በሚቀጥሉት ወራት የሰማያዊ ፓርቲ የውስጥ-ፖለቲካ ግለት እንደሚጨምር እጠብቃለሁ

(በዓርአያ ጌታቸው – እስከ መጋቢት 2005 የሰማያዊ ፓርቲ የወጣቶች ጉዳይ ሀላፊ የነበረ)

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጣም ጥቂት ቢሆኑም በሰማያዊ ፓርቲ ዙርያ አንዳንድ ጽሁፎችን ለማንበብ ችያለሁ፡፡ ነገር ግን ከነዚህ ጽሁፎች ጀርባ የሚሰጡ አስተያየቶችም ሆነ መልሶችን ሳይ በፖለቲካ ፓርቲ ዙርያ ያለን ግንዛቤ በጣሙን ደካማ እንደሆነና በፓርቲዎች ዙርያ እና በፖለቲካው መድረክ ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ሂደቶችን አንደ ትምህርት ወይም ልምድ ከመውሰድ እንደ ተረት ተረት እያየናቸው ይመስለኛል፡፡

ብዙ ሀታታ ሳለበዛ ባጭሩ የተሰሙኝን ነገሮች ማሳቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡ ዳዊት ሙሉጌታ የተባለው ወጣት ጽሁፍ አንብቤዋለሁ፡፡ ብዙም አስገራሚ አልሆነብኝም፤ ሰማያዊ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፤ በዚህ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ሰዎች ስብስብ ደግሞ ከአንድ ቦታ የመጡ ሳይሆኑ ከተለያየ ማህበረሰብ የተሰባሰቡ የተለያየ ባህሪ ያላቸው ሰዎች ሲሆኑ፤ የተሰባሰቡት ደግሞ በጣም ውስብስብ የሆነ እና ፍጹም በድህነት ውስጥ የምትገኝ ሀገርን ችግር እንፈታለን ብለው ነው፡፡ የፓርቲን ፖለቲካ ፈታኝነት እና ይህን ስብስብ ወደ አንድ አቅጣጫ ማምጣት እንዲህ በማህበራዊ ድረ ገጽ እንደመጻፍ ቀላል አይደለም፡፡

ከራሴ ልምድ ስነሳ ወደ ፓርቲ ፖለቲካ የተቀላቀልኩት በ1997 በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ተማር እያለሁ ነበር፡፡ ነገር ግን ወቅቱ ሁሉም ፖለቲካኛ የነበረበት ሰዓት እንደመሆኑ ያን ጊዜ ፖለቲከኛ ነበርኩ ለማለት አልደፍርም፤ ሆኖም የቅንጅት አመራሮች ተፈትተው እና የአሜሪካ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገርቤት እንደተመለሱ በትክክል ቀኑን በማላስታውሰው ቅዳሜ እለት ተወዳጇ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ በፊት ለፊት ገጿ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ሙሉነህ እዩኤል፣ ዶ/ር ሀይሉ፣ ኢ/ር ግዛቸው እና አቶ ብሩክ ከበደ በመኢአድ ቢሮ በር ላይ ቆመው የተነሱረት ፎቶ እና ወደ ግቢው እንዳይገቡ ስለመታገዳቸው የሚያትት ጽሁፍ ወጣ፤ በወቅቱም ለእንደኔ አይነቱ የፓርቲ ደጋፊ ልብን የሚያደማ ክስተት ነበር፤ እስከ አሁንም ድረስ በወቅቱ የተሰማኝ ህመም አስታውሳለሁ፡፡

እናም እነዚህ ሰዎች ቦታ ራሴን አስቀምጬ ሳስበው ምን ማድረግ ይችሉ ነበር? መልስ አልነበረኝም፡፡ ረጅም ጊዜ ከራሴ ጋር ተከራክሬ ውጭ ሆኜ ከምቃጠል በሚል የነብርቱካንን ግሩፕ በመቀላቀል የአንድነት ፓርቲ መሳራች ሆንኩ፡፡ ሆኖም ያ ከውጭ ሳየው የነበረው የፓርቲ ፖለቲካ ምን ያህል ፈታኝ እና ውስብስብ እንደነበረ ለመረዳት ከ6 ወር በላይ አልፈጀብኝም እኔም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ የአንድነት በር ተዘጋብኝ፡፡

ይሄ የውስጠ ፓርቲ ፖለቲካ በእኛ ሀገር ብቻ ያለ ሳይሆን አጠቃላይ የፓርቲ ፖለቲካ ባህሪ ነው፡፡ ልዩነቱ የምንፈታበት መንገድ እና የምንወያይበት መድረክ ብቻ ነው፡፡ በሀገራቸው የውስጥ ፖለቲካ ዲሞክራት የሚባሉ ሀገሮች እንኳ ፍጹም ለመስማት የሚዘገንኑ ተግባሮችን ሲፈጽሙ እንመለከታለን፡፡ ለምሳሌ የባለፉትን የአሜሪካ ምርጫዎች መመልከት በቂ ይመስለኛል፡፡

Photo - Araya Getachew - Semayawi Party - Ethiopia
Photo – Araya Getachew – Semayawi Party – Ethiopia

ዛሬም በሰማያዊ ፓርተሪ ዙርያ የተጻፈውን ጽኁፍ አይተው ብዙዎች ደንግጠዋል ወይም ሰማያዊ ፓርቲ አደጋ ላይ መስሏቸዋል፡፡ ለእኔ ሰማያዊ ፓርቲ አደጋ ላይ የሚሆነው ፓርቲውን የሚተች አባል ስለመጣበት ሳይሆን ይሄንን አይነት ጽሁፎች ወይም ትችቶች የሚያስትናግድበት መንገድ ነው፡፡ ምን አልባት ከጽሁፉ ስሜት እንደተረዳሁት ዳዊት ብቻውን አይመስለኝም ምናልባት ጥቂት አባላቶች ጥያቄ ሊኖራቸው እንደሚችል ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ፓርቲው አይደለም ጥቂቶች አንድም የፓርቲው አባል ወይም ፓርቲው መዋቅር ውስጥ ያለ ሰው ለሚያነሳው ጥያቄ እንዴት ነው የሚያስተናግደው የሚለው አጽንኦት መስጠት ያለበት ይመስለኛል፡፡

በሌላው ጎኑ ስናየውም ምናልባት እንደሰለጠነ ሰው ማሰብ ከቻልን እንዲህ አይነት ፅሁፎች በፓርቲው ጥንካሬ ዙርያ በርካታ አርእስቶችን የሚከፍቱ እና ስለፓርቲው እንቅስቃሴ አጠቃላይ ለህዝብ የውይይት መድረክ እድል የሚሰጡ ናቸው፡፡ በርግጠኝነት በዳዊት ከተጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ፓርቲውም የሚቀበላቸው እንደሚኖሩ አልጠራጠርም፡፡ የፓርቲው አመራሮችም በደፈናው ጸሀፊውን ከመኮነን እና ከማጣጣል በአደባባይ ለመጣ ትችት ህብረተሰቡን የሚመጥን መልስ መስጠት እና ከሁሉ በበለጠ ደግሞ ከአባላቶችቻው ጋር በቂ መድረኮችን ማማቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡

ምንም እንኳ ከፓርቲው ርቄ ብገኝም ሰማያዊ ፓርቲ አባላት እና እንቅስቃሴ ከዚህ በፊት በኔ እድሜ ካየኋቸው ፓርቲዎች ጋር እንኳ ለውድድር የማላቀርበው ጠንካራ ድርጅት እንደሆነ አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲ ታሪክ ውስጥም የሰላማዊ ትግል ምን እንደሆን በተግባር ፍንጭ ያሳዩን እና ፍጹም ሳያንገራግሩ መሰዋዕትነት ለመክፈል ከማንም በፊት ራሳቸውን አሳልፈው የሚሰጡ አባላት እና መሪዎች (ይልቃልን ጨምሮ) እነደሆኑ ለሰከንድ ሳላንገራግር መመስከር እችላለሁ፡፡

እንዲሁም አሁን ያሉት አመራሮች እና አባላት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ከተመሰረተ በ3 ዓመት ውስጥ ድርጅቱን መርተው ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ አድርሰውታል፡፡ ለእኔ ይህ ታላቅ ስኬት ነው፡፡ እነሱም ሊኮሩ ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ አሁን ካለው ስም እና የእድገት ጉዞው ፍጥነት አንጻር በርካታ አደጋች እንደሚጠብቁት ግልጽ ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ የአባላት ቁጥር ከመጨመርና የመዋቅር መስፋት ጋር ተደማምሮ ለሚመጡ የውስጥ ድርጅታዊ አሰራር ችግሮች መፍትሄ አሰጣጥ አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮችም አሁን አሁን በጥቂቱም ቢሆን እየታዩ ናቸው (ችግሮቹ ከፓርቲ ፖለቲካ አንጻር ተፈጥሯዊ ናቸው)፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር ጨምሮ ከስር ያሉትም አመራሮች የውስጥ ፖለቲካ ችግሮች ዙሪያ በቂ ልምድ ያላቸው ስለሚመስለኝ ነገሮችን ከስሜታዊነት ወጣ ብለው ከባለፉት ልምዶችም በመነሳት በሰከነ መልክ የማየት እና በቋሚነትም የአፈታት ዘዴዎችን በመቀየስ የፓርቲውን ጉዞ የማስቀጠል ከባድ ሀላፊነት ይጠብቃቸዋል፡፡ ከምንም በላይ የውስጥ ዲሞክራሲን ማዳበር እና ሁልጊዜ ለሀሳብ ልዩነት በራቸውን ክፍት ማድረግ አለባቸው፡፡

ሰማያዊ ፓርቲም በሚቀጥለው መስከረም ወር ላይ የተቅላላ ጉባኤውን የሚያካሂድ እን ሊቀመንበርም የሚመርጥበት ወቅት እንደ መሆኑ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት የፓርቲው የውስጥ ፖለቲካ ግለቱ እንደሚጨምር እጠብቃለሁ፡፡ ሆኖም አባላቱ በተለይ አመራሩ በተቻለው አቅም ፓርቲው በአጭር እድሜው በብዙ ዘርፉ ለሌሎች ሞዴል መሆን እንደቻለው በዚህም ዙርያ አርአያነቱን ማሳየት እና የጀመረውን ጉዞ መቀጠል አለበት፡፡

******

Guest Author

more recommended stories