ሰማያዊ ፓርቲ፡- የአንድነት አመራሮች ‘በእናንተ ምክንያት መታሰር አንፈልግም ሂዱ’ አሉን

  • አቶ ዳዊት አስራደ የሚባል የአንድነት ስራ አስፈፃሚ “አንድ ሰው የኢሕአዲግ ቲሸርት አድርጎ ቢመጣ ታባርረዋለህ ወይ?” ብለን ስንጠይቀው፤ “አላባርረውም፤ እንደውም እፈልገዋለሁ” አለን፡፡
    “ታዲያ ሰማያዊ ፓርቲ ቲሸርት አድርጎ ሲመጣ ለምንድነው የምታባርሩት” ተብሎ ሲጠየቅ፤ “ሰማያዊ ፓርቲ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እውቅና አልሰጠም ‘የሉም ‘ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ኢህአዴግ ቢያንስ ሰርተፊኬት ሰጥቷል…” አለ፡፡ ቃል በቃል ያለው ይሄንን ነው፡፡
  • ሀብታሙ አያሌው ‹‹ከኢሕአዴግ ለቀቅኩ›› የሚለው 2002 ዓመት ወደ ደቡብ አፍሪካ በሄደበት ወቅት ነው፡፡

ከአንድነት ፓርቲ በወጡ እና ሌሎች ግለሰቦች የተመሠረተው ሰማያዊ ፓርቲ፤ ባለፈው አንድ ዓመት ባሳየው ሚዲያ ተኮር እንቅስቃሴ በቀኝ ዘመም የፖለቲካ ካምፕ ውስጥ ትኩረት መሳቡ ይታወቃል፡፡

በዚያ ላይ ነው እንግዲህ፤ ባለፈው ሚያዝያ 19 ያደራጁት ሰልፍ አጀንዳ – ልክ በሳምንቱ በሚያዝያ 26 ከተዘጋጀው የአንድነት ፓርቲ ሰልፍ ጋር – ተመሳሳይ መሆኑ፤ የአንድነት አመራሮችን ቅር ከማሰኘት አልፎ ‹‹የአጀንዳ ንጥቂያ ተፈጽሞብናል›› ብለው በሚዲያ ላይ ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው እንግዲህ፤ አንድነት ፓርቲ ባዘጋጀው የሚያዝያ 26ቱ ሰልፍ ላይ ለመሳተፍ የሄዱ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት ተባረሩ የሚል ዜና የተሰማው፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ አዲስ አበባ የሚታተመው ሎሚ መጽሔት፤ ከሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ብርሀኑ ተክለያሬድ ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡ ቃለ-ምልልሱ የሆርን አፌይርስ አንባቢዎችን ትኩረት ይስባል ብለን ስላመንን፤ በኮምፒውተር በማስተየብ እዚህ አቅርበነዋል፡፡ [አንዳንድ የአርትኦት(editing) ስህተት የሚመስሉ የሚስተዋሉ ቢሆንም፤ በጣም እርግጠኛ ከሆንንባቸው በጣት የሚቆጠሩ ቦታዎች በቀር ዕርማት ለማድረግ አልደፈርንም]

[የአንድነት አመራር የሰጡትን ምላሽ ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ]

*****

ሎሚ መጽሔት፡- የሰሞኑ የአንድነትና የሰማያዊ ፓርቲ አለመተባበር ከምን የመነጨ ነው?

ብርሀኑ ተክለያሬድ፡- እኛ ልዩነት የለንም ብለን አናምንም ፤ ምክንያቱም ሁለት ፓርቲዎች ነን፡፡ ልዩነት ከሌለን አንድ ፓርቲ መሆን ነው ያለብን፡፡ በተወሰነ መልኩ የአሠራርም፣ የፕሮግራምም፣ የስልትም ልዩነት አለን ብለን እናምናለን፡፡ ግን በመከባበርና የጋራ በሚያደርጉ ጉዳዬች ላይ በመተባበር ልዩነታችንን እያጠበብን መሄድ አለብን የሚል እምነት ነው ፓርቲያችን ያለው፡፡Ethiopia---Semayawi-party-official--

አንግዲህ ሰሞኑን የተፈጠረውን ነገር ምንድነው? የሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ ሊደረግ ከታሰበበት ጊዜ ጀምሮ፤ ሰማያዊ ፓርቲን አጀንዳ ነጣቂ አስመስሎ፤ ግማሹ ‹‹አጀንዳ ነጥቋል›› – ግማሹ ‹‹በመሀል ገብቶ የአንድነትን ሰልፍ ለማደብዘዝ ያደረገው ነገር ነው›› ሲባል ነበር – በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ፡፡

ዞሮ ዞሮ ፓርቲያችን ያቀደውን ሰልፍ ለማድረግ ጥረት በምናደርግበት ወቅት ከ41 በላይ አባለት ታስረውብናል፡፡ የታሠሩት አባላት በሰልፉ ላይ መገኘት አልቻሉም፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የእኛ ሰልፍ ከተካሄደ በኋላ በሳምንቱ የአንድነት ሰልፍ ነበር፡፡ ቅዳሜ፣ ቅዳሜ በሚካሄደው የወጣቶች ውይይታችን ላይ፡- እሥር ቤት የነበሩ አባሎች ሰልፉን መሳተፍ አለባቸው፣ ሞራላቸው እንዳልወደቀ አሁንም ኢሕአዴግን ሊታገሉ እንደሚችሉ ለማሳየት፤ የአንድነትን ሰልፍ እንዴት መሳተፍ አለብን በግለሰብ ደረጃ እንሳተፍ ወይስ እንደፓርቲ እንሳተፍ? የሚል ውይይት ነበረን፡፡ በውይይታችን ላይ እንደፓርቲ መሳተፍ አለብን የሚል ሀሳብ መጥቶ ሀሳቡ አሸናፊ ሆኖ ወደ አንድነት ሰልፍ ለመሄድ ወሰንን፡፡

ሰልፉ ላይ ለመሄድ ምን ማድረግ አለብን? የሚለውን ስንነጋገር ‹‹የፓርቲውን አርማ፣ ባነሮች ይዘን እንሂድ›› የሚል ሃሳብ ቢመጣም ሰልፉ የአንድነት ፓርቲ ሰለሆነና በዛ ሰልፍ ላይ ተሳታፊ ብቻ ሰለሆንን፣ አርማም ባነርም ይዘን መሄድ የለብንም የሚል ነገር አስቀመጥን፡፡ ነገር ግን የሰማያዊ ፓርቲ ቲሸርት የትም ቦታ ስንሄድ የምናደርገው ሰለሆነ፤ አድርገን እንደምንሄድ ነው ተነጋግረን የነበረው፡፡ እንግዲህ በዕለቱ የተፈጠረው ነገር፤ እኔ በጥዋት ነው እዛ የደረስኩት፤ ብዙ አባላት ነን፡፡ አባለቱ ጥሩንባ እየነፉ ነው እዛ የገቡት፡፡ የአንድነት አባላት በጣም ደስ ብሎቸው እያጨበጨቡ፣ እያቀፉ ተቀበሉን፡፡

ከዛ አቶ ዳዊት ሰለሞን (የአንድነት የአዲስ አበባ ም/ቤት ም/ሊቀመንበር) ጠራኝና፡- ‹‹የጠራኋችሁ ቲሸርታችሁን እንድታወልቁ ነው›› አለኝ፡፡ ‹‹ለምን? ምንድነው ችግሩ?›› ስንል፤ ‹‹ማውለቅ ወይም ካልሆነ ደግሞ መሄድ ትችላላችሁ›› አለኝ፡፡ ከዛ ልጆቹን ሰብሰብኩና፤ እንደዚህ እንደዚህ እየተባለ ነው – ምንድነው ማድረግ የምንችለው? አልኳቸው፡፡ እየተነጋገርን በነበርንበት ወቅት የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፣ አቶ ዳዊት፣ ሌላ ስራ አስፈፃሚ፣ የአባታቸውን ስም የማላውቀው አቶ ድንቁ የሚባሉ የም/ቤት አባል፣ ም/ሊቀ-መንበርሩ አቶ ተክሌ መጡና እዛው አካባቢ መነጋገር ጀመርን፡፡ ‹‹ቲሸርቱን ብታወልቁ ጥሩ ነው›› አሉን፡፡ መጀመሪያ ጉዳዩን የግለሰብ አድርጌው ነበር፡፡

‹‹ቲሸርቱን አናወልቀውም፤ ተዘጋጅተን ነው የመጣነው፡፡ አናውልቀው ቢባል እንኳን አንዳንዶቻችን ከውስጥ ጉርድ ካኔቴራ ብቻ ነው የለበስነው፡፡ እናንተ በምትመሩን እና በምታስተባብሩት መንገድ መሄድ እንፈልጋለን፡፡ ግን የምንለብሰውን ልብስ ልትወስኑልን አትችሉም›› ስንላቸው፤ ‹‹እንደዛ ካልሆነ መሄድ ትችላላችሁ›› አሉን፡፡ በጣም የሚያሳዝነው አቶ ድምቁ ያልኩህ የም/ቤት አባልና አቶ ዳዊት አስራደ ‹‹እናንተ በሰልፋችሁ ወቅት አድዋ ድልድይን እናልፋለን ብላችሁ እንደፈጠራችሁት ነገር እንዲፈጠር አንፈልግም፡፡ በእናንተ ምክንያት መታሰር አንፈልግም፤ ሂዱ፡፡›› አሉን፡፡ እና ምንም ማድረግ አልቻልንም፡፡ ልጆቹን ሰብስበን ከሰልፉ ወጣን፡፡ የነበረው ሁኔታ ይህን ይመስል ነበር፡፡ አንዳንድ ከእኛ ጋር የነበሩ የፓርቲያችን የህግ ጉዳይ ኃላፊዎች ሄደው አመራሮቹን ለማናገር ጥረት አድርገዋል፡፡ ለመታየትና ሌላ ዓላማ አላቸው የሚል የማያሳምን ምክንያት ነው የሰጧቸው፡፡

ሎሚ መጽሔት፡- እናንተ የሰማያዊ ፓርቲ ዓርማ ያለበት ቲሸርት ለብሳቹ መሄዳችሁ፤ የአንድነትን ሰልፍ ድባብ ያደበዝዛል ለሚለው አስተያየት ምን ምላሽ አለህ?

ብርሀኑ ተክለያሬድ፡- እኔ ደግሞ በተቃራኒው ነው የማየው፡፡ ሰልፉን አንድነት ነው ያዘጋጀው፡፡ አስተባባሪዎች የአንድነት ሰዎች ናቸው፡፡ በሰልፉ ላይ ግን ሰማያዊ ተሳትፏል፡፡ ስለዚህ ፓርቲዎች በመተባበርና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ትግል እያካሄዱ ነው የሚል ምስል በህዝቡ ውስጥ ይፈጥራል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከዚህ በተረፈ በሰልፋችሁ ላይ ልንሳተፍ ነው ብለን ለአንድነቶች የምናሳውቀው ለምንድነው? አስተባባሪዎች ብንሆን የእኛ አስተባባሪዎችና የእነሱ አስተባባሪዎች በአካሄዳችን ላይ ቅድሚያ መነጋገር ይጠበቅብናል፡፡ የሰልፉ አስተባባሪዎች በሚመሩን መንገድ ልንሄድ፣ አስተባበሪዎች የሚያሰሙትን መፈክር ልናሰማ፣ የእርሱ መሪዎች የሚይዙትን መፈክር ልንይዝ ነው የሄድነው፡፡ የትም ቦታ ስንሄድ የምናደርገውን ቲሸርት ነው የለበስነው፡፡ ሰልፉን ለመጥለፍ ወይም ሰማያዊ ፓርቲን ለማጉላት አስበን አይደለም፡፡

እኛ እንደ ፓርቲ ሆነን ስንሄድ እንቅስቃሴያችንን የሚያስተባብረው እኮ አንድነት ነው፡፡ ሌላ የሚፈጠር ነገር የለም፡፡ አርማ ይዘን አልሄድንም፡፡ እነርሱ ከተነሱበት አላማ የወጣ መፈክር ይዘን አልሄድንም፡፡ ነገር ግን ቲሸርት አድርገን ሄደናል፡፡ ክልከላችው ግን ተገቢ አይደለም፡፡ በወቅቱ የለበስነው ቲሸርት በሰማያዊ ፓርቲ የመጀመሪያው ሰልፍ ላይ የተሠራ ቲሸርት ነው፡፡ ከሄድነው 114 ሰዎች መካከል 20 አንሞላም ይሄንን ቲሸርት የለበስነው፡፡ ያን ያህል ቲሸርቱ አጉልቶ የሚያሳየው ነገር የለም፡፡ ለምን መጣችሁ? ካልሆነ በስተቀር፡፡ ሰልፉን ለመስተባበር እነርሱ ኃላፊነት ይወስዱ እንጂ ሰልፉ ላይ የመገኘት መብት አለን ፡፡ ለምሳሌ ሰማያዊ ፓርቲ ሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ ሲጠራ ‹‹ጥቁር ለብሳችሁ ኑ›› ብሎ ለበር፡፡ ነጭ ለብሶ የመጣን ሰው ‹‹ጥቁር ብትለብስ›› ልንል እንችላለን፤ ምክንያቱም የሚለበሰውን ልብስ ቀድመን ተናግረናል፡፡ አንድነት ግን ‹‹እንዲህ ዓይነት ልብስ ልበሱ፤ እንዲህ ዓይነት ልብስ አይለበስም፤ ይሄን እንደዚህ አድርጋችሁ ኑ›› የሚል መልዕክት አላስተላለፈም፡፡

ሎሚ መጽሔት፡- እናንተ በወቅቱ ገብታቹህ ስትታዩ ፓርቲያችሁን የማስተዋወቅና ነገሮችን የመጋራት የማወክ ሁኔታ አይፈጥርም ወይ?

ብርሀኑ ተክለያሬድ፡- ሰላማዊ ሰልፍ ማነቃቂያ እንጂ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ ከሰላማዊ ሰልፍ ውጪ ብዙ የትግል ስልቶች አሉ፡፡ እነዚህን ተከትሎ ነው ለውጥ ይመጣል ብዬ የማስበው፡፡ አንድነት ይህንን ሰልፍ ሲያስተባብር፣ ልሳተፍ ዝግጁ ነኝ ብዬ ነው የመጣሁት፡፡ እንደ ትልቅ ነገር ተቆጥሮ በዚያ መልኩ መሄድ ተገቢ አልነበረም፡፡ ያ ቢሆን እንኳን፣ ተነጋግሮ የሆነ ነገር ማድረግ ሲቻል፤ ‹‹ውጡ›› ማለት ከፓለቲካ ፓርቲ አመራሮች የሚጠበቅ አይደለም፡፡

ቃል በቃል አንድ ነገር ልንገርህ፤ አቶ ዳዊት አስራደ የሚባል የአንድነት ስራ አስፈፃሚ ‹‹አንድ ሰው የኢህአዲግ ቲሸርት አድርጎ ቢመጣ ታባርረዋለህ ወይ›› ብለን ስንጠይቀው፤ ‹‹አላባርረውም፤ እንደውም እፈልገዋለሁ›› አለን፡፡ ታዲያ ሰማያዊ ፓርቲ ቲሸርት አድርጎ ሲመጣ ለምንድነው የምታባርሩት ተብሎ ሲጠየቅ፤ ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች እውቅና አልሰጠም፤ የሉም ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ኢህአዴግ ቢያንስ ሰርተፊኬት ሰጥቷል…›› አለ፡፡ ቃል በቃል ያለው ይሄንን ነው፡፡

ሎሚ መጽሔት፡- የባለ ራዕይ ወጣቶች ማህበር አባል በነበርክበት ወቅት የአንድነት ህዝብ ግንኙነት ሀብታም አያሌው አብሮህ ነበር? ምን ያህል ጊዜ አብራቹ ሰርታችኋል?

ብርሀኑ ተክለያሬድ፡- አንድ ዓመት ነው የሰራነው፡፡ ባለ ራዕይ ህዳር 2004 ዓመት ነው የተመሠረተው፡፡ መሥራች አይደለሁም፡፡ ከምሥረታው ጥቂት ወራት በኋላ ነው የገባሁት፡፡ እስከ 2005 ዓመት ሰኔ ወር ድረስ አብረን ቆይተናል፡፡

ሎሚ መጽሔት፡- ባለ ረእይ ወጣቶች በኢህአዴግ የሚደገፍ እንደሆነ ይነገራል፤…

ብርሀኑ ተክለያሬድ፡- ባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ከመንግስት ጋር ምንም ንክኪ የለውም፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር አመራር ነበርኩኝ፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ሲቪክ ተቋም ነው፡፡ ከመንግስት ጋር ምንም ንኪኪ የለውም፡፡ በራሱ በጀት ይተዳደራል፡፡ ይሄንን ነገር አይቼ ነው የገባሁት፡፡ አመራር በነበርኩበት ጊዜ ግን የማየው ነገር ግን ትክክል አልነበረም፡፡

አንደኛ በመንግስት የሚደገፍ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ የኢሕአዴግን ሥራ የሚሠራ ተቋም ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የኢሕአዴግ አባል ያልሆነ ሰው ተጽዕኖ ይደርስበታል፡፡ የሚሠራው ለሀገር ሳይሆን ለገዢው ፓርቲ ነው፡፡ ይሄንን በግልፅ መታገል ጀመርኩኝ፡፡ በተለያዩ ሚድያዎች ላይ ስለማህበሩ ማውጣት ጀመርኩኝ፡፡ በዚህ ምክንያት እስከመታሰር ደረስን፡፡ ከዛ በኋላ ባለ ረዕይ ወጣቶች ማህበርን ፎርም ወጣቶች እንደመሰረቱት ሰማሁ፡፡

ሎሚ መጽሔት፡- ሀብታሙ አያሌው የባለራእይ ወጣቶች ሊቀ-መንበር ነበር፡፡ የኢሕአዴግ አባል እንደነበር በግልፅ ተናግሯል፡፡ ያ ማለት ባለራእይ ወጣቶች ማህበር በኢህአዴግ ይደገፍ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንተም በዚህ ተቋም ውስጥ የኢሕአዲግ አባል ነበርክ ማለት ነው?

ብርሀኑ ተክለያሬድ፡- ይሄ ምንአልባት የተሞላ መረጃ ያለመኖር ይመስለኛል ፡፡ ባለራዕይ ወጣቶች ማህበር በሊቀመንበርነት ሀብታሙ የመራው በ2004 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ ‹‹ከኢሕአዴግ ለቀቅኩ›› የሚለው 2002 ዓመት ወደ ደቡብ አፍሪካ በሄደበት ወቅት ነው፡፡ ‹‹ከኢሕአዴግ ጋራ ይሠራ ከነበረው ወጣት ማህበር ጋራ እሠራ ነበር›› ብሎ የገለጸው የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም ፕሬዚደንት ስለነበረበት ጊዜ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ነበር፡፡ አንድም ለባለ ራእይ ወጣቶች መመሥረት ምክንያት የሆነው በኢሕአዲግ ሰዎች ጫና ይደርስብን ስለነበር እንጂ በጋራ ሰርተን አናውቅም፡፡ ባለራእይ ወጣቶች ማህበር ከኢህአዲግ ጋር የሚሠራ ማህበር አልነበረም፡፡

ሀብታሙ የተለያየ አስተሳሰብ ሊኖረው ይችላል፡፡ አንድነት ሊሆን ይችላል፡፡ ኢህአዲግ ሊሆን ይችላል፤ ብርሀኑም እንደዛው፡፡ ተቋሙ የሚገለፀው ግን ባለው መተዳደሪያ ደንብ፣ ባለው እንቅስቃሴ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምም ነገር ተነናግሬ አላውቅም፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በባለ ራእይ ወጣቶች ዙሪያ ካንተ ጋር ሳወራ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሚድያ ላይ የተሳሳተ ነገር ሲገለፅ አያለሁ፡፡ ባለ ረእይ በዚህ መልኩ አይደለም የተመሠረተው፤ በወጣትነታችን አንድ ነገር አበርክተን እንለፍ፤ ከገዢው ፓርቲም ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጥገኝነት የተላቀቀ ፓርቲ እንመስርት ብለን ተነስተን ነው የነበረው፡፡
*********

Daniel Berhane

more recommended stories