የአዲስ አበባ የውሃ ብክለት፣ እጥረትና ብክነት አነጋጋሪ ሆኗል

(ክፍለዮሐንስ አንበርብር)

የውሃ ብክለት፣ እጥረትና ብክነት ለአዲስ አበባ ከፍተኛ የራስ ምታት እየሆነ መምጣቱንና በቀጣይም ችግሩን ለማቃለል የሚረዳ አማራጭ መፍትሄዎች ላይ ማማተር እንደሚገባና ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ።

ትናንት በሂልተን ሆቴል የተበከለን ውሃ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል በሚቻልበት እንዲሁም የውሃ ብክነት፣ ብክለትና እጥረትን ለማቃለል የሚያግዝ ውይይት ተካሂዷል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ቴክኒካል ስፔሻሊስት አቶ ባሀሩ ወልደማርያም፤ አማራጭ የውሃ አቅርቦት ለግንባታ፣ መኪና እጥበት፣ አረንጓዴ ልማትና የከተማ ግብርና በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጽሁፍ፤ በአዲስ አበባ በየዓመቱ ከፍተኛ የውሃ ፍላጎትና ብክነት መኖሩን አመልክተዋል።

በጥናቱ ላይ እንደተጠቀሰው፤ በአዲስ አበባ በየዓመቱ 38 ከመቶ የሚሆነው ውሃ በተለያዩ ምክንያቶች ምንም ዓይነት ክፍያ አይከፈልበትም። በዚህም ምክንያት አገሪቱ 206 ሚሊዮን ብር ታጣለች። በየቀኑ ከሚመረተው 384ሺ486 ሜትር ኪዩብ ውሃ ውስጥም 30 ከመቶ የሚሆነው ለብክነት ይዳረጋል። በከተማዋም የሚከሰተው እለታዊ የውሃ እጥረት 293ሺ ሜትር ኪዩብ ነው።

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አካባቢ ብቻ በየቀኑ እስከ 12ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ አገልግሎት ላይ ይውላል። ለግንባታ፣መኪና እጥበት፣ የአረንጓዴ ልማትና የከተማ ግብርና ደግሞ እስከ 24ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ በየቀኑ አገልግሎት ላይ እንደሚውልና ይህም የውሃ አቅርቦቱ ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑን በጥናቱ ተረጋግጧል። በተለያዩ የመንግስት ተቋማትና ኢምባሲዎችም የውሃ ፍጆታው ከፍተኛ መሆኑ በጥናቱ ተመልክቷል። የከተማዋ እለታዊ የፍሳሽ ማሰባሰብና ማጣራት ሽፋንም በመስመር 10ከመቶ ሲሆን፤ በመኪና ደግሞ 18 ከመቶ ብቻ መሆኑን ነው ጥናቱ ያመለከተው።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ከአንዳንድ ፋብሪካዎች እንዲሁም የኢንዱስትሪ መንደሮች የሚወጡ ተረፈ ምርቶች ቀጥታ ወደ ወንዞች እንደሚለቀቁና በአካባቢው በሚኖሩ ሰዎች፣ እንሰሳትና እጸዋት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም የሚመለከተው አካል አስፈላጊውን አስተዳደራዊ፣ ሳይንሳዊ እንዲሁም ህጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል። በተለይም የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱ አነስተኛ በመሆኑና ቅንጅታዊ አሰራር መጓደሉ ለችግሩ መባባስ የራሱን ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ልዩ ረዳት አቶ ተስፋዬ ፊቻላ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ የውሃ ብክነት፣ እጥረትና ብክለት በጣም አሳሳቢ መሆኑን መገንዘባቸውን ገልፀዋል። ሚኒስቴሩና የሚመለከታቸው አካላትም በቅንጅት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። በማንኛውም መልኩ በከተማዋ ውስጥ የፍሳሽ አወጋገድና የውሃ አቅርቦት መቃረን የለበትም ሲሉ ጠቁመው፤ ችግሩንም በሚገባ በማጥናት አስፈላጊውን መፍትሄ መውሰድ እንዲሁም ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሚኒስቴሩ፤ ችግሮቹን በጥልቀት እንደ ሚመለከትና አስፈላጊውን የመፍትሄ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ አረጋግጠዋል። እንዲሁም ሌሎች አማራጮችን የመመልከትና የውሃ ብክነትን የሚቀንስ አሰራር መዘርጋት በተጨማሪም ጥቅም ላይ የዋለ ውሃን በድጋሜ አገልግሎት እንዲሰጥ ሳይንሳዊ አሰራርን ለመተግበር እያማተረ እንደሆነ አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል። የወንዞችን ብክለት ለመቀነስም አስፈላጊው ሥራ ይከናወናል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከኦሮሚያ ልዩ ዞን ተወካዮች፣ የአማካሪ ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። ጥቅም ላይ የዋለን ውሃ ያለምንም ኬሚካል በማከም በድጋሜ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ልምድ እንዳለው የተነገረለት ጆሳብ የተሰኘ ድርጅትም ልምዱን ያካፈለ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ቢደረግ አዋጭ እንደሚሆንና ችግሩንም በከፍተኛ ሁኔታ እንሚያቃልል ተጠቁሟል።

******

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን – ሐምሌ 2006

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories