የይቅርታ አሰጣጥና አፈፃፀም ሥነ-ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ

ባለፈው መጋቢት 02/2006 የይቅርታ አዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ ቀርቧል፡፡

በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ከተካተቱት መካከል:- ይቅርታ የማያሰጡ በሚል የተዘረዘሩ ማለትም ሙስና፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ ሽብርተኝነት፣ በመሰረተ ልማት አውታር ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ የሃሰት ገንዘብ መስራት ወይም ማዘዋወር ወይም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት የሚያስከትል ማናቸውም ሌላ ወንጀል፣ አደገኛ እጽ ማምረት፣ ማዘዋወር፣ ይዞ መገኘት ወይም መጠቀም፣ በሴቶችና በሕጻናት ላይ የሚፈጸም የጠለፋና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል፣ ግብረሰዶም፣ ሕገወጥ የቅርሶች ዝውውር፣ በወንጀል ሕጉ ከአንቀጽ 246 አስከ 252 ወይም ከአንቀጽ 299 አስከ 301 የተደነገገውን በመተላለፍ የሚፈጸም ወንጀል፣ በዚህ አዋጅ መሰረት በወጣ ደንብ የተዘረዘሩ ሌሎች ወንጀሎች ናቸው።

የሕግ ረቂቁ ‹‹የይቅርታ አሰጣጥና አፈጻጸም ሥነሥርዓትን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ 395/1996 ለማሻሻል የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ በማብራሪያነት የቀረበው ሰነድ አንደሚከተለው ይነበባል፡፡

********

የይቅርታ አሰጣጥና አፈፃፀም ሥነ-ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ

የይቅርታ አሰጣጥን ሥርዓት በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የሚሠራበት ሕግ በ1996 ዓ.ም የወጣው “የይቅርታ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 395/1996” ነው። ይህ አዋጅ የይቅርታ አሰጣጥን ሥርዓት የሚደነግግ ሕግ ባልነበራት ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣ ሕግ ሲሆን ይቅርታ የሕግን አግባብ ሳይከተል በዘፈቀደ ይሰጥ የነበረበትን አሰራር በማስወገድ በተሻለ መልኩ ይቅርታ ለመስጠትና የይቅርታ አሰጣጡንም ሁኔታ ፍትሐዊ እንዲሆን ያስቻለ ሕግ ነው።

ይሁን እንጂ ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በቆየባቸው ጊዜያት በአፈፃፀም ረገድ በታዩት ተጨባጭ እጥረቶች እና የይቅርታ የሥራ ሂደት አስመልክቶ በተደረገው የመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ጥናት አዋጁ ከፍተቶች ያሉበት መሆኑ ስለታመነበት ይህን ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ረቂቅ አዋጁ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን ከተዘጋጀ በኋላ የክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት መድረክ፣ በይቅርታ ቦርድ አባላት እና በፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ ቦርድ ታይቶ በየጊዜው ማስተካከያ እየተደረገበት የተዘጋጀ ነው።

ረቂቅ አዋጁ በ4 ክፍሎች፣ በ24 አንቀፆችና በበርካታ ንዑሳን አንቀፆች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ነው። የረቂቅ አዋጁ ይዘት ዝርዝር ማብራሪያ እንደሚከተለው ቀርቧል።

የአዋጁ ይዘት ማብራሪያ

ክፍል አንድ ጠቅላላ

የአዋጁ ክፍል አንድ ጠቅላላ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን አንቀፅ አንድ የአዋጁን አጭር ርዕስና አንቀፅ ሁለት ደግሞ በአዋጁ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉና ትርጉም ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ቃላትና ሐረጎችን ትርጓሜ ይዟል። ከዚሁ ውስጥ፡-

በቀድሞው አዋጅ ምክር ቤት ተብሎ በአንቀፅ 2/1/ የተሰጠው ትርጓሜ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትን የሚመለከት ሆኖ ም/ቤቱ ግን በአዋጁ ውስጥ አንድም ቦታ የተጠቀሰበትን ከአዋጁ ጋር የሚያገናኘው ነገር ባለመኖሩ እንዲወጣ ተደርጓል።

በአዋጁ አንቀፅ 2/3/ ላይ “ፍርድ ቤት” ለሚለው ሐረግ በተሰጠው ትርጓሜ ፍርድ ቤት የሚለው ስያሜ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 78/2/ መሠረት የተቋቋሙትንና የፌዴራል ጉዳዮችን የማየት ሥልጣን የተጣታቸውን ፍርድ ቤቶች እና ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችን እንደሚያካትት የተመለከተ ሲሆን ይህም ፍርድ ቤት በሚለው ትርጓሜ ሥር ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች አይካተቱም ለሚለው የተዛባ አተረጓጎም ምክንያት ሆኖ የቆየውን ችግር ለማስወገድ ታቅዶ የተሰጠ ትርጓሜ ነው።

ማረሚያ ቤት የሚለው ቀደም ሲል በትርጓሜው ውስጥ ያልተካተተ እና በአዋጁ ውስጥ በብዙ ቦታ የሚጠቀስ በመሆኑ በትርጓሜ አንቀጽ 2/6/ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል።

ይቅርታ ጠያቂ የሚለው ይቅርታ የተጠየቀበት ፍርድ የሚመለከተው ሰው በሚል ብቻ እንዲቀመጥ ሆኖ ግብረአበር ወይም አባሪ የሚለው ይቅርታ የሚሰጠው ግለሰቡ በማረሚያ ቤት ቆይታው በሚያሳየው የመታረምና የመፀፀት ባህርይ በመሆኑ እንዲወጣ ተደርጓል። የቀድሞው አዋጅ አንድ ታራሚ የይቅርታ ጥያቄ አቅርቦ ይቅርታ ከተደረገለት ግብረ-አበር ወይም አባሪ የሆነ ታራሚ አብሮት የነበረ ከሆነ እሱም ይቅርታ እንደሚያገኝ ይገልፅ ስለነበር ይህን ለመገደብ ሲባል የተደረገ ነው።

በዚሁ ክፍል ውስጥ ቀደም ሲል በአንቀፅ 11 የይቅርታ ዓላማ ተብሎ የተጠቀሰው አንቀጽ 3 ሆኖ እንዲካተትና ዓላማው ወደፊት እንዲመጣ ተደርጓል።

ክፍል ሁለት

ይቅርታን የሚሰጡና የሚያስፈፅሙ አካላት

አንቀጽ 4/1/ የፕሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባር የሚለው በቦርዱ የውሳኔ ሀሳብ መሠረት ይቅርታ ይሰጣል ተብሎ ተስተካክሏል። በዚህም መሠረት ይቅርታ የሚገባቸው ሰዎች ብቻ በቦርድ ታይተው ለፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ይላካሉ ማለት ነው። ይቅርታ የማይገባቸው ሰዎች በቃለ-ጉባኤ የማይካተቱና ወደ ፕሬዚዳንቱም የማይላኩ ይሆናሉ።

ቀደም ሲል በንዑስ አንቀጽ 2 ይቅርታ መሠረዝን በተመለከተ የነበረው ቦርዱ የመጨረሻ ውሳኔ በመስጠት ይሰርዛል በሚል ስለተቀመጠ ከፕሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባር ውጭ እንዲሆን ተደርጓል። ይህም የሆነበት ምክንያት በክፍል ሶስት በአንጽ 20 ማብራሪያ በዝርዝር ተሰጥቶበታል።

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 4/2/ ፕሬዚዳንቱ ስልጣኑን በሙሉ ወይም በከፊል ለክልል መንግስት አካል በውክልና ሊሰጥ እንደሚችል የተቀመጠ ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት ቦርዱ የራሱን ስልጣን ለክልል ይቅርታ ቦርድ የሰጠ በመሆኑና ፕሬዚዳንቱም ውክልና ቢሰጥ ጉዳዮች በክልሉ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲገኙ ለማስቻል ነው።

በክፍል ሁለት ስር ከሚገኙት አንቀጾች አንዱ በሆነው በአንቀጽ 5 ላይ የይቅርታ ጥያቄዎችን በመመርመር ለፕሬዚዳንቱ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ ቦርድ እንደሚኖርና የቦርዱም ተጠሪነት ለፕሬዚዳንቱ እንደሚሆን ተመልክቷል።

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 6 የቦርዱ አባላት ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ መሆን እንዳለባቸው ተመልክቷል። ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ክፍተት እንዳይፈጠር ወይም በቋሚነት ሥራው በሌላ የሥራ ኃላፊ እንዲሠራ ቢያስፈልግ ሚኒስትሩ የሚወክለው ሚኒስትር ዴኤታ ሰብሳቢ እንዲሆን ተደርጓል።

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ የቦርድ አባል እንዲሆን የተካተተ ሲሆን ይህም የሆነበት ምክንያት የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይን አስመልክቶ የሚቀርቡ የይቅርታ ጥያቄዎች ላይ የራሱ የሆኑ አስተያየት በማቅረብ በኩል አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይችላል በሚል ሃሳብ ነው።

የፌዴራል ፖሊስ ተወካይም አባል ያልነበረ በመሆኑ በረቂቅ አዋጁ አባል እንዲሆን ተካትቷል። ይህም የሆነበት ምክንያት ፖሊስ ከወንጀል ምርመራ ጀምሮ ተሳታፊ የነበረ በመሆኑ፣ ይቅርታ ሲሰረዝም ቦርዱ ይቅርታው የተሰረዘ ግለሰብን በቁጥጥር ሥር እንዲያውል ለፖሊስ ስለሚያሳውቅና በሁሉም ክልሎች የቦርድ አደረጃጀት የፖሊስ ኮሚሽን ተወካይ የተካተተ በመሆኑ ነው።

በረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 6 መሠረት የቦርዱን አባላት ከተለያዩ አካላት መሰየም በራሱ ለቦርዱ አባልነት ብቁ እንደማያደርግና ለቦርዱ አባልነት ብዙ ለመሆን መልካም ሥነ-ምግባር፣ ለህገ-መንግስት ታማኝ መሆን፣ የሙያ ብቃትን እና የሥራ አክባሪነትን መላበስ የግድ እንደሆነ በአንቀፅ 7 ላይ በግልጽ ተመልክቷል።

በአንቀጽ 9/1/ /ለ/ ቦርዱ ነባራዊ ሁኔታውን እያገናዘበ መስፈርት ሊያመጣ እንደሚችል በአዲስ መልክ እንዲካተት ተደርጓል። ይህም የተደረገበት ምክንያት ይቅርታ የማይሰጥ ወንጀል ተብሎ በህግ የተከለከለው በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 28/1/ እና በአዋጁ አንቀጽ 14/1/ የተጠቀሰው ብቻ በመሆኑ የህዝብንና የመንግስት ጥቅም ማስጠበቅ ዋናው የይቅርታ ዓላማ ስለሆነ ቦርዱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እያገናዘበ መስፈርቶች በማውጣት የህጉን ዓላማ ተግባራዊ ማድረግ ስለሚጠበቅበት ነው።

አንቀጽ 9/2/ በክልል ለሚገኙ የፌዴራል ታራሚዎች ቦርዱ በቀላሉ ተደራሽ ስለማይሆን ጉዳዮች በክልል የይቅርታ ቦርድ እየታዩ በዚያው በኩል የመጨረሻ ውሳ እንዲገኙ የሚያስችል ውክልና ለክልል ይቅርታ ቦርዶች መስጠት የሚቻልበት ሁኔታ ተመቻችቷል። ይህም የሆነበት ምክንያት ቀደም ሲል በክልል የሚገኝ የፌዴራል ታራሚዎች ጉዳይ በክልል ይቅርታ ቦርድ ታይቶ የሚፀድቀው በፌዴራል ይቅርታ ቦርድ ታይቶ ለፕሬዚዳንቱ እየተላከ ነበር። ይህንን ለማስቀረት በክልሉ ይቅርታ ቦርድ እየታየ በዚያው በኩል በክልል መስተዳድር ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጠው ለማስቻል ነው።

ክፍል ሶስት

የይቅርታ አሰጣጥና አፈፃፀም

አንቀጽ 14/1 የይቅርታን ዓላማ የበለጠ ለማሳካት ያመች ዘንድ በመንግስት ካልታመነበት በስተቀር የይቅርታ ጥያቄ የማይቀርብባቸው ወንጀሎችን ዘርዝሮ አስቀምጧል።

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 15 ለይቅርታ ጥያቄ የሚቀርቡ ማመልከቻዎች በተፈጥሮ ሰውና በህግ የሰውነት መብት በተሰጠው አካል መሟላት ያለባቸው ዝርዝር ነገሮች ተመልክተዋል። ይህም የሆነበት ምክንያት ቀደም ሲል ለይቅርታ ጥያቄ የሚቀርቡ ማመልከቻዎች የተፈጥሮ ሰውን ብቻ ታሳቢ ያደረጉ ስለነበሩ እና አሁን ካለው የአገራችን የኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ በህግ የሰውነት መብት የተሰጣቸው አካላት በሚያጠፉት ጥፋት መቀጮ ሲጣልባቸው ይቅርታ መጠየቅ እንዲችሉ ታስቦ የተካተተ ነው።

አንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 1/ሐ/ ቅጣቱ በከፊል ይቅርታ የተደረገለት አመልካች ከ1 ዓመት በፊት ድጋሚ የይቅርታ ጥያቄ      ማቅረብ አይችልም የሚል ተካትቶበታል። ይህም የሆነበት ምክንያት የይቅርታ ጥያቄ አቅርቦ በከፊልም ቢሆን ይቅርታ የተደረገለት ስለሆነ እንደሌሎቹ ይቅርታ እንዳልተደረገላቸው ታራሚዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ማለትም በ6 ወር ጊዜ ጥያቄ ማቅረቡ ፍትሀዊነት ስለማይኖረው ቢያንስ ከአንድ ዓመት በኋላ ቢያቀርብ ጥሩ ይሆናል በሚል ነው።

በረቂቅ አዋጅ አንቀጽ 18 ላይ የይቅርታ ጥያቄን በሚመለከት ምስክርት ወይም ሙያዊ አስተያየት /expert opinion/ የሚሰጡ ሰዎች የሀሰት ምስክርነት ወይም ከሙያቸው አንጻር ተቀባይነት የሌለው የተዛባ አስተያየት መስጠት እንደሌለባቸው ተመልክቷል። ይህም አንቀፅ ምስክርነት ወይም የሙያ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች በሕግ ፊት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመገንዘብ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ያስችላቸዋል በሚል ታስቦ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ የተካተተ ሲሆን ደም ሲል በነበረው አዋጅ ይህ አንቀጽ አልነበረም።

በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 19 ላይ በይርቅርታ አሰጣጥ ወይም በውሳኔ ሀሳብ አቀራረብ ረገድ ከግምት ውስጥ መግባት ከሚገባቸው ጉዳዮች የተወሰኑት ተመልክተዋል። ይህም አንቀጽ ይቅርታ ከመደረጉ ወይም ከመነፈጉ በፊት በአንቀጽ 19 ሥር በዝርዝር የተመለከቱትንና አግባብ ያላቸው ሌሎችም ለፍትህ እና ለሕግ የበላይነት መስፈን፣ ለመንግሥትና ለሕዝብ ጥቅም መከበር አስተዋፅኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ጉዳዮች በጥንቃቄ ከተፈተሸ በኋላ ተገቢው ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚገባ ለማስገንዘብ ታቅዶ የተካተተ ሲሆን ቀደም ሲል በይቅርታ አሰጣጥ ወይም በውሳኔ ሀሳብ አቀራረብ ረገድ ግምት ውስጥ መግባት ጉዳዮች በአዋጁ ውስጥ የተካተቱ አልነበሩም።

በአንቀጽ 20

ከአሁን በፊት ቦርዱ በተለያየ ምክንያት ይቅርታን የሚያሰርዝ መረጃ ሲያገኝ ይቅርታው እንዲሰረዝ የውሳኔ ሀሳብ ለፕሬዚዳንቱ በመላክ ቀደም ሲል የተሰጠው ይቅርታ እንዲሰረዝ ያደርግ ነበር። በዚህ ረቂቅ አዋጅ ቦርዱ ይቅርታ የሚሰጣቸውን ሰዎች ለይቶ ለፕሬዚዳንቱ ስለሚያቀርብ ፕሬዚዳንቱም በቦርዱ የውሳኔ ሀሳብ መሰረት ብቻ ይቅርታ ስለሚሰጡ የይቅርታ ስረዛን በተመለከተ ወደ ፕሬዚዳንቱ የውሳኔ ሀሳብ ማቅረብ ተገቢነት የሌለው በመሆኑ በራሱ በቦርዱ የይቅርታ ስረዛው የመጨረሻ እንዲሆን ተደርጎ ተካትቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የይቅርታ ስረዛ ጥያቄ የሚነሳው ቅድመ ሁኔታ ሲጣስ ወይም በማታለልና በማጭበርበር የተገኘ ይቅርታ ሲሆን በመሆኑና ይህንንም በማስረጃ ማረጋገጥ ስለሚገባ ቦርዱ በማስረጃ አረጋግጦ ውሳኔ ስለሚሰጥ ወደ ፕሬዚዳንቱ መላክ ተገቢነት የለውም በሚል ነው።

ይቅርታው ሲሰረዝ ለተሰረዘበት ሰው በሚገባው ቋንቋ የሚለው የፌዴራሉ ቋንቋ አማርኛ በመሆኑ በሚገባው ቋንቋ መባሉ ትክክል ስላልሆነ እንዲወጣ ተደርጓል። በቀድሞ አዋጅ አንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ መልሱን በ20 ቀናት ውስጥ ማቅረብ ይኖርበታል የሚል የነበረ ቢሆንም 20 ቀን በጣም ረጅም በመሆኑና 20 ቀን ድረስ የሚያቆይ ምክንያት ባለመኖሩ በ15 ቀናትውስጥ ምላሹን እንዲያቀርብ በሚል ተስተካክሎ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጸ 5 ውስጥ ተካትቷል። ምንም እንኳን ይቅርታ መብት ባይሆንም የተሰጠው ይቅርታ ተጥሶ ሲገኝ ይቅርታው ለተሰረዘበት ሰው ምላሽ እንዲሰጥ የሚደረገው የግለሰቡን የመደመጥ መብት ለማረጋገጥ ነው። በንዑስ አንቀጽ 6 ይቅርት ተደርጎለት የነበረ ሰው ይቅርታው ሲሰረዝ ተሰጥቶት የነበረው የምስክር ወረቀት መመለስ ያለበት መሆኑ ተገልጿል።

********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories