ህግ አልባ የኩርፊያ ፓርቲ ብዝህነት

የነበሩበት ፓርቲ ውስጥ ህግና ዲሞክራሲን ማስፈን ያቃታቸው ደካሞች በየጊዜው አኩርፈው እየወጡ ተመሳሳይና ህግና ዲሞክራሲን ማስፈን የተሳነው ደካማ ፓርቲ መፈብረክ እንደ ጉብዝና ሳይሆን እንደ በህዝብ ስም እንደሚደረግ ወንጀል መቁጠር መቻል አለብን። የፖለቲካ ፓርቲ የአኩራፊዎች ወይንም የተበቃዮች የግል የንግድ ድርጅት አይመስለኝም። በህዝብ ሥምና ለህዝብ የሚደረግ ሃገራዊ ወይንም ህዝባዊ ውልና ራእይ ስለሆነ የፓርቲዎቹ አባል ያልሆንነውም ህዝቦች ያገባናል። ህግ ከተጣሰ ህግ ነው መከበር ያለበት እንጂ ሌላ ፓርቲ እየመሰረቱ የሃገርን እና የፖለቲካ ሂደት አለመተማመን እና ተስፋ መቁረጥ ማስፈንን መንከባከብ ያለብን አይመስለኝም። ምርጫ ቦርድ ለዚህ ችግር ግድ የሚለው ተቋም ቢሆን ኖሮ የተመሰረቱ ፓርቲዎችን ሃገራዊ ሂደት መደገፍና ፓርቲዎችን ፓርቲ በሚያሰኝ ሃገራዊ መስፈርት እውቅና መስጠትና መንሳት የነበረበት ይመስለኛል። 

አኩራፊዎች ወይንም የፓርቲ ህግ የማያከብሩትን እንደ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረቻ መንስኤነት ሲሆን እያየ ምርጫ ቦርድ የአዲስ ፓርቲ እውቅና የሚሰጥበት መስፈርት መሰለኝ ዋናው የገዢው ፓርቲ የመከፋፈያ ይሁንታ። በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱዋ ውስጥ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ሃገሪቱዋ ውስጥ ካሉት የፖለቲካ አጀንዳዎች ቁጥር ብዙ የሚበልጥ ይመስለኛል።

ለነገሩ ‘ከአንድ የገዢው ፓርቲ ሹመኛ ጋር በመጣላቴ ብቻ ወደ ፖለቲካ ፊቴን አዞርኩ፤ ከገዢው ፓርቲ ምንም የተለየ የፖለቲካ አጀንዳ የለኝም’ ብለው ብቻ በግል የተወዳደሩት ግለሰብ ‘በከፍተኛ የህዝብ ድምፅ አሸነፍኩ’ ብለው የህዝባዊ ስልጣን ባለቤት የሆኑበት የምርጫ ጨዋታ ነው ያስተናገድነው። የህዝብ ሥምና ሃብት የነዚህን የሁለት ግለሰቦች ህዝባዊና ፖለቲካዊ ላልሆነ ቁርሾ የሚውልበትን ምክንያት የሚያስረዳኝ እና የሚያሳምነኝ ምጡቅ በሃገሪቱዋ ባገኝ ደስታዬ ወሰን ባጣ ነበር። አሁን ሃገሪቱዋና ያ መራጭ ህዝብ ዶክተር አሸብርን በዚያ የግል ፀብ አቋማቸው መርጦ የሚያገኘው ጥቅም ምንድነው? በተመሳሳይ ‘ስብሰባ መግባት አትችሉም፤ በዚህ ሥም መሰብሰብ አትችሉም’ ተባልን፤ ህግ ይከበር እያሉ ከአንድነት ወጥተው ሰማያዊ ፓርቲ አቋቁመው ‘ምንድነው ልዩነታችሁ’ ሲባሉ ‘በወጣቶች የተገነባን ነን’ ወደሚል አመለካከት መግፋት ለህዝቡ ፋይዳው ምንድነው?  አምኖ የተደራጀበትን የፖለቲካ አጀንዳ ‘ህግ ተጣሰ’ ብሎ ሌላ ፓርቲ ለመመስረት የሚሮጥ ወጣት ቀጥሎስ የሚመሰርተውን ፓርቲ ህጋዊና ህዝባዊ ህልውና ጠብቆና አስጠብቆ የመቀጠል አቋም እንዴት ሊኖረውስ ይችላል? ሰማያዊ ፓርቲን እንደማሳያ አነሳሁ እንጂ የኢዴፓም ሆነ የሌሎቹም ተመሳሳይነት ይታየኛል።

ህዝብ፣ ሃገር፣ ምርጫ፣ ፖለቲካና ሃገራዊ የፖለቲካ አጀንዳን ቁብ የማይሰጡት ሰዎች ካልሆነላቸው ፖለቲካውን ለቀው ወደ ግል ንግዳቸው የሚሰማሩበት ሁኔታ ለማስፈን የሃገራችን ህግ ቢያስብበት መልካም ሳይሆን አይቀርም። ሃገሪቱዋ ጊዜዋን እና ሃብትዋን  ፖለቲካዊ ያልሆነን ነገር ፖለቲካዊ በማስመሰል ምርጫ እያባከነች ይመስለኛል። እንደኔ እንደኔ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረትና የፖለቲካ ፓርቲን ሃገራዊ ራእይ አስጠብቆ መምራት በጣም የተለያዩ ነገሮች ይመስሉኛል። የፖለቲካ ፓርቲን የመሰረቱ ግለሰቦች በመሰረቱበት የፖለቲካ አጀንዳ ሽፋንነት የራሳቸውን ግላዊ አቋም በአባላት ላይ በተለያየ ሥልት ለመጫን በሚያደርጉት አምባገነንነት ተመሳሳይ እና እንደ ባክቴሪያ የሚፈለፈል ፓርቲ ሊያመርቱብን አይገባም። ፓርቲ ከመሰረቱ እና ካቋቋሙ በኃላ ፓርቲውን በአባላቱ እና በሃገሪቱ ህግ አስረው ለአባላቱ ሙሉ በሙሉ ማስረከብ አለባቸው። ከተወሰነ ጊዜም በኃላም ከኃላፊነት ወንበር ዞር ብለው ያቋቋሙት ፓርቲ እንዴት እራሱን ችሎ በሌላ አባላት ሲመራ ለመመልከት እድል መስጠት አለባቸው። ይህንን የፖለቲካ ዳዴ ካለፈ በኃላ ነው ፓርቲው መንግስትነትን ማሰብ ያለበት። አለበለዛ በግለሰባዊ ተራ ፀብ ቆሞ መሄድ ያልቻለን ፓርቲ ለሃገራዊ መንግስትነት መመኘት ‘ዛፍ በሌለበት …’ ዓይነት ካልሆነ በስተቀር ተራ ቀልድ ይመስለኛል።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት መንግስት በምርጫ ቦርድ በኩልም ሆነ በሌሎች ተቋሙ ሃገራዊ የፖለቲካ አጀንዳሆች ነጥረው እንዲወጡ ለተለያዩ የፖለቲካ አቋሞች እውቅና ከመስጠትና  ከመከልከል ጀምሮ እንዲሁም በቁሳቁስና በሚዲያ ሽፋን መወጣት የነበረበትን ኃልፊነት ባለመወጣቱ አላስፈላጊ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች መብዛትና ይህንን ተከትሎም መልካም ህዝባዊና ሃገራዊ አስተዳደር በምንፈልገው መልኩ ማግኘት እንዳንችል መሆናችን ይሰማኛል። የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲከፋፈሉ ‘መንግስትና ገዢው ፓርቲ በነዚህና በሌሎችም ድክመቶቹ አስተዋፀኦ አደረገብን’ ማለታቸው አግባብ ቢሆንም እራሳቸው ካሉበት በግለሰባዊ አምባገነንነት የመበታተን አቋም አንፃር ሌላውን ሲኮንኑ ማየት ከሞራልም አንፃር ሃገራዊ ፋይዳቸውን የሚያኮሰምንባቸው ይመስለኛል።

በተለያዩ ነፃ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ግንኙነቶች ላይ የተራው ህዝብ ፍላጎትና ሃገራዊ ራእይ ከገዢውም ይሁን ተቃዋሚዎቹ የህዝብ እና የሃገር ንቃተ-ህሊና አወዳድረን ‘እንታገልልሃለን’ ከሚሉት ህዝብ በጣም የወረደ መሆኑን ስንገመግም በጣም የሚያሳዝን እና የሚያሳስብ ነገን መገንዘብ ከባድ አይሆንብንም። የወረደ ለማለት ካስደፈሩኝ ምክንያቶች ዋናው ግን በየወቅቱ በሚደረጉት ምርጫዎች ህዝቡ የሚያስተላልፈውን መልእክትና ፓርቲዎቹ የሚረዱትን ግብረ-መልስ አራምባና ቆቦነት ስናገናዝብ ነው። ለምሳሌ በ1997 ዓ/ም ገዢው ፓርቲ ባልጠበቀው (ግን ቀድሞ በተነገረው) ምክንያት የህዝብ ድምፅ  ሲያጥረው ወዲያውኑ ህዝቡን በየቀበሌው ሰብስቦ ‘ምን አጠፋሁ አልኩ’ አለን። ከዛም ህዝቡ በአንድ ድምፅ ‘በአስተዳደርህ ብልሹነት ተከፋሁ እንጂ ለዚች ሃገር ከቅንጅት ይልቅ አንተ እንደምትሻለኝ አውቃለሁ’ ብሎኛል አለን።

ጥሩ ነገር ነበር። ግን ይህንን ግብረ-መልስ ከወሰደ በኃላ የወሰደው እርምጃ በምርጫ ክርክር ወቅት በተቃዋሚዎች በዋናነት ይዘረዘሩ የነበሩትን የመልካም አስተዳደሮችን ችግሮች ማስተካከያ እቅድ (ጤና፣ መንገድ፣ የሥራ እድል፣ የቤት ልማት) ያለምስጋና (ምስጋናው ይቅር አቋም የሌላቸው፣ ነውጠኞች በማለት እስር ቤት በማጎር) ቀን ከለሊት ወገቡን አስሮ መሥራት ጀመረ፤ ተመሳሳይ የሃገራዊ ክርክሮች እንዳይደረጉ የከፈታቸውን በሮች ገርበብ አደረጋቸው። አራምባና ቆቦ አንድ አትሉኝም። ህዝቡ ‘እድሜ ለቅንጅት’ እያለ ትንሽ መልካም ነገር ማየት ሲችል ተቃዋሚዎች ግን በምርጫ ጊዜ ‘እንሰራዋለን’ ይሉት የነበረውን እና አሁን ገዢው ፓርቲ የሚሰራቸውን ሥራዎች መቃወም፤ ህዝቡ “ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” አለን፤ አንድነት እያሉ እራሳቸው ለመከፋፈል ቀን ከለሊት መሥራት ጀመሩ – አራምባና ቆቦ ሁለት አትሉኝም። ህግ ማስከበር አቅቷቸው ህዝብ ከወደደላቸው ቅንጅት ይልቅ የራሴን ህልውና አስቀድማለሁ ብለው ያፈነገጡት እነ ልደቱ በቀጣይ ምርጫ ያውም ህዝብን በተሻለ መድረስ እየቻሉና በሙሉ ልብ ወደምርጫ ገብተው ህዝቡ ባዶዋቸው ሲሸኛቸው: መድረክ ሳይሆን ‘መድረክ ነኝ’ ብሎ ቢሮው ውስጥ ብቻ ሲራኮት ለከረመው መድረክ ግን ህዝቡ ከገዢው ፓርቲ የሚፎካከር ድምፁን ሰጠው። ህዝቡ ይህንን ሲያደርግ የመድረክን እውነተኛ መድረክነት ተርድቶ ሳይሆን አብረው ለመስራት ማሰባቸውን ማድነቁንና የገዢውን ፓርቲ አሁንም በድምጹ ለማስተማር የተጠቀመበት ብልህ ስልት ነበር ብዬ አምናለሁ። መድረክ ‘ይሄው አቋሜ የጠራ ለመንግስትነትም የበቃሁ ነበርኩ: ድምፅ ተጭበረበርኩ’ አለ – አራምባና ቆቦ ሶስት በሉኝ። ገዢው ፓርቲ ደግሞ ኢዴፓ ሰላማዊ ፓርቲ ነው፤ መድረክ ግን ነውጠኛ ነው አለ፤ ኢዴፓም ‘ሥሜ በሌሎች ተቃዋሚዎች ቀድሞ ስለጠፋ ነው ህዝቡ ያልመረጠኝ’ አይነት ግብረ-መልስ አገኘሁ አለን – አራምባና ቆቦ አራት።

እነዚህ የህዝቡን እና ‘ወካይ ነን’ የሚሉትን ፓርቲዎች ሃገራዊ ንቃተ-ህሊና ለመገመት እራስን ከወቅቱ የስልጣን ሽኩቻ እና ከሆድ አዳሪነት ነፃ ማድረግ ብቻ በቂ መሰለኝ። 

ለማጠቃለል ስልጣን ናፋቂዎች ‘ምርጫን ተንተርሰህ ተቃዋሚዎችን አጥላላህ’ አትበሉኛና ከምንም በላይ ተቃዋሚዎችን አንቆ የያዛቸው የራሳቸው ህግ ያለማክበርና ያለማስከበር ድክመት እና አምባገነንነታቸው እንደሆነ ያለፉትን የፖለቲካ ሂደቶች ማየቱ በቂ ነው። የባሰ ችግራቸውን እያሳደጉት ሄዱ እንጂ ሲያስተካክሉት አለመታየቱ ደግሞ ተስፋ አስቆራጭ ነው። ‘ለምን ተስፋ አስቆራጭ ይሆናል’ ብትሉኝ ያለፈ የፖለቲካ ታሪካችን እያሳደግን ባጎለመስነው ችግራችን ስንጠፋፋ ስላሳየን ነው። አሁን ተቃዋሚዎች ባሳደጉት ህገ-ወጥነትና አምባገነንነት የየራሳቸው የታጠቀ ኃይል ኖሮዋቸው ቢሆን ኖሮ ነጭ ሽብርና ቀይ ሽብርን የማንደግምበት ነገር የሚኖር አይመስለኝም። መፍትሄ ሳይሆን ችግርን የሚያሳድግ ፖለቲካን መንከባከብ ትልቁ ሃገራዊ ግዴታን አለመወጣት ነው። የፖለቲካ ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ መጪው ምርጫም ጥሩ እድል ነው ባይ ነኝ። የፖለቲካ ፓርቲ ሃገራዊ የፖለቲካ አጀንዳ እንጂ የተጣሰ ህግና ኩርፊያ መመስረቻ ምሰሶው ሊሆን አይገባም ባይ ነኝ። ምርጫ ደግሞ ሃገራዊ ራእይ እንጂ ኩፊያንና ህግ ለማስከበር ወይንም ለማክበር አለመቻልን መሰረት ማድረግ የለበትም።

********

Sisay Demeku

more recommended stories