ለህግም -ህግ፤ ለህግ አስከባሪም – ሌላ ህግ አስከባሪ አለ

“የሞሪያም ምድር” የሚልን ፊልም አይ ዘንድ የምወደው ጓደኛዬ ጋበዘኝና በእኩለ ለሊይ በቤቴ ውስጥ ቤቴን ሆኜ አየሁት። ቤቴን ቤቴ ይፍጀውና ውስጤን እተነፍስ ዘንድ ግን በአንድ ጊዜ ለብዙዎች እስትንፋስን ለሚበትነው ፌስቡክ እና የድህረ ገፅ ጡመራ እፍ ልበል።

እኛ ሰዎች ብዙ ችግር የሚገጥመንና ብዙ ችግር የምንሰራው ስንጠግብ ነው፤ አዎ  ብዙ እንጀራ ስንጠግብ ብዙ እንጀራ ይርበናልና። ብዙ እንጀራ ለማግኘት የብዙዎችን እንጀራ መቀማት ደግሞ ግድ ይሆንብናል። ብዙ እንጀራ ለመቀማት ደግሞ ብዙ ረሃብ በመቀስቀስ ብዙ ችጋራሞችን ማፍራትና በቅሚያው ማሰለፍ ግድ ይላል። ዛሬ በየፌስቡኩ የምንሳደብና የሰውን ማንነት የምንናከስ የነዚሁ የጠገቡ ረሃብተኞች ችጋራሞች እንደሆንን ይገመታል።

ሆድ ጠግቦ ሲርበው ጭንቅላት ሥራ ያቆማል፤ ሆድ ያለቦታው ጭንቅላት ልሁን ይልና ሰውነትን መምራት ይጀምራል። አፋችን ለአእምሮአችን መታዘዙን ያቆምና ለሆዳችን ይናገራል፤ ለሆዳችን ያለመሰልቸት ይውጣል፤ ከሆዳችን ስድብንና ጥላቻን ይለፈልፋል። አልጠግብ ያለው ሆድ መጨረሻ ሰውነታችንን ጨርሶ እራሱምንም ያፈነዳል። ሆድን ቁንጣን ሳይዘው ማስራብና የህሊናችን ተገዢ ማድረግ ግድ የሚለው ለዚህ መሰለኝ።

በዚህ ሰዓት (ይህ ፅሁፍ ሲፃፍ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች የአቢይ ፆም ላይ ነበርንና) ለህሊናቸውና ለፈጣሪያቸውና ያደሩ ወገኖቼ ሆድን የማስራብና ህሊናን የማበልፀግ ክርስቲያናዊ ቀኖናቸውን ምሉእነት ከላይ ካነሳሁት የስጋና የነብስ፣ የፈጣሪና የተፈጥሮ መስተጋብር ተደጋጋፊነት ቀድመው ገብቷቸዋል። ሆድን በአእምሮ ሥጋንም በነብስ ለማስገዛት በፆም ህግ ጋት ያስተዳድሩታልና። መልካም የፆም ፀሎትና የሱባኤ ወቅት ይሁንልን። ምድራዊ ተጋድሎዋችንም እስከመጨረሻው የምንፀናበት ያድርግልን። ይህን ስል ግን አሁን ያለሁበትን ወቅትና የራሴን ነገር አስታውሼ እንጂ ሙስሊም ወገኖቼም ሆነ ሌላውም በየእምነቱና በየፍልስምናው ስጋውን ከነብሱ አስተሳስሮ የሚያኖርበትን እርሱነቱን እረዳለሁም አከብራለሁም። ሁላችንም በየእምነታችን እና የህይወት ፍልስምናችን ፈጣሪ ከሰጠን አእምሮ ቢስነት እንድንድን መልካም ምኞቴ ነው።

የነገሬ መነሻ ወደሆነው ወደ “ሞሪያም ምድር” ፊልም ልመለስ።  የሚከተሉትን አባባሎች ከፊልሙ በቀጥታ ልዋስ።

  • “እውነት ማለት እኮ እራሱ ስምምነት የሆነበት ወቅት ላይ ነው ያለነው”
  • “ስስታምና እራስ ወዳድነት የነገሰበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው”
  • “በብዙኃን ሬሣ ጥቂቶች የሚከብሩበት ወቅት ላይ ነው ያለነው”
  • “ስለዚህ ከጥቂቶች ጋር ተሯሩጠህ ቤትህን ካልሰራህ ልጅህ አፈር ስትለብስ ቆመህ ትመለከታለህ”
  • “በድምፅ ብልጫ እንገላለን በድምፅ ብልጫ እናድናለን”

፩) መቼም በውሎና አዳራችን፣ በመስሪያ ቤትና በቤተሰባችን … ከላይ የተጠቀሰውን የወቅቱን ማሳያዎች ሳንመለከት ወይንም እራሳችንም ሳትሳተፍበት አንቀርም። እራሳችንን እንመረምር። ምን አስተያየትስ አላችሁ? ለእኛ ጥቅም ሌላው መጎዳት አለበት? ለጥቂቶች ሹመት ብዙዎች ወደመቃብር መውረድ አለባቸው? ደራሲው እኛን ለማስተማር እንደምንም ብሎ ዋና ገፀባህርያትን ህይወት በመከራም ቢሆን አኖረልን። ግን እነርሱን ለማኖር ሌላውን መግደል ግድ ሆነበት፤ የድራማው ድራማ!

፪) ህጉን እና የህግ አስከባሪውን የገዛው የጠገበው ረሃብተኛ መጨረሻው ላይ በህገወጥ መልኩ ተገደለ። ምክንያቱም ህጉ እራሱ ለህገወጦች መከበሪያ የህገወጦች ማሾፊያ ስለሆነ። ለህጉም ህግ፣ ለህግ አስከባሪውም ሌላ ሌላ ሌላ ሌላ … ህግ አስከባሪ ይቋቋም ይሆን?

፫) ሃገራችን ውስጥ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ የሚሰሩ ፊልሞች (በእርግጥ የውጪውን ብዙም የማየት እድል የለኝም) የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ፤ የህግ አስከባሪውን ህገወጥነት አበጥረው ያሳዩናል። ህግ አስከባሪው ሲንቀረፈፍ፣ ሲያመነታ፣ መረጃን ሲያንቋሽሽ፣ … ማየት የተለመደ ነው። ድራማውን ጨርሰን ወደመንገድ ስንወጣም ድራማው በተግባር በየመንገዱና በየችሎቱ ሲተገበር ማየት ከባድ አይደለም። እኔ እስከማውቀው ደረስ ከገጠር እስከ ከተማ ያለው የነዚህ ፊልሞች ተመልካች በዚህ ተመሳሳይ የፊልሞቹ ባህሪያት ቢደጋገሙም ሳይሰለች በተመስጦ ተከታታይ መሆኑን ነው። ገመና፣ ሰው ለሰው፣ ዳና እና የመሳሰሉትን ማስታወሱ በቂ ነው። እስከመቼ ምንም ሳንማርበትና ሳንሻሻል በማህበራዊ ህይወታችን ላይ ድራማ እየሰራን እና እያየን እንኖራለን ?

፬) በመጨረሻ እራሱን “የሞሪያም ምድር” ፊልምን ህጋዊነት ልጠይቅ። በውጪው አለም ፊልሞች ህጋዊ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ህፃናት ማየት የማይገባቸውን እንዳያዩ ማስጠንቀቅ አንዱ የህጋዊነት ማሳያ አካል ነው። ይህ ፊልም ግን ህፃናት እንዳያዩት አይደለም ህፃናት ማየት የምይገባቸውንም እንዲሰሩ ያደረገ ይመስለኛል። ይህ ህገ ወጥ ከሆነ ለምን? ማነው ተጠያቂ?

“በድምፅ ብልጫ እንገላለን በድምፅ ብልጫ እናድናለን።” ይለናል ገፀባህሪው እኛን ወክሎ። የዘመኑን በድምፅ ብልጫ ማታለል (paradox) ሲነግረን። እዚህ የድምፅ ብልጫ ማታለል ውስጥ ድምፃችንን ስናክል እያንዳንዳችን በማዳንና በመግደሉ ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ ነን። ድምፅን ማቀብና አለመቃወም ደግሞ ለሆድ አደሮቹ ህጉን በህገወጥነት እንዲተረጉሙት ይሁንታ ሰጠን ማለት ነው። እና ላለንበት ዘመን ህገወጥነት ከራሳችን በላይ ማን ተጠያቂ ሊሆን ነው? የኃይማኖት አባቱም ኃይማኖተኛውም ሁሉም ለችግሩ መባባስ የድርሻውን እያበረከተ ማን በማን ላይ ጣት ቢቀስር ያምራል?

ለህግም -ህግ፤ ለህግ አስከባሪም – ሌላ ህግ አስከባሪ አለ: አምላክ-ህሊና። አምላክ ከህሊናችን ያድርገን። አሜን። ህገመንግስታችንስ የመጨረሻውን ስልጣንና ተጠያቂነት ለህሊናችን አይደል የሚሰጠው።

ቸር እንሰንብት።
——

[“የሞሪያም ምድር” ፊልምን ለማየት ይህን ይጫኑ]

********

Sisay Demeku

more recommended stories