የቡሄን ባህላዊ አከባበር የመመለስ ጥረት

(ዳንኤል ወልደኪዳን)

«ሀገራችን የበርካታ ባህላዊ ትውፊቶች ባለቤት ናት» እያልን ለዘመናት በኩራት ዘምረናል። ሀገራችን ባህላዊ ትውፊቶቿን ጠብቃ የኖረች በመሆኗም አብዝተን ኮርተንባታል። በርከት የሚሉትን የባህል፣ የታሪክና ሌሎች ትውፊቶቻችንን ጠብቀው በማቆየቱ ረገድ የእምነት ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ ይዘው በማቆየታቸው በእነሱም ኮርተናል። በተለይ ደግሞ የማይዳሰሱ ቅርሶቻችንን በአግባቡ ጠብቆ ከማቆየት አንፃር የተለያዩ አካላት ጥረቶችን ማድረጋቸው አይካድም።

አሁን አሁን በተደረጉት ጥረቶች ቅርሶቻችንና ባህላዊ ትውፊቶቻችን የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ቀልብ በመሳባቸው እውቅና የማግኘታቸው አጋጣሚ እየሰፋ መጥቷል። ከመተዋወቅ አልፎም በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። ከጥረቶቹ በተቃራኒ ደግሞ የበርካታ ዘመን ባህላዊ ትውፊቶቻችን ለመጥፋት በመቃረብ ላይ በመሆናቸውና በአደጋ ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል። አንዳንዶቹ ባህላዊ ትውፊቶቻችን ከዘመን ዘመን ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ከመሸጋገር ይልቅ ተበርዘውና ተከልሰው ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

ለዘመናት ባህላዊ ይዘታቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የነበሩት ባህላዊ የበዓል አከባበሮቻችን ከመበረዝና ከመከለስ አልፈው ወደ መጥፋት በመቃረብ ላይ ናቸው። በተለይ የቡሄ በዓልን ብንወስድ ሕፃናት የገንዘብ መሰብሰቢያ አድርገውት ባህላዊ ይዘቱን ባልጠበቀ መልኩ በጎዳናዎች ላይ ሳይቀር ተገቢ ያልሆኑ ግጥሞችን እያወረዱ አላፊ አግዳሚውን ሲያስቸግሩና ገንዘብ ሲሰበስቡ ይስተዋላል።

እነዚህን የመበረዝና የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን ባህላዊ የበዓል አከባበሮችን ወደ ቀድሞው ይዘታቸው ለመመለስ ኢዮሃ ኢንተርቴመንትና ኤቨንት (ኢዮሃ ሲኒማ) አንድ መርሐ ግብር አቅዷል። የዘንድሮው የቡሄ በዓል ነባር ይዘቱን በማላበስና ጥንታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል።

ኢዮሃ ኢንተርቴይመንትና ኤቨንት (ኢዮሃ ሲኒማ)ም ይህንኑ የቡሄ በዓል ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ነሐሴ ስድስት ቀን ከምሽቱ አስር ሰዓት ጀምሮ በሀርመኒ ሆቴል ለማክበር ዝግጅቱን አጠናቋል። በእለቱ ከሃይማኖት ተቋማትና ከማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ጥናታዊ ፅሁፍ የሚቀርብ ሲሆን ፤ ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ባህላዊ ጭፈራው በድምቀት ይከናወናል። ባህላዊውን የቡሄ ጭፈራ ለሚያከናውኑ ሕፃናትም ባህላዊው የዳቦ ስጦታ እንደሚበረከትላቸው ከወጣው መርሐ ግብር ለመረዳት ችለናል።

የቡሄ በዓል መንፈሳዊ ይዘት ያለው ቢሆንም ባህላዊ ይዘቱ እየጎላ በመምጣቱ ከእምነቱ ተቋማት ውጪም በከተሞችና በገጠር በስፋት በመከበር ላይ የነበረ በዓል ነው። በተለይ በገጠሩ የሀገራችን አካባቢዎች ባህላዊ ይዘቱ የተወሰነ መለያየቶች ቢኖሩትም አላማውና ይዘቱ የተመሳሰለ ነበር። በዓሉ በተለይ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለየት ባለ ባህላዊ ክንውን ረዘም ላሉ ቀናት ነው የሚከበረው። በተለይ በእረኞችና በሕፃናት ዘንድ በተለየ ትኩረት እንደሚከበር ይታመናል።

ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፣ ወደ መፀው የሚዘለቅበት ወገግታ፣ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበትና የሚሸጋገርበት ወቅት በመሆኑ እና ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት ስለማይኖርም «ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፣ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት»

እየተባለም ይነገራል፡፡ በሌላም በኩል ዕለቱ በባህላዊ ግጥም ደምቆ ይውል ነበር…

መጣና መጣና፣ Ethiopia buhe tradition

ደጅ ልንጠና።

መጣና በአመቱ፣

ኧረ እንደምን ሰነበቱ።

ክፈቱልን በሩን፣

የጌታዬን።

ቡሄ በሉ፣ ልጆች ሁሉ

ቡሄ መጣ፤ ያ መላጣ፣

ቅቤ ቀቡት፣ እንዳይነጣ፣

ክፈቱልን በሩን የጌታዬን።

እዚያ ማዶ ነጭ ሻሽ፣

እዚህ ማዶ ጥቁር ሻሽ፣

የእኔማ ጌታ ነጭ ለባሽ።

የወንዜው ነብር የወንዜው ነብር፣

የኛማ ጌታ ሊሰጡን ነው ብር።

ሆይሾዬ ሎሚታ፣

ልምጣ ወይ ወደማታ።

ለብሩ ነወይ ሽርጉዱ

በአባትህ ጊዜ ሰንጋ ነው ልምዱ፡፡

እየተባለ ነበር የሚዘፈነው። ዛሬ ግን …

*********
ምንጭ፡- አዲስ ዘመን – ነሐሴ 2006

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories