በኦሮሚያ ክልል በዩንቨርስቲዎች ስለተከሰቱት ግጭቶች ከመንግስት የተሰጠ መግለጫ

ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ዩንቨርስቲዎች በተፈጠረ ግርግር በህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

ላለፉት አመታት ተከታታይ ዝግጅት ሲደረግበት ቆይቶ የህዝብ ውይይት የተጀመረበትንና በአዲስ አበባና በዙሪያው የሚገኘውን የኦሮሚያ ልዩ ዞንን በልማት ለማስተሳሰር የተነደፈውን የተቀናጀ የልማት ማስተር ፕላን አስመልክቶ ከፕላኑ ፋይዳና አላማ ጋር የሚቃረን መሰረተ ቢስ አሉባልታ በአንዳንድ ወገኖች በስፋት ሲሰራጭ ቆይቷል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግም በበርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ዘንድ ትክክለኛውን መረጃ የማወቅ ፍላጎት መኖሩን ከግምት በማስገባት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት በእቅዱ ልማታዊ አላማና በሚያስገኛቸው ጥቅሞች ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡ ቆይተዋል፤ በመስጠትም ላይ ይገኛሉ፡፡

በምክክር መድረኮቹ የተጀመረው ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ትክክለኛው መረጃ እንዲሰጣቸው ጥያቄ ላቀረቡ የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችንም በውይይቶቹ ውስጥ የማሳተፍ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወቃል ፡፡ ይሁንና በሁሉም ክልሎች ከሚገኙ ባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ይህ ህዝባዊ ምክክር ከመዳረሱ በፊት አስቀድሞ ጥርጣሬዎችን ለመንዛት ሆነ ተብለው በተሰራጩ አሳሳች አሉባልታዎችና ሃሜታዎች የተደናገሩ የተወሰኑ ተማሪዎች በፈጠሩት ሁከት በክልሉ በሚገኙ የተወሰኑ ዩንቨርስቲዎች በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በዚህ በሃይል በታጀበ ግርግር ሳቢያ በመደ ወላቡ የሶስት ተማሪዎች ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል፡፡በተለይም በአምቦ ዩኒቨርስቲ የተቀሰቀሰው ሁከት ወደ ከተማ በመዝለቁ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በአምቦ ከተማ ቢዝነስና ኮንስትራክሽን ባንክ ላይ በተደረገው የዘረፋ ሙከራና ሌሎችም ህገ ወጥ የነውጥ እነቅስቃሴዎች በአምቦና ቶኬኩታዮ ከተሞች የሰባት ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን ባንኩን ጨምሮ በበርካታ የመንግስትና የሀዝብ ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በተያያዘም በሃረማያ ዩንቨርሲቲ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች በሰላም የእግር ኳስ ጨዋታ በቴሌቪዥን በመከታተል ላይ በነበሩ ተማሪዎች ላይ በተወረወረ ፈንጂ ወደ 70 ያህል ተማሪዎች የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉ ተረጋግጧል፡፡

በፌዴራልና በክልል የፀጥታ ሃይሎች ትብብር ሁከቱ በተፈጠረባቸው ዩንቨርስቲዎች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋት ተችሏል፡፡ እስካሁን በተደረገው ማጣራት ከበስተጀርባ በመሆን ሁከቱን በማነሳሳትና በማቀነባበር ተግባር ላይ የተሰማሩት ጥቂት ፀረ ሰላም ሃይሎች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል ፡፡ከዚሁ ግርግር በስተጀርባ የቆሙትና ከዚህ ቀደም በነበሩ ግጭቶች እጃቸውን ሲያስገቡ የነበሩ የአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ያሉ ሃይሎች በሚቆጧጠሯቸው ሚዲያዎች እየታገዙ ይህንን የተማሪዎችን ጥያቄ ለጥፋት አላማቸው መጠቀሚያ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸው ታውቋል፡፡

እነዚሁ አካላት ህገ ወጥ እንቅስቃሴያቸውን ሰላማዊ ዜጎችን ሰለባ በማድረግ ጭምር ከማራመድ የሚቦዝኑ አልሆኑም፡፡ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሚሹ ተማሪዎችን ተገቢ ጥያቄ በአግባቡ እንዳይስተናገድ የሚፈልጉት የነውጥ አቀንቃኞች ከአንድ ጥግ ሆነው ብዙሃኑን ሰለባ በማድረግ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በመራወጥ ላይ ይገኛሉ ፡፡ ላለፉት ሃያ ሶስት አመታት በመገንባት ላይ ባለው ዴሞክራሲያዊው ስርአታችን ዜጎች በተናጠልም ሆነ በጋራ ማንኛውንም ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለመጠየቅና ለመወያየት ያላቸው ህገ መንግስታዊ መብት ተቋማዊ መሰረት ይዞ ያለ ገደብ ተረጋግጦ ሲተገበር ቆይቷል ፤በመተግበር ላይም ይገኛል ፡፡ ይህ ዴሞክራሲያዊ ባህል የእለት ተእለት ህይወታችን አካል በመሆን እየጎለበተ መጥቷል በመሆኑም ዴሞክራሲያዊው ስርአታችን ማንኛውንም አይነት ጥያቄ ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በማጤን ብዙሃኑ ወጣት ተማሪዎች ከጉዳዩ በስተጀርባ በሚንቀሳቀሱ ጥቂት የጥፋት ሃይሎች በሚነዙት የተዛባ ዘመቻና አሉባልታ ሳይደናገሩ ትምህርታቸውን በሰላም እንዲከታተሉ መንግስት አሳስቧል፡፡

በዚህ አጋጣሚ በተፈጠረው ሁከት ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸውና ወገኖችና ቤተሰቦቻቸው መንግስት የተሰማውን ሃዘን እየገለፀ የጥፋቱ ዋነኛ አንቀሳቃሽ የነበሩትን ተከታትሎ ለፍርድ ለማቅረብ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል ፡፡

ሚያዝያ 23/2006
አዲስ አበባ
—–

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories