ከስምንት ሀገራት የመጡ 853 ሰልጣኞች በመከላከያ ተቋማት ሰልጥነዋል።

(ቤተልሄም ባህሩ)

የመከላከያ ሰራዊት በአቅም ግንባታና ህብረተሰቡን በልማት በማገዝ በኩል ያደረገው አስተዋፅዖ የሚበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ እንደሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ፡፡

ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው አራተኛ የስራ ዘመን 21ኛ መደበኛ ስብሰባው የመከላከያ ሚኒስቴርን የግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት አድምጧል።

የሚኒስቴሩ ሪፖርት እንደሚያመለክተው ሰራዊቱን በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ እንዲሁም በአካዳሚክ ትምህርት የማብቃት ስራ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት አራት ሺህ የሚሆኑ የሰራዊት አባላት ከወታደራዊ ስልጠና በተጨማሪ ከዲፕሎማ ጀምሮ እስከ ዶክትሬት ድረስ ባሉ የትምህርት መስኮች እየሰለጠኑ የሚገኙ ሲሆን ከ 30 ሺህ 800 በላይ የሰራዊቱ አባላት ደግሞ ባለፉት ሁለት አመታት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተመርቀው ወደ ስራ ተሰማርተዋል።

ከተለያዩ አገራት ጋር ባለው የሁለትዮሽ ስምምነትም ከስምንት አገሮች የተውጣጡ 853 ሰልጣኞች በኢፌዴሪ መከላከያ ተቋማት ሰልጥነው ተመርቀዋል።

በምክር ቤቱ የመከላከያና የደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዳለውም ሰራዊቱ የአገሪቱን ሰላም ዴሞክራሲና ቀጣይነት ያለው ልማት ለማረጋገጥ ወቅቱ የሚጠብቀውን ዘመናዊ አደረጃጀትና አሰራር በመከተል አካላዊና አዕምሮአዊ ብቃቱን ለማሳደግ የተሰጡት ትምህርቶችና ስልጠናዎች የመከላከል አቅሙን የሚያሳድግ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

በሪፖርቱ እንደተገለጸው ሰራዊቱ ወታደራዊ ግዳጁን በብቃት ከመወጣቱ ባሻገር ህብረተሰቡን በተለያዩ የልማት ተግባራት እያገዘና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ሰራዊቱ በዘንድሮው ግማሽ ዓመት 10 ሺህ 13 ሄክታር ላይ የነበረን ሰብል በማረም ሰብስቧል። በተጨማሪም ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናትና ለአቅመ ደካሞች 380 ሺህ ብር የሚሆን የጉልበትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ በሪፖርቱ ተገልጿል።

የአካባቢ ጥበቃን በሚመለከት ደግሞ ባለፈው ክረምት ከ740 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል በረሃማነትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የደገፈ ሲሆን የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል 15 ኪሎ ሜትር የእርከን ስራም ሰርቷል።

በተጨማሪም 1 ነጥበ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የጉልበት መዋጮ በማድረግ አንድ የተፋሰስ ግድብ ሰርቶ ለአገልገሎት አብቅቷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሰራዊቱ ግዳጁን ከመወጣት ባለፈ ህብረተሰቡን በተለይም አቅመ ደካሞችንና ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን በመርዳት ያደረገው አስተዋፅኦ የሚደገፍና ሰራዊቱ ህዝባዊ መሆኑንና ለህዝብ ሰላም ብቻ ሳይሆን ልማቱንም በመደገፍ በኩል ትልቅ ሚና እየተወጣ እንደሆነ የሚያመለክት በመሆኑ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብሏል።

ሰራዊቱ ከአቅም ግንባታና ልማቱን ከመደገፍ ባለፈ በወታደራዊ ዲፕሎማሲና ሰላምን በማስከበር በኩል ያከናወነው ስራ ለአገሪቱ መልካም ገፅታ ግንባታ አኩሪ ተግባር እንደሆነ ገልጿል።
*******
ምንጭ፡- ኢዜአ – መጋቢት 26/2006 – ‹‹
የመከላከያ ሰራዊት በአቅም ግንባታና ህብረተሰቡን በልማት በማገዝ በኩል ያደረገው አስተዋፅዖ የሚበረታታ ነው››

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories