የመኢአድ ውዝግብ በድጋሚ አገረሸ

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ቀደም ሲል ያጋጠመው ውዝግብ በድጋሚ አገረሸ። የፓርቲው ዋና ፀሐፊ ሆነው ተመርጠው የነበሩት አቶ ተስፋዬ ታሪኩ ሌሎች አምስት የፓርቲውን የስራ አስፈፃሚ አባላት በመያዝ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልፀዋል።

አቶ ተስፋዬ ቀደም ሲል በፓርቲው ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት ሲያገለግሉ የቆዩ ቢሆንም ከሦስት ወራት በፊት ጀምሮ ከፓርቲው አካባቢ ጠፍተው ቆይተዋል። ከሦስት ወራት በኋላ የአሁኑ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እራሳቸው ከፓርቲው የመተደደሪያ ደንብ በላይ በማድረግ፣ የተሻሉ አመራሮችን ከጨዋታ ውጪ በማድረግና፣ ፓርቲውን በባንዳነት በማሰለፍ የፓርቲውን ህልውና አደጋ ላይ በመጣላቸው በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ መወሰኑን ገልፀዋል። ይህንን ውሳኔ ያሳለፈውም ፓርቲውን ለመታደግ የተቋቋመው አምስት የፓርቲውን የስራ አስፈፃሚ አባላት በአባልነት የያዘው ኮሚቴ መሆኑን አቶ ተስፋዬ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል።

አሁን እንቅስቃሴውን የጀመረው ኮሚቴም በዞንና በወረዳ ደረጃ ያሉ የአመራር አባላትና ተራ የፓርቲው አባላት ከጎኑ እንዲቆሙ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ ጨምረው ገልፀዋል።

አቶ ተስፋዬ በአሁኑ ወቅት ፓርቲውን እየመሩ ያሉት አቶ አበባው እራሳቸውን ከሕግ በላይ በማድረግ፣ የተሻለ ሐሳብ ያላቸውንና ጥያቄ የሚጠይቃቸውንና ለፓርቲው መጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ የሚባሉትን ሁሉ እየመረጡ በማገድ የባንዳነት ስራ እየሰሩ በመሆኑ፣ ፓርቲውን ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ እንቅስቃሴ ማድረግ በማስፈለጉ ነው ብለዋል። እንቅስቃሴውም ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ የተጀመረ ቢሆንም የፓርቲውን ህልውና አደጋ ላይ ላለመጣል በሚል ዝምታ መምረጣቸውን ጠቅሰው ነገር ግን ከእሳቸው በተጨማሪ የሕዝብ ግንኙነትና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊዎች መታገዳቸውን በአባላትም መካከል የመከፋፈል ስራ በመሰራቱ ከታገዱት የአመራር አባላት ጋር ስምምነት ላይ በመደረሱና ትናንት (ማክሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2006 ዓ.ም) ባካሄዱት ስብሰባ ችግሩን ይፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በፓርቲው ፕሬዚደንት ላይ የተነሳው ቅሬታ በተመለከተ የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ አበባው መሐሪ ተጠይቀው በጉዳዩ ላይ ከወዲሁ ማብራሪያ ለመስጠት እንደሚቸገሩ፣ ነገር ግን አቶ ተስፋዬ ታሪኩ ከፓርቲው ከተለዩ ከሦስት ወራት በላይ እንደሆናቸውና አልፎ ተርፎ ፓርቲውን ክደው ወደ ገዢው ፓርቲ ጠቅልለው መግባታቸውን ተናግረዋል። ተጨማሪ ማብራሪያ በሕዝብ ግንኙነት በኩል ማግኘት እንደሚቻል በመግለፅ ወደፊት በግላቸው ሰፊ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

*******

ምንጭ፡- ሰንደቅ ጋዜጣ፣ መጋቢት 3-2006.

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories