር ማጣቷን መካድ የለብንም፡፡ ኘሮፌሰር ባህሩ ‹‹ቀይ ሽብር በኢትዮጵያ ታሪካዊ ይዘትና አንድምታው›› በሚል ጥናታዊ ፅሁፋቸው እንዲህ ይላል፡፡

ዞሮ ዞሮ ግን የነገሩ ፋይዳ ከብዛቱ ሳይሆን ከጥራቱም ነው፡፡ ኢህአፖ አገሪቱ ካፈራቻቸው ምርጥ ልጆች ውስጥ ብዞዎቹን ለማሰለፍ የቻለ ድርጅት ነበር፡፡ መኢሶንም ቢሆን ተመሳሳይ ባህሪ ነበረው፡፡ እነዚያ እንደዋዛ የረገፉ ወጣቶች በህይወት ቆይተው ቢሆን ኖሮ ያገራችን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሕይወት ምንኛ የበለፀገ በነበረ በያሰኛል፡፡ አንጋፋው የማቲማቲክስ መምህር የነበረው ኘሮፌሰር ዓለማየሁ ኃይሉ የቀይ ሽብር ሰለባ ሆኖ ዩኒቨርሲቲ ደጃፍ ሬሳው የተጣለውንና ብዙ ተስፋ የተጣለበትን ወጣት የማቲማቲክስ መምህር በምን አይነት ፀፀት ያስታውስ እንደነበር ምንግዜም የማይረሳ ሁኔታ ነው፡፡

ዶ/ር መረራ በመፅሀፋቸው የፖለቲካ እስረኞችን በተመለከተ አሁንም ቢሆን የሚል አስተያየታቸው ለክርከር መቅረቡ ብዙም አሳማኝ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡

ምናልባት ይህ በወታደራዊው ዘመን የነበረውን የፖለቲካ እመቃን በተመለከተ ተቀጥላ አድርገው ያስቀመጡት ‹‹የዛሬም ቢሆን›› ድምዳሜና ትርጓሜ ሁለት ጥቅሞችን ለማግኘት ታቅዶ የተሰነዘረ ነው ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ አንደኛውና ቀጥተኛው አሁን በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ጥላሸት ለመቀባት ሲሆን ሌላኛውና ተዘዋዋሪ የአንድምታ ጥቅም ደግሞ ፀሐፊው ራሳቸው በሂሳሚ ድጋፍ መርህ አብረው ሰለባዎችን ስቃይ ማቃለልና ገሸሽ ማድረግ ነው፡፡

በኔ ምልከታና እምነት በኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ቅድመ 1983 እና ድህረ 1983 ዓ.ም በአንድ መነፀር ለመመልከት በመጀመር የአንድ ሙሉ ትውልድ ስቃይን ማጣጣልን ይጠይቃል፡፡

ዶ/ር መረራ ‹‹የፖለቲካ ምስቅልቅል›› ጋር አያይዘው በአቀረቡት የሕይወት ትዝታቸው የወታደራዊውን መንግስት መውደቅ የገለፁት እንደአብይ የፖለቲካ ሁነት ሳይሆን የሊቀመንበር መንግስቱ የዙምባቤ ሽሽት ‹‹ፍርጠጣ›› ነው ከተባለ የነኃይሌ ፊዳ ሕቡዕ መግባት ጋር በማመሳሰል በመሆኑ ዶ/ር መረራ ኢህአዴግ የመንግስት ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሕዝቦች የፖለቲካ ህይወት ውስጥ 1983 እንደለውጥ ምዕራፍ ለማየት አለመፋቀዳቸው የሚገርም አይሆንም፡፡ እኔ የሌለሁበት ሁነት እንደሁነት አይቆጠርም ማለት ይመስላል፡፡ ‹‹አገሩ ጠረጴዛ ሕላዌ የሚኖረው እኔ ስላየሁት ብቻ ነው›› የሚለውን ፍልስፍና ያስታውሰኛል፡፡

5. ስድብ/ቂመኛ እንደመሣሪያ

ዶ/ር መረራ በመፅሐፋቸው ውስጥ እንደሆኑ በራሳቸው ላይ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ ከ1966 ለውጥ በኋላ ሂሳብ ለማወረረድ አምቦ እንደሄዱ ይገልፃሉ፡፡ ያወራረዱት /የተበቀሉት ምን ይሆን; ዶ/ር ወረራ ጉዲና ባገኙት የፖለቲካ መድረኮች ሁሉ የያዙትን የፖለቲካ አመለካከትና አቋም ሲገልፁ ንግግራቸው ፈገግ በሚያሰኙ ቀልዶችና ፊዞች የታጀቡ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ መፅሀፋቸዋ ይህው የንግግርና የገለፃ ግላዊ ሥልታቸው ይንፀባረቅበታል፡፡ ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ይህ የቀልድ አቀራረባቸው መፅሐፋቸውን አንባቢው ፤ ሳይሰለች እንዲያነብ ያግዘው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከቀልድ ጀርባ ያለው ለመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ለተቋማት እውቅና በመንፈግ የማቃለልና የማዋረድ ዓላማን ያነገበ በመሆኑ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብዬ አልጠብቅም፡፡

እዚህ ላይ በመድብለ ፖርቲ ሥርዓት ፤ መንግስት ሲያጠፋ መተቸት ‘ በጎ ሲሰራ ደግሞ መበረታታት አለበት የሚለውን መርህ እንደማይዘነጋ ላሳስብ እወዳለሁ፡፡ የዶ/ር መረራ መፅሀፍ ሳነብ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ፀሐፊው የአሽሙርና የሽርደዳ ፍቅራቸው ለሚታገሉለት የፖለቲካ አላማ ላይ ጥላ እንደጠላበት ነው፡፡ በዚህ በተጨማሪ በፅሁፋቸው እንደታየው የሰላም የትግል ስልት እየተከተሉ መንግስትን እንደመንግስት ተቋማትን እንደተቋም እውቅና ለመስጠት ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ በኔ አረዳድ ተቃውሞ ትችት እንጂ ስድብ አይመስለኝም፡፡ አንደ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የዓመታት ሙያዊ ያለው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር በእውቀት እንጂ በስድብ ይታገላል ብዬ አልጠብቅም፡፡ ተተኪ ፖለቲከኛ ምሁራን የዶ/ር መረራን የአደባባይ የስድብ ፍቅር እንዳይወርሱና እውቀትን በክፍል ውስጥ ብቻ እንዳይቆልፉበት ያሰጋል፡፡

ማጠቃለያ

በመፅሐፉ ውስጥ የተረዳሁት ነገር ቢኖር አንደኛ፡ ያሉትን መልካም ጎኖች በመጠበቅ፣ በመቀበልና ችግሮችን በመፍታት ላይ ያተኮረ አይደለም፡፡ ሁለተኛ፡ ሂሳቸው የተቋማትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ላይ ሳይሆን በግለሰቦች ላይ ያተኮረና ድምዳሜ የሚወስድ መሆኑ፣ ሶስተኛ፡ የአገራዊ ጥቅም ሳይሆን ግላዊ ፖለቲካዊ ጥቅም በሁሉም መድረክ ላይ አራምደዋል፡፡ አራተኛ፡ በግል ገጠመኝና ፍላጎት ላይ በመመስረት አገራዊ የፖለቲካ አቋሞችን በመውሰድ በሁሉም የፖለቲካ ህይወታቸው መነሻና መድረሻ አድርገውታል፡፡ አምስተኛ፡ የብሄርና የመደብ ትግል የማይነጣጠሉና ተመጋጋቢ ሆኖ ሳለ ዶ/ር መረራ የመደብ ትግል ብቻ እስከ መጨረሻ መረጡ፡፡ አንድ ጥያቄ ብቻ እዚህጋ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ብጎናፀፉ በምን ቋንቋ ነው ለኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የተጎናፀፉትን መብት የሚነግራቸው፡፡ ስድስተኛ፡ የመፃፉ ድምዳሜ ከአንድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ፖለቲከኛ የማይጠበቅ ርካሽ የሆነ የፖለቲካ ጥቅምን ለማግኘት መሰረት የሌላቸውን በጥናትና በምርምር እንዲሁም እሳቸው በመፃፋቸው ውስጥ ያቀረቡልንን አንዳንድ መረጃዎችን የሚፃረር መሆኑነው፡፡

በነዚህንና በሌሎች ነጥቦች የፖለቲካ ህይወታቸውን ስንፈትሽ የዜሮ ድምር ፖለቲካ መሆኑን ያሳየናል፡፡ እኔ ከሞትኩ ሳርዶ አይብቀል አይነት፡፡

******

* Shimelis Abdisa is a guest author on HornAffairs.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories