በኢ/ር ይልቃል አምባገነናዊ መዳፍ ሥር የወደቀው ሰማያዊ ፓርቲ

(በዳዊት መሉጌታ – የሰማያዊ ፓርቲ የወጣቶች ጉዳይ ም/ሀላፊ)

Highlights:

* ‹‹ኢ/ር ይልቃል ሰማያዊ ፓርቲ ሲመሰረት አንድነትና መኢአድ ፓርቲ ድራሻቸው ይጠፋል፣ ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ ብቻውን ነጥሮ ይወጣል በሚል የግሉ እሳቤ ነበር።››

* ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ አዲስ የኢትዮጵያ ህገመንግስት እያረቀቀ ነው፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለውይይት ይቀርባል በማለት ኢ/ር ይልቃል ከተናገረ ዓመት ሊሞላው ነው። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ለህዝብ ለውይይት የቀረበ ረቂቅ ህገመንግስት የለም።››

* ‹‹አማራ የሚባል ብሔር የለም የሚለን ኢ/ር ይልቃል ለምንድነው አማራ የለም የምትለው ብላችሁ ብትጠይቁት የለም አልኳችሁ የለም ነው! ካላመናችሁኝ ፕ/ር መስፍንን ሄዳችሁ ጠይቋቸው ከማለት ውጪ ምንም አይነት ተጨባጭ ምክኒያታዊ ትንተና አያቀርብላችሁም።››

* ‹‹60ና ሰባ ሺህ ህዝብ አደባባይ ይዞ ሰልፍ ይወጣ የነበረው ፓርቲ 400 እና 500 ሰው ይዞ መውጣቱ ሰማያዊ ፓርቲ የተያያዘውን የቁልቁለት ጉዞ…››

* ‹‹አንድነት ፓርቲ ውስጥ ይባል የነበረው ህገወጥ አሠራር እውነትም ኖሮ ከሆነ ግን አሁን ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ከሰፈሰነው የረቀቀ ህገወጥ አሰራር አይብስም።››

* ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ መዋቅሩም ድርጅታዊ አሠራሩም አንድ ይልቃልና በዙሪያው ያሰባሰባቸው ግለሰቦች ሆነዋል።››

* ‹‹የመለመላቸው አባላት ቁጥርም ከ980 አይበልጡም። ነገር ግን ኢ/ር ይልቃል በተለያዩ ሚዲያዎች 40ሺህ አባላት አለን ብሎ ህዝብን አታሏል።…. በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ የአባላቱ ቁጥር 4 ሺህ እንደሆነ አውቃለሁ።››

* ‹‹ኢ/ር ይልቃል የልደቱን፣ ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ የኢዴፓን ሚና እንዳይተኩ እሰጋለሁ።››

ታህሳስ 24 2004 ዓ.ም የሰማያዊ ፓርቲ መሥራች ጠቅላላ ጉባዔ የተካሔደበት ቀን ነው። በፕሮግራሙ ማብቂያ ላይ ከተጋባዥ እንግዶች መካከል ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም የመዝጊያ ንግግር እንዲያደርጉ ከመድረኩ ተጋበዙ። ቃል በቃል ባይሆንም እንዲህ አሉ። “በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማሳካት ያቃተን ትልቅ ነገር ቢኖር ለሥልጣን ልጓም ማበጀት አለመቻላችን ነው። እዚህ ፓርቲም ለስልጣን ጥም ልጓም ማበጀት ካልቻላችሁ ይህ የስልጣን ጥም እያደር ይመጣል። . . ዛሬ አይደለም እያደር ይመጣል።” ብለው ነበር። እውነት ነው ጋሽ መስፍን፤ይሄ የስልጣን ጥም በሽታ አድሮ በሰማያዊ ፓርቲያችን መጥቷል። ነገር ግን ምነው ታዲያ ይሄ የስልጣን ጥም ልጓም እንዴት እንደሚበጅ ሳያሳዩን ቀሩ?!

በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የግለሰቦች የሥልጣን ጥም መገራት ሳይችል ሲቀር የፖለቲካ ፓርቲዎች ስራ አምባገነኖችን ማምረት ይሆንና ጥሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ማጣታችን አይቀሬ ይሆና። በሰማያዊ ፓርቲም ውስጥ የተከሰተው ይሄ ነው። አንድ ቀን ነው ከኢ/ር ይልቃል ጋር ቢሮ ውስጥ የፓርቲው አባላት ስለሚያደርጉት ውስን ተሳትፎና በጥቂት የፓርቲው ሰዎች ላይ ስለወደቀው የሥራ ጫና ተቀምጠን እያወራን ነው። በመሀል በህይወቴ የማልረሳውን ነገር ምርር እያለ ነገረኝ። ‹‹አሁን እኔ አምባገነን ብሆን ምን ይፈረድብኛል? ለካ ሰዎች ወደው አይደለም አምባገነን የሚሆኑት ብቻቸውን የሚከፍሉት መስዋትነት ቢበዛ እንጂ!›› እኔ ግን ሰዎች እንዴት አምባገነን እንደሚሆኑ በራሱ በኢ/ር ይልቃል እና በሰማያዊ ፓርቲ አይቻለሁ። የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት በተደጋጋሚ ለፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተለይም ለኢ/ር ይልቃል ጌትነት ህገወጥ የሆነ አሰራሩን እንዲያስተካክል ከዚህ በፊት የተሰሩ ስህተቶችንም እንዲያርም ቢያሳስብም ይሄን ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ችላ በማለት ወይም የፓርቲውን ምክር ቤትና አባላት በመናቅ በህገወጥ አሰራሩ ቀጥሎበታል። የፓርቲው አባላትም ነገሩን በሆዳቸው ይዘው ከዛሬ ነገ ስህተቱን ያርማል፣ ፓርቲውንም ወደ ትክክለኛ አሰራር ይመልሳል በሚል ተስፋ ቢጠብቁም ችግሩ እየባሰና ከቁጥጥር ውጪ እየወጣ ይገኛል።

Photo - Dawit Mulugeta - Semayawi Party - Ethiopia
Photo – Dawit Mulugeta – Semayawi Party – Ethiopia

የፓርቲው አባላትም ለሶስት ዓመት ያክል በትዕግስት ከወያኔና ከፓርቲው ሊቀመንበር ህገወጥ አሰራር ጋር እኩል መታገላቸውንም ቀጥለዋል። የመሰታወት ቤት ላይ ድንጋይ አይወረወርም እንዲሉ የፓርቲው አባላት ባልጠነከረና ምንም አደረጃጀት በሌለው ፓርቲያቸው ላይ በአደባባይ ሃሳብ መወርወር ፓርቲውን ፍርስርሱን ያወጣው መስሏቸው ከወያኔ በላይ ራሳቸውን በራሳቸው አፍነው ነገሩን ወዲያና ወዲህ ሲሉት ከርመዋል። ሃሳባቸውን በአደባባይ አውጥተን እንግለጽ ቢሉ እንኳን ፓርቲውን እንደ ግል ንብረታቸው የሚያሽከረክሩት ጥቂት ግለሰቦች ጥርሳቸውን ስለሚነክሱባቸውና ከፓርቲው ስለሚያገሏቸው በብዕር ስም ለመጻፍ ይገደዳሉ። ለዚህ ማሳያም በቅርብ ለሰማያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተልኮ በነበረው የሰሜን አሜሪካ የጉብኝት ግብዣ እኔ ነኝ የምሔድ፣ እኔ ነኝ የምሄድ በሚል የስራ አስፈጻሚ አባል እስከማገድ ድረስ የዘለቀውን ግጭት በሰንደቅ ጋዜጣ የሰማያዊ ፓርቲ አባል በብዕር ስም ስለጻፈ ብቻ ሰማያዊ ፓርቲ እንዴት በአንድ እግሯ እንደቆመች ማየት በቂ ነው። ይህ አፈና ደግሞ ነገሩን እያለዘበው ሳይሆን እያባሰው ይገኛል።

ስለሆነም በፓርቲው ውስጥ ታፍነው ያሉ ሃሳቦችን ወያኔ የሚያውቃቸውን ነገር ግን ህዝብ የማያውቃቸውን የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች እንዲያውቁት እና እንዲወያዩበት የፈለኩትን እውነታ እንደሚከተለው በዝርዝር አስፍሬዋለሁ:-

1/ በኢ/ር ይልቃል አማካኝነት በተለያዩ ሚዲያዎች ከተሰራጩ የሰማያዊ ፓርቲን አቋም የሚጻረሩ ሀሳቦች መካከል፣ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ  በኢትዮጵያ ውስጥ ፓርቲ አለ ብሎ አያስብም፤ ከፓርቲዎችም ጋር አብረን አንሰራም›› የሚለው ይገኝበታል። ኢ/ር ይልቃል ይሄን የተናገረው ሰማያዊ ፓርቲ ሲመሰረት ‹‹አንድነትና መኢአድ ፓርቲ ድራሻቸው ይጠፋል፣ ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ ብቻውን ነጥሮ ይወጣል›› በሚል የግሉ እሳቤ ነበር። ነገር ግን እሱ እንደተመኘው ሳይሆን ቀረና አንድነትና መኢአድ ካንቀላፉበት ተነስተው እንደገና አንሰራሩ።

ይህ ብቻ እንዳይመስላችሁ ኢ/ር ይልቃልን እንቅልፍ የነሳው፤ ከሰማያዊ ፓርቲ አባላት የተነሳው ‹‹ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብረን እንስራ›› የሚለው ጥያቄ መበርከቱ እንጂ። ታዲያ ለስለስ ባለ አነጋገር ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ከ ዶ/ር ነጋሶ ጋር ቡና እንደሚጠጣ ከኢ/ር ኃይሉ ሻወል ጋር ስልክ እንደሚደዋወል ይገልጽ የነበረው ወይም በማስመሰል ይገለጽ የነበረው ተቀይሮ በቁጣና በግልፍተኝነት ‹‹ከሰማያዊ ፓርቲ በስተቀር ፓርቲ የለም፤ አንድነቶችም አምባገነናዊ አሰራር አላቸው። መኢአድ ቢሮው ብቻ ነው አፉን ከፍቶ የቀረው›› በማለት የሰማያዊ ፓርቲንና የሌሎች ፓርቲዎች ግንኙነትን በማሻከር የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ጥያቄን በማፈንና ተስፋ በማስቆረጥ ከፓርቲዎች ጋር አብረን እንስራ የሚሉትን የፓርቲውን ብዙሃን ጸጥ በማስባል በዙሪያው ባሰባሰባቸው ጥቂት ግለሰቦች አማካኝነት የሰማያዊ ፓርቲ ግንኙነት የባሰ እንዲሻክርና መልሶም እንዳያገግም በተለያዩ ጋዜጦችና በፌስቡክ አማካኝነት የጉንተላና የስድብ ዘመቻ አስከፈተ። በተለይ ደግሞ በአንድነት ፓርቲ ላይ (ልብ በሉ ይህ ዘመቻ የሚመራው በራሱ በይልቃል አማካኝነት ነው)፡፡

ታዲያ ለምንድነው ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ በቀጥታ በራሱ አንደበት ሲሰነዘሩ የነበሩ ዘለፋዎችንና ጥላቻዎችን በተዘዋዋሪ በሌላ አባላት እንዲባሉ የፈለገው? የሱ ስም እንዳይጠፋ ነው? ‹‹እኔ የፓርቲው አባላት አንድነትና መኢአድ ላይ ዘመቻ እንዲከፍቱ አላደረኩም›› ብሎ ይክድ ይሆን? እውነት እንደዛ ከሆነስ ለምን እሱ በሚመራው ፓርቲ ውስጥ ያሉ አባላት ከፓርቲው አቋም ውጪ በሆነ መልኩ ከሌላ ፓርቲ አባላት ጋር አፍእላፊ ሲካፈቱ ‹‹ተዉ እኛ የራሳችንን ሥራ እንስራ ትግላችን ከወያኔ ጋር እንጂ ከአንድነት ፓርቲ ጋር አይደለም›› በማለት ፋንታ በተሳደቡት ቁጥር ልክ ውለታ የሚመስል ነገር ያደረገላቸው? ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚገርመው በመሰዳደብ ሥራ ላይ በህቡዕ የመደባቸው ወጣቶችን እንደዚያ ሲያበረታታቸውና ሲደግፋቸው ምነው ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ የሚሯሯጡ አባላት ላይ ጥርሱን መንከሱና እነሱን ከፓርቲው ለማባረር ወይም ከፓርቲው ለማራቅ ደፋቀና የሚለው?

የምታስታውስ ከሆነ? አንድ የፓርቲ አባል ለምንድነው ሰማያዊ ፓርቲ ምንም አይነት ግንኙነት ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት እንዳይኖረው የምትፈልገው ብሎ ሲጠይቅህ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ፓርቲ አለ ብለህ ነው›› ነበር ያልከው፡፡ እኔ ግን ትክክለኛ ምክንያቱን ልንገረው፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ውጪ ምክትል ጠ/ሚም ሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመሆን እቅድ በጭንቅላታቸው የሌለው ኢ/ር ይልቃልና ጥቂት ጓደኞቹ ሰማያዊ ፓርቲ ከሌላ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት እንዲኖረው የማይፈልጉበት ምክንያት ይህ ግንኙነት እያደገ ሔዶ ወደ ውህደት ቢያመራ ኢ/ር ይልቃልና ጓደኞቹ በዛ ውህድ ፓርቲ ውስጥ የሥራ አስፈጻሚን ቦታ ላናገኝ እንችላለን፤ እንዲሁም ያን ውህድ ፓርቲ ልክ እንደ ሰማያዊ ፓርቲ በአንድ ጣታችን ላናሽከረክረው እንችላለን፣ ይህም ለስልጣን መወጣጫ የሆነውን መሰላላችንን ያሳጣናል በሚል ተልካሻ ምክንያት የሀገራቸውንና የህዝባቸውን ነጻነት ገና ባልመጣ ሥልጣን ስለለወጡት እንጂ!

ልብ በሉ ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት የሚፈጸመው በፓርቲው ምክርቤት ሆኖ ሳለ ኢ/ር ይልቃል ባልታዘዘውና እንዲያስፈጽም ባልተሰጠው የፓርቲዎች ግንኙነት ዙሪያ ባሰራጨው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ፓርቲው እጅግ ዋጋ ከፍሎበታል። ነገር ግን እውነታው በወቅቱ ሰማያዊ ፓርቲ በፓርቲዎች ግንኙነት ጉዳይ በፓርቲው ደንብና መመሪያ በሚያዘው መልኩ ይፈጸም ከማለት ውጪ ሌላ ምንም ዓይነት ውሳኔ እንዳላስተላለፈ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። ስለሆነም በታፈነው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ስም እንዲህ እላችኋለሁ፡-

እስከዛሬ በሰማያዊ ፓርቲ ስም ሲነገር የነበረው ሰማያዊ ፓርቲ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር አብሮ መስራት አይፈልግም የሚለው ሃሳብ በፍጹም ፓርቲውን የማይወክል ሃሳብ ሲሆን ሰማያዊ ፓርቲ ለኢትዮጵያችን ነጻነት የሚበጅ እስከሆነ ድረስ ውህደትን ጨምሮ በማንኛውም መልኩ ከፓርቲዎች ጋር አብሮ እንዳይሰራ የሚያግደው ምንም ምክንያት እንደሌለ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። በሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በኢ/ር ይልቃል ጌትነትና በአንዳንድ የፓርቲው አባላት እንዲሁም በወያኔ ሰርጎ ገቦች አማካኝነት ሲሰነዘሩ ለነበሩ ጉንተላዎችና መረን የለቀቁ ንግግሮች በሰማያዊፓርቲ ቅር የተሰኛችሁ የአንድነት የመኢአድ እንዲሁም የሌሎች ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎችን የበደሉትን አይደለም፤ የበደሏቸውን ይቅር በማለት በሚታወቁት በሰማያዊ ፓርቲ አባላት ስም ይቅርታ እጠይቃችኋሁ።

ይቅርታዬን ከተቀበላችሁኝ ዘንዳ ለ 23 ዓመት ረግጦ የገዛንን አምባገነን ቡድን ያለማንም አጋዥ እዚህ ጋር በቃህ እንደምንለው እርግጠኛ በመሆን ሰማያዊ ፓርቲን መስርተን ለሶስት አመታት ያህል ስንታገል ቆይተናል። ነገር ግን የወያኔን ለዓመታት የፈረጠመ ክንድ በጥላቻ የደደረ ልብንና በኢሰብዐዊነት የታሰረ ዓይኑን ታግሎ መጣል አይደለም፣ መግፋት ትልቅ ፈተና እንደሆነ አይተናል። በጀመርነው የትግል አማራጭም ሀገራችንን ነጻ ለማውጣት ምናልባት 20 እና 30 አመታት ሊፈጅ እንደሚችል ተገንዝበናል። ታዲያ እስከመቼ ነው መሬታችንን በሽፍቶች እያስቆረስን ስናሸጥ የምንኖረው? እስከመቼስ ህዝባችን በአምባገነናዊ ስርአት ታፍኖ ይኖራል? እስከመቼ ነው ወጣቶች በአቅመ ደካማ ወላጆቻቸው ሲጦሩ የሚኖሩት? እስከመቼ ነው እውነትን ያሉ ዜጎች ሲታሰሩ፣ ሲገደሉ፣ ሲሰደዱ የሚኖሩት? እስከመቼ ነው ጀግኖቻችን እንደበግ እየተጎተቱ እስርቤት ሲጋዙ የምንመለከተው? መቼ ነው ሃይማኖታችንን በነጻነት የምናራምድባት ሃገር የምንመሰርተው? ይሄን አምባገነን ቡድን ቀይረን በሰላም ውለን የምንገባባትን፣ ልጆቻችንን በነጻነት ት/ቤት ልክን ጥሩ እውቀት የምናስገበይባትን፣ ነግደን ምናተርፍባትን የሃገሪቷ ሃብት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የተከፋፈለባትን ለጥቂት አምባገነን ግለሰቦች የቆመ ሳይሆን ሃገሩን የሚወድ ለሀገሩ ዘብ የሚቆም የመከላከያ ሰራዊት የምንገነባበትን፣ ሃገራችንን እንድንመሰርት የሌሎችን ፓርቲዎች ትንፋሽ መዋስ ግድ ብሎናል። ከነገወዲያ ስለሚመጣው ሥልጣን ሳይሆን ነገ በሃገራችን ስለሚሰፍነው ነጻነት አብረን እንድንታገል ጥሪዬን አቀርባለሁ።

‹‹ሰማያዊ ፓርቲ አዲስ የኢትዮጵያ ህገመንግስት እያረቀቀ ነው፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለውይይት ይቀርባል›› በማለት ኢ/ር ይልቃል ከተናገረ ዓመት ሊሞላው ነው። ነገር ግን እስካሁን ድረስ ለህዝብ ለውይይት የቀረበ ረቂቅ ህገመንግስት የለም። ታዲያ ለህዝብ ሊቀርብ የነበረው ረቂቅ ህገመንግስት የት ገባ?

ነገሩ ወዲህ ነው፤ ሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የወደፊቱ የኢትዮጵያ ህገመንግስት በዚህ መልኩ ቢሆንስ በማለት ያዘጋጁትን የህገመንግስት ረቂቅ ዶሴ ሰማያዊ ፓርቲ እንዲወያይበትና ሃሳብ እንዲሰጥበት እንዲሁም እንዲያጠናክረው ወደ ሀገር ቤት ይልኩታል። ይህ ዶሴ በእጁ የገባው ኢ/ር ይልቃል ከፓርቲዎች ጋር የገባበት አጉል ቀድሞ ጎል የማስቆጠር ፉክክር አጣድፎት ኖሮ ከስራ አስፈጻሚ ጓደኞቹ ጋር ሳይመክር እንዲሁም የፓርቲውን ምክር ቤት ፍቃድ ሳይጠይቅ ሰማያዊ ፓርቲ አዲስ የህገመንግስት ረቂቅ አዘጋጅቷል በሳምንት ጊዜ ውስጥም ህዝብ ጠርተን ለውይይት ይፋ እናደርገዋለን ብሎ በሰንደቅ ጋዜጣ አወጀ። የፓርቲው የስራ አስፈጻሚና የምክር ቤት አባላትም እንደሌላው ህዝብ ሁሉ ከጋዜጣ አነበቡት፤ የጅብ ችኩል.. ይሉዋችኋል ይሄም አይደል? ህገመንግስት እንዴት እንደሚዘጋጅና እንደሚጸድቅ የማያውቅ ፓርቲና መሪ በሚልም ሰማያዊ ፓርቲ መሳቂያ መሳለቂያ ሆነ። ኢ/ር ይልቃልም ታዲያ እኔ ፓርቲ መምራት እንጂ ህግ ማወቅ አይጠበቅብኝም ብሎ ግግም አለ። ታዲያ ምን ነበረበት ቀድሞ ከጓደኞቹ ምክር ቢጤ ቢጠይቅ ኖሮ? ነገሩም ሁለተኛ እንዳይነሳ ተብሎ ተደባብሶ ቀረ። ይሄው አመት ሊሞላውም አይደል?

ሌላ ጊዜ ደግሞ የሙስሊሞች ጥያቄ ፖለቲካዊ እንጂ ሀይማኖታዊ አይደለም አለ። ኢ/ር ይልቃል ህግ አለማወቁ አይደለም የሚያስጨንቀኝ። ነገር ግን ሰማያዊ ፓርቲ ተወያይቶ ያላስተላለፈውን ሀሳብ ከየት እያመጣ እንደሚዘባርቅ እንጂ! የሙስሊሞች ጥያቄ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ወይስ ሀይማኖታችንን ካለመንግስት ጣልቃገብነት እንምራ የሚል ጥያቄ ውስጥ አልገባም። ይሄን መቼም አንድ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ ይመልሰዋል ብዬ እገምታለሁ። ይህ የኢ/ር ይልቃል አባባል ብዙ የሙስሊም እምነት ተከታዮችን ቅር ያሰኘ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ነገር ግን በዚያኑ ሰሞን የሰማያዊ ፓርቲ የህግ ጉዳይ ሃላፊ የሆነው አቶ ይድነቃቸው ከበደ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ ፖለቲካዊ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ነው በሚል ያቀረበው ግለ-ሀሳብ ኢ/ር ይልቃል የተናገረው የግሉን ሃሳብ እንጂ የሰማያዊ ፓርቲን አቋም እንዳልሆነ ለብዙዎች ግልጽ እንዲሆንላቸው ሆኗል። በወቅቱ በአቶ ይድነቃቸው ጽሑፍ ኢ/ር ይልቃል ቅሬታ እንደተሰማው በግል አጫውቶኛል።

ኦሮምኛ ቋንቋ በላቲን ሳይሆን በግዕዝ ነው መጻፍ ያለበትም አለ። አሁንም ኢ/ር ይልቃል ለምን የማያውቀውን ነገር ዝም ብሎ እንደሚናገር ባይገባኝም በአንድ መጽሄት ላይ የኦሮምኛ ቋንቋን ለመጻፍና ለማንበብ የሚያገለግለውን ቁቤን ኢህአዴግ የፈጠረው የሚያስመስልና ኦሮምኛ በግዕዝ ቢጻፍ የተሻለ እንደሆነ ተናገረ። ጋዜጠኛውም ቁቤኮ ኢህአዴግ ከመምጣቱ 30 ዓመት በፊት የተፈጠረ ነው፤ ሰማያዊ ፓርቲስ መቼ ነው የዚህ አይነት ውሳኔ ላይ የደረሰው ብሎ አልሞገተውም። የኢ/ር ይልቃል ንግግር ያቃጠላቸው የኦሮሞ አክቲቪስቶችም ጸረ ሰማያዊ ፓርቲ ዘመቻ እንዲከፍቱ ምክንያት ሆናቸው። ነገር ግን ይህ የሰማያዊ ፓርቲ አቋም አልነበረም።

አማራ የሚባል ብሔር የለም በሚል ኢ/ር ይልቃል በብዙ መድረኮች ለይ የፕ/ር መስፍንን አባባል እየተዋሰ ወይም እየቀዳ ሲናገር ገጥሟችሁ ይሆን ይሆናል። አማራ የሚባል ብሄር የለም ብሎ የተናገረውም ከጋሽ መስፍን በቀዳት አባባል ነው። ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ፈላስፋ ናቸው። አማራ የሚባል ብሔር የለም ሲሉ ምክኒያታዊ በሆነ ትንተና ያቀረቡትን ጽሁፍ አይቼዋለሁ። ነገር ግን የአማራ ህዝብ ከቀዬው እየተፈናቀለ ነው፣ ከሀገሩ እየተሰደደ ነው ሲለን ይቆይና ወደ በኃላ ደግሞ አማራ የሚባል ብሔር የለም የሚለን ኢ/ር ይልቃል ለምንድነው አማራ የለም የምትለው ብላችሁ ብትጠይቁት የለም አልኳችሁ የለም ነው! ካላመናችሁኝ ፕ/ር መስፍንን ሄዳችሁ ጠይቋቸው ከማለት ውጪ ምንም አይነት ተጨባጭ ምክኒያታዊ ትንተና አያቀርብላችሁም። ለማንኛውም ሰማያዊ ፓርቲ አማራ የሚባል ብሄር የለም የሚል አቋም እንዳልያዘ እንድታቁልኝ እወዳለሁ።

2. የሰማያዊ ፓርቲ የቁልቁለት ጉዞ ለምን?

በአመት የ 26 ሚሊዮን ብር በጀት ያጸድቅ የነበረው ፓርቲ ካለምንም እቅድና በጀት መመራት መጀመሩ 60ና ሰባ ሺህ ህዝብ አደባባይ ይዞ ሰልፍ ይወጣ የነበረው ፓርቲ 400 እና 500 ሰው ይዞ መውጣቱ ሰማያዊ ፓርቲ የተያያዘውን የቁልቁለት ጉዞ የተመለከቱ ብዙ ሰዎች የራሳቸውን ግምት ሲወረውሩ ይስተዋላሉ። ነገር ግን ትክክለኛውን ምክንያት ይረዱ ዘንድ እንደሚከተለው በዝርዝር አስቀምጬዋለሁ።

ሀ. በ ኢ/ር ይልቃል አጉል ማበጥና ማናለብኝነት ቅር የተሰኙ ነባር የፓርቲው አባላት ፓርቲውን በሙሉ ልባቸውና በሙሉ አቅማቸው ማገልገል ማቆማቸው፣

ለ. በ ኢ/ር ይልቃል የሚመራው የሰማያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰማያዊ ፓርቲ ለዓመታት ያክል እንደ ድርጅት ቀጥ ብሎ እንዲቆም የሚያስችል መሠረታዊ መዋቅሮችን መዘርጋት አለመቻሉ ለቁልቁለቱ ጉዞ ዋነኛ ምክንያቱ ነው ብዬ እገምታለሁ። ሰማያዊ ፓርቲ ከተመሰረተ ሶስት አመት ሊሞላው ነው። ነገር ግን በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢ/ር ይልቃል የመሠረተው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ እንኳን አንድ ክፍለከተማ ማደራጀት አለመቻሉ አነጋገሪ ነገር ሆኗል፣

ሐ. በኢ/ር ይልቃል የሚመራው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መርህን የተከተለና ተጠያቂነት ያለበትን አሠራር መዘርጋት አለመፈለጉ (በተለይም በገንዘብና ንብረት አጠቃቀም ዙሪያ)፣

ኢ/ር ይልቃል ከአንድነት ፓርቲ የወጣሁት ከፓርቲው ተባርሬ ሳይሆን በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በነበረው መርህንና ህግን የጣሰ አሠራር ደስተኛ ባለመሆኔ ነው ይላል። አንድነት ፓርቲ ውስጥ ይባል የነበረው ህገወጥ አሠራር እውነትም ኖሮ ከሆነ ግን አሁን ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ከሰፈሰነው የረቀቀ ህገወጥ አሰራር አይብስም። ህገወጥ አሠራርን ተጠይፎ መርህ ይከበር ብሎ ከአንድነት ፓርቲ እግሩን ነቅሎ ከወጣ ሰው ግን አንድነት ፓርቲ ውስጥ አለ ከሚለው ህገወጥ አሠራር የረቀቀ ህገወጥ አሠራር ይገነባል ብሎ መገመት ደግሞ በጣም ከባድ ነበር። በአሁኑ ወቅት የሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ስላለው ሚስጥራዊ አሠራርም ይሆን ግልጽ አሰራር ለማወቅና የስራው አካል ለመሆን ወሳኙ ነገር በፓርቲው ውስጥ የሚኖርህ የሀላፊነት ደረጃ ሳይሆን ለኢ/ር ይልቃል የምታሳየው የአጎብዳጅነት ደረጃ ነው። ይህም ጉዳይ ያሳሰባቸው የፓርቲው ኦዲትና ምርመራ ኃላፊዎች ይህ የሎሌነት ባህል እንዲቆም ለፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት በምክርቤት ስብሰባ ላይ አሳስበዋል። የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ግልጽነት ስለጎደለው የገንዘብ አጠቃቀምና አጠቃላይ አሠራር ጥያቄ ያነሱ እንደሆነም በፍጥነት በኢ/ር ይልቃል አማካኝነት ከፓርቲው የሥራ ሀላፊነታቸው ይታገዳሉ። በቦታቸውም የኢ/ር ይልቃል አጎብዳጅ ሎሌዎች ይተኩባቸዋል። ይሄም የኢ/ር ይልቃል ቀኝ እጅ ከሆነው የብሔራዊ ም/ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰኢድ ኢብራሂም ውጪ እውን አይሆንም ነበር።

የፓርቲዎችንም የገንዘብና የንብረት አጠቃቀም እንዲመረምር ሥልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎች ከሚፈራርሱበት መንገድ ውስጥ ዋንኛው የሆነው የገንዘብ ጉዳይ እንደሆነ ስለሚያውቅ ነገሩን እያራገበ ዝም ከማለት ውጪ ምንም ዓይነት የማስተካከያ እርምጃ እንደማይወስድ ከበፊትም ጀምሮ ይታወቃል።

አንድን ድርጅት ድርጅት ከሚያሰብለው ነገር ዋነኛው የድርጅቱ መዋቅርና ውስጣዊ አሰራር ነው። ነገር ግን ሰማያዊ ፓርቲ መዋቅሩም ድርጅታዊ አሠራሩም አንድ ይልቃልና በዙሪያው ያሰባሰባቸው ግለሰቦች ሆነዋል። በአጠቃላይ ሰማያዊ ፓርቲ ከነበረው ድርጅታዊ አሰራር ወጥቶ ወደ ቤተዘመድ ማህበርነት መቀየሩ ለቁልቁል እድገቱ መሰረት ነው። የሰማያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በፓርቲው ብሔራዊ ም/ቤት ተጠያቂነት ቢኖርበትም የስራ አሥፈጻሚ ኮሚቴው በተለይም ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ድረስ የተነከረበት ህገወጥ አሰራር በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት እንዳይጋለጥበት ፓርቲው ከተመሰረተ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ አንድም ዝርዝር የንብረት አጠቃቀም የፋይናንስና የስራ አፈጻጻም ሪፖርት ማቅረብ አልፈለገም። እስከዛሬ የቀረቡት ሁለት ሪፖርቶችም ከአንድ ገጽ ያልበለጡ ከስምንት መስመር ያላለፉ ናቸው። የመጀመሪያውን እቅድና ሪፖርት እንደምሳሌ ማየት እንችላለን።

የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም ከፓርቲው አቅም አኳያ ገምግሞ በአንድ አመት ውስጥ 26 ሚሊዮን ብር እንደሚሰበስብና 73 ሺህ አባል እንደሚመለምል በመላው የኢትዮጵያ ክፍለሀገሮችም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን እንደሚከፍትና አደረጃጀቱንም እንደሚዘረጋ በአመታዊ እቅዱ ላይ አስፍሮ ለብሔራዊ ም/ቤቱ እንዲያጸድቅለት ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን በዓመቱ መጨረሻ ግን የሰበሰበው 300 ሺህ ብር ሲሆን የመለመላቸው አባላት ቁጥርም ከ 980 አይበልጡም። ነገር ግን ኢ/ር ይልቃል በተለያዩ ሚዲያዎች 40ሺህ አባላት አለን ብሎ ህዝብን አታሏል። ወያኔን ታግሎ መጣል የሚቻለው ደግሞ ህዝብን በውሸት በመደለል ሳይሆን ባለው አባል ተጨባጭ ስራን በመስራት ነው ብዬ አስባለሁ። በአሁኑ ሰዓት አጠቃላይ የአባላቱ ቁጥር 4 ሺህ እንደሆነ አውቃለሁ።

ኢ/ር ይልቃል ሰማያዊ ፓርቲን እየገደለው ቁልቁል እየቀበረው ይገኛል። አሁንም የሰማያዊን መዳከም ሊያምን አልፈለገም። 170 ሺህ ብር የወጣበት ሰላማዊ ሰልፍም 400 ሰዎች ብቻ ሲገኙም አልደነገጠም። አሁንም ከሰማያዊ በቀር ሌላ ፓርቲ አልተፈጠረም ማለቱን ቀጥሎበታል። ሰማያዊ ፓርቲ ሌሎች ፓርቲዎችን ጥሎ እያደገ ነው ይላችኋል። እንዴት፣ የታለ እድገቱ ብላችሁ ብትጠይቁ ደግሞ ይሄው የአለም አቀፍ አምባሳደሮች ጠርተው እያናገሩኝ፣ የእንግሊዝ አምባሳደር ምሳ እየጋበዘኝ ብፈልግ የአሜሪካ ቪዛ በ 30 ደቂቃ እያሰራሁ ይላቹሃል። ሰው ሁሉ መንገድ ላይ ሠላም እያለኝ፣ አሜሪካ አገር እነሜሮን ጌትነት የሰለጠኑትን ዓይነት ስልጠና እየተጋበዝኩ ይላችኋል። የለም፣ የለም እኛ ያልነው የሰማያዊ ፓርቲን ዕድገት እንጂ የግል ስኬትህን አልጠየቅንህም ብትሉት ሰማያዊ ፓርቲን እንደ ግል ንብረቱ የሚያየው ኢ/ሩ ጓዴ ቱግ ቱግ ይላል። እኛ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሰፋ የሰማያዊ ፓርቲን አደረጃጀትና የትግል እድገት እንጂ የኢ/ር ይልቃል የግል ስብዕናና እድገት አንፈልግም።

3/ ወያኔ አንድነት ፓርቲ እንዲጠፋ ከሚፈልገው በላይ ኢ/ር ይልቃል አንድነት እንዲጠፋ ይፈልጋል

ኢ/ር ይልቃል ሰማያዊ ፓርቲን የሚቀላቀሉ አዳዲስ አባላትን የሰማያዊ ፓርቲን ፕሮግራም ከማስተዋወቅ ይልቅ በአንድነት ፓርቲ ጥላቻ ይሰብካቸዋል። ምን እንደሚያስነካቸውም አላውቅ፤ እነሱም ጸረ አንድነት ፓርቲ ሆነው ሌሎችን መስበክ ይጀምራሉ። የአንድነት ፓርቲ አባላት በማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እየተከታተሉም ስድቡን ያጧጧፉታል። የዚህ አይነት ሰዎች ሎሌ ለመሆን ካላቸው አባዜ በመነሳት ብቻ እንጂ በውስጣቸው ምንም ክፋት ኖሮ አይደለም። አንድነትንም ለምን እንደሚቃወሙ ብትጠይቋቸውም ዓይናቸውን ከማጉረጥረጥ በቀር ምንም ምክንያት ሊነግሯችሁ አይችሉም። ኢ/ር ይልቃል ለወያኔ የአባልነት መዋጮ የሚከፍልበትን ደረሰኝ ከኪሱ ባላገኝም ለወያኔ ያለምንም ክፍያ የመከፋፈሉን ሥራ እያቀላጠፈለት እንደሆነ ግን ማየት ይቻላል።

በሴቶች ታላቁ ሩጫ ሾላ አካባቢ የሚገኘው እስር ቤት ታስረው የነበሩ አባሎቻችንን ለመጠየቅ ሄደን ከእስር ቤት ስንወጣ እኔ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ(የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ም/ር ቤት ም/ል ሰብሳቢ) ኢ/ር ይልቃልና ዮናታን ተስፋዬ (የወጣቶች ጉዳይ ሰብሳቢ) ሆነን በአቅራቢያው ባለ አንድ ሬስቶራንት ተቀምጠን ፖለቲካችንን ስንሰልቅ በመሀል ኢ/ር ይልቃል ከተለያዩ የውጭ ሀገር አምባሳደሮች ጋርና ከተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የነበረውን ውሎ ፍንክንክ እያለ ሲተርክልን ቆየ። እኔም ያላንዳች መቼም እንዲህ እንዳልተፍነከነከ ገብቶኛል። ቢዘገይም እንዲያ ያፍነከነከውን ነገር አደራ ለማንም አይነገርም ብሎ እንዲህ ነገረን ‹‹ከቆየንበት ስብሰባ ስንበተን የመኢአድ ፕ/ት የሆኑት አቶ አበባው መሀሪ ወደኔ መጡና አንድነትና መኢአድ እያደረጉት ባለው የውህደት ጉዞ ደስተኛ እንዳልሆኑ፣ ውህደቱም ይሳካል ብለው እንደማያስቡ ነገሩኝ›› አለ። በሰአቱ የፓርቲዎች ውህደት መስተጓጎል በሚዲያ አልወጣም ነበር። እኔን ጨምሮ ብዙ ህዝብ የፓርቲዎችን ውህደት በጉጉት ስንጠባበቅ ስለነበር በሆዴ ይቺ ይቺ የፓርቲዎቹ ውህደት እውን እንዳይሆን ሌት ከቀን ደፋ ቀና ሲሉ የነበሩት የወያኔና የኢ/ር ይልቃል ምኞት ነች ብዬ አለፍኳት። ነገር ግን በሳምንቱ ጓድ አበባው መሀሪ በጋዜጣ ብቅ ብለው ጨዋታው ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ ብለው በሚዲያ ለፈፉ። ኢ/ር ይልቃል የነገረንም እውነት ሆነ። እሱም አላልኳችሁም፤ ውህደት የሚባል ነገር አይሰራም እኮ በሚል ሰማያዊ ፓርቲ ኩሽና ውስጥ ከበሮ አስደለቀ። ህዝቡም እርር ኩምትር ቅጥል አለ፣ እኔም እንደዚሁ።እንዲህ የሆንኩት ምንም እንኳን የሰማያዊ ፓርቲ አባል ብሆንም ወያኔን ታግሎ የሚጥል ትልቅ ፓርቲ ቢመሰረት ምኞቴ ነበርና ነው።

4/ሰማያዊ ፓርቲ የ 33 ፓርቲዎችን ስብስብ ለምን መሠረተ?

በሰማያዊ ፓርቲ ሀሳብ አፍላቂነት በመድረክ በተለይም በአንድነት ፓርቲ አሰባሳቢነት የተመሠረተው የ33ቱ ፓርቲዎች ስብስብ አላማ የወያኔ መጠቀሚያ የሆነው ምርጫ ቦርድ ነጻና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ እንዲያካሂድ ለማስገደድና ካለ ምንም ቅድመሁኔታ የ33 ፓርቲዎችን ጥያቄ እንዲመልስ ለማድረግ ነበር። ከምርጫ ቦርድ ጋር የነበረው ጉዳይ ባይሳካም ፓርቲዎች ባንድላይ ሲቆሙ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ሀይል አይተንበታል። ነገር ግን በኢ/ር ይልቃል ሌሎችን ፓርቲዎች የማንቋሸሽ ዘመቻ ያልተደሰቱት የ33ፓርቲዎች ስብስብ ፓርቲዎች ሰማያዊ ፓርቲ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጠን እንፈልጋለን ብለው ቢጠይቁም ምንም ማብራሪያ ከሰማያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለማግኘታቸው ሰማያዊ ፓርቲን ከስብስቡ እንዲያግዱ ተገድደዋል።

ሰማያዊ ፓርቲ ከስብስቡ ከመታገዱ በፊትና የ33ቱ ፓርቲዎች ስብስብ በተጧጧፈበት ወቅት ነው፤ እኔና ኢ/ር ይልቃል የቢሮው በር ተቆልፎብን በር ላይ ቆመናል። ይሄኔ የኢ/ር ይልቃል ስልክ ጠራ። የወቅቱ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ ሰማያዊ ፓርቲ ምርጫ ውስጥ ገባ ተብሎ ሰምቼ ነው አሉት። ኸረ በፍጹም! አለ ኢ/ር ይልቃል። ብቻ አውርተው ስልኩ ተዘጋ። አየህ አንድነቶች ከኛ ጋር ያላቸውን ፉክክር አለኝ። እኔ እኮ ወደ ምርጫ ብንገባ አንድነትም ወደ ምርጫ ይገባል፤ እኛ ገና አቅም ስላልገነባን ይሄን ምርጫ በአድማ ብናልፈው የ2007 ምርጫ ላይ አንድነት ከኛ ጎን የሚቆምበት ትከሻ አይኖረውም ብሎ የውስጡን ጥላሸት አሳየኝ። በ2007 ምርጫ አንድነት፣ ሰማያዊ፣ መኢአድና አረና ፓርቲ ተዋህደው አዲሱን ቅንጅት እንደሚያሳዩን እገምታለሁ። ነገር ግን በዚህ አዲስ ውህደት ውስጥ ኢ/ር ይልቃል የልደቱን፣ ሰማያዊ ፓርቲ ደግሞ የኢዴፓን ሚና እንዳይተኩ እሰጋለሁ። በ1997 ለቅንጅት ፓርቲ መፍረስ ከመኢአድ ፓርቲ ወጥተው ኢዴፓን በመሰረቱ ግለሰቦችና በመኢአድ ፓርቲ አባላት መካከል የነበረው የማይሽር መቋሰል ዋንኛ ምክንያት ነበር። አሁንም ሰማያዊ ፓርቲ ኢ/ር ይልቃልን መስከረም ላይ በሚደረገው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ መቀየር ካልቻለ የኢትዮጵያን የባርነት ጊዜ በአንድ ግለሰብ አማካኝነት ማራዘም ይሆናል። ከዘር፣ ከሀይማኖትና ከፖለቲካ አመለካከት የጸዳ የሀገር ፍቅርን ለልጆቻችን እናስተምር።

*********

ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ ሰነኔ 18/2004

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories