(Tazabi Yehunta)

ሀገራችን ታላቅነትን ፣ ውርደትን ፣ የውጭ ወረራን፣የእርስ በርስ ግጭትን፣ የተለያዩ የፖለቲካ ስርዐቶችን ሁሉን አይታ ፣አሳልፋ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ በብዙ ትውልድ መስዋዕትነት ዛሬን አይታለች፡፡

አሁን ሀገራችን ስላለችበት ሁኔታ ብዙ አይነት እይታ እና ምዘና ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን በሁሉም ዘንድ ሊኖር የሚገባ አንድ የማይካድ ሃቅ አለ :: ይኸውም ጊዜው ወደተሻለ ነገር ለመድረስ የማኮብኮቢያ አለበለዚያ ግን እንደ ሀገር የመክተሚያ ጊዜ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ውድድር እና ፉክክር በበዛበት አለም የሃገሮች ወቅታዊ ጥያቄ “እንዴት ወደ ፊት እንገስግስ?” “በአለም ያለንን ስፍራ እንዴት ከፍ እናድርግ?” የሚሉት ናቸው፡፡ ጊዜው ደግሞ በአለማችን የውድድር መድረክ ብዙ ተጫዋቾች የበረከቱበት ሆኗል፡፡ በዚህ ጊዜ ማንቀላፋት፤ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ትኩረትን ማጣት ራስን ለተፎካካሪዎች የመጫወቻ ሜዳነት አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ በሀገራችን የተጀመሩ፣የተሳኩ እንዲሁም ያልተሳኩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡በዛው መጠን ደግሞ ያልተጀመሩ፣ ያልታሰቡ ፣ሊታሰቡ የሚገባቸው ብዙ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ልንመልሰው የሚገባን ጥያቄ ታዲያ እንዴት ወደሚቀጥለው ደረጃ እንሸጋገር የሚለው እነደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ያሉም የሌሉም ፣ የሞሉም ያልተሟሉም ነገሮች ባሉበት ሁኔታ እንዴት አንድም እርምጃ ወደ ኋላ ሳንመለስ ወደ አዲስ ደረጃ እንሻገር የሚለው ጥያቄ ዋነኛው ይሄ ትውልድ ሊፈታው የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ ይህንን የትውልድ ጥያቄ ከሌሎች ሀገሮች እንደተማርነው ከሆነ በስሜት መመለስ አይቻልም፡፡ በግምት መመለስ አይቻልም፡፡ ሲባል እንደሰማነውም መመለስ አይቻልም፡፡ በሌሎች እንዳየነውም መመለስ አይቻልም፡፡ አለ ዕውቀት መመለስ አይቻልም፡፡ በዘፈቀደ መመለስ አይቻልም፡፡ ሌሎች እንደነገሩንም መመለስ አይቻልም ፡፡ ለምን? ውጤቱ የከፋ አደጋ እንደሚሆን የአለማችን ወቅታዊ ሁኔታ በግልፅ አሳይቶናልና ነው፡፡ ስለዚህ የሀገራችን የአዲስ ደረጃ ሽግግር ጥያቄ በዕውቀት በሆነ እና በውስጥም በውጭም ያሉ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ባስገባ ሀገራዊ እይታ እና ምላሽ ብቻ ይፈታል ፡፡

እንግዲህ ይህ ትውልድ ከእልፍ አእላፋ ሰማዕታት የተረከባትን ሀገር ለሚቀጥለው ትውልድ ለማሻገር የራሱን ድርሻ የሚወጣበት ሰዓት ላይ ደርሷል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በምንቸገረኝነት ፣ በእኔነት እና ለእኔ አመለካከት መሸሽ ፣ ማምለጥ ወይም ለሌሎች አሳልፎ መስጠት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከታሪክ ተጠያቂነት ባሻገር ዞሮ መግቢያ የማጣት አደጋን በጎረቤትም፣ በመካከለኛ ቅርበትም ፣በሩቅም ካሉ ሀገራት ከምናየው እና ከምንሠማው መገመት ይቻላል፡፡

ታዲያ ይህንን የታሪክ አደራ ትውልዱ እንዴት ይወጣው ? የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ሃይለማረያም በአንድ ወቅት እንደጠየቁት በውይይት ነው ? በሠላማዊ ሠልፍ ነው ? ወይስ ታጥቆ በመዋጋት ነው?

ከላይ እንደተገለፀው የትውልዱ ድርሻ በሀገራችን የተጀመሩ ነገሮች እንዲቀጥሉ ፣ያልተጀመሩትም እንዲጀመሩ፣ የተበላሹትም እንዲስተካከሉ በማድረግ ሀገራችንን ወደ ሚቀጠለው ደረጃ አድረሶ ለተከታይ ትውልድ ማስረከብ ነው፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ ትውልዱ የአሁኑን ዘመን እና የመጪውን ጊዜ ለመረዳት መንቃት ይገባዎል፡፡ ከአሉ ተባሉ እና ጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት በዘለለ ደረጃ በሀገሪቱ እንዲሁም በአለም ዙሪያ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን መገንዘብ ፣መተንተን ይገባዋል፡፡ በመቀጠልም ሀገራችን አሁን ያለችበትን ሁኔታ አልፋ በቀጣይ ለዜጎቿ ጥቅም፣ ምቾት እና ኩራት፤ በአለም ደግሞ ተፈላጊ እና ተወዳዳሪ ሀገር ሊያደርጓት የሚችሉትን ልትደርስባቸው የሚገቡትን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ደረጃዎች ማሰብ እና ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ለሀገር እና ለሕዝብ ይጠቅማሉ የሚባሉ ዕውቀቶችን፣ አሠራሮችን እና መንገዶችን ፈተሾ እና መርምሮ መያዝ፣ ከአለፈው ታሪካችንም በመማር የሚያዋጣውን ለሀገር እና ሕዝብ ብዙ ዋጋ የማያስከፍለውን ጎዳናን በመምረጥ ለተግባራዊነቱም በመስዋዕትነት ራስን መሥጠት ያስፈልጋል፡፡

ይህ ትውልድ እንደቀደምት አባቶቹ የውጭ ጠላትን የመከላከል ወይም ደግሞ ለአመነበት አመለካከት የመሞት ድርሻ ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን ከቀደምት አባቶቹ ይልቅ ከባድ ሸክም ይጠብቀዋል፡፡ ጊዜው የዕውቀት እና የማስተዋል እንጂ የስሜት እና የወኔ ብቻ አይደለም ፡፡ይህንን ጊዜ በድል አድራጊነት ለማለፍ ደግሞ ከስሜታዊነት የፀዳ ፣ጥላቻን እና ደም መፋሰስን ያራቀ፣ ለጊዜያዊ እና ለግል ጥቅም ብቻ ያልዋለ ፣ በአሉባልታ እና ወሬ የማይፈታ፣ በማስተዋል የተሞላ የትላንት ፣የዛሬ እና የነገ ትንተና ያለው ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አቋም ያለው፣ በፅናት የሚቆም ሰው መሆንን ይጠይቃል፡፡

እንግዲያስ ይህ ትውልድ ይህንን ማንነት እና ስብዕና ይዞ ፣ የተጣለበትን አደራ በሚያኮራ ድል ተወጥቶ፣ ቀጣይ ትውልድ ለሚቀጥል ሃላፊነት ሀገር ተረክቦ ማየት ይሁንልና!

Tazabi Yehuneta (Pen name)

more recommended stories