ግብፅ <ከኢትዮጵያ ጋር ያለኝን አለመግባባት ወደ አለም አቀፍ ገላጋዮች እወስደዋለሁ> ስትል እንደፎከረችው አሁን ተግባራዊ ለማድረግ ጫፍ ላይ የደረሰች ትመስላለች፡፡ በሙባረክ ዘመነ ስልጣን የህግና ፓርላማ ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩትና የአረብ ሊግን ዋና ፀሃፊነት ስልጣን ከአሚር ሙሳ እንዲረከቡ በሙባረክ እጩ ሆነው ተመርጠው የነበሩት ሙፊድ ሼሃብ <<የህዳሴውን ግድብ ጉዳይ ለአለም አቀፍ አካል ለማቅረብ የሚያስችለኝን ሁሉን አቀፍ ጥናት አጠናቅቄ ለፕሬዝዳንቱ አቅርቤያለሁ>> እያሉ ነው፡፡

አል ሚኒተር እንደዘገበው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሰነዱ ላይ ከፈረሙበት በኋላ ወደ ተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ የሚቀርብ ይሆናል፡፡ የግብፆቹ ፍላጎት ጠቅላላ ጉባዔው ሰነዱን መርምሮ ጉዳዩን ለፀጥታው ም/ቤት ወይም ለአለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንዲመራላቸው ነው፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ፈጣን ምላሽ ይሰጡበታል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ምን አልባትም ቀጣዩ ፕሬዝዳንት እስኪመረጥ ሊዘገይ ይችላል፡፡

ም/ቤቱ ይህን ሰነድ ሲያዘጋጅ በምክክር ላይ የተሳተፉ አንድ የጥናት ባለሙያ ጉዳዩ በቀጥታ በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንዲታይ ያልተደረገው ፍ/ቤቱ እንዲህ አይነት ጉዳዮችን ለማየት የሁለቱንም ወገኖች ስምምነት የሚጠይቅ በመሆኑና ኢትዮጵያ ይህን እንደማትቀበለው ስለተገመተ ነው ብለዋል፡፡

አንድ የግብፅ የቀድሞ ሚኒስትር ደግሞ <<የእስካሁኖቹ ውይይቶች ውጤት አላመጡም፤ አሁን ያለን አማራጭ በአለም አቀፍ ገላጋዮች አማካኝነት ኢትዮጵያ አነስተኛ ግድብ እንድትገነባ ማድረግ፤ ሌላ አለም አቀፍ አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም ማድረግ ወይም ጉዳዩን ወደ ሄግ ፍ/ቤት መውሰድ ናቸው>> ብለዋል፡፡

<<እነዚህ ሁሉ ካልተሳኩልን ደግሞ ግድቡ በሀገራቱ መካከል ግጭት የፈጠረ ስለሆነ ማናቸውም አለም አቀፍ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉ መጠየቅ እንችላለን>> ብለዋል፡፡ <<90 ሚሊዮን የግብፅ ህዝብን ለውሃ ጥም የሚዳርግ በመሆኑ ለቀጣናው ስጋት የሆነ ግድብ እንደሆነ ጠቅሰን እንከሳለን>> ሲሉም ዝተዋል፤፤

አል ሚኒተር ዘገባውን ሲጨርስ <<እውን ይህ ጉዳይ ለአለም አቀፉ ፍርድ ቤት ይደርሳልን?>> ሲል ስጋቱን በጥያቄ አስቀምጧል፡፡

አሁን እኛ ኢትዮጵያውያን ሁለት አማራጮች አሉን፡፡ አንደኛው በሂደቱ ውስጥ ተሳትፈን ግብፅን መርታት ሲሆን ሁለተኛው ተቀባይነት ያላቸውን ህጋዊ ምክንያቶችን በማቅረብ በሂደቱ ያለመሳተፍ ነው፡፡ የተሻለውን የመምረጥና ሀገራዊ ጥቅማችንን የማረጋገጥ ሃላፊነት የመንግስታችን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሁለቱም መንገዶች አዋጭ ይመስሉኛል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ግብፆቹ እንደሰጉት ኢትዮጵያ ጉዳዩ በአለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንዳይታይ መቃወም ትችላለች፡፡ ከሁለቱ ወገኖች አንድኛቸው ከተቃወሙት ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን አይኖረውም፡፡ የፀጥታው ም/ቤትም ጉዳዩ ለአካባቢው የደህንነት ስጋት መሆኑን ወይም የጦርነት መንስዔ መሆኑን ካላረጋገጠ ሊመክርበት አይችልም፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የሁሉንም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸውን የም/ቤቱን አባል ሀገራትን ይሁንታ ማግኘት ግድ ይለዋል፡፡

ያም ሆኖ ጉዳዩ ከሁለት ባንዱ ተቋሞች የሚታይ ቢሆን እንኳን ግብፅ ያቀረበቻቸው ክሶች ተጨባጭነትና በአለም አቀፍ ህግም ተቀባይነት ያላቸው አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ የጣሰችው አለም አቀፍ ህግም ሆነ የተባበሩት መንግስታት መርህ የለም፡፡ እንደውም አለም አቀፍ ህግ የሚደግፈው ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀምን ነው፡፡ ግድቡ እንኳን 90 ሚሊዮን ህዝብን በውሃ ጥም ሊጨርስ ቀርቶ በታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ይህ ነው የሚባል ጉዳት እንደማያስከትል የራሷ የግብፅ ተወካዮች በተሳተፉበት በአለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን አስቀድሞ የተረጋገጠ ነው፡፡

በእኔ እምነት ግብፆች ያላቸውና ሊያደርጉት የሚችሉት አማራጭ ሚኒስትሩ በመጨረሻ ያስቀመጡት ነው፡፡ <<አለም አቀፍ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉ መማፀን>>፡፡ በዚህ ረገድ የረጅም ግዜ ልምድና ስኬታማ አፈፃፀም ስላላቸው የሚያዋጣቸው ይመስለኛል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍፃሜ የሚያግደው አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ግድቡ ቀድሞውንም በውጭ ሀገራት ብድርና እርዳታ ሳይሆን በሀገር ውስጥ አቅም የሚገነባ በመሆኑ፡፡

ግብፅንና የተለያዩ ዘመን አስተዳዳሪዎቿን ልንወቅስ የሚያስችሉን አንድ ሺ አንድ ምክንያቶች አሉን፡፡ ታሪክ የመዘገባቸው ግፎችን በሀገራችን ላይ አድርሳለች፡፡ ኢትዮጵያ ግን ያለፉ ስህተቶችን በሚያርምና ሁላችንንም ተጠቃሚ በሚያደርግ ልማት ውስጥ በጋራ እንሳተፍ እያለች ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደግሞ የዚህ አዲስ ምዕራፍ መክፈቻ ቁልፍ እንዲሆን ትሻለች፡፡ ያም ሆኖ ግብፅ አሁንም ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ እንደሚጮህ ኢትዮጵያን በመክሰስ ተጠምዳለች፡፡ የሰሞኑ እንቅስቃሴዋም የተበላሸ ታሪኳን የማደስ ሳይሆን በሞላው የግፍ ፅዋዋ ላይ ሌላ በደል የመጨመር ነው፡፡

ይህ ጉዳዩን አለማቀፋዊ ይዘት የማላበስ ዘመቻ የሚያስገኝላትን ትርፍና ኪሳራ ኋላ ራሷ የምታወራርደው ይሆናል፡፡ ዘለቄታዊ ውጤቱ ግን ለግብፅ አዎንታዊ እንደማይሆን መረዳት አይከብድም፡፡ በተጨባጭ የመፈፀም አቅሙ ያልነበራቸው የቀደሙት መሪዎቻችን <አባይን እንገድባለን> እያሉ በማስፈራራት ግብፅን ወርቅ አስገብረዋታል፡፡ እኛ ደግሞ ለማስፈራራት ባንጠቀምበትም የመገደብ አቅሙ እንዳለን በተጨባጭ እያሳየን ነው፡፡ በዛም ተባለ በዚህ በአባይ ወንዝ ላይ የሚኖረን ስልጣን ከእንግዲህ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ የሚሄድ አይደለም፡፡ እናም የማይቀርልህን እንግዳ አጥብቀህ ሳመው እንደሚባለው ግብፆች የሚያተርፉት ፍቅር ቢጀምሩ ነው እንጂ በደል ቢጨምሩ የሚጠቅማቸው አይሆንም፡፡ ይህኛው ትርፉ ቂም ነው፡፡ ቂም ደግሞ በቀልን ይወልዳል፡፡

*********

For your reference here is the link for the news – click here

Kebede Kassa

more recommended stories