የዜጎች ቅሬታ፡- ምክንያትና ዕቅድ ሳይሆን ተግባራዊ ምላሽ ይሻል

(ወንድወሰን ሽመልስ)

«ውሃ አጥቶ መኖር ከባድ እንደሆነ እማኝ መፈለግ አይገባም» በማለት የውሃ ነገር በአዲስ አበባ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን በከተማ አንዳንድ አካባቢዎች ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ከውሃው በባሰ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና መጥፋት በንብረታቸው ላይ ጉዳት እያስከተለባቸው መሆኑን በመግለጽ «ቅሬታችን ይሰማ» ይላሉ። አብዛኛዎቹ የሞባይል ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ደግሞ «አገልግሎቱ የለም ቢባል ይሻላል» ሲሉ ምሬታቸውን ይገልጻሉ። ሦስቱም ለደንበኞቻቸው «ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አይደለም» ሲሉ ነው የሚያማርሩት።

እንደ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከሆነ ውሃ ለሳምንት ከዚያም በላይ ለሁለትና ሦስት ሳምንታት ይጠፋል። ውሃ መጥፋቱን ቢያመለክቱም አፋጣኝ ምላሽ አያገኙም። በተለይም አንዳንድ ባለሙያዎች ደንበኛው «እጁ የማይፈታ ከሆነ» የሚፈለገውን አገልግሎት ለመስጠት ፍቃደኛ አይደሉም። ጉዳዩንም ቢያሳውቁ ተከታትሎ የሚፈታ አካል ባለመኖሩ ለከፋ ችግር ይጋለጣሉ። እንደቅሬታ አቅራቢዎቹ ውሃ ጠፍቶ በሚመጣበት ወቅት አንዳንዴ ይቆሽሻል።ያልተገባ ጠረንና ጣዕምም ይኖረዋል።

ጉዳዩን አስመልክቶ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የውሃ ማምረት፣ ማሰራጨትና ሲስተም ቁጥጥር ንዑስ የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ፍቃዱ ዘለቀ እንደሚናገሩት፤ ችግሩ የሚስተዋል ቢሆንም በተለይ አቃቂ፣ ሳሪስና ጎፋ አካባቢ ቀድሞ ያልነበረ አዲስ ችግር ተፈጥሯል። በወቅቱ በነበረው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ሲባል የውሃው ኃይል ለሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ቅድሚያ እንዲሰጥ በመደረጉ ምክንያት የተፈጠረ ነው።

የመልክዓ ምድር ልዩነት በመኖሩና የተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ በመሆናቸው ከቦታ ቦታ የውሃ ችግር ሊኖር ይችላል። ነገር ግን በዝቅተኛና የመሠረተ ልማት ግንባታ በማይከናወንባቸው አካባቢዎች የ24ሰዓት የውሃ አገልግሎት እያገኙ ነው። በከፍተኛ ቦታ ያሉና የመሠረተ ልማት ግንባታ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ይቸገራሉ። ችግሩን ለመፍታትም ሆነ ፍትሐዊ ስርጭቱን ለማረጋገጥ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።

«እኛ የምናቀርበው ውሃ በየደረጃው የሚፈተሽ በመሆኑ የጥራት ችግር የለውም» የሚሉት አቶ ፍቃዱ በተለያዩ ቁፋሮዎች ምክንያት ቱቦዎች በሚፈነዱበት ወቅት ጥገና ሲካሄድ የደፈረሰ ውሃ የመግባት ሁኔታ እንደሚኖርና ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ውሃው ከመነሻው ክሎሪን ተጨምሮበት ወደኅብረተሰቡ የሚደርስ መሆኑን ይናገራሉ። ከፍሳሽ ጋር የመቀላቀል ጥርጣሬ ሲኖርም አስፈላጊው እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ይገልጻሉ።

በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ያሉ ደንበኞች ሮሮ የሚበዛበት የኤሌክትሪክ ኃይል አንዱ ነው። የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ ጠፍቶ መቆየት፣ የኃይል ማነስና መዋዠቅ፤ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች መቃጠል፣ ለሥራና ማኅበራዊ ሕይወት መስተጓጎል ምክንያት ሆኗል። ደንበኞች ለሚያቀርቡት ጥያቄ ባለሙያዎች ተገቢውን ምላሽና አገልግሎት ያለመስጠት ችግሮችም ተጠቃሾቹ ናቸው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የውጭ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ እንደገለጹት፤ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ምክንያቶች በዋናነት የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአቅም ውስንነት እንዲሁም የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮች ላይ የሚያደርሱት ችግሮች ናቸው። እነዚህንም ችግሮች ለመፍታትና መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ድርጅቱ እየሠራ ይገኛል። መስሪያ ቤቱ የአቅም ውስንነት ያለባቸውን ማሰራጫ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅም ለማሳደግና በተቻለ መጠን ያልተቆራረጠ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲኖር ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም ያስረዳሉ።

«በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ፍላጎትና አቅርቦት ክፍተት የለም» የሚሉት አቶ ምስክር፤ የመቆራረጥ ችግሩ አልፎ አልፎ የሚከሰትባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንዲሁም የትራን ስፎርመሮች አቅም ያላደገባቸው ቦታዎች መሆናቸውን ተናግረዋል። እነዚህም ቢሆኑ በመሠራት ላይ ይገኛል። የተሻሻሉና የተቀየሩ መስመሮች፣ ማከፋፈያዎችና ትራንስፎ ርመሮች የአቅም ውስንነት እንደሌለባቸውና መሠረታዊ ችግራቸው እንደተፈታም ይገልጻሉ።

ለተገልጋይ ፈጣን ምላሽ አለመስጠትንና ማጉላላትን በተመለከተ አቶ ምስክር «ካልከፈላችሁን አንሰራም፤ የሚሉ ሠራተኞች ካሉ ኅብረተሰቡ አጋልጦ ሊሰጣቸው ይገባል» ሲሉ ነው የገለጹት። ከዚህ በፊት የተጀመረውን እጅ ከፍንጅ የማጋለጥ ተግባር በመከተል ለሕግ እስከማቅረብ መድረስ መሄድ ይገባዋል። በመሆኑም«ኅብረተሰቡ ለጥገና» በሚል ከሕጋዊ ደረሰኝ ሌላ የሚፈጽመው ክፍያ ያለመኖሩን አውቆ በየደረጃው ላሉ የመስሪያ ቤቱ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትም ሆነ ለሕግ በማመልከት እነዚህን ኪራይ ሰብሳቢዎች በጋራ ሊዋጋቸው ይገባል።

እንደ ውሃና ፍሳሽ፣ እንደኤሌክትሪክ ኃይል ሁሉ ኢትዮ ቴሌኮምም የተገልጋዮች ቅሬታ የሚቀርብበት ሌላው አካል ነው። የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች እንደሚሉት የሞባይል ኔትዎርክ አይሠራም። ከሠራም የመቆራረጥና በአንዳንድ ቦታዎች ረዘም ላለ ጊዜ ጠፍቶ የመቆየት ሁኔታ ያጋጥማል። የ3ጂ አገልግሎት እየተሰጠ አይደለም። የቅድመ ክፍያ አገልግሎት ካርድ ለአገልግሎት የተዘጋጀ አለመሆን፣ ከተመደበለት ደቂቃ ቀድሞ ማለቁን ደንበኞች እንደችግር ይጠቅሳሉ። አንዳንዴም ለሌላ ሰው በ806አማካይነት ገንዘብ ከተላከ በኋላ ወደ ሞባይላቸው እንደማይገባ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

የሲ.ዲ.ኤም.ኤ አገልግሎት ደካማ መሆንና በተመሳሳይ ያለምንም አገልግሎት ሂሳብ በመጨረስ ደንበኞቹን ለኪሳራ እየዳረገ መሆኑንም ይጠቁማሉ። አገልግሎት ፈላጊዎች በኔትወርክ እጥረት በመቸገራቸው «ኖ ወርክ» አገልግሎት የሚል ስያሜ እስከመስጠት ደርሰዋል።

ከኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን የተሰጠ የጽሑፍ ምላሽ እንደሚጠቁመው፤ የተጠቀሱት ችግሮች በሀገርና በተቋም ደረጃ ይታወቃሉ። በተለይም በአዲስ አበባ የኖኪያ ኤሪያ በሚባል አካባቢ ማለትም ከአስኮ እስከ ሃና ማርያም ድረስ ከ10 ዓመት በፊት የተተከለ አሮጌ ኔትወርክ በመሆኑ ከፍተኛ የአገልግሎት ጥራት ችግር ይታያል። በተጨማሪ የኔትወርክ መጨናነቅ በአገልግሎት ላይ ከሚታዩት ችግሮች ዋነኞቹ ናቸው።

ለ3ጂ አገልግሎት ከዚህ በፊት የተተከለው የ3ጂ አቅም ተሸጦ የተጠናቀቀ ስለሆነ አዲስ አገልግሎት እየተሰጠ አይደለም። የአገልግሎት ካርዶች ለመሞላት ዝግጁ ሳይሆኑ ገበያ ላይ የመድረስ (የመውጣት) የተሞሉ ካርዶችንና የተሳሳቱ ፒኖችን (የምስጢር ቁጥሮችን) ደጋግሞ የመሞከር፣ አንዳንድ ጊዜም በአገልግሎት መስጫ መሣሪያ ላይ በሚደርስ የቴክኒክ ችግር ምክንያት ሂሳብ መሙላት ያለመቻልና ምን ያህል እንደተሞላ ያለማወቅ ችግር እንደሚከሰት ተገልጿል።

ከተመደበለት ደቂቃ ቀድሞ ማለቅ ለሚለው፤ ሲስተሙ አውቶማቲክ እንደመሆኑ መጠን ደንበኛን ለይቶ ቀድሞ ሂሳብ የሚቆርጥበት ምንም ምክንያት አለመኖሩን፤ እንዲሁም ለሌላ ሰው በ806 አማካይነት የተላከ ገንዘብ ወደ ሞባይላቸው የማይገባው ወደ ፈለጉት ቁጥር ሳይሆን ወደ ሌላ የማስተላለፍ ሁኔታ ስለሚከሰት እንደሆነም ተጠቁሟል።

የሲ.ዲ.ኤም.ኤ ዳታ አገልግሎት ደካማ መሆን ዋና ምክንያት ከዚህ በፊት የተተከለው ሲ.ዲ.ኤም.ኤ ዳታ ኔትወርክ አቅም በአንዳንድ ቦታዎች ተጠቃሚዎች በመብዛታቸው ምክንያት የኔትወርክ መጨናነቅ በመፈጠሩ እንደሆነም ተገልጿል።

ለሞባይል ኔትወርክ መቆራረጥ እና አለመስራት ዋና ዋና ምክንያቶች የኤሌክትሪክ ኃይልና በተለያየ ምክንያት የፋይበር መቆረጥ፣ አንዳንድ ያረጁ የሞባይል ዕቃዎች የመለዋወጫ እጥረት ሲያጋጥም የሚከሰት መሆኑ ተጠቁሟል። ይህንን ችግር ለመፍታት የአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ፕሮጀክት በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

*********

ምንጭ፡- አዲስ ዘመን መጋቢት 1/2006፣ ርዕስ ‹‹ደንበኞች ለጥያቄዎቻቸው ምክንያትና ዕቅድ ሳይሆን ተግባራዊ ምላሽ ይሻሉ››

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories